በአንድ ወቅት በአንድ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ተገኝቼ ነበር። በዩኒቨርሲቲው የስራ ጉብኝት ለማድረግ ነበር ወደዚያ ያቀናሁት። የመሰረተ ልማት ግንባታዎችንና የትምህርት ጥራቱን ያሻሽላሉ ተብለው በግንባታ ላይ የሚገኙ የቴክኖሎጂ ስራዎችን ከተመለከትኩ በኋላ ከመምህራን፣ የአስተዳደር ሰራተኞችና አመራሮች ጋርም በትንሹ ለመወያየት እድሉን አግኝቼ ነበር። በወቅቱም ከአንድ የትምህርት ክፍል ኃላፊ ጋር ለኢትዮጵያ እድገት ማነቆ በሆነ ጉዳይ ላይ ያደረግኩት ጭውውት አይረሳኝም። የዚህን መምህር ስም ማንሳት አስፈላጊ ባይሆንም፣ የውይይታችን ጭብጥ ግን ዛሬ በስፋት ለማነሳው ርእሰ ጉዳይ ጠቀሜታ ያለው ሆኖ አግኝቼዋለሁ።
ነገሩ እንዲህ ነው። በጨዋታ መልክ “ዶክተር የሚወራው ነገር እውነት ነው እንዴ፤ የአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች መምህራን በቅጡ ስለሚያስተምሩት ነገር አያውቁም ሲሉ ተማሪዎች ይገልጻሉ” ስል ጠይቅኋቸው፡፡ ጥያቄውን ሳቀርብ ትንሽ መዳፈር እንዳይመስልብኝ እየፈራሁ ነበር፡፡ እሳቸውም የነገሬ ውል ገብቷቸዋልና ትከሻዬን ነካ አድርገው፣ ፈገግታዬን በፈገግታቸው ተቀብለው “ ወዳጄ መቼም እሳት በሌለበት ጭስ አይታይም” አይደል የሚባለው ሲሉ መልሳቸውን ያነሳሁት ጉዳይ መሰረት ያለው መሆኑን ቁጭት በሚነበብበት ቅላፅ አስረግጠው ነገሩኝ።
ለምላሹ ብዙም የጥሞና ጊዜ ሳይሰጡኝ። “ መፍትሄው ከስር ጀምሮ የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ ነው። ከስር ያልተገራ ትውልድ ጊዜው ካመለጠ በኋላ ለምን ጎበጠ ማለት አይቻልም” በማለት ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት እንዲመጣ አጥብቆ መስራት እንደሚያስፈልግ ነገሩኝ። እሳቸውና መሰሎቻቸው አገር ወዳድ ምሁራን በሙሉ በዩኒቨርሲቲና ሌሎች የትምህርት ተቋማት ላይ መሻሻሎች እንዲታዩ ምርምርና የመፍትሄ ሃሳቦችን ለማመንጨት ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ጠቆሙኝ።
ከላይ ካነሳሁት መምህርና የዩኒቨርሲቲ አመራር ጋር አሳሳቢ በሆነው ከትምህርት ጥራት ጉድለት ጋር በተያያዘ ትውልዱ እየተጎዳ ባለበት ሁኔታ ላይ ከተወያየን አራት ዓመታት አልፈዋል። ችግሩ አሁንም ድረስ እንዳለ ነው። ዛሬም በዩኒቨርሲቲዎቻችንና በመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚሰሙትና የሚስተዋሉት ነገሮች አሳዛኝ ናቸው። ሳያውቅ የሚያስተምር መምህር፤ ሳይማር የሚመረቅ ተማሪ የኢትዮጵያ ትልቁ ችግር መሆኑ ቀጥሏል።
እስቲ ለነገረ ጉዳዬ የሚረዳና ተመሳሳይ አስገራሚ ጨዋታ ላንሳላችሁ። ጓደኛዬ ነው። ባለትዳር እና የዘጠኝ ዓመት ልጅ አባት ነው። ጓደኛዬ እኔ ባለፍኩበት ህይወት ልጄ ማለፍ የለበትም፤ የተሻለ ህይወት እንዲመራ ትምህርቱ ላይ መስራት አለብኝ ከሚሉት መካከል ነው፡፡ በመሆኑም ብዙ ገንዘብ እያወጣ ልጁን በግል ትምህርት ቤት ያስተምራል። ክፍያው ራስ ምታት ቢሆንም፣ ለአንድ ልጁ ግን አልቦዘነም። ወንድሙም የእርሱ እኩያ የሆነች ሴት ልጅ አለችው። የምትማረው የመንግስት ትምህርት ቤት ነው። የሁለቱ አባት ምርጫ ለየቅል ነው። ታዲያ በእረፍት ቀን ቤተሰብ ይሰባሰባል። ጭውውቱ ይደራል። በዚህ ጊዜ የሁለቱ ልጆች የትምህርት ጉዳይ በመሃል ይነሳል። በግል ትምህርት ቤት የምትማረው ልጅ ውጤት ሲታይ ሁሌም ልዩ ነው። ከፍተኛ ነው። ይሁን እንጂ በትምህርት እውቀትና ንቃተ ህሊና ግን በመንግስት ትምህርት ቤት የምትማረዋ የወንድሙ ልጅ የተሻለች ነው።
ጓደኛዬን ይሄ ጉዳይ ለብዙ ጊዜ ያብሰለስለዋል። በትንሹ ቀለም ቀመስ ስለሆነ የሁለቱን ልጆች እውቀት ይመዝናል። ታዲያ የልጁ ነገር ስለሚያስጨንቀው የችግሩን መፍትሄ ለማግኘት ሙከራ ያደርጋል። የትምህርት ሁኔታዋን ውጤቶቿን መከታተል ይጀምራል። ከዚህ ቀደም የሰማው ነገር አለ። እርሱ ይበልጥ ጥርጣሬውን አጉልቶበታል።
ለወራት የልጁን የትምህርት ብቃትና ውጤቷን ሲገመግም ቆየ። ግኝቱ አስገራሚ ነበር። የልጁ እውቀትና የምታገኘው ከፍተኛ ነጥብ ትክክል አልነበረም። የሰማው ጉዳይም ይሄው ነበር። አንዳንድ የግል ትምህርት ቤቶች ወላጆች እስከከፈሉ ድረስ ውጤት አላግባብ ይሰጣሉ። “በውጤቱ ዝቅተኛ የሆነ ተማሪ በዚያ ትምህርት ቤት ካለ ቤተሰብ ትምህርት ቤቱን ሊቀይር ይችላል፤ ስለዚህ ውጤቱን ከፍ አድርጋችሁ ሙሉላቸው” የሚል እጅግ አሳፋሪ ትውልድ ገዳይ ድርጊት መኖሩን ሰምቶ ነበር። ይሄን ግን ለብዙ ጊዜያት ጆሮ ሳይሰጠው ቆይቷል። በልጁ ላይ ባደረገው ማጣራት ደረሰበት። በዚያ ምክንያት ልጁን ትምህርት ቤት ቀይሮ በአግባቡ እየተከታተለ ማስተማር መጀመሩን አጫውቶኛል።
ይህ አይነት ታሪክ በግል ትምህርት ቤት ብቻ ላይሰራ ይችላል። በአገራችን ጥሩ ጥሩ መምህራን ያሉበት፤ በንቃት የሚሳተፉ ተማሪዎች የሚገኙበት የግልም ሆነ የመንግስት ትምህርት ቤቶች እንዳሉ ሁሉ በተቃራኒው ደካማና ለተማሪዎች አለፍ ሲልም ለትውልድ የማያስቡ ትምህርት ቤቶች ስለመኖራቸው የማያውቅ ያለ አይመስለኝም።
በመግቢያችን ላይ እንዳነሳነው ግን አስተማሪው በአግባቡ ሳይማር መምህር ሆኖ ያልተማረ ተመራቂ ያፈራል። በዚህ ላይ ገንዘብን ማእከል አድርገው የሚሰሩ የትምህርት ተቋማት ሲኖሩ ደግሞ ችግሩ ላይ ይበልጥ ቤንዚን ያርከፈክፉበታል። በጥረቱ እውቀት የገበየው ዝቅተኛ ውጤት ሲያገኝ ቤተሰቡ ገንዘብ የከፈለለት ደግሞ ከፍተኛ ‹‹ውጤት›› ያገኛል። ኢ-ፍትአዊነት ይወለዳል። ይሄ ትውልድ ነው ሳይማር ተመርቆ በግልና መንግስት መስሪያ ቤቶች የሚሰገሰገው። ያን ጊዜ ነው አገር እምታነክሰው።
ይሄ ችግር እኛም ቤት አለ። ወንድሜ በአዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሶስተኛ ዓመት “የባዮ-ሜዲካል” ተማሪ ነው። ከወራት በኋላ ደግሞ የአራተኛ ዓመት ተማሪ ይሆናል። በቀለም ትምህርቱ እጅግ ጎበዝ ከሚባሉት መካከል ነው። በቤት ውስጥም ከፍተኛ ድጋፍና ክትትል ይደረግለታል።
ለእረፍት በመጣ ሰዓት ግን አንድ ልባችንን የሰበረው ነገር አረዳን። ተመርቄ ስጨርስ “የሞባይልና ኮምፒተር ጥገና እንድሰራ በዚህ ክረምት አጭር የቴክኒክ ሙያ የሚያስተምሩ ማሰልጠኛዎች ጋር አስገቡኝ” ሲል ጠየቀን። ሁላችንም ደነገጥን “ እንዴ አንተ የህክምና መሳሪያዎችን ለመጠገንና ለመፍጠር የሚያስችል የዩኒቨርሲቲ ትምህርት በታላላቅ መምህራን እየተማርክ ተመርቀህ ለመውጣት የተቃረብክ ልጅ ሞባይል ካልጠገንኩ ትላለህ” በማለት በግርምት መልሰን ጠየቅነው።
እሱም ትንሽ ፈራ ተባ እያለ “ ባለፉት ዓመታት በዩኒቨርሲቲ ውስጥ አንድ ጊዜ ብቻ ነው የህክምና መሳሪያዎችን በርቀት በላብራቶሪ ያሳዩን። እሱንም እንዳይበላሽ ብለውን መንካት እንኳን አልቻልንም። የፅንሰ ሃሳብ እንጂ የተግባር ትምህርት አያስተምሩንም። የህክምና መሳሪያዎች ፈጣሪና ጠጋኝ ተብዬ ተመርቄ ስወጣ ግን ምንም መስራት እንደማልችል አውቀዋለሁ። ታዲያ ምን አለፋኝ፤ ይሄን ብማር አይሻልም፤ በጊዜ እድሌን ከማበላሽ” ብሎን አረፈው።
ሁላችንም በዝምታ ተዋጥን፤ ምንም ልንመልስለት አልቻልንም። በጥያቄው መስማማታችንን ገለፅንለት። በትምህርት ተቋሞቻችን አዝነን “መፍትሄው ምን ይሆን ስንል” በእኛ የግል ጥረት ብቻ የማይፈታ ድድር ጥያቄ አንስተን ስንጨቃጨቅ ዋልን። በዚያ ቀን “የከፍተኛ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ኤጀንሲ” የሚባለው የመንግስት ተቋም እንዳለ ትዝ አለኝ። ይሄን አገራዊ ችግር እንዴት ይፈታው ይሆን? ስል በግሌ ራሴን ጠይቅሁ፤ ለዚህ የጋራ ችግራችን መፍትሄ ካላችሁ ምላሻችሁን እጠብቃለሁ። እስከዚያው ቸር እንሰንብት!
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ሰኔ 22/2013