በዋና የመተላለፊያ ጎዳና አካባቢ ይገኛል:: አሁን ደግሞ ከመስቀል አደባባይ እስከ አዲስ አበባ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ድረስ በተከናወነው የመንገድ ፕሮጀክት ሥራ ከሰፋው የእግረኛ መንገድ እና በአካባቢው በተለያየ የዕጽዋት ተክል መዋብ ጋር ለእይታ ሳቢ ሆኗል:: በሐውልቱ ላይ የተለያዩ ምስሎች ተቀርፀዋል:: ከቅርጾቹ አንዱ ኢትዮጵያን ለ50 ዓመታት መምራታቸው የሚነገርላቸው አፄ ኃይለሥላሴ በፈረስ ላይ ሆነው ከሥራቸው ደግሞ የሚማፀኑ ህፃናት የያዙ ሴቶች፣ በወቅቱ ወሎ ጠቅላይ ግዛት ተብሎ በሚጠራው ተከስቶ የነበረውን ድርቅ የሚያስታውስ፣ መፈክር የሚያሰሙ ሰዎች ዓይነት እጃቸውን ጨብጠው ወደላይ የሰቀሉ ወታደሮች ይታያሉ::
በሌላኛው የሐውልቱ ወገን ደግሞ ለ30 ዓመት ያህል ኢትዮጵያን የመሩት የወታደራዊው መሪ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ምስል ይታያል። የህብረብሄራዊ ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት የሚል መግለጫም በሥሩ ይገኛል:: በእርሳቸው በኩል ደግሞ ስንቅ የሚያዘጋጁ ሴቶች፣ ያልሰራ አይብላ በሚል የጽሁፍ መግለጫ መሳሪያ የታጠቁ ወታደሮች ተሰልፈዋል::
ረጅሙ ሐውልት በነጭ እብነ በረድ የተሰራ በመሆኑ እይታን ይስባል::በጎንና ጎን ደግሞ በመስታወት ውስጥ ብዛት ያላቸው የተለያዩ ሰዎች ጉርድ ፎቶግራፎች ይገኛሉ:: በፎቶ ግራፉ ላይ የሚታዩት ሰዎች ብዙዎቹ ኢትዮጵያውያን አለመሆናቸው በቀለማቸው ይለያል:: ሐውልቱና ፎቶ ግራፎቹ ቁልጭ ብለው የሚታዩ ቢሆኑም በጽሁፍ መግለጫ ታግዞ ጎብኝው በቀላሉ በሚረዳው መንገድ ታሪካዊነቱን የሚያጎላ ነገር ባለመኖሩ አንዳንዶች ሐውልቱን ለመረዳት ሲቸገሩ አስተውያለሁ:: በሥፍራው በነበርኩበት ወቅትም ከአጠገቤ የነበሩት አንደኛው ከአዲስ አበባ ከተማ ውጭ ነዋሪ የሆነ፣ሌላኛዋ ደግሞ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ነዋሪ የሆነች ስለሀውልቱ ሀሳብ ሲለዋወጡ እንደሰማኋቸው ሁለቱም ታሪኩን ለማወቅ ጉጉት ነበራቸው:: ሆኖም ግን በጽሁፍ የተደገፈ ባለመሆኑ በሐውልቱ ላይ ያሉትን ምስሎች በማየት ብቻ ታሪኩንና ሀሳቡን ለመረዳት አልቻሉም:: የሚያስረዳም ሰው ባለማግኘታቸው ጉብኝታቸው እንደፈለጉት አልሆነላቸውም:: ታሪኩን ከሐውልቱ ጋር ፎቶ በመነሳት ማስቀረት ችለዋል::
በነበረኝ ቆይታ ሐውልቱ ከተሰራ ጀምሮ እድሳት እንዳልጎበኘው የሚያመላክቱ ምልክቶችን ታዝቤያለሁ:: ሐውልቱ የተሰራበት ነጩ እብነ በረድ ቀለሙ ደብዝዟ:: በሐውልቱ ጀርባም የግንባታ ግብዓቶችን ጨምሮ የተለያዩ ዕቃዎች ክምችት መኖራቸው በሐውልቱ ገጽታ ላይ ተጽዕኖ አሳርፏል:: ሐውልቱ መግቢያ በር ላይ ለውበት የተሰራው ፋውንቴን ወይንም ወደ ላይ እየወጣ ወደ ታች የሚመለሰው ውሃ አሁን ላይ የለም:: ይህም ሥፍራ ንጽህናው ተጓድሏል:: በኤሌክትሪክ ኃይል ታግዞ በተለያየ ቀለማት ወደ ላይና ወደ ታች ይል የነበረው ውሃ (ፋውንቴን) ለሐውልቱ ሳቢ እይታ መፍጠሩንና አላፊ አግዳሚውንም በመያዝ መስህብ እንደነበር ታሪኩን ያስታወሱ ሰዎች ነግረውኛል::
እንዲህ በአንድ ወቅት አድናቆትን ያገኘ፣ ለከተማዋም ጥሩ መስህብ በመሆን የተሰራ ሥራ ከጊዜ በኋላ ባልተጠበቀ ሁኔታ ውበቱን አጥቶ ይስተዋላል:: ይህ ሐውልትም እንክብካቤና ትኩረት ከተነፈጋቸው የከተማዋ ሀብቶች መካከል ይጠቀሳል:: ሐውልቱ በወቅቱ ሲሰራ ታሪክም ምክንያትም ነበረው:: ከፍተኛ የሆነ ገንዘብና የሰው ጉልበትም እንደፈሰሰበት ሥራው ይመሰክራል::
ለመሆኑ እንዲህ ያሉ ተግባሮች ሲከናወኑ ከወቅታዊነት ባለፈ ጥቅም እያስገኙ ታሪካዊነታቸው እንዲቀጥል ምን ያህል ታስቦባቸዋል ተብሎ ሲፈተሸ በትክክል የሚያስረዳ ሰው አይገኝም:: በመሪዎች ፍላጎትና ወቅቱ በፈጠረው አጋጣሚ ይሰራሉ:: ቅርስነታቸው ተጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፉ እና የቱሪስት መስህብ በማድረግ የገቢ ምንጭ ሆነው አካባቢያዊ ጠቀሜታ ሲፈጥሩ አይስተዋልም:: ይልቁንም ባሉበት አርጅተው ሲወድቁና ወይንም ለሌላ ተግባር ሲውሉ ማየት እየተለመደ መጥቷል:: በለስ የቀናቸው ደግሞ መልሰው ሲያንሰራሩና ከወደቁበት ዳግም ሲያንሰራሩ፣ አቧራቸው ተራገፎ ወርቅ ሲሆኑ አስተውለናል:: ባለቤት አጥተው በኃላፊነት ስለቅርሶቹ ደፍሮ የሚናገርም እንክብካቤ የሚያደርግም የማይገኝበት አጋጣሚም እንዲሁ የበዛ ነው:: እንዲህ ባሉ እና በተለያዩ ምክንያቶች ብዙ የቅርስ ሀብቶች መባከናቸውም በተለያዩ ሰዎች ይነገራል::
እኔም በአረንጓዴ ልማት በተከበበው ታሪካዊና መልካም የሆነ ገጽታ በያዘው ሥፍራ በነበረኝ ቆይታ ሥፍራው ሁለት ዓይነት ገጽታዎች መያዙን ተረድቻለሁ:: አንዱ የአረንጓዴ ልማት ሲሆን፤ ሌላው ሐውልት ነው::የአረንጓዴ ልማቱ በልደታ ክፍለ ከተማ ተፋሰስና አረንጓዴ ልማት ጽህፈት ቤት የሚከናወን ሲሆን፤ ጽህፈት ቤቱ በፓርክነት ይዞታ ነው የሚያለማው::የሐውልቱ ባለቤት ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ ባህል ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ነው:: ሁለቱ በከተማ አስተዳደሩ ሥር ያሉ ተቋማት ቢሆኑም የየራሳቸውን ኃላፊነት ከመወጣት ባለፈ አንዱ ለሌላው ተቆርቁሮ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን በማሟላቱ ላይ ተናብቦም ለጋራ ዓላማ የመንቀሳቀሱ ዙሪያ ክፍተት መኖሩን ነው የታዘብኩት:: ሌላው ቢቀር በግቢው ውስጥ ያለው የጥበቃ ሠራተኛ አንድ ኤጀንሲዎች በሚያቀርቡት የጥበቃ ሠራተኛ የሚሰራ ሌላው ደግሞ በተቋም ተቀጥሮ የሚጠብቅ እንደሆነ ነው በጉብኝቴ ወቅት የተረዳሁት:: እዚህ ላይም ግልጽ የሆነ አሠራር አለመኖሩን ተረድቻለሁ።
ትዝብቴን መሰረት አድርጌ በአዲስ አበባ ከተማ ባህል ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ተገኘሁ:: በአጋጣሚም ቢሮው መጠነኛ የዳሰሳ ጥናት በማካሄድ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎችንና መናፈሻዎችን የመለየት ሥራ ሰርቶ ለቀጣይ ተግባራቶቹ የሚያግዘውን የቅድመ ዝግጅት እንቅስቃሴ ላይ እንደሆነ መረጃ አገኘሁ:: ለመነሻ ጥያቄዬና የቢሮውን የዳሰሳ ጥናትና ቀጣይ አቅጣጫ በተመለከተ ያነጋገርኳቸው በአዲስ አበባ ከተማ ባህል ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ከፍተኛ የቅርስ ጥናት ባለሙያ መምህር መክብብ ገብረማርያም፤ ሌላው ደግሞ በቢሮው የቱሪዝም መዳረሻ ልማት ብቃት ማረጋገጥ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አምደማርያም ማሞ ናቸው::
በቅድሚያ መምህር መክብብ ስለታሪካዊው ሐውልትና እየተደረገለት ስላለው እንክብካቤ፣ አጠቃላይ በክፍላቸው እየተከናወነ ስላለው ተግባር እንደገለጹልኝ፤ ሐውልቱ ‹‹ትግላችን›› የሚል ስያሜ ያለው ሲሆን፤ በወቅቱ የነበሩት የኢትዮጵያ መሪ መንግሥቱ ኃይለማርያም በ1969 ዓ.ም የሶማሌው የዚአድባሬ አስተዳደር ኢትዮጵያን ለመውረር ያደረገውን ሙከራ ላከሸፉ ጀግኖች መታሰቢያነት የቆመ ሐውልት ነው:: ኢትዮጵያ ከወደ ምሥራቁ የገጠማትን ጠላት መክታ ለመመለስ ስታደርግ ለነበረው ትግል የኩባ መንግሥት ከጎኗ በመሆን እስከ ህይወት መስዋዕትነት በመክፈል ድጋፍ አድርጓል:: በጦርነቱም ብዙ የኩባ ወታደሮች ህይወት አልፏል:: በሐውልቱ በሥተ ግራና ቀኝ በመስታወት ውስጥ የሚገኘው ፎቶ ግራፍም ለኢትዮጵያ መስዋዕትነት የከፈሉ የኩባ ወታደሮች ናቸው:: ውጊያው የተካሄደበት ሥፍራ ካራ ማራ ተብሎ የሚጠራ በመሆኑ በጦርነቱ የተሳተፉ ኢትዮጵያውያንና የተጎጂ ቤተሰቦች ታሪኩ እንዳይረሳና እንዲታወስ በአካባቢው ስም ማህበር መስርተው የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ላይ ይገኛሉ:: በየዓመቱም በልዩ ሥነ ሥርዓት ቀኑ ይታሰባል::
እንዲህ ያለ ታሪክ ያላቸው ሐውልቶችና በከተማዋ የሚገኙ የተለያዩ ቅርሶችን በቢሮው ከአንድ ዓመት በፊት የተደራጀው የቅርስ ክፍል ዋና ተግባር መዝግቦ መያዝ፣ እንዲለማ (እድሳት) እንዲደረግለት፣ እንዲጠበቅ፣ እንዲታወቅ እና ታሪኩም እንዲነገር ማድረግ ነው:: የሐውልቱ ይዞታ በከተማዋ ካሉት ሌሎች ተመሳሳይ ሀብቶች አንጻር ከፍ ባለ ጉዳት ላይ ባይሆንም መጠነኛ የሆነ ጉዳት እንዳለው ግንዛቤ ተይዟል:: ይህም የሆነው እስካሁን እድሳት ስላልተደረገለት ነው:: ባለሙያው እስከሚያውቁት እንዲታደስ በዕቅድ አልተያዘም:: ከእርሱ ቅድሚያ የተሰጣቸው ሌሎች ናቸው በመታደስ ላይ የሚገኙት:: የዕድሳት ሥራቸውም ተጠናቅቆ ለተለያዩ ተግባራት የዋሉም አሉ:: ከነዚህ መካከልም የአቡነ ጴጥሮስ፣ አራት ኪሎ የሚገኘው የድል ሐውልትና ስድስት ኪሎ አካባቢ የሚገኘው የካቲት 12 የሰማዕታት መታሰቢያ እንዲሁም በቅርስነት ከተያዙት መኖሪያ ቤቶች ደግሞ በአራዳ ክፍለ ከተማ የሚገኝ በከተማዋ የመጀመሪያ የሆነው በአርመናውያን የተሰራው የህፃናት መዋያ ህፃን ዓለም የተባለ ተቋም ይጠቀሳሉ:: የአንዳንዱ የእድሳት ሥራም በበጎ ፈቃደኞችም ጭምር በመከናወን ላይ ይገኛል::
ቅርሶችን አድሶ በማቆየት ሂደት በተለይም ከቤት ጋር የተያያዘው ውጣ ውረድ አለው:: አብዛኞቹ ለመኖሪያና ለተለያየ አገልግሎት የዋሉ በመሆናቸው ነዋሪውን አስወጥቶ ለማደስ አስቸጋሪ በመሆኑ ምክንያት በእንጥልጥል ላይ የሚገኙ ቅርሶች አሉ:: ቅርሶችን በማልማት ከሚነሱት አንዱ ይኸው ጉዳይ ቢሆንም አብዛኞቹ ቅርሶች በጣም የተጎዱ በመሆናቸው ወጪያቸውም ከፍተኛ እንደሆነና ከከተማ አስተዳደሩ አቅም በላይ መሆኑ በተደጋጋሚ ተገልጿል:: ችግሮች ሥር ከሰደዱ በኋላ አጣብቂኝ የሆነ ነገር ውስጥ ከመግባት ኃላፊነት የወሰደው አካል ቀድሞ መንቀሳቀሱ ይበጃል::
ሌላው በከተማዋ የሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻና መናፈሻዎችን በመለየት ለቀጣይ የሥራ አቅጣጫ የሚያግዙትን ተግባራት በማከናወን ላይ የሚገኘው የቢሮው ክፍል የቱሪዝም መዳረሻ ልማት ብቃት ማረጋገጥ ዳይሬክቶሬት የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን የማስፋፋት፣ ለሆቴልና ሬስቶራንት አገልግሎቶች ድጋፍና ክትትል ማድረግ፣ መዳረሻዎችን የማልማት ሥራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ የሚንቀሳቀስ ክፍል መሆኑን አቶ አምደማርያም ማሞ ነግረውኛል::
እርሳቸው እንዳሉት ክፍሉ ከተዋቀረ ገና የአንድ ዓመት ጊዜ ያለው ሲሆን፤ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ብዙ ርቀቶች ባይሄድም እየተገባደደ ባለው በጀት ዓመት በከተማዋ ያሉትን መዳረሻዎችና መናፈሻዎች ታሪካዊ ዳራ፣አድራሻቸውን፣ በውስጣቸው የያዟቸው ነገሮች፣ መናፈሻና መዳረሻ መሆናቸውን እንዲሁም የሚያስተዳድራቸውን አካል መለየትንና ሌሎችንም ባካተተ ከቱሪዝም ኢንዱስትሪው አንጻር መጠነኛ የጥናት ሥራ ሰርቷል::አሁን ባለው ሁኔታ ሙዚየሞችንና ፓርኮችን የሚያስተዳድሯቸው የተለያዩ አካላት ናቸው:: ጥናቱ 18 ሙዚየሞችና 22 ፓርኮች ላይ ነው ትኩረቱ:: በተደራጀው መረጃ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር የጋራ መድረክ ለማካሄድ ዝግጅት ተደርጓል::
የመዳረሻ መለኪያዎች ብዙ መስፈርቶችን የሚጠይቁ መሆናቸውን የተናገሩት አቶ አምደማርያም፤ ከመስፈርቶቹ መካከል በውስጣቸው የምግብ፣ የመኝታ፣የተለያዩ መዝናኛዎች፣ በቂና ንጹህ መፀዳጃ ቤቶች፣ የህፃናት መጫወቻ፣ ከመሰረተ ልማት የመግቢያ መንገዱ፣ በቂ የሆነ የመብራትና ኢንተርኔት አገልግሎት፣ ወደ ፓርኩ የሚያስገባ ግልጽ በሆነ ቦታ ጠቋሚ ነገር መኖሩና በውስጥ የሚገኙ አገልግሎቶችን የሚገልጽ መረጃ በተገቢው ሥፍራ ላይ መኖር የሚል ነው።
እንዲሁም ከደህንነት ሥጋት ነፃ መሆኑ፣ በተለያየ ዕድሜ ለሚገኙ ሰዎች ምቹነታቸው፣ የገፀ በረከት መሸጫ ሱቆችና የመጀመሪያ ደረጃ ህክምና የሚሰጥ መኖራቸው በአጠቃላይ ከቱሪስት እይታ አንጻር የተሟላ ነገሮች አሉት ወይ የሚሉት ከብዙ ጥቂቶቹ መሆናቸውንና መዳረሻ ትልቅ ኢንቨስትመንት የሚጠይቅ መሆኑን ያስረዳሉ::
በቱሪዝም እሴት ሰንሰለት ውስጥ ያሉ ይጠቀሙ ከተባለ እያንዳንዱ መስህብ ላይ መሰራት ያለባቸው ደረጃቸውንም የጠበቁ ስራዎች መሆን አለባቸው። መነሻ ጥናቱም ይህን ታሳቢ ባደረገ ሥራዎች እንዲሰሩ ማስቻል ነው:: መስህብ ከመዳረሻ እንደሚለይ፣ ጎብኝው የተለየ መስተንግዶ የማይጠይቅበት፣እስከፈለገው ሰዓት ቆይቶ መውጣት የሚችልበት የአገልግሎት ስፍራ መስህብ እንደሚባል ልዩነቱን አስረድተዋል:: በዚህ መስፈርት መሰረት በከተማ አስተዳደሩ የሚገኙት በመስህብ መስፈርት ውስጥ ናቸው::
እንደ አቶ አምደማርያም ገለጻ መስህቦችን ወደ መዳረሻ ለማሳደግ ባለድርሻ አካላትን ማሳተፍ ይጠይቃል:: የከተማዋን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ በማሳደግ ተጠቃሚ ለመሆን ደግሞ መንግሥትና አቅሙ ያላቸው አካላት በጋራ መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል:: እስካሁን ባለው በከተማዋ ለሚገኙ የቱሪዝም መስህብ ሀብቶች በበቂ ሁኔታ ትኩረት ተሰጥቷል ብለው አያምኑም:: በከተማዋ ያለው ባለሀብትም በዚህ ላይ እንዲሳተፍ ግንዛቤ አልተፈጠረም::ቱሪዝም ኮሽ ሲል የሚጠፋ ነው የሚሉ አስተሳሰቦች መለወጥ አለባቸው›› ሲሉም ይናገራሉ:: እርሳቸው እንዳሉት ባለሙያው ጋርም እኩል የሆነ መነሳሳት ተፈጥሯል ለማለት አያስደፍርም:: ከደመወዝና ከጥቅማ ጥቅም ጋር የሚነሱ ቅሬታዎች፣ ለዘርፉ ሥራ የሚመደበው በጀት በቂ አለመሆን፣ በእንቅስቃሴው ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል:: የቱሪዝሙ መጠናከር የሰዎችን የእርስ በርስ ግንኙነት ለማጠናከር ፋይዳው የጎላ መሆኑንም መገንዘብ ይገባል:: ይኼ ሁሉ መፈተሽ አለበት::
አዲስ አበባ ከተማ ዋና መዲና እና የዓለም አቀፍ መቀመጫ እንደመሆኗ ካላት የመሬት ስፋት አንጻር ደረጃቸውን የጠበቁ ብዙ መናፈሻዎችና መዳረሻዎች ሊኖሯት ይገባል:: እንደ ባንክ ያሉ ትላልቅ ተቋማት ሙዝየሞችን በማቋቋም ሚና ሊኖራቸው ያስፈልጋል:: በዚህ ረገድም ከሚመለከታቸው ጋር በመነጋገር ጥረት እየተደረገ ነው::
ቀጣይ አቅጣጫውን አስመልክቶ አቶ አምደማርያም ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ መረጃው ከተሰበሰበ በኋላ ሀብቶቹን ለሚያስተዳድሩ አካላት በተለያየ ዙር ሀብቶቹ መሰረታዊ የሆኑ ነገሮች ተሟልቶላቸው ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችል የግንዛቤ ስልጠና ተሰጥቷል::
ልማቱ ከፍተኛ በጀት የሚጠይቅ በመሆኑም ቅድሚያ በሚሰጣቸው ላይ ትኩረት እንዲሰጥም ጥረት ተደርጓል:: በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ተነሳሽነት እየተወሰደ ያለው የመዳረሻዎች ልማት ሥራ ወደ ታችም ወርዶ የተፈጠረው መነቃቃት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት::
አቶ አምደማርያም ቻይናን የመጎብኘት ዕድል አጋጥሟቸው በአንድ የመናፈሻ ሥፍራ ብቻ በቀን ከስምንት መቶ ሺህ በላይ መጎብኘቱና 90 በመቶ የሚሆነው ጎብኚም የሀገሬው ዜጎች መሆናቸው መንፈሳዊ ቅናት አሳድሮባቸዋል:: በአዲስ አበባ ከተማም ተመሳሳይ እንዲሆን ነው ፍላጎታቸው::
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሰኔ 20 ቀን 2013 ዓ.ም