ከሰብዓዊ ባህርያት መካከል አንዱ አኩራፊነት ነው። ኩርፊያ በአንዳች ጉዳይ ተቀይሞ፣ ተከፍቶና “ሆድ ሻክሮ” ከወትሯዊ ጨዋታ፣ ንግግርና ተሳትፎ በራስ ላይ ገደብና ማዕቀብ በመጣል በዝምታ ወይንም በእምቢታ መቆዘምን ያመለክታል። ይህ የመጀመሪያው የመዛግብተ ቃላት ብያኔ ነው። ሁለተኛው የኩርፊያ ፍቺ “የተፈጠመ ያርፋል፤ የተኛ ያኮርፋል” እንዲል ብሂላችን በእንቅልፍ ዓለም ተረትተን በሰርነቃችን (በአፍንጫችን ውስጥ ያለ የትንፋሽ መመላለሻ ሰረገላ) በኃይል ስንተነፍስ ወይንም ትራሳችን አልመች ሲለን እንዳሸለብን የምናወጣው ሸካራ ድምጽ ኩርፊያ ይሰኛል። አንዳንዶች በተለምዶ አንኮራፋ/አንኮራፋች ማለታቸው ሳይዘነጋ። ሁለቱም ድንጋጌዎች ለተነሳንበት ጭብጥ ጥሩ ማሳያዎች ስለሆኑ እያፈራረቅን በመጠቀም እንገለገልባቸዋለን።
ሰው ከቤተሰብ አባላት ጋር ይኳረፋል። ከሌላ ሰው ጋር በሃሳብ ወይንም በተግባር መግባባት ሳይኖር ቀርቶ ግጭት ሲፈጠር መገለጫው ኩርፊያ ሊሆን ይችላል። ከኩርፊያ ከፍ ሲልም በቀል ሊከተል ይችላል። ይህ ክፉ ውሳኔ ነው። የከረረ የኩርፊያ ደረጃ የሚባለው ከማሕበረሰብ ጋር የሚፈጠር መቃቃር ነው። ከማሕበረሰብ ጋር የሚደረግ ኩርፊያ ከግለሰቦች ወይንም ከቡድኖች ጋር እንደሚደረገው ኩርፊያ ቀላል የሚባል አይደለም። በማሕበራዊ ተራክቦ ውስጥ ኩርፊያ እንዳይፈጠር ጥረት ቢደረግም በፍጹም ሊቀር የማይችል የተፈጥሮ ትዕዛዝ ስለሆነ በይሁንታ ልንቀበለው እንችል ይሆናል። ዘመንን አኩርፎና ትውልድን ተጠይፎ ራስን ብቻ አግንኖ “በእንቅልፍ ልብም ሆነ በእውን ዓለም ማንኳረፍ” ግን ተፈጥሯዊ ባህርይ ብቻ የሚባል ሳይሆን የሥነ ልቦና ቀውስና ህመም ሊሰኝ የሚችል ክፉ ደዌ ነው።
ነፍሰ ሄሩ ገጣሚ ደበበ ሰይፉ “ለምን ሞተ ቢሉ” በሚል ርዕስ የጻፈው ባለ አራት ስንኝ ግጥም “ከዘመን ጋር እልህ ተጋብቶ” ለሚፈጸም ኩርፊያ በጥሩ አብነት ሊጠቀስ የሚችል ድንቅ የብዕር ውጤት ስለሆነ በዚህ ቦታ ማስታወሱ አግባብ ይሆናል።
ለምን ሞተ ቢሉ
ንገሩ ለሁሉ
ከቶ ሳትደብቁ፤
“ከዘመን ተኳርፎ
ከዘመን ተጣልቶ።”
እንዴት ሰው ከዘመን ይኳረፋል? እንደምንስ ከማሕበረሰብ ጋር ቅይማት ፈጥሮ “ሆድ ሊሻክር ይችላል?” በተለይም “የእኔ ርዕዮተ ዓለም ብቻ ካልነገሰ፣ የእኔ የፖለቲካ ፍልስፍና ብቻ በትረ ሥልጣን ካልጨበጠ፣ እኔ ያልኩት ካልሆነ፣ የእኔ የውሳኔ ድምጽ ካልታከለበት በስተቀር ወዘተ.” ብሎ በስሜት መዶረር፣ መኮፈስና በሃሳብ ሸምቆ ማሕበርሰብን ለመፋለምና በዘመን ላይ የበቀል እርምጃ ለመውሰድ ማድባት፤ ደግሜ አረጋግጣለሁ ተፈጥሯዊ ስሜት ብቻ ተብሎ የሚታለፍ ሳይሆን ከራስ ጋር የሚጣሉበት ክፉ የእብሪት ካንሰር ነው።
ዛሬ የሀገሬን አየር እያጠነ ያለው ይህን መሰሉ “የዘመን ኩርፈኞች” ትንፋሽ ነው። እነዚህ አኩራፊ ምንዱባን በተጨባጩ እውነት ሳይሆን በራሳቸው “የይሆናል ወይንም መሆን አለበት” ትዕቢት ውስጥ ደንዝዘው ሀገርን ሲተቹ፣ ከታሪክ ሲፋለሙ፣ ማሕበረሰቡን ሲያወግዙ፣ በሃሳብ የማይገጥሟቸውን እያብጠለጠሉ ውለው ሲያድሩ ኅሊናቸው አይወቅሳቸውም፤ ሰዋዊው ባህርያቸውም በውስጣቸው ሲጮኽ ቁብ ሰጥተው አያደምጡትም።
የዘመን ኩርፈኞች ዋና መገለጫቸው በአስተሳሰባቸው በትናንት ኃላፊ ጊዜ የሚኖሩ፤ በተግባርም ከዛሬ እውነታ ጋር እየተፋለሙ ላያሸንፉ የሚላላጡና “የጠብ ሽታ” በአካባቢያቸው ካልጨሰ በስተቀር ቆሌያቸው የሚያቅበዘብዛቸው ብጤ ናቸው።
ከላይ ግጥሙንና ስሙን የጠቀስኩት የተባ ብእረኛ ደበበ ሰይፉ እነዚህን መሰል የዘመን ጠበኞች በሌላ ሥራው የገለጻቸው በሚከተለው ተጨማሪ አባባል ነበር። “እናንት የአባቶቻችሁ ልጆች፤ የአያቶቻችሁ ቅድመ አያቶች”፤ ይህ በአያዎ (አይ እና አዎ) ዘይቤ የተጎላመሰው አባባል ትልቅ ትርጉም አዝሏል። እርግጥ ነው ማናችንም የምንወለደው ከአንድ አባት የአብራክ ውርስ ስለሆነ ስንጠራ ያለመጠራጠር አቤት የምንለው ይሄ እውነት “አዎ” ስለሆነ ነው። ለምን ቢሉ ለአባቶቻችን ልጆች ነና። ችግሩ እንዴት በመወለድ የአያቶቻችን ቅድመ አያቶች ልንሆን እንችላለን የሚለው ተቃርኖ ነው።
ከቅድመ አያቶቻችን የዘር ሀረግ ብንመዘዝም በምንም ተዓምር ግን በስጋ የአያቶቻችን ቅድመ አያቶች ልንሆን ስለማንችል መልሳችን “አይ” ይሆናል። አባባሉን ጠለቅ ብለን ስንፈትሸውም በመወለድ ሳይሆን በአስተሳሰባችን በቅድመ አያቶቻችን ዘመን ውስጥ ካልኖርን እያልን በጥልቅ እንቅልፍ ውስጥ ወድቀን እያኮረፍን (እያንኮራፋን) ብንቃዥ ወይንም ከዛሬ እውነታ ጋር እየተቃረንን የትናንትን ጀንበር በማሽሞንሞን ብናላዝንና ብናነባ ግን “በአስተሳሰባችን ቅድመ አያቶች” ብንባል ቢያንስብን እንጂ አይበዛብንም።
ዛሬ በሀገራችን የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ የሚስተዋለው ክፉ የዘመን ጥልና ኩርፊያ ምክንያቶቹ በርካታ ሆኑም አልሆኑ በዚህ ጸሐፊ እምነት ዋነኛው ችግራችን ፖለቲከኞቻችን ከዘመን ጋር የፈጠሩት የእንኪያ ሰላንትያ ጠብና የኩርፊያ መዘዝ ይመስለኛል። አንዳንዶች በዕድሜ ወጣቶች መስለው ሊታዩ ይችሉ ይሆናል። አስተሳሰባቸው ሲመዘን ግን የቅድመ አያቶቻቸውን (የዘመኑን ሳይሞቅ ፈላ አብዮተኛ የኮሌጅ ተማሪዎች) ያረጀ “የሃሳብ ዩኒፎርምና ካፖርት” ደርበው ሲንጋፈፉ ማስተዋል እንግዳችን አይደለም። ዛሬም በተማሪነት ዘመናቸው እጃቸውን አውጥተው የፈከሩበትን ስታሊናዊ “የብሔር ጥያቄ በኢትዮጵያ – On the questions of nationalities in Ethiopia” ያፈጀ ፍልስፍና እንደ ዋነኛና ብቸኛ ሰነድና ሀገራዊ መፍትሔ ደጋግመው በመጥቀስ ሕዝቡን ካልጋትን እያሉ ሲወራጩ መመልከትን ተላምደነዋል። “አይተኬው የነበር ትውልድ” እያሉ ሲመጻደቁም የዚህን ትውልድ ሞራል እየተፈታተኑ ስለመሆናቸው አይረዱትም ብሎ ለመደምደም ቢያስቸግርም በእነርሱ ጦስ ምክንያት አሳሩን ሲበላ የኖረውን ይህንኑ ትውልድ ለማብሸቅ ስለመጠቀማቸው ግን ለማንም ሰው ይጠፋዋል ተብሎ አይገመትም። ይህንን መሰሪ አስተሳሰባቸውን ሊግቱን ሲሞክሩ ተሰላችተን በዝምታ ስናስተውላቸው ሃሳባቸውን የተቀበልን እየመሰላቸው በነጋ በጠባ ያደነቁሩናል።
ይህ ማለት ግን የቅድመ አያቶቻችን ሃሳብ በሙሉ ይኮነን ማለት እንዳይደለ በደማቁ እንዲሰመርልኝ እፈልጋለሁ። ቅድመ አያቶቻችን ጀግንነትን ከክብር ጋር አውርሰውናል። ይህ የምንኮራበት የታሪካችን አካል እንጂ ልንሸማቀቅበት የሚገባን አይደለም። ቅድመ አያቶቻችን ታላላቅ የመታሰቢያ ቅርሶችን አኑረውልናል። ለዚህን መሰሉ ልግስናቸው ከወንበራችን ከፍ ብለን ነዎሩ! በማለት ልናሞግሳቸው ይገባል። ኋላ አፈግፍገን ልንተቻቸው የሚያስችል የሞራል ብቃትም አይኖረንም። እንዲያም ቢሆን ግን የቅድመ አያቶቻችን የዘመን ዐውድ ከዛሬው ትውልድ አስተሳሰብ ጋር ሙሉ ለሙሉ ሊገጥም ይችላል ብሎ መከራከር ግን ጅልነት ነው። “ለምን አይገጥምም?” ብለን “በትናንት በሬ” የዛሬውን የፖለቲካ ማሳ ካላረስን ብለን ጠብ የምንገጥም ከሆነ ግን ትርፉ መላላጥና ትዝብት እንጂ ጎሽታ የሚያተርፍ ቅቡል ሃሳብ ሊሆን አይችልም።
ምልከታችንን ጠበብ አድርገን በማየት ሃሳቡን እናብላላ። ከዛሬ ሃምሳና ስድሳ ዓመታት በፊት ተማሪ የነበሩና “በዘመኑ ትግታግ” ይባሉ የነበሩ የያኔዎቹ ጎረምሶች ቢያንስ በዕድሜም ሆነ በአመለካከት አቅማቸው ከዛሬ ወጣቶች ፊት ተሰልፈው ከትውልዱ ዘመን ጋር ዘመናቸውን ለውድድር ለማሰለፍ ቢፍጨረጨሩ የፍልስፍናቸውና የወኔያቸው መቅኒ ስለደረቀባቸው በምንም ተዓምር በአሸናፊነት ሊወጡ አይችሉም። እውነቱ ቢኮመጥጣቸውም ከተፈጥሯዊ ሐቅ ጋር መፋለም ስለሆነ እውነታውን ቢረዱት አይከፋም። እንኳንስ ዘመንና ትውልድ ይቅርና ተፈጥሮን ራሷን ዛሬ በምልዓት ብንፈትሽ የትናንት ልትሆን በፍጹም አትችልም። ፍልስፍናውም ሆነ “የዲሞክራሲ” አተገባበሩ ልክ እንደ ባለቤቶቹ ግሪካዊያን ዘመን ዛሬም “እሽሩሩ” እየተባለ በአንቀልባ ሊታዘል ግድ አይደለም። ለካንስ “አንቀልባ” ስሙ እንጂ ግብሩ ለብዙዎቹ ባዕድ ነው – ዘመኑ ነዋ! ምን ይደረግ? ከዘመን ጋር መኳረፍም ሆነ መቋሰል የሚያዋጣ ፍልሚያ አይደለም።
ሌላ አንድ ምሳሌ እናክል። አሸባሪው ህወሓት የተወለደውና ያደገው በረሃ ውስጥ ነው። አካሉ ከተማ ገብቶ በሥልጣን ላይ ለ27 ዓመታት ያህል ቢቆይም ግብዓተ መሬቱ እስከተፈጸመበት ዕለት ድረስ ቀልቡ ትቶት ከመጣው የበረሃ ኑሮ ሊላቀቅ ስላልቻለ ሲያንጎራጉር የኖረው “ጥራኝ ጫካ እረ ጥራኝ ዱሩ” እያለ ነበር። በዚህም ቅዠቱ ምክንያት ራሱ በፈጠረው ሀገራዊ ቀውስ ምክንያት አናቱ ተመትቶ መንፈራፈር ሲጀምር ዘሎ የተሸሸገው እዚያው ተወልዶ ያደገበት ዋሻ ውስጥ ነው።
ይህ ድርጊቱ ከዘመን ጋር ለመኳረፉና ከእርሱ በኋላ ለመጣው ትውልድ ቁብ እንደሌለው ጥሩ ማሳያ ነው። “በፋሲካ የደነቆረች ሁሌም ፋሲካ ይመስላታል” እንዲሉ የትናንቱ ጫካ ዛሬ ሊሸሽጋቸው እንደማይችል፣ የትናንቱ ዘርፎ በልነት እንደማያዋጣቸው፣ የትናንቱ የሽምቅ ውጊያም “የድንጋይ ዘመን ብልሃት” እንደሆነ ከቶም ሊረዱት አልቻሉም። ስለዚህም አለን እያሉ ይንፈራገጣሉ፤ አልሞትንም እያሉም በረሃ ለበረሃ እየተሽሎከለኩ በማንኮራፋት አረፋ ይደፍቃሉ።
ከዘመን የተኳረፈ ግለሰብም ይሁን ቡድን ህልሙም ሆነ ቅዠቱ “ትናንት ሁሉም ነገር ቀረ” ይሉት ዓይነት ፍልስፍና ነው። የዜማው ቅኝትም ልክ እንደ ሀገራችን ቡሄ ጨፋሪ ሕጻናት የሥልጣን ሙልሙል ልመና ስልታቸው “እንደ አሮጌ ጅብ አልጩኽብህ” የሚል ማስፈራሪያ ነው። ልባቸው እንደ ፀጉራቸው የሸሻቸው አንዳንድ የዘመን ኩርፈኞች ቢገባቸው ወይንም ምክር የመቀበል ልብ ካላቸው የሚበጃቸው ከትውልዱ ጋር ላያሸንፉ መጋፋቱን አቁመው ራሳቸውን ቢያሰክኑ ነው።
ከዘመን ጋር መኳረፍ ወይንም ዛሬን በትናንት አለንጋ ለመግረፍ መሞከር ትርፉ ውድቀትም፣ ክስረትም ነው። የሚያዋጣው መስከን ብቻ ነው። የሚያምረውም እንደ እድሜ ተከብሮ አንቱ መባል ነው። የሚመረጠው ትውልዱን በማክበር መከበር ነው። ከሁሉም የሚበጀው ከራስ በላይ ሀገር የሚሏት እናት ዘለዓለም ነዋሪ መሆኗን ማመን፤ ትውልድ ሁሉ መጭም ሂያጅም መሆኑን አምኖ በመቀበል ለተፈጥሮ ሕግ መገዛት ነው።
ጥንታዊው የግሪክ ጸሐፌ ተውኔት ሶፈክሊስ የሰውን ልጅ የዕድሜ ዘመን የገለጸው እንዲህ በማለት ነበር። “ጠዋት በአራት እግሩ የሚሄድ (ዘመነ ሕጻንነትን በማስታወስ)፣ ቀትር ላይ በሁለት እግሩ የሚራመድ (የወጣትነትንና የጉልምስናን ዕድሜ ለመወከል)፣ ምሽት ላይ በሦስት እግሩ የሚንገዳገድ (ምርኩዝ ግድ የሚልበትን የዕድሜ ምሽት ለማመልከት) በማለት ነበር። አንድ ሰው ከዘመን ተኳረፈ የሚባለው እነዚህን የተፈጥሮ ሥርዓቶች ሲቃረንና ሁልጊዜ በአራትም ይሁን በሁለት እግር ካልተራመድኩ ብሎ መንገታገት ሲጀምር ነው። ዕድሜውን ካደለ ምርኩዝ መደገፍም ግድ ነው። የዘመን ጠብ ይሏል ይህን እውነታ ላለመረዳት ልብን መድፈን ነው። ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ሰኔ 19/2013