“ከዚያ በፊት የነበረውን ሁኔታ ለመግለጽም ይቸግረኛል፤ እጅግ በከፋ ሁኔታ ውስጥ ሆኜ ነበር የምኖረው። የአምስት ዓመት ልጅ አለችኝ። እርሷን ይዤ በየቤቱ እየተንከራተትኩ በየግድግዳው ስር፣ በየበረንዳው፣ በየማዕድ ቤቱ ተጠግቼ እያደርኩ ነበር የምኖረው” እንዲህ የሚሉት በቅርቡ በህገ ወጥ መንገድ ተይዘው ከነበሩ የቀበሌ ቤቶች መካከል በከተማ አስተዳደሩ አማካኝነት ከሌቦች ተነጥቀው ቤት ከተሰጣቸውና መኖሪያ ቤት ካልነበራቸው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ውስጥ የሚገኙ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች መካከል አንዷ የሆኑት ወይዘሮ ፀሐይ ሰይድ ናቸው።
ወይዘሮዋ ይቀጥላሉ፤ “በዚህ መንገድ በየቤቱ እየዞርኩ በየቀኑ የሰው ፊት ማየቱ፣ ሰው ማስቸገሩ፣ ልጅ ይዤ በየበረንዳው ማደሩ ቢቸግረኝ የሰዎችን ልብስ እያጠብኩና የቀን ስራም ቢሆን ሰርቼ በማገኛት ገንዘብ መነን አካባቢ በወር ስምንት መቶ ብር አንዲት ትንሽዬ መጠለያ ቢጤ ተከራየሁ። ሆኖም በየሰው ቤቱ እየተንከራተትኩ በየበረንዳው እየተሳቀቅኩ ከማደር በመውጣቴ ለጊዜው ደስ ቢለኝም ውሎ አድሮ ግን ለህይወቴ አስጊ የሆነ ከበፊቱ የባሰ ሌላ ከባድ ችግር ገጠመኝ። ቤቷ በጣም ጠባብ ከመሆኗ የተነሳ እግር ስለማታዘረጋ ለረጅም ጊዜ እግሬን አጥፌ ከግድግዳው ጋር ተደግፌ ስለምተኛ ከአንዴም ሁለት ሶስት ጊዜ የአንጀት መጠላለፍ አጋጥሞኝ እግዚአብሔር ይስጣቸው በምኒልክ ሆስፒታል እርዳታ ቀዶ ጥገና ተደርጎልኝ ከሞት ተርፌያለሁ”።
መኖሪያ ቤት በሌለበት ሁኔታ የሚኖረው እንዲህ ዓይነቱ ህይወት እንግዲህ ቤት ምን ያህል ለሰው ልጆች አስፈላጊ ነገር መሆኑን የሚያሳይ ነው። እንዲህ የምንለው ግን ቤት ከሰው ልጅ መሰረታዊ ፍላጎቶች መካከል አንዱ መሆኑን አጥተነው ሳይሆን የባለ ታሪኳን ሁኔታ “ቤት ከመሰረታዊ ፍላጎትም በላይ ነው” በሚለው የፀሐፊው የግል ፍልስፍና መነጽር ልናስመለክታችሁ ስለወደድን እንጂ። የሰው ልጅ መሰረታዊ ፍላጎቶች የሚባሉት ምግብ፣ ልብስና መጠለያ ወይም መኖሪያ ቤት ሲሆኑ መሰረታዊ ፍላጎት የሚለው ጽንሰ ሃሳብ ትርጉሙም ዋና፣ ሊታጣ የማይገባው፣ በህይወት ለመኖር የግድ አስፈላጊ የሆነ ማለት ነው።
ልብ በሉ እንግዲህ ሰዎች እዚህ ጋር የመኖሪያ ቤት “ከመሰረታዊ ፍላጎትም በላይነት” ከስሙ ይጀምራል። ምክንያቱም መሰረታዊ ፍላጎት ማለት የሰው ልጅ በህይወት ለመኖር ሊያጣው የማይገባው፣ ለመኖር የግድ አስፈላጊ ጉዳይ ከሆነ መሰረታዊ ፍላጎት የሚባሉት ደግሞ ምግብ፣ ልብስና መጠለያ ቤት ከሆኑ ሁሉም መሰረታዊ ፍላጎቶች “መኖሪያ” ናቸው ማለት ነው፤ ግን አይደሉም። ለምን? ምክንያቱም የአንድ ሃሳብ ትርጉም ከስያሜው ይጀምራል። በዚህም መሰረት ለመኖር የግድ አስፈላጊ ከሆኑት ከሦስቱም መሰረታዊ ፍላጎቶች “መኖሪያ” የሚለው ስያሜ የተሰጠው ለ“መኖሪያ ቤት” ብቻ ነው። ሌሎቹ “ምግብ”፣ “ልብስ” ተባሉ እንጂ “መኖሪያ ምግብ”፣ “መኖሪያ ልብስ አልተባሉም። እናም ምግብና መጠለያ “ለመኖር የሚያስፈልጉ መሰረታዊ ፍላጎቶች” ሲሆኑ መኖሪያ ቤት ግን “ለመኖር የሚያስፈልግ” መሰረታዊ ፍላጎት ከመሆኑም በላይ “መኖሪያ” ጭምር ነው። እዚህ ጋር “ለመኖር የሚያስፈልግ” የሚለው ሃረግና “መኖሪያ” የሚለው ቃል ከፍተኛ የትርጉም ልዩነት አላቸው። ምክንያቱም ሰው ለመኖር ምግብና ልብስ ያስፈልጉታል፤ መኖሪያ ሊሆኑት ግን አይችሉም። ባለታሪካችንን ወይዘሮ ፀሐይንም ያጋጠማቸው ይኸው ነው።
ምግባቸውን የቀን ሥራም ቢሆን ሰርተው እንደምንም አገኙ፤ የሚለብሱትን ልብሳቸውንም እንደዚሁ። በመከራና በችግር ውስጥ ሆነውም ለመኖር ከሚያስፈልጉ የሰው ልጅ መሰረታዊ ፍላጎቶች መካከል ሁለቱን ምግብና ልብስ እያገኙ ነበር፤ ሆኖም መኖሪያ ቤት አልነበራቸውምና ሴትዮዋ መኖር አልቻሉም። “ወንድሜ መብላት መጠጣቱ ትርጉም የለውም ዋናው መጠለያ ነው” የሚሉት ወይዘሮ ፀሐይም የሚያረጋግጡት ይህንኑ እውነታ ነው። እናም እዚህ ጋር “መኖር” ሲባል “በህይወት መኖር” ማለት እንዳልሆነ ይሰመርበት። መኖር አልቻሉም ሲባል “ሰው መኖር እንደሚገባው” መኖር አልቻሉም ማለታችን ነው። ሰው መኖር እንደሚገባው ሆኖ ለመኖር በህይወት ለመኖር የሚያስፈልጉት ምግብና ልብስ ብቻ ሳይሆኑ የሰው ልጅ መኖር እንደሚገባውን ለመኖር የሚያስፈልገው መኖሪያ ያስፈልጋልና! ለሰው ልጅ ለመኖር አስፈላጊም፣ መኖሪያም ሊሆን የሚችለው ደግሞ ቤቱ ብቻ ነው። ይህም ቤት የሚያስፈልገው ለመኖር ብቻ ሳይሆን የተሻለ ህይወትም ለመኖር ጭምር መሆኑን አመላከች ነው።
ይህንን የተገነዘቡት ወይዘሮ ፀሐይም ከሰባት ዓመታት በፊት ካለፈው ሥርዓት ጀምረው ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ቤት ለማግኘት መንግስትን ደጅ ጠንተዋል። ሆኖም በጊዜው የነበረው የጁንታው መንግስት ለራሱ እንጂ ለዜጎች ደንታ አልነበረውምና፣ “ቤት ለመጠየቅ ስንሄድ ገና ሳንጠይቃቸው የሚያሳዩህ ፊት እጅጉን ይከብዳል፤ ሃሳባችንን እንኳን በሥርዓት ሳይሰሙ ‘ማን ጠርቶሽ መጣሽ’ ብለው አመነጫጭቀው ይመልሱናል” ይላሉ ወይዘሮ ፀሐይ። “የአሁኑ መንግስት ግን” ይላሉ ወይዘሮ ፀሐይ… “የአሁኑ መንግስት ግን ወዲያውኑ ምላሽ ባይሰጡኝም ችግሬን ቀርበው ስለሚያዳምጡኝ ወዲያው እንደሰጡኝ ነው የምቆጥረው፤ ደግሞም አይዞሽ ይሰጥሻል ባሉኝ መሰረት ይኸው ከጥር 26 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ የምኖርበት ወረዳ(አራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 ማለታቸው ነው) አስተዳደርና አመራሩ ባደረገልኝ ከፍተኛ ጥረት እግሬን ዘርግቼ እንደልቤ የምተኛበት መኖሪያ ቤት አግኝቻለሁ። ለዚህም የወረዳችን አመራሮች እጅግ አድርጌ አመሰግናለሁ”።
የበፊቱን ህይወትና የአሁኑን ሲያነጻጽሩትም ወይዘሮ ፀሐይ፤ “መብላት መጠጣቱ ትርጉም የለውም ዋናው መጠለያ ነው ብዬሃለሁ፤ አሁን እግዚአብሔር ይመስገን ቤት አግኝቻለሁ፣ የቤት ኪራይ ምን እከፍላለሁ እያልኩ በየወሩ አልጨነቅም፣ ሰርቼ የማገኛትንም ለዕለት ጉርሴ እና ለልጄ አውላታለሁ፣ ቆርቆሮ በቆርቆሮ መጠለያም ብትሆን አዕምሮዬን አሳርፌ የምኖርባት ቤት አግኝቻለሁ፣ ትልቁ ጭንቀቴ ተቃልሎልኛል” ይላሉ።
የወረዳ 9 ቤቶች ልማት አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ማሞ በበኩላቸው “ወረዳችን በማህበረሰቡ ትብብርና ጥቆማ አማካኝነት በህገ ወጦች ተይዘው የነበሩ የቀበሌ ቤቶችን አስለቅቀን ከፍተኛ ችግር ለነበረባቸው የማህበረሰባችን ክፍሎች በችግራቸው ልክ በቅደም ተከተል ለይተን ቤቶችን ሰጥተናል። በዚህም በወረዳችን ባለፉት አስር ወራት ውስጥ አስር የሚሆኑ ቤቶችን ለችግረኞች አስተላልፈናል። ከእነዚህ መካከል ወይዘሮ ፀሐይ አንዷ ናቸው” ይላሉ። ይህም በመንግስትና በህብረተሰቡ መካከል ከፍተኛ መተማመን እንዲፈጠር አድርጓል። መኖሪያ ቤት ያገኙ ችግረኛ የማህበረሰብ ክፍሎችም በኢኮኖሚያቸውና በኑሯቸው ላይ መሻሻል እንዲመጣ አስተዋፅኦ አድርጓል። ይህም አሁን ላይ ያለውን ኑሮ ውድነት ተቋቁመው እንዲያልፉ ከማገዙም በላይ አጠቃላይ በኑሯቸው ላይ የበለጠ ተስፋ እንዲያደርጉ ስንቅ ሆኗቸዋል። እኛም እንላለን በጎጥ፣ በብሔር፣ በዝምድና፣ በሙስና ሦስት አራት ኮንዶሚኒየም በስማቸው እያስተዳደሩ፣ ያም አልበቃ ብሏቸው ወርደው ድሃውና የድሃ ድሃው ጉሮሮ ላይ ቆመው አስርና አስራ አንድ ክፍል የቀበሌ ቤት ከሚያከራዩ አይጠግቤ ስግብግቦች ተቀንሶ በዚህ መንገድ ችግር ውስጥ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን የመስጠቱ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥል እንላለን። ምክንቱም እንዲህ ዓይነቱ አሰራር ለድሃ ወገኖቻችንን ብቻ ሳይሆን በሌቦች ምክንያት ድሃ ለሆነችው ሃብታሟ አገራችንም ተስፋን የሚሰጥ መልካም ተግባር ነውና
ይበል ካሳ
አዲስ ዘመን ሰኔ 21/2013