ኢትዮጵያውያን ለወራት የተለየ ትርጉም የመስጠት ልማድ አላቸው፡፡ አንዳንዶች ወራትን እየለያዩ ብሩህና መልካም ነገር ይዞ የሚመጣ ነው እያሉ ያስባሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ መዓቱን፣ ጉዱን ሰብስቦ እንደሚመጣ
ይገምታሉ፡፡ እኔም ብሆን ከወራት ጋር ተያይዞ ጥቂት የማይባሉ አጋጣሚዎችን አስተውያለሁ፡፡
ከግብርና ስራ እና ከትምህርት ቤቶች መዘጋት ጋር ሲያያዝ የቆየው የሰኔ ወር ደግሞ አሁን አሁን በአዲሲቷ ኢትዮጵያ የፖለቲካ ሂደት ውስጥ የራሱን አሻራ ማሳረፍ ጀምሯል፡፡ በተለይም በተከታታይ ያሳለፍናቸው ሰኔዎች የአሁኒቷን ኢትዮጵያ መከራና ጭንቀት፣ ተስፋና ድል ፍንትው አድርገው የሚያሳዩ ናቸው ለማለት ይቻላል፡፡
ወቅቱ ታኅሣሥ ወር ዓመቱ ደግሞ 2010 ዓመተ ምህረት ነው። ኢህአዴግ ከሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች እየደረሰበት ያለውን ውግዘትና ተቃውሞ ለመቀልበስና ስልጣኑንም ለማረጋጋት ጥልቅ ተሃድሶ ውስጥ መግባቱን ይፋ አድርጓል ። በዚህ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ለሀገርና ለህዝብ ጥቅም ሲባል ስልጣን መልቀቃቸውን ገለጹ፡፡ የኢህአዴግ የጥልቅ ተሃድሶ ግምገማ በዝግ መካሄዱን ቀጠለ። በመጨረሻም ለ17 ቀናት የተደረገው ሚስጢራዊ ግምገማ እንደ ኢህአዴግ አጠራር ‹‹ጥልቅ ተሃድሶ ›› ሲጠናቀቅ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ‹‹እፎይ…›› አለ።
ከጊዚያት በኋላ በበርካታ ሰዎች ልብ ውስጥ ቦታ የነበራቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ አዲሱ የኢትዮጵያ መሪ መሆናቸው ታወጀ። መጋቢት 23 ቀን 2010 ዓ.ም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ከኢህአዴግ መሪዎች አንደበት ተደምጠው የማያውቁና ጆሮ ገብ የሆኑ ውብ ቃሎች፣ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ አንደበት ዘነቡ። ዓለም በአድናቆት አድምቆ አጨበጨበ፡፡ በዚህ የትላንቶቹ አንዳንዶች ክፉኛ ተከፉ፣ አኮረፉ፤ የውስጣቸው ቁጭትና ንዴት ሲግም የጥቅማቸው መንበር ሲናጋ ደግሞ ለበቀል አሴሩ፣ ተዘጋጁ፡፡
ሰኔ 16 /2010
አሁን ለ27 ዓመታት በኢህአዴግ ላይ ተቃውሞውን ሲያሰማ የነበረው ህዝብ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይዘውት በመጡት አዲስ የመደመር ሃሳብ በደስታ ተሞልቷል። እያንዳንዱ ሰው በተገናኘ ቁጥር ስለ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ብልህነት፤አርቆ አሳቢነት ያወጋል፡፡ ስለማንነታቸው እያነሳ ያደንቃል፣ ያመሰግናል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የሰብአዊነት ባህሪ የተላበሱ መሪ መሆናቸውን እየጠቀሰ ካለፉት መሪዎች ጋር ያወዳድራል፡፡ የለውጥ ንፋስ በየአገሩ ደርሷል፡፡
ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያለውን አክብሮትና ፍቅር ለማሳየት ዕድሉን መጠቀም የሻተው ታላቁ ህዝብ የውሰጡን ስሜት ለመግለጽ፣ የደስታውን ጥግ ለዓለም ለማሳየት ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓመተምህረት አይቀሬውን ቀጠሮ ይዟል። ከአራቱም የሀገሪቱ አቅጣጫ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ ወደ መስቀል አደባባይ ተመመ። የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይን ምስልና አወዳሽ መልዕክቶችን ከፍ አድርገው የያዙ ሰልፈኞች ስፍራውን ማጥለቅለቅ ጀምረዋል፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ፎቶ የደመቁ ቲሸርቶችን የለበሱ በርካቶች በታለቅ ድምጽ የውሰጣቸውን እውነት እየተነፈሱ ነው፡፡
አንዳንዶች ከሌሊቱ 10 ሰዓት ጀምሮ በአደባባዩ ተገኝተው የዝግጅቱን መጀመር ሲጓጉ ቆዩ፡፡ ሌሎችም ርቀት አቋርጠው በማለዳ ደርሱ፡፡ የታሪካዊ ቀን ዝግጅት ተጀመረ። ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ከደቂቃዎች በኋላ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከመድረኩ ከፍታ ተከሰቱ። ደጋፊው በሆታ ተንጫጫ፣ የደስታ ዕንባዎች ረገፉ፣ ፈገግታ የተላበሱ ገጽታዎች ጎልተው ታዩ፡፡ ዓለም በአድናቆት አፉን ከፈተ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላከበራቸው ህዝብ የአክብሮት ሰላምታ ሰጥተው ወደ መልዕክታቸው ገቡ። ብዙም ሳይቆይ አስደንጋጭ ፍንዳታ ተሰማ። ጠቅላይ ሚኒስትሩና ሌሎች የሥራ ባልደረቦቻቸው በተደናገጠ ስሜት መድረኩን ለቀው ወረዱ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለመግደል ያሴሩ እጆች ቦንቦችን ወረወሩ። ይህ ሲሆን በመስቀል አደባባይ የተሰበሰበው ህዝብ ጉዳዩን በቅጡ አልተረዳም፡፡ በድንጋጤ፣ በግፊያና ትርምስ ውስጥም አልገባም፡፡ ይህ አጋጣሚ የበርካታ ሰዎችን ህይወት አተረፈ፡፡ ያም ሆኖ በወቅቱ ፍንዳታ የሁለት ሰዎች ህይወት አልፎ ከመቶ በላይ ሰዎች ቆሰሉ፡ ፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተረፉ። ያችም ቀን ከደብዛዛ ቀናት መሀል አንዷ ሆና ዛሬ በታሪክ ትታወሳለች፡፡
ሰኔ 15/ 2011
የሰኔ 15 ትዕይንት ወደ አማራ ክልልና አዲስ አበባ ከተማ ይመልሰናል። የአማራ ክልል ለበርካታ ጊዜያት ሰላምና መረጋጋት ርቆት ቆይቷል። በየቦታውም በሚከሰቱ የጸጥታ መደፍረሶች የበርካቶች ህይወት እያለፈ ነው፡፡ በአመራሩና በክልሉ የጸጥታ ኃይሎች መካከል አለመግባባት መኖሩ ሲነገር ቆይቷል። ክልሉን ለማረጋጋት ሁነኛ አመራሮች ተመርጠው መሪነቱን ተረከቡ። ከእነዚህ አመራሮች መካከል ምስጉኑ እና ተወዳጁ ዶክተር አምባቸው መኮንን ፤ አቶ እዘዝ ዋሴና አቶ ምግባሩ ከበደ ይገኙበታል።
እነዚህ የህዝብ ልጆች የተጣመመውን ለማቃናት፤ የደፈረሰውን ለማጥራት ከህዝብና መንግሥት የተሰጣቸውን አደራ ተቀብለው ፈታኝ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ክልሉን ማስተዳደር ጀምረዋል። እኩይ ተልዕኮ ያነገቡ እጆች የእነዚህን የህዝብ ልጆች ህይወት ለመንጠቅ አሲሮ ተነሳ።
በዕለቱ አመራሮቹ በአንድ ተገኝተው የህዝብንና ሀገርን ጉዳይ እየመከሩ ነበር፡፡ ክፉ አሳቢዎቹ በባህርዳር ከተማ የምክርቤት አዳራሽ ድረስ በመዝለቅ የዶክተር አምባቸውን፤ የአቶ እዘዝ ዋሴንና የአቶ ምግባሩ ከበደን ህይወት ነጠቁ። በወቅቱም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ እንዳሉትም‹‹ ዶክተር አምባቸው መኮንን እንኳን ሊገድሉት ሊቆጡትም የሚያሳሳ ዓይነት ሰው ነበር።›› በእዚያው ዕለት በአዲስ አበባ ውስጥ ተመሳሳይ የጥፋት እጆች ተዘረጉ። የመከላከያ ሠራዊት ኢታማዦር ሹም ሰዓረ መኮንና ጄኔራል ገዛኢ አበራ በኢታማዦር ሹሙ ቤት ተገደሉ። ሀገሪቱም ዳግም በኀዘን ጽልመት ተዋጠች። ቀኗም የኢትዮጵያውንን ልብ ከሰበሩ ቀናት አንዷ ሆና ትታወሳለች፡፡
ሰኔ 22/ 2012
በነፃነት ታጋይነቱ ይታወቃል። ብዙዎች አንደበታቸው በተዘጋበት ወቅት የብዙዎች አንደበት ሆኖም አምባገነንነትን፣ ኢፍትሐዊነትንና ፀረ ዴሞክራሲያዊነትን አውግዟል። ሞትን ፊት ለፊት ተጋፍጧል። ከአንደበቱ በሚወጡት ውብ ቃላትና ልብ አንበርካኪ ዜማው የብዙዎችን ቀልብ ገዝቷል። አርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ። ገና ወጣት ነው። በዚህ የወጣትነት ዕድሜው ግን ዘመን ተሻጋሪ ሥራዎችን ሠርቶ የነፃነት ተምሳሌት ሆኗል። ይህ ወጣት በአረመኔ እጆች ሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ/ም ህይወቱ ተቀጥፋለች። እኩይ ዓላማ ያላቸውና ህዝብን በህዝብ ላይ በማነሳሳት ሀገሪቱን ለማፍረስ የሚፈልጉ ስውር እጆች ሀጫሉን አሳጡ። ሆኖም ሀጫሉ ከዚህ በኋላም የኦሮሞ ህዝብም ሆነ የኢትዮጵያ ህዝብ የነፃነትና የትግል ተምሳሌት ሆኖ ለዘላለሙ ይኖራል። ቀኗም ኢትዮጵያውያን የሃዘን ማቅ ከለበሱባቸው ቀናት አንዷ ሆና ትታሰባለች፡፡
ሰኔ 14/2013
በሦስቱ ሰኔዎች በተቀጠፉ ወድ የኢትዮጵያ ልጆች መስዋዕትነትም ፍትሐዊነትና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ ምድር ላይ ያበበባት ቀን ናት፡፡ በሶስቱ ሰኔዎች በአረመኔዎች የተቀጡ ውድ ኢትዮጵያውያን ይህችን ቀን ማየት ባይችሉም በእነሱ መስዋዕትነት ጭምር የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድነት የቆመበት፤ ለእኩልነትና ለፍትህ አሻራውን በአንድ ድምጽ ያሳረፈበት፤ ድምጹን በመስጠት ወኪሎቹን የመረጠበትና ለዴሞክራሲ መሰረት የጣለበት ልዩ ቀን ነው፡፡ በዚች ቀን የታየውን ዴሞክራሲ ወጋገን የኢትዮጵያ ህዝብ እንዳያይ በርካታ ሴራዎች ቢጎነጎኑም የኢትዮጵያ ህዝብ የሚወዱትን የሚያኮራ የጠሉትን የሚያሳፍር ቀናኢ ህዝብ ነውና ሰኔ 14 ቀን 2013 ደማቁንና በታሪክ መዝገብ ውስጥ የሚሰፍረውን ምርጫ በማካሄድ የሶስቱን ሰኔዎች ሴራ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማምከን ችሏል፡፡
እስማኤል አረቦ
አዲስ ዘመን ሰኔ 18/2013