የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የመመስረቻ ስምምነት (The Charter of the United Nations) ሰፊ ውይይት ተደርጎበት መፈረም የተጀመረው ከ76 ዓመታት በፊት ሰኔ 19 ቀን 1937 ዓ.ም ነው፡፡ ቻርተሩ ከሚያዝያ 17 ቀን 1937 ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት ወራት ያህል ውይይት ሲደረግበት ከቆየ በኋላ ለመጨረሻ የፊርማ ስምምነት ክፍት ሆኖ መፈረም የተጀመረው፡፡
ከቅኝ ገዢ ኃይሎች ነፃ የነበረችው ኢትዮጵያም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መስራች ነበረችና በወቅቱ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በራስ ቢትወደድ መኮንን እንዳልካቸው የተመራው የልዑካን ቡድን ከ75 ዓመታት በፊት (ሰኔ 19 ቀን 1937 ዓ.ም)፣ ሳንፍራንሲስኮ ከተማ ላይ፣ በሳንፍራንሲስኮ የጦር መታሰቢያና ኪነ ጥበብ ማዕከል ውስጥ የድርጅቱን የቃል ኪዳን ሰነድ/የመመስረቻ ስምምነት (Charter) ፈረመ፡፡
ሰነዱን የፈረሙትም ብላታ ኤፍሬም ተወልደ መድኅን (በአሜሪካ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥትመንግሥት መልዕክተኛ፣አምባሳደርና የልዑካን ቡድኑ አባል)፣ አቶ አክሊሉ ሀብተወልድ (የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የልዑካን ቡድኑ አባል) እና አቶ አምባዬ ወልደማርያም (የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ምክትል የፍትሕ ሚኒስትርና የልዑካን ቡድኑ አባል) ናቸው ፡፡
አዲሱ ገረመው
አዲስ ዘመን ሰኔ 20/2013