አለም ለሃይል ፍጆታ ከሚያውላቸውና ከማይተኩ የተፈጥሮ ሃብቶች ውስጥ የድንጋይ ከሰል፣ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ በዋናነት ይጠቀሳሉ::ይህ ሃይል አካባቢን በመበከል በሰዎች ጤና ላይም ከፍተኛ ችግር እየፈጠረ ይገኛል::በተለይ ደግሞ ከግዙፍ ፋብሪካዎች ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቀው በካይ ጋዝ ለኦዞን መሸንቆር አስተዋፅኦ በማድረግ ተለዋዋጭ የአየር ንብረት እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል::
በዚሁ ተለዋዋጭ የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የአለም ሙቀት መጨመርና የጎርፍ መከሰት ያስደነገጣቸው አብዛኛዎቹ የአለም ሀገራትም የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለ ያለውን ሁሉን አቀፍ ተፅእኖ ለመቀነስ ፓሪስ ላይ እ.ኤ.አ በ2016 ስምምነት ፈርመዋል::ይህንኑ ተከትሎም በርካታ ሀገራት ከነዳጅ ሃይል ይልቅ ወደታዳሽ ሃይል ፊታቸውን ካዞሩ ሰንበትበት ብለዋል::የነዳጅ ሃይል አቅርቦት እምብዛም የሌላቸው ሀገራትም የሃይል ምንጫቸውን ከነፋስና ፀሃይ ካደረጉ ቆዩ::
ታዳሽ ሃይል የአየር ንብረት ለውጥ ሚዛንንና የአካባቢን ስነ ምህዳር በመጠበቅ ረገድ ጉልህ ሚና እንዳለው ታምኖበት በርካታ ሀገራት ወደዚህ የሃይል ምንጭ ፊታቸውን ባዞሩበት በዚህ ጊዜ አውስትራሊያ በድንገት የ36 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር የንፋስ፣ ፀሃይና ሃይድሮጅን ግዙፍ ፕሮጀክት በአካባቢ ላይ ተፅእኖ ያሳድራል በሚል ውድቅ አድርጋለች ሲል ቢዝነስ ስታንዳርድ በዚህ ሳምንት መግቢያ ፅፏል::ውሳኔው በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ ካሉት ታላላቅ የአረንጓዴ ኃይል ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ የሆነውን ፕሮጀክት ያስቀረ መሆኑም ተነግሯል::
ዘገባው መንግስት በምዕራባዊ አውስትራሊያ ራቅ ባለ አካባቢ በ36 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ለመገንባት አቅዶ የነበረውን የነፋስ ፣ የፀሐይ እና የሃይድሮጂን ታዳሽ ሃይል ፕሮጀክት እቅድ ውድቅ ማድረጉን ገልፆ፤ እቅዱ ተግባራዊ ቢሆን በዓለም ላይ ካሉ ትላልቅ የአረንጓዴ የሀይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ሊሆን ይችል እንደነበር አስታውቋል ::
በሀገሪቱ የአካባቢ ጥበቃ ዲፓርትመንት ድረ ገፅ በታተመውና ሰኔ 15 ቀን 2021 በሰፈረው ውሳኔ የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስቴር ሱዛን ሌይ ‹‹ኤዢያን ሪኒዌብል ኢንርጂ ኸብ›› የተሰኘው ፕሮጀክት አለም አቀፍ እውቅና ባለው የእርጥበታማ መሬትና በስደተኛ የወፍ ዝርያዎች ላይ ግልፅ የሆነና ተቀባይነት የሌለው ተፅእኖ እንዳለው መናገራቸውንም ዘገባው ጠቅሷል::
‹‹ኤዢያን ሪኒዌብል ኢነርጂ ኸብ›› የተሰኘው ፕሮጀክት ፒልባራ በተሰኘ የሀገሪቱ አካባቢ 15 ጊጋ ዋት አቅም ያለው ታዳሽ ሃይል ለማመንጨት ታስቦ ዲዛይን የተደረገና በሂደት ደግሞ ወደ 26 ጊጋ ዋት በማስፋት አረንጓዴ ሃይድሮጂንና አሞኒያን ወደ ውጪ ለመላክ ውጥን የተያዘለት እንደነበርም በዘገባው ለትውስታ ተቀምጧል::መንግስት ፕሮጀክቱ ለአካባቢው የሚያበረክተውን የንፁህ ኃይል ኢንዱስትሪና ሊያመጣ የሚችለውን ሰፊ የኤክስፖርት ዕድል በመለየት ፕሮጀክቱ በፍጥነት ወደ ስራ እንዲገባ ባለፈው መስከረም ወር እውቅና ሰጥቶት የነበረ መሆኑም በዘገባው ተጠቁሟል::
ፕሮጀክቱ ኤዢያን ሪኒዌብል ኢነርጂ ኸብ /AREH/ በግል ባለቤትነት የያዘው መሆኑንና ኢንተርኮንቲኔንታል ኢነርጂ ፣ ሲ ደብሊው ፒ ኢነርጂ እስያና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የንፋስ ኃይል ማመንጫ አምራች በሆነው ቬስታስ እና በማኳሪ ቡድን ግሩፕ እየተዘጋጀ መሆኑም በዘገባው ተነግሯል::የአካባቢ ሚኒስቴሩ ውድቅ በሆነው ውሳኔ ውስጥ የፕሮጀክቱን ማስፋፊያ እቅድ መጠቀሳቸውንና የፕሮጀክቱ ዋና እቅድ ባለፈው ታህሳስ ወር የአካባቢ ተፅእኖ ግምገማ ማረጋገጫ አግኝቶ እንደነበር ማስታወቃቸውንም ዘገባው አያይዞ ጠቁሟል::
የታሰበው ማስፋፊያ ሃሳብ የመጣው አሞኒያ ለተሰኘውና ከውሃ፣ አየርና ፀሃይ ለሚሰራ ታዳሸ ሃይል የወደብ መሰረተ ልማት ለመገንባትና የፕሮጀክቱን ሰራተኞች ጨምሮ 800 ያህል ነዋሪዎች የሚይዝ ከተማ ለመመስረት ታስቦ እንደነበርም በዘገባው የተገለፀ ሲሆን በእርጥበታማ መሬቶች ውስጥ አሞኒያን፣ የባህር ውሃንና ብራይንን ለማጓጓዝ የሚያስችል የቱቦ መስመር ዝርጋት ስራን እንደሚያጠቃልልም ታውቋል::
“አሁን የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስቴሩን ስጋቶች ለመረዳት እየሰራን ሲሆን በፕሮጀክቱ ዝርዝር ዲዛይንና ኢንጂነሪንግ ዘርፎች ላይ በጋራ መስራታችንን ስንቀጥል ይበልጥ እየተግባባን እንመጣለን” ሲል የ“AREH” ጥምረት በመግለጫው ማስታወቁንም ዘገባው አመልክቷል::
ፕሮጀክቱ እ.ኤ.አ. ከ2014 ጀምሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የታቀደው የነፋስ እና የፀሐይ ኃይልን ለማመንጨት እና በባህር ውስጥ ለውስጥ ይህን ሃይል በቱቦ አማካኝነት ወደ እስያ ለማስተላለፍ የነበረ መሆኑንም ዘገባው ጠቅሶ፤ ነገር ግን ባለፈው ዓመት እቅዶችን ቀይሮና ዓላማውን ለውጦ ሃይድሮጂን እና አሞንያን በማምረት ውሃ ለማከፋፈልና ንፁህ ሀይልን ለመጠቀም እንደነበርም አስታውቋል::
‹‹የአውስትራሊያ ክሊን ኢነርጂ ምክር ቤት እንዳስታወቀው፤መንግስት ማንኛውንም የአካባቢ ተጽዕኖዎችን ለመገምገም እና መፍትሄ ለመስጠት ከ “AREH” ጋር ይሠራል›› ማለታቸውንም ዘገባው ተናግሯል::
የአውስትራሊያ ኮርፖሬት የአየር ንብረት እና የአካባቢ ዳይሬክተር ዳን ጎቸር በበኩላቸው ‹‹የሃይድሮጂን ኢኮኖሚ ልማት ላይ መንግስት ጠንካራ አቋም ካለው ለእውነተኛ ዜሮ የካርበን ልቀት ፕሮጀክቶች ቅድሚያ የሚሰጡ ኩባንያዎች የመጨረሻ የኢንቨስትመንት ውሳኔ ላይ እንዲደርሱ መታገዝ አለባቸው›› ማለታቸውን ዘገባው በመቋጫው አስቀምጧል::
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሰኔ 16/2013