ሰዎች ለዘመናት ልብስን ለአካላቸው መሸፈኛ አድርገውት ቆይተዋል። በዘመን ዑደት ግን አልባሳት አካልን መሸፈኛ፣መዋበያና ጤንነት መጠበቂያ አድርገው በመጠቀም ጠቀሜታውን ከፍ አድረገውታል። አልባሳት ዋነኛ ተግባራቸው የሆነውን አካላችንን ከመሸፈን ባለፈ አምረንና ተውበን እንድንታይ ያደርጉናል።
የበጋውን ሙቀት ለመቋቋም የዚያን ወቅት ወበቅ ለመቻል ሳሳ ያለና ለነፋሻማው አየር ተስማሚውን አለባበስ መከተል ግድ ይላል። ያኔ የወቅቱን ፋሽን ተከትሎ የሚቀርቡ የበጋ ልብሶች ሸመታ ይፈጸማል። በበጋው ወቅት ኧረ ሙቀቱ ገደለኝ እንደው ምን ተሻለኝ?” ላለ ወቅትን ያገናዘበ አለባበስ ተከተል ብለን የመከርነውን ያህል አሁን ክረምቱ ገብቶ ሰዎች “እትት” ማለት መጀመራቸውን ስናይ ወፈር ያለ ጃኬት አልያም ሹራብ ለብሳችሁ እትቱ ማለቱን አቁሙ ማለታችን የግድ ነው።
አዎ ፀሀይ ጉልበት አጥታ ጭጋጉ ሲበረታ ሙቀት ቦታውን ለቅዝቃዜ ስትለቅ ደግሞ ሰውነት በብርድ እንዳይጎዳ አካላችን በቅዝቃዜ እንዳይረታ የሰውነት ሙቀትን የሚጠብቁ አልባሳት መፈለጋችን ግድ ነው። ሰኔ ይዞት የመጣውን ቅዝቃሴ ወራት የሚዘልቅ ነውና ለክረምት የቀረቡ አልባሳት ላይ ትኩረት አድርገን በክረምቱ ፋሽንም ሙቅትም የሚያደርጉን አልባሳትን የተመለከተ ፅሁፍ በዚህ መልክ አሰናድተን እነሆ ብለናል።
አልባሳት እንደየ ወቅቱና ጊዜው የተለያየ ጠቀሜታን ያላብሱናል። የክረምቱን ቅዝቃዜ ተከላክለው ሰውነታችን ሙቀቱን እንደጠበቀ እንዲቆይ በጋው በሚያስከትለው ሙቀት አካላችን በሙቀት ምቾት እንዳያጣ ዋነኛውን ሚና ይጫወታሉ። ዛሬ ላይ በተለያየ ጥናትና ምርምሮች በመታገዝ አልባሳት ለሰዎች የተለየ ውበት እንዲያላብሱና ጤንነትን የሚጠብቁ ብለውም የሚንከባከቡ እንዲሆኑ ተደርገው ተሰርተው ለገበያ ቀርበዋል።
በተለይም ወቅትን መሰረት አድርገው የሚለበሱ አልባሳት ተጠቃሚዎች ይመርጡዋቸው ዘንድ ለዲዛይናቸውም ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ይዘጋጃሉ። የክረምት አልባሳት የሰውነት ሙቀትን ከመጠበቅ ባለፈ እንደ ፋሽን ተወስደው ውበትን የሚያጎናፅፉ አምረንና ሽክ ብለን እንድንታይ የሚያደርጉም ናቸው። የአዲስ አበባ ጎዳናዎች ክረምቱን በአዳዲስ የክረምት ፋሽን ልብሶች መሙላታቸው ያለምክንያት መች ሆነና።
የክረምቱን ወቅት መግባት ተከትሎ የሰዎች አለባበስ ተቀይሯል።በፊት የነበረው ቀለል ያለ አለባባስ ሙቀት ወደሚሰጡ ሹራቦችና ካፖርቶች ተለውጧል። በከተማዋ የተለያዩ ዋና ዋና ጎዳናዎች ላይ የበዙት የተዘጋጀ ልብስ መሸጫዎችም በየመደብሮቻቸውና ደጆቻቸው ላይ ክረምቱን ያማከለ፣ በሰዎችም ወቅቱን ተከትሎ የሚፈለጉ ውበትም ጥራትም የተላበሱ አልባሳት በልብስ መስቀያዎቻቸው በርክተዋል።
በሱቆቹ ወቅቱን ያገናዘበ የክረምት ፋሽን አልባሳት በየበራቸው በልብስ ማሳያ አሻንጉሊቶች ተወድረው ለተመልካች አጓጊ ተደርገው ይቀርባሉ። ታዲያ በጋውን በተለያዩ አልባሳት ከፊት አሰልፈው ለተጠቃሚ ሲያቀርቡ የቆዩት የተዘጋጁ ልብሶች መሸጫ ሱቆች በአሁኑ ወቅት የሚፈለጉት የክረምት አልባሳት መሆናቸውን አሳምረው ያውቁታልና የልብስ መስቀያቸውን በክረምት አልባሳት ሞልተውታል።
በመዲናችን በፋሽን አልባሳት በስፋት ከሚታወቁት ሰፈሮች መካከል ፒያሳ አንዱ ነው። የክረምት አልባሳት አይነቶች፣ ገበያና ተፈላጊነት ምን ይመስላል? የሚለውን ምላሽ ለማግኘት ቅኝት ስናደርግ ከሲኒማ ኢትዮጵያ ጀርባ የሚገኙ ተርታውን ተሰልፈው ከሚገኙት የፋሽን አላባሳት መካከል አንዱ ወደሆነው ገባን።
ሳባ በአካባቢው ላይ ታዋቂ ከሆነው የፋሽን አላባሳት መሸጫዎች መካከል አንዱ ላይ ለተጠቃሚዎች አልባሳት ለመሸጥ ድርድር ላይ ሆና አገኘናት። በክረምት ወቅት እጅግ ተፈላጊ የሆኑ አልባሳት በሴቶችም በወንዶችም ወፈር ያሉና የሰውነት ሙቀት የሚጠብቁ እንዲሁም ዝናብን የሚቋቋሙ ልብሶች መሆናቸውን ትገልፃለች።
ከወንድሟ ጋር በጋራ የምታስተዳድረው የፋሽን አልባሳት መሸጫ ሱቅዋ ውስጥ በርከት ብለው የተሰቀሉ ልብሶች ይታያሉ፤ ሁሉም ወቅቱን ያገናዘቡና በተጠቃሚዎች የሚፈለጉ መሆናቸውን የምትገልፀው ሳባ አልባሳቱ ተፈላጊነታቸው ስለሚጨምር በብዛትና በአይነት በስፋት እንደሚያቀርቡ ትናገራለች።
አካባቢው ላይ ባሉ ሱቆች በብዛት ለገበያ የሚቀርቡት አልባሳት የሰውነትን ሙቀት ለመያዝ የሚጠቅሙ ከመሆናቸው ባለፈ ፋሽን የሆኑና በደንበኞች የሚመረጡ በተለያየ ዲዛይን የተዘጋጁ መሆናቸውን ታብራራለች። የአልባሳቱ ዋጋ እንደተሰሩበት ጥሬ እቃና ተፈላጊነት እንደሚለያይ ትገልፃለች። እዚያ አካባቢ ላይ ባሉ ሱቆች የሚገኙ የወንዶች ጃኬትና ካፖርት የክረምት አልባሳት ዋጋ በአማካይ ከ800 እስከ 4300 እንደሚሸጥና በአንፃራዊነት ከሌሎች ጊዜያት የዋጋ ጭማሪ እንዳላቸው ትገልፃለች።
እዚያው አካባቢ ካለው ኖ 7 ፋሽን ጎራ አልኩ። ልብስ ሲገዛ ወዳገኘሁት ግለሰብ ተጠግቼ አወራሁት። ለክረምት የሚሆን ሹራብ ሊገዛ እንደገባ የነገረኝ ወጣት ሰለሞን ባዬ ሁሌም ክረምት ላይ ለወቅቱ የሚሆን ልብስ እንደሚሸምትና አሁን ለዚያ እንደተገኘ ያስረዳል። የሚፈልገውን እየመረጠ እንደሆነና የአልባሳቱ ዋጋ እጅግ የተጋነነ መሆኑን በአስተያየት ምልክ ተናግሯል።
በአብዛኛው ደንበኞቻቸው የሚፈለጉ የክረምት አልባሳት የሴቶችና የወንዶች ጃኬትና ካፖርቶች በጥጥና በሹራብ የተሰሩ የተለያዩ ወፍራም አልባሳት፣ ቡትስ ጫማ፣የአንገት ስካርቮችና በእራስ የሚጠለቁና ከሹራብ የሚሰሩ ኮፊያዎች መሆናቸውን የሚገልፀው ደግሞ በሜክሲኮ ቡናና ሻይ ፊት ለፊት በሚገኘው የተዘጋጁ ልብሶች መሸጫ ሱቁ ውስጥ ያገኘነው አብዲ ሲሆን፣ አልባሳቱ የሚሸጡበት ዋጋ ከሰፈር ሰፈር ከሱቅ ሱቅና ከሚዘጋጁበት ጥሬ እቃ አንፃር ይለያያል ይላል።
እዚያ አካባቢ ባሉና የበዙ የተዘጋጁ ልብሶች መሸጫዎች ውስጥ የሚገኙ አልባሳት ከፒያሳ አካባቢ ካሉ ሱቆች በዋጋ የሚቀንሱ መሆኑን ታዝቤ ጥያቄውን ለአብዱ አነሳሁለት። እዚያ አካባቢ በአማካይ ከ450 እስከ 3500 ድረስ የወንዶችና የሴቶች አልባሳት ሹራቦች፣ ጃኬቶችና ካፖርቶች በብዛት እንደሚሸጡ ነገረኝ። ለዚህ ልዩነት መነሻ የአካባቢው የገበያ ሁኔታና በአካባቢው የሚኖረው ህብረተሰብ የመግዛት አቅም እንዲሁም የሱቆቹ የኪራይ ዋጋ መብዛትና ማነስ ምክንያት አድርገው የመሸጫ ሱቆቹ ልብሶቹን በተለያየ ዋጋ ያቀርባሉ።
በአንፃራዊነት ከሴቶች አልባሳት ይልቅ የወንዶች የሚወደድ ሲሆን የወንዶች አልባሳት ከሴቶች ይልቅ በአብዛኛው የልብስ መሸጫ ሱቆች ውስጥ በርክተው ይገኛሉ። ለወንዶች የሚሆኑ የክረምት ቡትስ ጫማዎች በአማካይ ከ1000 እስከ 3000 ብር የሚሸጡ ሲሆን ለሴቶች የሚሆኑ ቡትስ ጫማዎች ደግሞ በአማካይ ከ750 እስከ 2500 ድረስ ይሸጣሉ።
የተለያዩ በሹራብ የተሰሩ የራስ ቅል ከብርድ የሚከላከሉ ኮፊያዎች፣ ለክረምቱ የሚሆኑ ስካርቭ በወንድና በሴቶች ተፈላጊ መሆናቸውን የምትገልፀው ሜላት ደምሴ በተዘጋጁ ልብሶች መሸጫዋ ውስጥ ለክረምቱ ብላ ገዝታ ለመሸጥ ያቀረበችው መሆናቸውን ትናገራለች። በምትሸጥበት ሱቅ ውስጥ እንደ ደንበኞች ፍላጎትና ምርጫ ኮፊያዎቹን ከ100 ብር እስከ 350 ብር እስካርቮቹን ደግሞ ከ300 እስከ 500 ድረስ ትሸጣቸዋለች።
ክረምቱን ተከትሎ የክረምት ፋሽን አልባሳት ፍላጎት ማደጉን የምትገልፀው ሜላት፤የአልባሳቱ ዋጋ መናር ግን ከሌላው ጊዜ አንፃር ከፍተኛ መሆኑን ትናገራለች። እኛም የክረምት አልባሳት አይነቶች ተፈላጊነትና የገበያው ሁኔታ የዳሰስንበትን መሰናዶ በዚሁ አበቃን፤ ቸር ይግጠመን።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ሰኔ 21/2013