‹‹የከተማዋ የውሃ ችግር የሚቀረፈው የተጠኑ የውሃ ግድብ ፕሮጀክቶችን መገንባት ስንችል ነው›› አቶ ፍቃዱ ዘለቀ  የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ የውሃ አቅርቦትና ሥርጭት ምክትል ሥራ አስኪያጅ

የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣንን ለመጀመሪያ ጊዜ በአዋጅ ቁጥር 68/1963 ዓ.ም፤ በድጋሚ በአዋጅ ቁጥር 10/87 የተቋቋመ መንግሥታዊ ተቋም ነው። የከተማዋን የመጠጥ ውሃ እና ፍሳሽ ለማስተዳደር የተቋቋመው መሥሪያ ቤቱ የረጅም ዓመታት እድሜ ቢኖረውም በተለያዩ ምክንያቶች የእድሜውን ያህል አገልግሎት ፈላጊዎችን የሚያረካ አገልግሎት መስጠት ሳይችል ቀርቷል።

ተቋሙ አሁን ላይ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ለነዋሪዎቿ በሚፈለገው ደረጃ ማቅረብ ባለመቻሉ ተጠቃሚዎች በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ለማለፍ እየተገደደ ያላባቸው ሁኔታዎች አሉ። ከዚህ ጋር ተያይዞም ከተገልጋዮች የሚቀርብበት ቅሬታ በየጊዜው እየጨመረ ነው።

አሁን አሁን በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች የመጠጥ ውሃ በሳምንት አንድ ጊዜ፤ ከዛም አልፎ በ15 ቀን አንድ ጊዜ የሚያገኙበት ሁኔታ ተፈጥሯል ፤ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ከተቋቋመበት ዓላማ አንጻር ለከተማዋ አስፈላጊውን የንጹህ መጠጥ ውሃ ለምን ማቅረብ አልቻለም ?፤ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ጨምሮ በበርካታ ሰፈሮች የሚታየው የውሃ እጥረት ምንጪ ምንድን ነው ? ችግር ለዘለቄታው ለመፍታት ምን እየተደረገ ነው ? ችግሩን ለምን መቅረፍ አልቻለም ? በሚሉና መሰል ጉዳዮች ዙሪያ የባለሥልጣኑ የውሃ አቅርቦትና ሥርጭት ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍቃዱ ዘለቀ አነጋግረን እንደሚከተለው አቅርበነዋል ።

ባለሥልጣኑ የውሃ አቅርቦትና ሥርጭት ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍቃዱ ዘለቀ አነጋግረን እንደሚከተለው አቅርበነዋል ።

አዲስ ዘመን፡- አዲስ አበባ በቀን ምን ያህል ውሃ ያስፈልጋታል? እናንተስ በቀን ከሚያስፈልጋት የውሃ መጠን ምን ያህሉን እያቀረባችሁ ነው?

አቶ ፍቃዱ፡- የከተማዋ ነዋሪ አራት ሚሊዮን ነው በሚል ስሌት፤ በቀን የምናመርተው ውሃ 677ሺ ሜትር ኪዩብ ነው። የሚያስፈልገው ደግሞ አንድ ነጥብ ሶስት ሚሊየን ሜትር ኪዩብ ነው። ይህ የሚያሳየው በአቅርቦት እና በፍላጎት መካከል ልዩነት እንዳለ ነው። ችግሩንም ለመፍታት በውሃና መሠረተ ልማት ማስፋፊያ ዘርፍ በኩል እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች አሉ። ለምሳሌ በቀን 80ሺ ሜትር ኪዩብ ውሃ ከተማ ውስጥ ከሚቆፈሩ ጉድጓዶች ለማቅረብ እየተሠራ ነው።

አዲስ ዘመን፡- ከተማችን ውስጥ ሰዎች ለመኪና ማጠቢያ፤ ለቤት ግንባታ፤ ለመጸዳጃ ቤቶች እና ለመሳሰሉት ንጹህ ውሃን እየተጠቀሙ ነው ፤ ሁኔታው ችግሩን አያባብሰውም ? ተቋማችሁስ ይሄንን ዓይነቱን ችግር ለመፍታት ምን እየሰራ ነው?

አቶ ፍቃዱ፡- ይህ ጉዳይ የሚያያዘው ከግንዛቤ ጋር ነው። ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ለእነዚህ አገልግሎቶች ከፍሳሽ ማጣሪያ የሚወጣውን ውሃ እንዲጠቀሙ ለማድረግ ጥረት እያደረግን ነው። ለምሳሌ ከውበትና ከአረንጓዴ ልማት ቢሮ ጋር በጋራ እየሰራን ነው። የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያዎች አሉን። ከዚያ ተጣርቶ የሚወጣውን ውሃ ለአረንጓዴ ልማት ሥራው ይጠቀሙበታል።

በግለሰብ ደረጃ ለመኪና እና ለግቢ ማጠቢያ ንጹህ ውሃን የሚጠቀሙ ሰዎችን ግንዛቤ በማሳደግ ለውጥ ማምጣት ይቻላል። እኛ እንደዚህ የሚያደርጉ ግለሰቦችን ስናገኝ ምክር እንሰጣለን። በጣም የከፋ አጠቃቀም ያላቸውን ደግሞ መስመራቸውን እናቋርጣለን።

የውሃ ችግር አለ። ችግሩ የማያንኳኳበት ቤት የለም። ይህ ሁሉ ችግር እንዳለ እያወቀ አትክልት በታከመ ውሃ የሚያጠጣ እና መኪና የሚያጥብ ካለ ማህበራዊ ኃላፊነት የማይሰማው ነው ፤ የአመለካከት ለውጥ ያስፈልገዋል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ሰዎች መጸዳጃ ቤት ከተጠቀሙ በኋላ በአንድ ጊዜ አምስት ሊትር ውሃ ይለቃሉ። በአንዳንድ ሀገራት ለመጸዳጃ ቤት የተለየ መስመር ተዘርግቶ የታከመ ውሃ እንዳይባክን ይደረጋል። በኛስ ከተማ መስመር ለመለየት ወይም በሌላ መንገድ ችግሩን ለመፍታት ምን ታስቧል?

አቶ ፍቃዱ፡– ይህ የሥልጣኔ ውጤት ነው። ሀገራችን እንደሚታወቀው የውሃ ችግር የለባትም። ውሃውን አልምቶ ለመጠቀም ያለባት የፋይናንስ ችግር ነው። ይህ ጥያቄ የሚመለሰው ስናድግ ነው። አሁን ባለው ሁኔታ አላማችን በሁሉም ቤት የመጠጥ ውሃ ማድረስ፤ ፍላጎቱን እና አቅርቦቱን ማጣጣም እና ብክነትን መቀነስ ነው።

ለመጸዳጃ ቤት የሚሆን ውሃ መስመር ለይቶ ወደ ቤት ማድረስ ይቻላል። እውቀቱም አለን። ነገር ግን ከሥልጣኔያችን እና ከኢኮኖሚ እድገታችን ጋር ተያይዞ ሊከወን የሚችል ነው። መስመር ለመዘርጋት ኢንቨስትመንት ይፈልጋል። የዚህ ዓይነቱ የውሃ አጠቃቀም ያላቸው ሀገራት ታዳጊ ሀገራት ሳይሆኑ ያደጉ ሀገራት ናቸው። እኛም ስንበለጽግ እንደርሳለን።

ውሃ ከሚፈለገው መጠን በላይ ያባክናሉ ተብለው በሚታሰቡ ተቋማት ላይ ዘመናዊ የሆኑ መሳሪያዎችን በመጠቀም ውሃ እንዲቆጥቡ ማድረግ ያስፈልጋል። አሁን ያለንን ሀብት የውሃ አቅርቦታችንን ለማሳደግ ብንሰራበት መልካም ነው። እንደ ሃሳብ ግን ኢኮኖሚያችን ሲያድግ የመጠጥ ውሃ ብዙ ወጭ የሚስወጣ ስለሆነ ከመጠጥ ውጭ ላሉ አገልግሎቶች ሌሎች መስመሮችን ዘርግተን መጠቀም ያስፈልገናል።

በከተማዋ ከስምንት ሺ ኪሎ ሜትር በላይ የውሃ መስመር አለን። ጥያቄውን ለመመለስ የተጣራ ውሃ የሚተላለፍበት ሌላ ስምንት ሺ ኪሎ ሜትር መስመር መገንባት ያስፈልገናል። ይህ ደግሞ አሁን ላይ የሚቻል አይደለም። እንደ ተቋም በተያዘው የ10 ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ በዋናነት ለመሥራት ያቀድነው ፍላጎቱን እና አቅርቦቱን ማጣጣም፤ ብክነትን ለመቀነስ ያረጁ መስመሮችን መቀየር እና ውሃን ለመቆጠብ የሚያስችሉ መንገዶችን መፍጠር ነው።

አዲስ ዘመን፡- ደህንነቱ የተጠበቀ የከርሰ ምድር እና የገጸ ምድር ውሃን አጣርቶ ለማቅረብ የቴክኖሎጂ አቅማችሁ ምን ያህል ነው ?

አቶ ፍቃዱ፡- አዲስ አበባ በቀን 210ሺ ሜትር ኪዩብ ከከርሰ ምድር እና 467ሺ ሜትር ኪዩብ ከገጸ ምድር ውሃ ታገኛለች። ከተማዋ ላይ 240 የውሃ ጉድጓዶች አሉን። ከገፈርሳ እና ከለገዳዲ የገጸ ምድር ውሃን ለማጣራት መቶ በመቶ በሚባል ደረጃ ችግር የለብንም። ክረምት ላይ ውሃ ይገባል። ጣቢያዎቹም ላይ ራሳችን ውሃውን እናጣራለን። መብራት ሲጠፋ ውሃው እንዳይቋረጥ ጀኔሬተሮች ተገጥመው በቋሚነት ውሃ ለተጠቃሚ እናቀርባለን።

ከለገዳዲ እና ከገፈርሳ የውሃ አቅርቦት የሚያገኙ ተጠቃሚዎቻችን ፍጹም ቅሬታ የላቸውም ባንልም ከሌሎቹ አካባቢዎች የተሻለ የደንበኛ እርካታ አላቸው። እኛም ፈረቃውን ጠብቆ ከማቅረብ አኳያ ጥሩ አፈጻጸም አለን። ይሄም የሆነው ውሃው ስለማይቋረጥ ነው። ከከርሰ ምድሩ የሚቀርበው ውሃ ጋር “የኦፕሬሽን” ችግር የለም ‹‹የካዳ ሲስተም›› አላቸው። እየሰራ ነው ወይስ ቆሟል የሚለውንም “በሪሞት ኮንትሮል” እንከታተላለን።

ነገር ግን የምርት አፈጻጸሙ እንደ ገጸ ምድሩ ቀላል አይደለም። 240 ጉድጓድ አለን ስንል 240 ትራንስፎርመር አለን ማለት ነው። ሁሉም ትራንስፎርመሮች ከአንድ የኃይል ጣቢያ ኃይል የሚያገኙ ሳይሆን ከተለያየ ‹‹ሰብስቴሽን›› ኃይል የሚያገኙ ናቸው። አንድ ቦታ ላይ መብራት ጠፋ ማለት ውሃ ይቋረጣል። 240ውም ጉድጓድ ላይ ጀነሬተር ማስቀመጥ ወጪውን ከፍ ያደርጋል። ሌላ አማራጭ የሌለበት ቦታ ላይ ጀኔሬተር እናስቀምጣለን። ውድም ቢሆን ሌሊት እና ቀን ነዳጅ እያመላለስን እንዲሰራ እናደርጋለን፡፡

በከርሰ ምድር የውሃ አቅርቦት ላይ ያቀድነውን ከ80 በመቶ በላይ መፈጸም ከባድ ነው። ይህም የሚሆነው በሁለት ምክንያት ነው። አንደኛው ምክንያት የመብራት መቆራረጥ ነው። ሁለተኛው ደግሞ 240 ጉድጓድ ዓመቱን ሙሉ ጤነኛ ሆኖ ሊሰራ ስለማይችል ፓምፖች ይቃጠላሉ። ሲቃጠሉ በሌላ ፓንፕ መተካት አለባቸው። የጉድጓዶቹ ጥልቀት 150 እስከ 250 ሜትር ድረስ ነው። ይሄውም ፓምፕ የመቀየሩን ሥራ ያከብደዋል።

አንድ ፓምፕ ሲቃጠል ለመቀየር በአማካይ ስምንት ቀናትን ይወስዳል። በነዚያ ስምንት ቀናት ውሃ አይመረትም። በዓመት ውስጥ ከአስር በመቶ በላይ ፓምፕ ይቃጠላል። ስለዚህ እቅዳችንን መቶ በመቶ ማሳካት አንችልም። ከከርሰ ምድር ውሃ የሚያገኙ አካባቢዎች ፈረቃ የማስጠበቅ አካሄዳችን ችግር አለበት። በመብራት መቆራረጥ እና በፓምፖች መቃጠል የውሃ አቅርቦት ችግር ይፈጠራል።

አዲስ ዘመን፡- ችግሩን ለመፍታት ምን እያደረጋችሁ ነው ?

አቶ ፍቃዱ፡- ይሄንን ችግር ለመፍታት ለኤሌክትሪክ አገልግሎት እኛ ጋር ቢሮ ሰጥተናቸው በጋራ አብረን እየሰራን ነው። በሀገራችን ሙሉ በሙሉ የኃይል አቅርቦት ችግር ሲፈታ ጥሩ የውሃ አቅርቦት ይኖራል። ከዚህ ባለፈ የኦፕሬሽን ችግርን ለመፍታት ‹‹ሴንትራል የካዳ ሲስተም›› እየገነባን ነው።

ካሉን 240 ጉድጓዶች 145 የሚሆኑት በየመንደሩ ውስጥ ያሉ ጉድጓዶች ናቸው። እዛ ላይ ያለውን ሥራ የሚያከናውኑት ሰዎች ናቸው። ለውጤታማነቱ ጠንካራ ክትትል ይፈልጋል። የምንመራው ሰው ስለሆነ የሥራ ሥነ ምግባር ያስፈልጋል። ሁሉም ሠራተኛ የተሰጠው ኃላፊነት ገብቶት ሥራውን በሚገባ ይሰራል ማለት አንችልም።

በጣም ጥሩ ሥነ ምግባር ያላቸው ሠራተኞች እንዳሉ ሁሉ ጉድለት ያለባቸውም ይኖራሉ። በዋና ቢሮ በኩል ለ145ቱም የጉድጓድ ውሃ ማውጫ ጣቢያዎች በመደወል ስለምርቱ ይጠየቃሉ። ነገር ግን ይሄንን ችግር በቋሚነት ሊፈታልን የሚችለው ሲስተም ነው። በሚቀጥለው ዓመትም ‹‹የሴንትራል ካዳ ሲስተሙ›› ሲጠናቀቅ ችግሩ ይቀረፋል፡፡

አዲስ ዘመን፡- አዲስ አበባ መቼ ከፈረቃ የውሃ አቅርቦት ተላቃ በየዕለቱ ውሃ ታገኛለች?

አቶ ፍቃዱ፡– አዲስ አበባ ከውሃ ችግር የምትወጣው ገቢያችንና የውጭ ምንዛሬ የማግኘት አቅማችን ሲያድግ እና ግድቦቻችንን ገንብተን ስንጨርስ ነው። የውሃ ሥራ እንደ ፋብሪካ ተገንብቶ በቃ አሁን አለቀ የምንለው አይደለም። እያደግን ስንመጣ የውሃ ፍላጎታችን ያድጋል፤ ሰው ንጹህ መሆን አለበት። ውሃን ለሚያስፈልገው ነገር ሁሉ መጠቀም መቻል አለበት። የውሃ ፍላጎት የሆነ ጊዜ ተጀምሮ የሆነ ጊዜ የሚጠናቀቅ አይደለም።

የነብስ ወከፍ ገቢያችን ሲያድግ ፍላጎታችንም ይጨምራል። ከተማ ውስጥ የሚኖሩ ሆቴሎች እና ህንጻዎች የውሃ አቅርቦት ፍላጎታቸውም ይጨምራል። ለዚህም ተከታታይ ሥራ ያስፈልጋል። አሁን ላይ በዘርፉ ያሉትን ዋና ዋና ችግሮች ለመፍታት የ10 ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ አስቀምጠናል።

የአዲስ አበባ የውሃ እጥረት በውሃ አቅርቦትና ፍላጎት መካከል ያለው ልዩነት ሰፊ በመሆኑ ነው። ይህ ሲፈታ ብዙ ነገሮች ይፈታሉ። የውሃ ችግር የዕድገት፤ የፋይናንስ ችግር ነው፤ ገንዘብ ካለ ውሃ አለ፤ ስለዚህ እጥረቱ የድህነት ችግር ነው። ስናድግ ገንዘቡ ሲኖረን ውሃ አለ። ከእኛ የባሰ በረሃ ውስጥ ያሉ ሀገሮች ገንዘቡ ስላላቸው ውሃ አላቸው። የውሃ እጥረቱ ከፋይናንስ ጋር የሚገናኝ በመሆኑ የከተማዋ የውሃ ችግር የሚቀረፈው የተጠኑ የውሃ ግድብ ፕሮጀክቶችን መገንባት ስንችል ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ውሃን አጣርቶ ዳግም ጥቅም ላይ ከማዋል አኳያ ያላችሁ እንቅስቃሴ ምን ይመስላል? አሁን ካሉት የማጣሪያ ጣቢያዎችስ ምን ያህል ሜትር ኪዩብ ውሃ በቀን ይገኛል?

አቶ ፍቃዱ፡- አሁን ካሉት የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያዎች ውስጥ ትልቁ ቃሊቲ ያለው የፍሳሽ ማጣሪያ ነው። በቀን እስከ 100ሺ ሜትር ኪዩብ ፍሳሽ ያጣራል። ከዛ የሚወጣውንም ውሃ በመኪና ለግንባታ ቦታዎች እና ለአረንጓዴ ልማት እንዲውሉ ይደረጋል። ሌሎችም ተለምዷዊ የሆኑ የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያዎች አሉን።

ከእነዚያ የሚወጡ ውሃዎችን ማጣራት ብቻ ሳይሆን ኬሚካሎችም ይጨመሩባቸዋል። ለመጠጣት ሥነ ልቦናችን ስለማይፈቅድ እንጂ ሌላ ችግር የለውም። ያንንም ለግንባታ እንሰጣለን። በየክፍለ ከተማው ለአትክልቶች የሚያጠጧቸው ውሃ መቶ በመቶ ከእኛ ማጣሪያ ጣቢያዎች የሚወጣ ውሃ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- የ10 ዓመቱ ስትራቴጂክ እቅድ ለመጠናቀቅ አምስት ዓመታት ናቸው የቀሩት እና እቅዱን ለማሳካት ምን እየሠራችሁ ነው? በቀሩት ዓመታት እቅዱን ማሳካት ይቻላል?

አቶ ፍቃዱ፡– የኮሪደር ልማቱን ማየት ይቻላል። በአጭር ጊዜ ምን ያህል ሥራዎች መከናወን እንደሚችሉ ማሳያ ነው። የጊዜ ችግር የለብንም ጥያቄያችን የገንዘብ ነው። ገንዘቡን ማግኘት ከቻልን ሥራዎቹን መሥራት እና ማጠናቀቅ እንችላለን። ጥናቶች ተጠንተው እጃችን ላይ አሉ። አሁን ላይ ባለው አምስት ዓመት የሚሰራው ሥራ በበፊት 10 ዓመት እና ከዛ በላይ የሚወስድ ሥራ ነው። እኛ ያቀድነው እንችላለን ብለን ነው። ነገር ግን አሁን ትልቁ ተግዳሮት የሚሆነው የውጭ ምንዛሬ ነው። የውሃ ፕሮጀክቶች በዓመታዊ በጀት የሚሰሩ አይደሉም። በብድር እና በፌዴራል መንግሥቱ ድጋፍ የሚሰሩ ናቸው። ገንዘቡን እንዳገኘን ወደ ሥራ እንገባለን።

አዲስ ዘመን፡- ከተማዋን ከማስዋብ ጋር በተያያዘ እየተሠሩ ላሉ የውሃ ፏፏቴዎች የውሃ አቅርቦቱን ከየት እያገኙ ነው? ብክነትስ እንዳይኖር ምን እየተሠራ ነው?

አቶ ፍቃዱ፡- ከተማዋን የማስዋብ ሥራ እየተሠራ ነው። ከቃሊቲ የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያዎች ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው። ስለዚህ ለውሃና ፍሳሽ ፈተና አይሆንም። ውሃው የሚገባው ወንዝ ውስጥ ነበር። የሚገባው ውሃ 100 ሺ ድረስ አቅም አለው። ከፍሳሽ ማጣሪያ የሚወሰደውን ውሃ እየተጠቀሙ ነው። ስለዚህ ለፋውንቴኖች የሚውለው ውሃ ለንጹህ መጠጥ ውሃ የሚውለውን ሳይሆን ወንዝ ውስጥ የሚገባውን ውሃ ነው።

አዲስ ዘመን፡- ውሃ ከሚባክንባቸው ምክንያቶች አንዱ የመስመር ጥገና ሥራ ነውና ጥገና የምታደርጉበት የአሠራር ሂደት ምንድነው? እንደመስፈርት የተቀመጠ አሠራር የለም?

አቶ ፍቃዱ፡- ከለገዳዲ የሚነሳ መስመር የጥገና ጊዜ እና አንድ ሰፈር ውስጥ አገልግሎት የሚሰጥ መስመር ቢሰበር ከተማዋ ውስጥ ያለው የውሃ እጥረት ስላለ እንደተቋም መስመር ከተሰበረ በ24 ሰዓት ውስጥ ይሰራል። መስመር ከተሰበረ መረጃ እስኪመጣ የሚወስደው ጊዜ አለ። መስመር ተሰበረ ማለት ወዲያው ሂዶ ወደ ጥገና መግባት አይቻልም። መስመሩ ተሰብሯል ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን አይተው አልዘጉትም የሚሉ ሃሳቦች ይነሳሉ። ነገር ግን መስመሩን ለመጠገን ውስጥ ያለው መስመር መውጣት አለበት። ስለዚህ ታይቶ የሚቀየር ከሆነ ይቀየራል፤ የሚታሰርም ከሆነ ይታሰራል። እንደ ጉዳቱ ሁኔታ ታይቶ በአዲስ ይቀየራል።

ይህን ሥራ ለመሥራት ወጥ የሆነ የአሠራር ሂደት የለም። እንደሚገጥመው የችግር ሁኔታ የሚወሰን ነው። ተቋሙ ከአንድ ሺ 400 ኪሎ ሜትር ጀምሮ አንድ ነጥብ አራት ሜትር እስከ ቧንቧ አፍንጮቹ ድረስ በተቻለ መጠን ይጠገናል። ጥገናው ሁለት፤ ሶስት ቀን 24 ሰዓት እየተሰራ ሊጠገን ይችላል። ከዚያም በላይም የሚወስድበት አጋጣሚ አለ።

ይህ ግን እንደቦታውና እንደሚገጥመው ችግር የሚወሰን ነው። ከፍተኛ ጉዳት ካጋጠመም አንድ ሳምንት ሊወስድ ይችላል። ይህንንም በፍጥነት ለማጠናቀቅ ለባለሙያዎች በየጊዜው ስልጠና እንሰጣለን። አሁን ላይ የውሃ መስመር በሀገር ውስጥ አቅም መዘርጋት ጀምሯል።

አዲስ ዘመን፡- ነዋሪዎች የውሃ መስመር ይግባልኝ ጥያቄ ሲያቀርቡ በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ምላሽ ትሰጣላችሁ?

አቶ ፍቃዱ፡- ይህ የሚመለስበት ስታንዳርድ አለው። አሁን ላይ ችግር የሆነብን የእቃ አቅርቦት ችግር ነው። እቃ መግዛት አልቻልንም። እቃ የሚገዛው ደንበኛው ነው። ስለዚህ መስመር እንዲገባለት የሚፈልግ ነዋሪ የእቃ ዝርዝር ተሰጥቶት ግዛ ይባላል። ከዚያ ቀን ጀምሮ ሲያስብ ሳምንት ከፈጀበት እስከ 12 ቀን ጊዜ ውስጥ ሊወስድበት ይችላል። ከዚህ አንጻር ቀደም ሲል የወጣውን ደንብ ክለሳ ተደርጎበታል። ይህ ከወጣ በኋላ በሁለት ቀን ውስጥ የሚያገኝበት ሁኔታ ይፈጠራል።

አዲስ ዘመን፡- በእናንተ መስፈርት አንድ አካባቢ በሳምንት ምን ያህል ጊዜ ውሃ ማግኘት አለበት?

አቶ ፍቃዱ፡– በሳምንት ሁለት ቀን፤ ሶስት ቀን፤ አንድ ቀን የሚያገኙ አሉ። እንደየሰፈሩ ይለያያል። የውሃ ሥርጭት ጉዳይ በአንድ ቦታ ላይ የማሰራጨት ያህል አይደለም። እያንዳንዱ ሰፈር የሚያገኝበት ምንጭ ይለያያል። ከለገዳዲ፤ ከገፈርሳ፤ ጉድጓድ የሚመረት ውሃ የሚያገኙ ሰፈሮች አሉ። ስለዚህ የገፈርሳ ውሃ አቅርቦትና የለገዳዲ አቅርቦትና ፍላጎት አንድ አይደለም።

ለምሳሌ ለገዳዲ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ይሰጣል፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፤ አራት ኪሎ የሚያገኘው ከለገዳዲ ነው። ስለዚህ ለገዳዲ ጫና አለበት። በዚህ ምክንያት አንዳንድ የጉለሌ ሰፈሮች ውሃ የሚያገኙት በሳምንት አንድ ቀን ነው። ይህ የሆነው አየር መንገድን፤ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታልን ፈረቃ ማስገባት አይቻልም። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም ቀን እንጂ ማታ ውሃ አያገኝም። ማታ ማታ የሚዘጋው ጉለሌ ቀጨኔ፤ ሽሮ ሜዳ ማታ ማታ ውሃ እንዲያገኙ ለማስቻል ነው። ሁሉም አካባቢዎች ውሃ የሚያገኙበትን መንገድ ተመሳሳይ ማድረግ አይቻልም።

አዲስ አበባ ውሃ ሥርጭት ፍትሃዊ አይደለም የሚል ጥያቄ ይነሳል። ከለገዳዲ ውሃ የሚያገኘው አያት የሚኖረው ሕዝብ ገፈርሳ ጋር አንድ ማድረግ አይቻልም። በተለያየ የመሬት አቀማመጥ የሚገኝ ሰፈር የአዲስ አበባ ማህበረሰብ የተለያየ የውሃ ሥርጭት ማግኘቱ አይቀርም። ኮንዶሚኒየም ቤት ላይ ውሃ የሌለው ከሶስተኛና አራተኛ ፎቅ በላይ ነው፡፡

የታችኛው ውሃ ሲያገኝ የላይኞቹ ተመልካች የሚሆኑበት ሁኔታ ይታያል። ይህ ከቴክኒሻኖች ጋር እሰጥ እገባ እምንገባበት ነው። ከፍላጎቱ ባነሰ ውሃ ሲሰራጭ ሁልጊዜም የቀደመ እና ቅርብ የሆነ ውሃ የሚያገኝበት ሁኔታ ይፈጠራል። ይህን ለማስተካከል 1400 ቫልቮች ገጥመን እየሰራን ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- የተቋሙ ሠራተኞች ሥራቸውን አክብረው እንዲሰሩ ከማድረግ አንጻር ቁጥጥር እና ክትትላችሁ ምን ይመስላል?

አቶ ፍቃዱ፡– የውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ከውሃ አቅርቦትና ፍላጎት ጋር ተያይዞ ሰፊ ቅሬታ አለበት። አንድ ሰው ውሃ ሲያጣ ይከፋል፤ በዛ መስመር ሲታሰብ በህብረተሰቡ በኩል በርካታ ጥያቄዎች ይነሳሉ። የሚነሳውም ከታች ወዳለው ሠራተኛ ይሄዳል። ለእኛ አንዱ መለኪያችን ህብረተሰቡ ቅሬታ ሲያቀርብ ማን የሚባል ቴክኒሻን ብለን ስንጠይቅ እከሌ የሚባለው ካሉን ለርምጃና ለቁጥጥር ጥሩ ነው።

ከ2011 ዓ.ም በኋላ ከህንድ ሀገር በዓለም ባንክና በኔዘርላንድ መንግሥት ድጋፍ የመስክ መለኪያ አመራር የሚባል ከአመራር እስከ ባለሙያ ያለው ሠራተኛ በሙሉ እስከ ሶስተኛ ወገን ማለትም ቆፋሪ፤ ቆጣሪ አንባቢ ማሰልጠኛ ተቋም ገብተው እንዲሰለጥኑ ተደርጓል። በዚህም የሚታይ ለውጥ መጥቷል። ለኬንያ ለሌሎች ሀገራት ሥልጠና እንድንሰጥም አስችሎናል።

ከሥልጠና በኋላ ያለውን ለውጥ ሶስተኛ ወገን መዝኖ ማደግ አለበት በሚል እሳቤ ኦሮሚያ፤ አማራና ሌሎች ክልሎች እንዲጠቀሙበት ተሞክሮ ሆኖ ቀርቧል። በተቋሙ ቋሚና የኮንትራት ሠራተኛው ብዛት ከአራት ሺ በላይ ነው። በተጨማሪም በሶስተኛ ወገን የምናሰራቸው ያን ያህል ሠራተኞች አሉ።

ቆጣሪ የሚነበበው በሶስተኛ ወገን ነው። ስለዚህ ቋሚና ጊዜያዊ እንዲሁም ሶስተኛ ወገን የሆኑ ሠራተኞች ከስምንት ሺ እስከ 10 ሺ ሰው በንቃት የሚሳተፍበት ተቋም ነው። ይህ ሁሉ ሠራተኛ በቀጥታ ከሕዝብ ጋር የሚገናኝ ነው። ቆጣሪ አንባቢ፣ ጠጋኝ ወደ የማህበረሰቡ ቤት ሄዶ አንኳኩቶ ገብቶ ነው የሚሰራውና በዚህ ሂደት በህብረተሰቡ የሚነሱ ቅሬታዎች አሉ፡፡

ሠራተኞቻችን ላይ ማሻሻል ያለብን ሥራ አለ። ካለው ውስብስብ ችግር አኳያ 1127 ፈረቃ አለ። በዚህ መንገድ መሥራታቸው ለማረጋገጥ 30 ሺ ደንበኞች ከባለፈው ሐምሌ አንድ እስከ ባለፈው መስከረም 30 ደንበኛ አረጋግጠናል። ባለሙያዎች ቢሮ ተቀምጠው የውሃ አቅርቦት ጥያቄና መሰል አገልግሎቶችን ጠይቆ በአግባቡ መስተናገዱን እየደወሉ ያረጋግጣሉ። እነዚህ ሰዎች ለቴክኒሻኑ ሪፖርት አያደርጉም፤ ሰፈርም አይሄዱም በድንገት የሚያረጋግጡት ስልክ እየደወሉ ውሃ ማግኘትና አለማግኘታቸውን ነው። 80 በመቶውን ለማረጋገጥ አቅደን አሳክተናል። ይህም ሠራተኛው በጥሩ ሁኔታ እየሰራ እንደሆነ ማሳያ ነው። ይህ የሚሆነው ውሃ ችግር ሆኖ በሳምንት አንድ ቀን ሁለት ቀን ነው የሚገኘው ሌሊት ነው የሚመጣው የሚለን በጣም ደስተኛ ባልሆነ ማህበረሰብ ገብቶ የሚሰራ ሥራ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- በአሠራር ሕግ ጥሰት ምክንያት እስካሁን ተቋሙ ርምጃ የወሰደባቸው ሠራተኞች የሉም?

አቶ ፍቃዱ፡- እኔ ጋር መረጃ የለም። ያለው እርካታ የሌለው ደንበኛ ነው። 240 ጉድጓድ አለ ሲባል የሚሰሩት በሽፍት ነው። ከሶስተኛ ወገን ውጭ አንድ ጉድጓድ ላይ አራት ሰው አለ። በየጊዜው ርምጃ ይወሰዳል። ማስጠንቀቂያ ከመጻፍ እስከ ደሞዝ ቅጣት ብሎም ከሥራ እስከ ማሰናበት የደረሰ ርምጃ ይወሰዳል። ሥራው ከህብረተሰቡ ጋር የሚያገናኝ በመሆኑ ሠራተኛ በየጊዜው ርምጃ የሚወሰድበትና የሚቀጣበት ሁኔታ አለ።

አዲስ ዘመን፡- ከባለድርሻ አካላት ጋር ያላችሁ ቅንጅታዊ አሠራር ምን ይመስላል?

አቶ ፍቃዱ፡- አሁን ላይ ተናቦ ከመሥራት አንጻር በአንጻራዊነት የተሻለ ነው። ከኤሌክትሪክ ኃይል፤ ከመንገዶች ባለሥልጣን ጋር ከበፊቱ በተሻለ መንገድ በቅርበት እየሰራን ነው። ነገሮች ከዚህ በላይ ሊሆኑ የሚችሉት ቴክኖሎጂ መጠቀም ስንችል ነው። በመተባበርና በመተጋገዝ በቅንጅት ቴክኖሎጂን አስደግፈን መሥራት ስንችል ነው።

አንድ ቦታ ላይ ችግር ሲገጥም የሆነ ሰፈር ውሃ የማይጠጣ አለ። አንድ ሳምንት ውሃ ተቋረጠ ማለት ውሃ በፈረቃ የሚያገኝ ማህበረሰብ አንድ ፈረቃ ዘለለው ማለት ነው። ስለዚህ ከዚያ በላይ ቀናት ውሃ ሊያጡ ነው። ችግሩ አለ፤ ማህበረሰቡ የችግሩን ስፋት ሊረዳ ይገባል። ያለው የውሃ እጥረት የድህነት ጥያቄ ነው። ድህነት ሲቀረፍ ችግሩም ይቀረፋል። የውሃ አቅርቦት ችግር የፈቱ ሀገሮች ድህነትን ያሸነፉ ሀገሮች ናቸው። ውሃ ትልቅ ኢንቨስትመንት ነው። እዚህ ተጀምሮ እዚህ አያልቅም። ስለዚህ ትልቅ ገንዘብ የሚጠይቅ በመሆኑ ለውሃ እጥረት እየተዳረግን ነው። ይህን በቀጣይ የፋይናንስ እና የኢኮኖሚ አቅማችን በማሳደግ የሚፈታ ነው።

አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን።

አቶ ፍቃዱ፡- እኔም አመሰግናለሁ።

መክሊት ወንድወሰን እና ሞገስ ተስፋ

አዲስ ዘመን ህዳር 4/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You