በትን ያሻራህን ዘር
በጓጥ በስርጓጉጡ፣
በማጥ በድጡ፤
እንደ ተንጋለልክ እንደ – ዘመምክ፣
ትንፋሽህን እንደ ቋጠርክ፤
የተልእኮህን አባዜ፤
የሕይወትህን ቃል ኑዛዜ፤
ወርውር!
የእጅህን ዘገር፡፡
በትን!
ያሻራህን ዘር፡፡
ይዘኸው እንዳትቀበር፡፡
«ማስታወሻነቱ፤ የምቾት ሱስ ለሌለባቸው ለአገር ልማትና ዕድገት የትምና መቼም ደፋ ቀና ለሚሉ፤ ደበበ ሰይፉ፤ የብርሃን ፍቅር – ለራስ የተጻፈ ደብዳቤ፡፡»
«አሻራ» የሚለው ቃል ሰሞኑን በእጅጉ እየተወራለት፤ በእጅጉም ከአገራዊ የተለየ የተግባር ተልእኮ ጋር ተደጋግሞ እየተጠቀሰ እንዳለ ሳናስተውል የቀረን አይመስለኝም፡፡ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መሪ አርማም (ሎጎ) ይኼው የጣት አሻራ ምሳሌ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ይህ «አሻራ» የሚለው ግዙፍ ቃል አዋዋሉ ለብሔራዊ ጉዳያችን በምሳሌነት፣ ለአገራዊ ተልእኮ ባላደራነትም መገለጫነት መዋሉ ብቻም ሳይሆን የወቅታዊ የመጽሐፍ ርዕስ በመሆንም ከፍታው ገዝፎ የተለቀበት ወቅት ነው፡፡
«አሻራ» በሚል ርዕስ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የታተመውና የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተወካዮች ምክር ቤት ንግግር የተሰነደበት ይህ መጽሐፍ የተመረቀው ራሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩና ከፍተኛ የክልልና የፌዴራል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ግንቦት 30 ቀን 2013 ዓ.ም በሸራተን ሆቴል ነበር፡፡ የንግግሮቹ ቁጥር 16 ያህል ሲሆን የሚሸፍነው ጊዜም ከበዓለ ሲመታቸው ዕለት ከመጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ እስከ መጋቢት 14 ቀን 2013 ዓ.ም ያሉትን 36 ወራት ነው፡፡ በዚህ ጽሑፍ ትኩረት የማደርገው በመጽሐፉ ቅኝት ላይ ሳይሆን «አሻራ» የሚለውን ቃልና ጽንሰ ሃሳብ በድርበቡ ለመፈተሽና እንደምን በአሁኑ ወቅት ተደጋግሞ ሊጠቀስ እንደቻለ መለስተኛ ሃሳብ ለመፈነጣጠቅ በማሰብ ነው፡፡
የእጅ ጣት የውስጠኛው ክፍል እንደ መስታወት ባለ ቁስ ላይ ሲያርፍ የሚተወው ቅሪት (ሰንበር መሰል ቅርስ) ወይንም ጣታችንን ቀለም አስነክተን በማንኛውም ነገር ላይ ስንጭን የምናሳርፈው ምልክት አሻራ ይባላል፡፡ አሻራ በፖሊሳዊ የቴክኒክ ጥበብ ሲፈተሽ ማንነታችንን ያለ ስህተት ስለሚወክል በተለይም በወንጀል ምርመራ ወቅት አገልግሎቱ ከፍ ያለ ነው፡፡ (ሃሳቡ የተወሰደው ከዘርጋው የአማርኛ መዝገበ ቃላት ነው፡፡)
በዘመናዊው ሳይንስ አዲስ ግኝት «አሻራችን» የሚፈተሽ እንደ ቀዳሚ ዘመናቱ በጣታችን ብቻ ሳይሆን «የምላሳችን አሻራ» ልዩነትም ከጣታችን እኩል ማንነታችን የሚገለጥበትን የረቀቀ ምስጢር መያዙም በምርምር ተደርሶበታል፡፡
እስካሁን ለመተንተን የተሞከረው አሻራ የሚለው ቃል የተሸከመውን ጥሬ ትርጉም (Denotation) ለማስተዋወቅ ነው፡፡ ከመዛግብተ ቃላት ፍቺው እጅግ የላቀው ጽንሰ ሃሳብ (Connotation) አደራ ከተጫነበት ከአገራዊ የተለየ ተልእኮ ጋር እንዴት እንደሚሰናኝ ለማሳየት ጥቂት ጉዳዮች ለመጠቃቀስ ልሞክር፡፡
የተከበረው ነፍሰ ሄሩ መምህሬ ደበበ ሰይፉ ለዚህ ጽሑፍ በመንደርደሪያነት የተጠቀምንበትን አጭር ግጥም ያዋቀረው ታታሪው የአገሬ ገበሬ በእጆቹ ዘግኖ የሚዘራውን የክረምት ዘር ለማመልከት ሳይሆን ዜግነት የሚፈተንበትን የማንነት አቋም በጥበበ ቃላት ለማመላከት በማሰብ ነው፡፡
የግጥሙ መሠረታዊ መልእክት እያንዳንዱ ሰው ይብዛም ይነስ በአገርና በትውልድ ላይ የሚዘራው በተፈጥሮና በትምህርት ያገኘው እውቀትና ጥበብ እንዳለው ለማመላከት ነው፡፡ እንደ ቅዱስ መጽሐፍ አገላለጽ አንዳንዱ በእጁ የጨበጠውን ዘሩን በለም አፈር ላይ እየበተነ መቶ፣ ስልሳና ሠላሳ እጥፍ ምርት ሲያፍስ ይስተዋላል፣ አንዳንዱም በጭንጫ ላይ፣ አንዳንዱም በእሾህ መካከል ዘሩን እየበተነ ሲመክንበት ማስተዋላችን አልቀረም፡፡ በአጭር አነጋገር «አሻራ» ውክልናው በግል ሕይወት፣ በቤተሰብ ጓዳ፣ ከፍ ሲልም በማኅበረሰቡ የኑሮ ማሳ ላይ ቁምነገር ለመዋል የሚያስችለውን ብርታቱን የሚወክል አገላለጽ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በአይረሴ አባባል እንወክለው ከተባለም «ልጄ ሆይ! እንደምትኖር ሆነህ ሥራ፤ እንደምትሞት ሆነህ ኑር!» በሚለው የአዛውንቶች ብሂል መጠቅለልም ይቻላል፡፡
ታሪክ ያተምንበት የአሻራችን ውሎ፤
ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ለትውልድ የሚሸጋገር የዜጎች የዴሞክረሲ መሠረት አሻራ በስፋትና በምልዓት የታተመበት ዕለት ነበር፡፡ አሻራው የታተመበት ሰሌዳ ደግሞ ስድስተኛው ብሔራዊ ምርጫ ነበር፡፡ የምርጫው ውሎ ለእኛ መሪዎቻችንን የመረጥንበት ዕለት እንደሆነ ብናስብም ሰፋ አድርገን ካየነው ግን ነግ ተነገወዲያ መጻኢው ትውልድ እየተቀባበለ የሚተርከው ደማቅ ታሪክ እንደሆነም ሊዘነጋ አይገባም፡፡
በምርጫው ላይ የዴሞክራሲን ደማቅ ቀለም በጣታቸው ጠቅሰው ዘላቂ አሻራቸውን ለማኖር አደባባይ የዋሉ ከ38 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የመኖራቸውን ያህል፤ በአንጻሩ ደግሞ በአገር ክህደት የተጨማለቀ «አሻራቸውን» ለማሳረፍ የተጣደፉና የተወራጩ ጥቂት ባንዳዎችና ባዕዳን እንደነበሩ ለእኛ የዛሬ ክስተት፤ ለነገ ደግሞ ታሪክ ሆኖ የሚመዘገብ «የጠቆረ» እውነታ ነው፡፡
አገራዊ ጥረቱና ድካሙ መና ቀርቶ ብሔራዊው ምርጫ እንዲደነቃቀፍ በውስጥና በውጭ ያልተቀነባበረ የሴራ ዓይነት አልነበረም፡፡ ክፉ የትውልዳችን አረማሞዎች የአዳፋ ህሊናቸውን፣ የእጃቸውንና የምላሳቸውን አሻራ በንጹሕ የኢትዮጵያ ገላ ላይ ለማተምና ለማሳረፍ ያልቧጠጡት ተራራና ያልተጓዙበት መስክ ያለመኖሩን በዝርዝር ለማመላከት ባያዳግትም «ከሰደቡን መልሰው የነገሩን» እንዳይሆን በሆድ ይፍጀው ትእግስት ማለፉ ይቀላል፡፡ ሙከራቸው ቢሳካና አገር በእፍረት ብታቀረቅር ደስታቸው ብቻም ሳይሆን የአሸናፊነታቸው መገለጫ አድርገው ለመቦረቅ ጭምር ተዘጋጅተው ስለነበር የሄዱበት ርቀት እንዲህ በቀላሉ ደርሶ መልስ የሚባል ብቻ አልነበረም፡፡
ከወገናቸው ፊት ቆርሰው ወደ ባዕዳን ዞሮ ለመዋጥ ህሊናቸውን የገደሉት እኒህን መሰል የጥፋት መልእክተኞች አሻራቸው የሚወከለው እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) አገላለጽ «በአቧራ ላይ የሚያርፍ» እንጂ በጽኑ አለት ላይ የሚታተም ባህርይ የለውም፡፡ የፑሽኪንን ቅኔ ወደ ቋንቋችን የመለሰው ወዳጄ ታደለ ገድሌ (ዶ/ር) እኒህን መሰል ባለ ልሙጥ የጥቋቁር አሻራ የታሪክ ጉድፎች የገለጻቸው እንዲህ በማለት ነበር፡፡
«እነርሱን ተዋቸው ሥራህን ይናቁ፣
አንተ ባጋጋልከው በወይራ ፍልጥ እሳት ምራቅ እየተፉ፡፡»
የፖለቲካ መቅኒያቸው የደረቀው፣ የአመለካከት አድማሳቸው ከአፍንጫቸው ሥር ያልራቀው፣ «ሆዳቸው አምላካቸው፤ ነውራቸው ክብራቸው» የሆኑት እነዚህ ፀረ አገርና ፀረ ታሪክ ኢምንቶች የአገሪቱን ክብርና ሁለንተናዊ ገጽታ ጭቃ ለመቀባት ያልፈነቀሉት ድንጋይ፣ ያልማሱት ጉድጓድ አልነበረም፡፡ ችግሩ ድንጋዩን ለመፈንቀል ሲሞክሩ ተግባራቸው እፉኝት ሆኖ ሲነድፋቸው፣ የተንኮል ጉድጓድ ሲምሱም ሃሳባቸው እንደሚቀበርበት አለማወቃቸው ነው፡፡ የአገርን ገመና እንደተመኙት በዓለም ፊት አራቁተው ለማሳየት የሞከሩበት አካሄድም አሸክላ ሆኖ ራሳቸውን በወጥመድ ውስጥ ጣላቸው እንጂ አላተረፉበትም፡፡
የስድስተኛው ዙር ብሔራዊ ምርጫ እንደ ካሁን ቀደምቶቹ የአደባባይ ላይ ተውኔቶች በኮሚዲና በትራጄዲ ዘውግ እየተቀናበረና «በሜክ አፕ በተለበጠ አሻራ» የተጠናቀቀ አልነበረም፡፡ እያንዳንዱ ዜጋ የመብቱን ልክ ያህል እውነተኛ አሻራውን ያተመበት ታሪካዊ ዕለት ብቻም ሳይሆን ለትውልድ የሚተላለፍ ታሪክ የተከወነበትም ጭምር ነበር፡፡
እንኳንስ እኛን መሰል የዴሞክራሲ ተለማማጅ አገር ቀርቶ «መሠረታችን የፀናው በጠንካራ የዴሞክራሲ አለት ላይ ነው» እያሉ የሚፎክሩት አገራትም ቢሆኑ የምርጫ ባህላቸው ከጥቃቅን ስህተቶች የፀዳ ነው ለማለት ያዳግታል፡፡ በእኛም ዐውድ አንዳንድ ህፀፆች መንፀባረቃቸው ባይቀርም ከዋናው ስኬት አንጻር ሲገመገሙ ግን እዚህ ግባ የሚባሉ ዓይነት ያለመሆናቸውን በሚገባ እንድንረዳ ተደርጓል፡፡ ስለዚህም ይህ ብሔራዊ ምርጫ እንዲሳካ ቀንበሩን ተደጋግፈው የተሸከሙትን ሁሉ በጅምላ ብናመሰግናቸውና ብናጨበጭብላቸው ቢያንስባቸው እንጂ አይበዛባቸውም፡፡
ልምሻ ይዞት መሬት ለመሬት ሲንፏቀቅ የኖረው የአገራችን ዴሞክራሲ ዛሬ በእግሩ ቆሞ ዳዴ ሲል እያስተዋልን «ወፌ ቆመች» በማለት ማበረታታት እንጂ ከአውሮፓና ከሰሜን አሜሪካ የምርጫ ታሪክና ተሞክሮ ጋር እያጣቀስን ብናነጻጽር «የህልም ሯጭ» ከመሆንና ከመባል ነፃ ልንወጣ አንችልም፡፡ ስለዚህም ነው በአሻራችን ያተምነው የሰኔ 14ቱ ብሔራዊ ምርጫ ለእኛ የዕለት ውሎ ብቻ ሳይሆን ለትውልዶች የሚተላለፍ የጎላ ታሪክ ነው የምንለው፡፡ የብሔራዊ ምርጫው አሸናፊ ኢትዮጵያ መሆኗ የተረጋገጠው በብዙ መስፈርት ነው፡፡
የሟርተኞች ሟርት መክኖ ምርጫው በሰላም ተጠናቋል፡፡ የሞት ድግስ ዛቻ ሲጋብዙን የከረሙት ሁሉ በአፍረት አቀርቅረው ተክዘዋል፡፡ ከውጭ ሆነው «የቁራ ጩኸት ሲያሰሙ የነበሩ ተወላጅ ጉጉቶችና ባዕዳን ጆፌዎች» የቋመጡለት የደም ግብር በዜጎች የጨዋነት መከባበር መክኖ ኢትዮጵያ «ዕልል» ብላ ልጆቿን አመስግናለች፡፡ ይህን መሰሉ አስደማሚ ውጤት ሊገኝ የቻለው በሕዝባችን አርቆ አሳቢነት፣ በምርጫው አስፈጻሚ አካልና ተባባሪዎቹ፣ በጸጥታ ክፍሎች ትጋት፣ በተፎካካሪ ፓርቲዎች ስክነትና ማስተዋል፣ በብዙኃን መገናኛ ባለሙያዎች ቁርጠኝነት፣ በመንግሥት የልብ ስፋትና ድጋፍ ስለሆነ አሸናፊዋ ኢትዮጵያ «ታሪካዊ አሻራቸውን ያሳረፉትን» ልጆቿን ሁሉ ደግማ ደጋግማ አመስግናለች፡፡ ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ሰኔ 18/2013