ከሰሞኑ የህወሓት የዲጂታል ሚዲያ ክንፍ በዲጂታል ሚዲያው በኩል የኢትዮጵያ ጦር ኃይል ጀቶች ቶጎጋ በሚባል ስፍራ የገበያ ቦታን እንደደበደቡ አስታውቋል።እንደሚገመተውም የምዕራቡ ዓለም የጁንታው ወዳጆች ጥቃቱን አውግዘው ዘለግ ያለ መግለጫ አውጥተዋል።በሌላ መልኩ የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት የተባለው ጥቃት በገበያ ቦታ ንጹሃንን አላማ አድርጎ ጥቃት እንዳልፈጸመ አስተባብሏል።ሂደቱ በጥቅሉ ሲታይ ያለፈው ወራት ላይ ስናየው የነበረው ሂደት ተመሳሳይ ነው።በጦርነቱ ሽንፈት የደረሰበት የጁንታው ኃይል በፕሮፖጋንዳው ዘርፍ ድልን ለመቀዳጀት ክስ ያቀርባል፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ያስተባብላል፤ የምዕራቡ መንግሥታት የኢትዮጵያን መንግሥት ያውግዛሉ።ኡደቱ ይሄው ነው።
ለኢትዮጵያውያን ግን ይህ የሰሞኑ ክስ የሚያስታውሳቸው አንድ ታሪክ አለ።እሱም የሀውዜን ታሪክ ነው።የሀውዜን ታሪክ ከ33 ዓመታት በፊት ሰኔ 15 ቀን 1980 ዓ.ም የደርግ ጦር በሀውዜን ከተማ የገበያ ስፍራ አደረሰ የሚለው የቦንድ ድብደባ ታሪክ ነው።በወቅቱ ህወሓት ተበዳይ በመሆን ያቀረበው ክስ የመላውን ዓለም አንጀት መብላት ያስቻለው ሲሆን፤ ከደርግ ጋር ዓይንና ናጫ የነበሩት የምዕራቡ ዓለም መሪዎች ደግሞ ደርግን የሚያወግዙበት ለህወሓት ያላቸውንም ድጋፍ የሚጨምሩበት ጥሩ ምክንያት በማግኘታቸው የተደሰቱበት ክስተት ነበር።በወቅቱ የአየር ድብደባው ሲፈጸም እንኳን ያኔ ዛሬም ቢሆን እልም ያለች ገጠር በነበረችው ሀውዜን ከተማ በካሜራ ተቀርጾ የተገኘ ሲሆን፤ ይህ ቪዲዮም ለምዕራቡ ዓለም ሚዲያ የአንድ ሰሞን ደንበኛ የወሬ አጀንዳ ሆኖላቸው ነበር።ዘመናት ካለፉ በኋላ ግን የእውነት ጀንበር ወደ ሀውዜን የአውሮፕላን ድብደባ ታሪክ ላይ ማብራት ጀመረች።በወቅቱ በህወሓት ውስጥ አብረው ይታገሉ ከነበሩት አካላት አንዱ የነበረው ታጋይ ገብረመድህን አርአያ እውነቱን አፈረጠው።
ገብረመድህን እንደሚለው በወቅቱ የተደረገው ነገር ደርግ የሀውዜን ገበያን ደበደበ ከሚባል ይልቅ ወያኔ የሀውዜን ገበያ እንዲደበደብ አደረገ ቢባል ይቀላል።ገብረመድህን እንደሚለው በዚያን ጊዜ ህወሓት በምትሰራው ሥራ ምክንያት እጅግ በጣም ተጠልታ ነበር። ሰው አጣች። ምልምል ጠፋ። እናስ? ተንኮል አሰቡ። የዚያን ጊዜ የትግራይ አስተዳዳሪ ለገሰ አስፋው ነው። ከዚያ ወያኔ ሀውዜን አንድ ክፍለ ጦር እያስገባች እያስወጣች ወያኔ ሀውዜን ስብሰባ ልታደርግ ነው የሚል ወሬ ለደርግ ደህንነት እንዲደርሰው አደረገች። ኃይሉ ሳንቲም (ሳንቲም ቅጽል ስሙ ነው) የሚባል የወያኔ የጦር ደህንነት፡ የወያኔ ጦር ሀውዜን ሊሰበሰብ ነው የሚለውን መረጃ ለለገሰ አደረሰ። እውነት እንዲመስልም በገበያው ቀን የተወሰኑ ታጋዮች በአካባቢው ውር ውር ሲሉ እንዲታዩ ተደረገ። የሀውዜን ገበያ መቼም እጅግ የታወቀ ነበርና ከብዙ ቦታ ብዙ ሰዎች ለንግድ ይመጣሉ። በዕለቱ ስድስት የደርግ ሚጎች እየተመላለሱ በመስቀልያ ቅርጽ ገበያውን ደበደቡት። ይሄ ሁሉ ሲደረግ ቪዲዮ ይነሳ ነበር። ነገሩ ለረጅም ጊዜ የተቀነባበረ መሆኑ የሚታወቅባቸው ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸው። ወደ አስራ ሁለት ፎቶ አንሺዎች ሱዳን ውስጥ ሄደው እንዲሰለጥኑ ተደርጓል። እነ ተክለወይን አስፍሀ፣ እነ ሱራፌል ምህረተአብ እና እነ እያሱ በርሄ ካሜራ ቀራጭነት ሱዳን ውስጥ ተምረው መጡ። ያ ሁሉ ድብደባ ሲደረግ ተራራ ላይ ቆመው እያንዳንዱን ሚግ ከሁሉም አቅጣጫ ቪዲዮ ያነሱ ነበር። ይቀርጹ ነበር። በነጋታው ይሁን ማታውኑ ያ ሁሉ ፊልም ሱዳን ውስጥ በቲቪ ታየ። ደርግ ህወሓት በሰራችለት ወጥመድ ውስጥ ሰተት ብሎ ገባ።ህወሓት ንጹሃን ተጋሩን አስበልታ እየሞተ የነበረው የፖለቲካ ሕይወቷ እንዲያገግም አደረገች።
አሁንስ? አሁንም ህወሓት አሮጌውን ድራማ በድጋሚ ልትሰራው ፈለገች።አሁን ግን እንደቀድሞው አልተሳካም።ጦሩም የህወሓት ወጥመድ ውስጥ አልገባም፤ ጁንታውም እንደተለመደው ካሜራ አዘጋጅቶ መቅረጽ አልቻለም።ዘመቻ አሉላ አባነጋ ብሎ የተነሳው ኃይል በከባድ ኩርኩም እንዲመለስ ተደረገ።የሰማዕታት ቀንን ለማክበር በሚል ምገበ ሀይሌ በተሰኘ ግለሰብ መሪነት የተካሄደው ዘመቻ በመከላከያ ሰራዊቱ ከባድ ቡጢ ቀምሶ የጁንታው ኃይል ወደወጣበት ጉድጓድ እንዲመለስ ሆኗል።ነገር ግን ጁንታውን በተመለከተ እየተካሄደ ያለው አሮጌ ድራማ ይህ ብቻ አይደለም።ወዳጃቸው እና ታዛዣቸው ህወሓትን ወደ መንበሩ ለመመለስ የሚፈልጉ ኃይሎች የዛሬ 36 ዓመት የሰሩትን ድራማ አሁንም ሊደግሙት ጥረት ላይ ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ይህን አሮጌ ድራማ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት እና ባለፈው ረቡዕ በተላለፈው ቃለ መጠይቅ ላይ በሚገባ አብራርተውታል።ጠቅላይ ሚኒስትሩ ታሪክን አጣቅሰው እንደሚናገሩት ከሆነ ከ1977 በፊት ወያኔ ለደርግ ብዙም ችግር የማትፈጥር መጠነኛ የሽፍታ ቡድን ነበረች።1977 ላይ ድርቅ ሲከሰት ግን የትግራዩ ረሀብ ለወያኔ የጥጋብ ዘመን ጅማሮ ሆነለት።የደርግ ጠላቶች በሰብአዊ ድጋፍ ስም በሱዳን በኩል እርዳታ እናስገባለን በማለት የቻሉትን ያህል መሣሪያም፤ ገንዘብም፤ ሥልጠናም ለወያኔ አስታጠቁ።ወያኔም ለትግራይ ሕዝብ ከመጣው እርዳታ የተቻለውን ያህል እየሸጠ መሣሪያ ሸመተበት።ከዚያ በኋላ የሆነው ሁሉ ታሪክ የሚያውቀው ነው።ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዛሬም አንዳንድ ኃይሎች ይህን ታክቲክ መጠቀም ይፈልጋሉ ግን አይሰራም ብለዋል።ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንም በቅርቡ በሰጡት መግለጫ በእርዳታ ስም መሣሪያ ለማሾለክ የሚሞክሩ ኃይሎችን ተጠንቀቁ ብለዋል።
ይህ ክስተት በአንድ ጎን ታሪክ ራሱን እንደሚደግም፤ በሌላ ጎን ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተደጋጋሚ እንዳሉት ሰዎቹ ሀሳብ እንደነጠፈባቸው ነው።እንዲያ ባይሆንማ ኖሮ 30 ዓመት ያለፈበትን ድራማ እንደአዲስ ሊሰሩት አይሞክሩም ነበር።የሆነው ሆኖ አሮጌው የጁንታው እና የአጋሮቹ ድራማ ብዙም ተመልካች ሳያገኝ ከመድረክ እየወረደ ነው።እንደ 1980ው የሀውዜን ድራማ ዓይነት አሁን መድገም አልተቻለም።እንደ 1977ቱም በእርዳታ ስም መሣሪያ ማጋዝ አይቻልም።ጁንታው በዚህኛው ዙር የተሳካለት አንድ ድራማ ቢኖር ልክ እንደ ዛሬ 40 ዓመቱ ዛሬም ትግራይን የመከራ ምድር ማድረጉ ብቻ ነው።
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን ሰኔ 20 ቀን 2013 ዓ.ም