ዛሬ በጉጉት የምንጠብቀው ምርጫ እያካሄድን ነው። ከፊታችን በምርጫ የፈኩ በርካታ ብርሃናማ ማለዳዎች ይታዩኛል። ስለ ኢትዮጵያ የሚዘምሩ፣ ስለ ጥቁር ህዝቦች የሚናገሩ በርካታ የውዳሴ ድምጾች ከዚያም ከዚህም ይሰሙኛል። የጥንቱን ታላቅነታችንን የሚመልሱ የብስራት መለከቶች በሀገሪቱ አራቱም አቅጣጫ አታሞአቸውን ይጎስማሉ። ይህ የማንቂያ ድምጽ መላው ሀበሻ በአንድ የሚሰማው የድል ዜማ ሆኖ በየቤታችን አለ። ብዙዎቻችን ከፊታችን ባለው ታሪካዊ ምርጫ ነጋችንን አድምቀን ልንጽፍ የብዕራችንን አፍጢም ብራናችን ላይ ተክለናል። በብርሃናማ ነጋችን ጠየምያማ ትላንቶቻችንን ለማደስ ቀን የምንቆጥርም ብዙዎች ነን። ተለያይተን በቆምንባቸው በነዚያ የእኔነት ዘመን ላይ ውብ ጸዐዳ መልካችንን አሳድፈን ወያባ ገጽን የእኛ አድርገናል።
በከሰርንባቸው በርካታ ዓመታት ውስጥ እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ማህበረሰብ ያጣናቸው በርካታ ነገሮች አሉ። እነዚህ ሀገራዊ ትሩፋቶቻችን እንዲመለሱ ደግሞ ምርጫ የዋጀው ብርሃናማ ነገ ያስፈልገናል። ኢትዮጵያን ያገነኑ፣ በሃሳብ የበላይነት የታጀቡ የኢትዮጵያ የከፍታ ማለዳዎች ግድ ይሉናል። ከፊታችን ይሄን እውነት የሚያረጋግጥ የሰማንያ ብሄረሰብ የጋራ ስዕል አለ። ከፊታችን ይሄን እውነት የሚጠብቅ መቶ ሃያ ሚሊዮን አካልና ነፍስ አለ። በዚህ የህዝቦች ፍትሀዊ የምርጫ ሂደት ታጅበን ነጋችንን ብሩህ የምናደርግበት የአንድነት ሃይል አለን። በዚህ የጋራ እውነት ተመርተን አሸወይና የሚሉ የህዝብ ድምጾች የሚሰሙበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም። ይህ ወቅት ለእኔም ለትውልዱም ታሪካዊ ወቅት ነን። ሀገራችን በታሪኳ አይታው የማታውቀውን ነጻና ፍትሀዊ ህዝባዊ ምርጫ እያደረገች ነው። በዚህ ምርጫ ሀገራችን ኢትዮጵያ ሰንኮፏን ጥላ በታደሰ አዲስ ማንነት ዳግም ልትነሳ ዋዜማ ላይ ናት።
ሁሉም የዓለም ሀገራት የራሳቸው የሆነ ታሪክ አላቸው። ወደ ኋላ ሄደን ታሪክ ብናገላብጥ ዓለም ላይ በስልጣኔአቸው ጥግ የደረሱ ሀገራት ከምንምነት ወደ ላቀ ስልጣኔ የተመነደጉበትን ትላንትናዊ ታሪክ እንደርስበታለን። አንድ ወቅት ላይ ድሃ የነበሩ ሀገራት በመሪዎቻቸው ብርታትና በህዝቦቻቸው የላቀ ተሳትፎ ከዜሮ ተነስተው ዛሬ ላይ ግዙፍ ኢኮኖሚን የገነቡ ናቸው። ራሷን እንደ ዓለም ፖሊስ የምታየው ታላቋ ሀገር አሜሪካ እንኳን አንድ ወቅት ላይ ሀገር ለመባል ያልደረሰች በደን እና በአራዊት የተሸፈነች ምድር ነበረች። የኮሎንቦስን ጥሪ ተከትለው ከተለያየ የዓለም ሀገራት ወደ ስፍራው በመሄድ በተባበረ ክንድ አሜሪካንን መሰረቷት። የአሜሪካ ስልጣኔ የተባበረ ክንድ ውጤት ነው። ከሀገር ኋላ፣ ከሰው ልጅ ኋላ፣ ከታሪክና ከስልጣኔ ኋላ ተነስታ ዛሬ ላይ አሜሪካ የታላቅነት ምሳሌ ሆና ቆማለች። በነገራችን ላይ ሀገራችን ኢትዮጵያ የስልጣኔ አልፋና ኦሜጋ ናት። የመጀመሪያው የሰው ልጅ የተገኘባት በኩረ ዘፍጥረት ተብላ ትጠራለች። ይሄ ብቻ አይደለም የኢትዮጵያ ስልጣኔ የአሜሪካንን ስልጣኔ በሁለት ሺ አምስት መቶ ዓመት (2500) ይቀድመዋል። ይህ ማለት የዛሬው የአሜሪካና አሜሪካውያን ስልጣኔ መሰረቱ የኢትዮጵያ ስልጣኔ ነበር ማለት ነው።
አሜሪካ የተነሳችው ኢትዮጵያን እያየች ነው። ሁሉም ቀርቶ ለብዙ ሀገራት እንደ ምሳሌ የምትታየውን ቻይናን ማየቱ በቂ ነው። የቻይና አሁናዊ እድገትና ስልጣኔ በትናንት የተፈጠረ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ነው። ከቅርብ ዓመታት በፊት ቻይናውያን ድሃ ከሚባሉ የዓለም ሀገራት የሚመደቡ ነበሩ። ከዛሬ ሃምሳ ዓመት በፊት በመሪያቸው የላቀ አስተሳሰብ ቻይና የዓለምን ግዙፍ ኢኮኖሚ መገንባት ችላለች። አሜሪካንን ጨምሮ በርካታ ሃያላን ሀገራትን በኢኮኖሚ አቅሟና በጦር መሳሪያዋ እያስፈራራች ያለችው ደቡብ ኮርያ እንኳን ትናንትና ከትናንት ወዲያ ታሪክ ያልነበራት የቅርብ ጊዜ ክስተት ናት። ሁሉም የዓለም ሀገራት ዛሬ ለነበሩበት ስልጣኔ መነሻ ታሪክ አላቸው። የሀገራችንም ትንሳኤ ከምርጫ በኋላ እንደሚመጣ የሚተነብዩ ብዙ ናቸው።
ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ የአትዮጵያውያን የከፍታ ዘመን እንደሆነ የሚመሰክሩ በርካታ ሙያዊ ትንታኔዎች እየወጡ ይገኛሉ። በርካቶች ከምርጫ በኋላ ያለችውን ኢትዮጵያ ለማየት እጅግ ጓጉተዋል። እንደ ቻይናና ደቡብ ኮርያ ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫም የኢትዮጵያ የመነሳት ዘመን ነው የሚሉ ተበራክተዋል። ጠንካራዋና በሁሉ ነገሯ የተሳካላት ኢትዮጵያን ለመፍጠር እንደመስፈንጠርያ ሆኖ ሊያገለግል እንደሚችልም በርካቶች እየተናገሩ ነው። ኢትዮጵያ ቀደምት ብትሆንም ስልጣኔ ርቋት እስካሁን ድረስ የቆየችው ሁሉን አቀፍ የሆነ የጋራ ሃሳብና ህዝብን ያስቀደመ የአመራር ጥበብ ስላልነበረን ነው እላለሁ። ያለፉ በርካታ ታሪኮቻችን ከእድገት ይልቅ ለኋላ ቀርነት፣ ከብልጽግና ይልቅ ለክስረት የዳረጉን ሆነው ያለፉ ናቸው።
ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር የተረጋገጠባት ሀገር እንዳለችን ውሸት በተካኑ የንጉስ አፈ ቀላጤዎች ተነግሮናል። በብዙ መስዋዕት ውስጥ አልፈው በሁሉ ነገሯ ምቹ የሆነችን ሀገር እንደፈጠሩልን በየሚዲያው የሚነግሩን ብዙ ናቸው። ለወጣቱ የተመቸች፣ ማንም ሰርቶ የሚለወጥባት ሀገር እንዳለችን ሰምተናል። ሁሉም ነገር ወደ መሬት ሲወርድ ግን ሌላ ነው። ከሌሎች የምንሰማት ኢትዮጵያና እየኖርናት የምናውቃት ኢትዮጵያ የተለያዩ ናቸው። አንዳንድ ጊዜ ሌላ ኢትዮጵያ ትኖር ይሆን እንድንል ያስገድደናል። ውሸታሞቹ በተለቪዥን መስኮት ቀርበው የሚነግሩን ኢትዮጵያ ጭራሽ የማናውቃት ናት። በምላሳቸው የማናውቃትን ገነትን ይስሉልናል። ያለፉት በርካታ ዓመታት ለኢትዮጵያውያን ምቹ ያልነበሩ ብዙ ዋይታዎች፣ በርካታ የታፈኑ ድምጾች የሚሰማባቸው እንደነበሩ ለብዙዎቻችን ድብቅ አይደለም። ከነዚህ የማስመሰል ትዕይንቶች ውስጥ ደግሞ ያለፉት አምስት ምርጫዎች ቀዳሚ ተጠቃሾች ናቸው። በኢትዮጵያ ታሪክ ህዝብን የዋሹ፣ ህዝብን ያደናገሩ በርካታ አጋጣሚዎች ተከስተው ያውቃሉ።
እንደ አለፉት አምስት ሀገራዊ ምርጫዎች ግን ሀገርና ህዝብ በይበልጥ የተጭበረበረበት አጋጣሚ አለ ብዬ አላምንም። በህዝብ እንባና ደም የተጻፉ የተዋጣለት የማስመሰል ድራማዎች ነበሩ። ውሸት ለብሰው፣ ውሸት ተንተርሰው በንጹሀን ሞትና ስቃይ ያጌጡ መነሻና መድረሻቸው ሞት የሆነ አስከፊ ታሪኮች ነበሩ። ግን ደስ የሚለው ሁሉም ነገር ከህዝብ የተደበቀ አለመሆኑ ነው። በነገራችሁ ላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ከጥንት እስከዛሬ ተሸውዶ አያውቅም። እንደምታውቁት ሥርዓትን ለሚያወግዝ፤ መንግስትን ለሚተች ማህበረሰብ የሚሆን አልነበረም። እድሉን ቢያገኝ ሁሉም ሰው የሚናገረው ታሪክ አለው። ካለፈው አስከፊ ሥርዓት ለመውጣት አዲስ ቀን የሚጠብቅ ብዙ ነበር።
እነሆ ዘመን ተቀይሮ አዲስ ማለዳ ለማየት ችለናል። ከሁሉም ግን የሚመጣው ይበልጣል። ከፊታችን ትንሳኤአችንን የሚያበስሩ በርካታ የመንጋት ዘመኖች አሉ። የማጭበርበር ዘመን አልፏል። የውሸትና የማስመሰል ጊዜ ከእንግዲህ የለም። በከንቱ ያለፉና የባከኑ ዘመኖቻችንን በጠንካራ ሀገራዊ ለውጥ ለመካስ የተሰናዳንበት ጊዜ ላይ ነን። በዚህ ጊዜ ላይ ትናንት አይመለስም። በዚህ ጊዜ ላይ የህዝቦች ድምጽ እኩል ዋጋ አለው። ከክብረ ነክ ነውሮች በመራቅ ለሀገር ክብርና ለህዝቦች ደህንነት ቅድሚያ በመስጠት ወደ ፊት የምንገሰግስበት የመፍካት ዘመን ላይ ነን። ዛሬ ሁላችንም በጉጉት ስንጠብቀው የነበረው የምርጫ ቀናችን ላይ እንገኛለን። ይህቺ ቀን ልዩ ናት። አንድ ወቅት ላይ ታሪክ እንዳልነበራቸው ሃያላን ሀገራት ታሪካችንን የምንጀምርበት፣ ወደ ፊት ለመፈንጠር ወደ ኋላ የምንንደረደርበት የመነሻ አውዳችን ነው። በሳይንሱ ብንሄድ ሁሉም ነገር ከምንምነት ወደ ላቀ ማንነት ለመሄድ የሚነሳበት የራሱ የሆነ መነሻ ነጥብ (ተርኒንግ ፖይንት) እንዳለው ይነግረናል። በዚህም እሳቤ ዛሬ እያደረግን ያለነው ሀገራዊ ምርጫ ወደ ፊት ለመሄድ በምናደርገው ጽኑ ፍላጎት የተፈጠረ የመነቃቂያ መንፈስ ነው ማለት ነው።
ይህ ጊዜ ለኢትዮጵያውያን ከየትኛውም ጊዜ በተሻለ አስፈላጊ ጊዜ ነው። ሀገራዊም ሆነ ግለሰባዊ ለውጦቻችን ይሄን የምርጫ ማግስት ታከው የሚመጡ እንደሆኑ ምንም የሚያጠራጥር ነገር የለም። በርካታ ሃሳቦች ከዛም ከዚህም እየተሰሙ ነው። አይተን በማናውቀው ነጻነት፣ ሰምተን በማናውቀው ዴሞክራሲ ዜጎች ሃሳባቸውን በነጻነት እየገለጹ ነው። ፓርቲዎች በግልና በቡድን ለመሪነት የሚያበቃቸውን ሃሳብ ይዘው ካለምንም ተግዳሮት ወደ ህዝብ እየቀረቡ ነው። ይህ የለውጡ አንድ አመላካች እንደሆነ ማሰብ እንችላለን። በርካታ የህዝብ ጥያቄዎች መልስ እያገኙ ነው። ለሀገር የሚበጁ በርካታ የታፈኑ ድምጾች ከዛም ከዚህም እየተሰሙ ነው። ይህ ጊዜ ለብዙዎቻችን የመልካም እድል ጅማሮ ነው። ሀገራችን ልታሳካው ላሰበችው ሀገራዊ ስኬት ይህ ጊዜ ከምንም በላይ ያስፈልጋታል። ዓላማችን አንድ ሀገርና ህዝብ ከሆነ ከመቼውም ጊዜ በላይ እጅ ለእጅ የምንያያዝበት ጊዜ ላይ ነን። ከጨለማ ወጥተን ወደሚደነቅ ብርሃን እየሄድን ነው። ከፊታችን በምርጫ የፈኩ ብርሃናማ ነገዎች ተስለዋል። በህዳሴና በመንጋት ዘመን ላይ ናችሁ።
ምርጫ በሀሳብ ብልጫ እንጂ እንዳለፈው ሥርዓት ህዝብ በማጭበርበር የሚሆን አይደለም። እንደዛ እናድርግ ብንል እንኳን ጊዜውና ሁኔታዎች አይፈቅዱልንም። ወደ ፊት ለመሄድ በመንደርደር ላይ ነን። የዘመናት ህልምና ራዕያችን ፍሬ ሊያፈራ እርካቡን ረግጠናል። ከምርጫ በኋላ የሚፈኩ በርካታ ማለዳዎች አሉን። አሁን ጊዜው የእኛ ነው። ወደ ፊት ለምንራመድበት የእድገትና የብልጽግና ጉዞ መነሻውም መድረሻውም ህዝብ መሆን አለበት። በመንጋት ዘመን ላይ ቆመን ብርሃናችንን የሚያጨልም ምንም አይነት አስነዋሪ ድርጊት አንፈጽምም። እንደ ነውር ካወራናቸው በርካታ ትናንትናዊ ነውሮች አሉን። እንደ ታሪክ ከያዝናቸው ብዙ አስጸያፊ ትናንትናዎችን አልፈናል። ለምንም ነገር ያለፈው ይበቃናል።
ህዝብ ከመጥቀም ባለፈ ሀገርና ህዝብን የሚጎዳ ማናቸውንም ነገር ለማድረግ የቀረ ሞራል የለንም። ጊዜው አቅማችንን አሟጠን በመጠቀም የተሻለ ነገር ለመፍጠር የምንፍጨረጨርበት ነው። በውሸትና በማጭበርበር የፈረሰ እንጂ የቆመ ሀገርና ህዝብ የለም። ከፊታችን ብርሃን አለ። ተስፋ በጣልንበት የምርጫ ቀን ላይ ነን። በኢትዮጵያ ታሪክ ወርቃማው ትውልዶችም ነን። በዚህ ሁሉ መባረክ ውስጥ ቆመን የምንሰራው ሀገራዊ ስህተት ይኖራል ብዬ አላስብም። በብዙ ነገር ቁጭት ውስጥ ነን። ባልተኖረ ትናንትናችን፣ ባላሳካነው ሀገራዊ ስኬት፣ ባሳለፍነው የጦርነት ጊዜ፣ ባሳለፍነው የባከነ ጊዜ በዚህ ሁሉ የምንቆጭ ነን። ከእንግዲህ ከልማት ባለፈ የምናባክነው ጊዜ አይኖርም። ምርጫ ይዞልን በሚመጣው ሀገራዊ በረከት ተጠቅመን ሀገር ለመለወጥ መትጋት እንጂ በዋዛ ፈዛዛ የምናጠፋው ጊዜ አይኖርም። ይሄንን እውነት በመቀበል ለአዲስ ሀገራዊ ለውጥ ራሳቸውን ያዘጋጁ በርካታ ኢትዮጵያውያን በሀገሪቱ ሁሉም ክፍል አሉ። እኔና እናተም ከምርጫ በኋላ በምትፈጠረው ሀገራችን ላይ የራሳችንን ወጣታዊ አሻራ ለማሳረፍ ከወዲህ ታጥቀን መነሳት ይኖርብናል እላለሁ። በብርሃን በተሸነፉ ዳግም በማይመሹ የህዳሴ ማለዳዎች ላይ ቆመን ታላቋን ሀገራችንን አድምቀን እንጻፍ እያልኩ ላብቃ ቸር ሰንብቱ።
ዘለዓለም የሳጥን ወርቅ (የእፀ ሳቤቅ አባት)
አዲስ ዘመን ሰኔ 14/2013