የዛሬው አዲስ ዘመን ድሮ ዓምዳችን አዲስ ዘመን ጋዜጣ በ1956 ሰኔ ወር እትሞቹ በልማት ላይ በማተኮር ካስነበባቸው ዘገባዎች የተሰባሰቡ ናቸው። ዘገባዎቹ ዜና ብቻ አይደሉም፤ በወቅታዊ ሁኔታ ላይ የተጻፈ አርቲክልም ተካቶበታል።
ክረምትና ግብርና
ከሊቀ ስዩማን አክሊሉ ግብረኪሮስ
ክረምት ከረመ ከሚለው ከግእዝ ግስ የተገኘ ነው። መክረም አከራረም፣ ማለት ይሆናል። እንደ ግእዙ አነጋገር በአተ ክረምት ማለት የክረምት መግባት ማለት ነው። እስከአሁን ጸደይ የተባለው የበልግ ወራት ነበር። ከትናንት ከሰኔ ፳፮ ቀን ጀምሮ ክረምት ወራት ይቀጥላል። ከመጋቢት ፳፮ ቀን ጀምሮ የዘነመው የበልግ ዝናም ነው። ከእንግዲህ ወዲህ ግን በጸደይ ስፍራ ክረምት ስለተተካ የሶስት ወር ክረምት ገባ ፤የክረምት ዝናም ዘነመ ይባላል።
የክረምት አገልግሎት ከትናንት ከሰኔ ፳፮ ጀምሮ እስከ መስከረም ፳፮ ቀን ፶፯ አ.ም ድረስ ይቀጥላል። በዚህ በክረምት ወራት የውሃ ባህርይ የበለጠ ሀይል እንደማግኘቱ መጠን ምንጮች ይመነጫሉ፤ ወንዞች ይሞላሉ፤ አዝርእትና አትክልት ይበቅላሉ። ሙቀቱ ለውሃው ይሰማዋል። በዚህ አለም ያሉ አዝርእትና አትክልት ይበቅላሉ። ይባዛሉ ፤ያፈራሉ።
ምድር በዚህ በክረምት ወራት በጥንተ ፍጥረት የተሰጣትን መልካም ዝግጅት ይዛ ትታያለች። ዘራቸው ፍሬያቸው ከአካላታቸው ውስጥ የሚገኝውን እነዱባን ፣እነቅልን፤ ዘራቸው ከታች ከስራቸው የሚገኘውን እነሽንኩርትን ፣እነድንችን ፤ ዘራቸው ፍሬያቸው ከጎናቸው ከወገባቸው የሚገኝውን እነ ባህር ማሽላን እነባቄላን ፤ዘራቸው ፍሬያቸው ከራሳቸው ላይ የሚገኘውን እነ ስንዴንና እነገብስን በማስገኘቷ የተፈጥሮዋን ስርአት ትመሰክራለች፡
እንዲሁም በጥፍር የሚቀጩ እነወይንን እነ ትርንጎን ፣ በማጭድ የሚታጨዱ እነባቄላን እነ ስንዴን በመጥረቢያ የሚቆረጡ እነዋንዛን እነዝግባንና እነ ወይራን በጥንት ተፈጥሮዋ ሁኔታ ይዛ በልምላሜ ስትታይና ስታሸበርቅ ተመልካቾቿን ሁሉ ወደ ጥልቅ አድናቆት ትስባለች።
በኢትዮጵያ ስራ ፈትነት በጣም የተወገዘና የተረገመ ነው፤ በስጋውያኑም በመንፈሳውያኑም ዘንድ የተጠላ ነው። የገበሬነትን ስራ የሚፈጽሙና በማረስ በመቆፈር ራሳቸውን ረድተው ሌሎችን የሚረዱ በዚህ በአለሙ ውስጥ ያሉት ስጋውያኑ ብቻ አይደሉም።
ሰኔ 27 ቀን 1956 ዓ.ም
የምድር ባቡር መስመር ለመዘርጋት የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ
ከአዲስ አበባ እስከ ጅቡቲ ካለው የኢትዮጵያና የፈረንሳይ የምድር ባቡር መስመር አንስቶ ወደ ኢትዮጵያ ደቡብ ማለትም ወደ ሲዳሞ የሚወስድ የምድር ባቡር መስመር ለመዘርጊያ የሚሆን የገንዘብ ብድር ስምምነት ኢትዮጵያና ፈረንሣይ ፓሪስ ላይ የተፈራረሙ መሆናቸውን የደረሰን ወሬ አመልክቷል።
ይህን የአምሳ አምስት ሚሊዮን ፍራንክ ብድር ስምምነት ፓሪስ ላይ የተፈራረሙት በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ክቡር አቶ ማሞ ታደሰ በጠቅላይ ሚኒስትር ሚኒስትር ዴኤታ ሲሆኑ በፈረንሣይ መንግሥት በኩል ደግሞ በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ተራድኦ አሰጣጥ ም/ሚኒስትር ሙሴ ሚሼል ሐቢብ ደ.ሎንክ ናቸው።ይህን አዲስ የባቡር መስመር ለመዘርጋት አስፈላጊውን መሣሪያ እንዲያቀርቡ የሚመደቡት የፈረንሣይ ኩባንያዎች መሆናቸውን ወሬው በድጋሚ አስታውቋል።
(ሰኔ 30 1956 ዓ.ም የወጣው
አዲስ ዘመን በፊት ገፁ የዘገበው)
ከኢትዮጵያ ወደ ኬንያ የሚወስደው 430 ኪ.ሜ
መንገድ ጥናት ተከናወነ
የአውራ ጎዳና ባለሥልጣን ከዲላ እስከ ሞያሌ 430 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው፤ ለአገር ውስጥና ለኢንተርናሽናል አገልግሎት የሚውል ታላቅ አውራ ጎዳና ለመቀየስ የመጀመሪያ ደረጃ ጥናት አከናውኗል።
ባለሥልጣኑ ይህንን ረዥም አውራ መንገድ ቅየሳ ሥራ ለመፈጸም ከ፲፫ እስከ ፲፭ ወሮች ጊዜ እንደሚያስፈልገው በጥናቱ ተረጋግጧል። የቅየሳውም ሥራ የሚጀመረው በሐምሌ ወር አጋማሽ ግድም ሲሆን፤ ይህንን መንገድ እጅግ ለምነቱ በታወቀው በቦረና አውራጃ ውስጥ አቋርጦ ኢትዮጵያንና ኬንያን በየብስ በኩል ያለባቸውን ችግር ሊያገናኝ የሚችል ነው።
ኢትዮጵያንና ኬንያን ቀደም ብሎ ለበጋ ወራት ብቻ የሚያገለግል የየብስ መገናኛ የነበራቸው ቢሆንም ይህ አሁን ከዲላ እስከ ሞያሌ ድረስ የሚቀየሰው መንገድ ሲፈጸም ሁለቱን ወዳጅ ሀገሮች በመገናኛ በኢኮኖሚና በባህል ረገድ ከመቼውም ይልቅ በይበልጥ ሊያቀራርብ የሚችል መሆኑ አያጠራጥርም ።
የአውራ ጎዳና ባለሥልጣን ይህን ፬፻፴ ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውን መንገድ ለመቀየስ በመጀመሪያ አራት የቅየሳ ጓዶች ለመላክ አስቧል። እንዲሁም በሚቀጥለው ነሐሴ ወር ሌላ አራት ተጨማሪ የቅየሳ ጓዶች በመላክ ሥራውን በተቻለ መጠን ፍጻሜ ለማድረስ ወስኖአል።
ባለፈው ሚያዝያ ወር አጋማሽ ቶኪዮ ላይ ተሰብስበው የነበሩ የአርባ አገር መልእክተኞች ኩታ ገጠም ከሆኑት አገሮች ጋር የየብስ መገናኛ ዘዴን በበለጠ ለማስፋፋት ስምምነት ያደረገ መሆኑ የሚታወስ ነው። የአውራ ጎዳና ባለሥልጣንም የሁለተኛውን የአምስት ዓመት ፕላን መሠረት በማድረግና የዚህንም የስብሰባ ዓላማ በመደገፍ፤ ለሁለተኛ ጊዜ የወሰደው ርምጃ ይህንኑ ከኬንያ ጋር የሚገናኘውን ታላቅ የኢንተርናሽናል አውራ መንገድ ቅየሳ ሥራ መጀመር ነው ሲል ከአውራ ጎዳና ባለሥልጣን የማስታወቂያ ክፍል የተላለፈው ወሬ ገልጧል።
120 ቤቶች በዘመናዊ
ዕቅድ ተሠርተው
ለሕዝብ ሊሰጡ ነው
የሕዝቡን የመኖሪያ ቤት ችግር ለማቃለል በሚመጣው ዓመት ፩፻፳ ቤቶች በአዲስ አበባ ከተማ በአራቱም ማዕዘን የሚሠሩ መሆናቸው ታውቋል። እነዚህን ቤቶች የሚያሠራው የብሔራዊ ሎተሪ አድሚኒስትራሲዮን ነው ።
በደብረዘይት መንገድ በጅማ መንገድ በደሴ መንገድና በአምቦ መንገድ የሚሠሩት እነዚህ ቤቶች ስፋት ከ፪፻ ካሬ በማያንስ ቦታ ላይ መሆኑ ታውቋል። በእያንዳንዱ ሥፍራ የሚሠራው ቤት መጠን ፴ ነው።
ቤቶቹ ከአሁን በፊት የሕንፃ ኰሌጅ የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት በመተባበር በፊት በር ከፖሊስ ጋራዥ ከፍ ብሎ ለዓይነት ሠርተዋቸው ከነበሩት ባለ ፫ ከፍል ቤቶች ጋር ተመሳሳይ ይሆናሉ። ቤቶቹ በጥንካሬም ሆነ በዘመናዊነት እቅድ ውበት እንዲኖራቸው ሆነው የሚሠሩ ናቸው።
የብሔራዊ ሎተሪ ደርጅት ይህን ያቀደው ፤በየጊዜው በሎተሪ ዕድል በርካታ ገንዘብ የደረሳቸው ሰዎች ብዛት ከፍ ያለ መሆኑን ቢያውቅም ፤በልዩ ልዩ ምክንያት ዝንባሌያቸውን ወደ ቤት ሥራ ያሠማሩት ጥቂቶች ብቻ በመሆናቸው ድርጅቱ ራሱ አርአያ በመሆን የመኖሪያ ቤቶችን ችግር ለማቃለል በማሰብ መሆኑ ተገልጧል።
ይህ ዓይነቱ የዕቁብ ቲኬት ዕጣ የሚወጣው በወር በወሩ ሲሆን ፤ለየወሩ ዕድለኞች የተመደቡት አስር አስር ቤቶች ናቸው። ስለዚህ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ፩፻፳ ሰዎች የራሳቸው የሆነ ቤትና ቦታ ባለቤቶች ይሆናሉ ማለት ነው።
ዕድለኞቹ በ፶ ሳንቲም ቲኬት የነዚህን ቤቶች አሸናፊ ቁጥሮች እየያዙ ሲቀርቡ ፤አድሚኒስትራሲዮኑ ቤቱን ከነቁልፉ ወዲያውኑ ያስረክባቸዋል።
በጠቅላይ ግዛት ፤በአውራጃዎችና በወረዳዎች የሚኖሩ ዕድለኞች ቤቱን ተረክበው ለመኖሪያ ፤ወይም ለኪራይ ሊያውሉት ባይሹ አድሚስትራሲዮኑ የቤቱን ግምት ወዲያውኑ ይከፍላቸዋል።
ሰኔ 24 ቀን 1956 ዓ.ም
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ሰኔ 21/2013