ለአንድ ሀገር ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እንዲሁም በፖለቲካውም ሆነ ማህበራዊ ጉዳዮች ከሚገጥሙ መሰናክሎች ለመውጣት ችግር ፈቺ ምርምር ቁልፍ ሚና እንዳለው ይታመናል። ያደጉ ሃገሮች የእድገት ምስጢርም ከዚህ የመነጨ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው። በዩኒቨርሲቲዎች የሚደረጉ የጥናትና ምርምር ስራዎችና ውጤቶቻቸው በተግባር የህዝብን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መፍታት የሚያስችል ቁመናን መላበስ ይጠበቅባቸዋል። ከዚህ አኳያ የሀገራችንን ቁመና ስንመለከት የጥናትና ምርምር ውጤቶች በተግባር የህዝብን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ከመፍታት ረገድ ክፍተቶች አሉባቸው።
በሀገራችን የጥናትና ምርምር ሥራዎች ከተጀመሩ ከ70 ዓመታት በላይ ቢቆጠርም ምርምሮቹ ለማህበረሰቡ ችግር መፍቻ ይውሉ እንዳልነበር ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል። በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ገንዘብና እውቀት ፈሶባቸው የሚካሄዱ የምርምር ሥራዎች የሕብረተሰቡን ችግሮች መፍታት እንዲችሉና የታለመላቸውን ግብ እንዲመቱ መንግስት በትኩረት እየሰራ ይገኛል። በመሆኑም በዩኒቨርሲቲዎች የሚካሄዱ የምርምር ሥራዎች በቁጥር እያደጉ መጥተዋል። በተግባር የህዝብን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ወደ መፍታት መሸጋግራቸውን ቀጥለን የምንመለከተው ይሆናል።
የመስከረም 29ኙ ክስተት
ሚኒስቴሩ የተጀመረውን ለውጥ ማጠናከር የሚያስችል ሥራ እየተሰራ መሆኑን መስከረም 29 ቀን 2013 ዓ.ም ባወጣው መረጃ ማስታወቁ ይታወሳል። መረጃው፤ በኢትዮጵያ ስምንት የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች የምርምር ልህቀት ማዕከል በመባል መለየታቸውን የሚያመላክት ነበር። የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በሃገሪቱ ከሚገኙ 46 ዩኒቨርሲቲዎች የምርምር ልህቀት ማዕከል ተብለው ስምንቱ የተለዩበት ሦስት መስፈርቶች እንደነበሩት አስታውቋል። ዩኒቨርሲቲዎች በምርምር፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም በአጠቃላይ ትምህርት በሚሉ መስፈርቶች ተጠቅሟል። በተጨማሪም ባለፉት አመታት በርካታ ችግር ፈቺ የምርምር ውጤቶችን ሲያበረክቱ የቆዩና ወደፊትም አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል የተባሉ ስምንት ዩኒቨርሲቲዎች በምርምር ዘርፍ የልህቀት ማእከል እንዲሆኑ መለየታቸውን ነበር ያስታወቀው፡፡
በዚህም መሰረት ጎንደር፣ አዲስ አበባ፣ ባህርዳር፣ መቀሌ፣ ጅማ፣ ሃዋሳ፣ አርባምንጭና ሀሮማያ ዩኒቨርሲቲዎች የምርምር ልህቀት ማእከል እንዲሆኑ ተለይተዋል። የምርምር ዩኒቨርሲቲዎቹ በአለም አቀፍ ደረጃ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር አቻ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ አቅማቸውን ለመገንባት በትኩረት መስራት የሚያስፈልግ መሆኑ እሙን ነው። ይሄንኑ መሰረት በማድረግ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከሚገኙ 45 ዩኒቨርሲቲዎች “የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች” ተብለው ከተለዩ ስምንት ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አንዱ የሆነው ጎንደር ዩኒቨርሲቲን እንቅስቃሴ እንመለከታለን።
67 ዓመታት ወደ ኋላ
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በሃገራችን በቀዳሚነት የጤና ሙያተኞችን ለማፍራት የሕዝብ ጤና አጠባበቅ ኮሌጅና ማሰልጠኛ ማዕከል በሚል ስያሜ በ1947 ዓ.ም ከተመሰረተ 67 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ በእነዚህ ዓመታት ጉዞው በጅማሮው ምዕራፍ የሕዝብ ጤና አጠባበቅ ኮሌጅና የማሰልጠኛ ማዕከል፣ በሁለተኛው ምዕራፍ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ፣ በሶስተኛው ምዕራፍ አሁን እስካለበት ጊዜ ድረስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅና ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በሚሉ የተለያዩ ስያሜዎች የተለያዩ ምዕራፎችን አልፏል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ከመማር ማስተማሩ ጎን የምርምርና የተለያዩ የማህበረሰብ አገልግሎቶችን ለህብረተሰቡ ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከአንድ ኮሌጅነት ወደ አራት ኮሌጆች፣ ሶስት ትምህርት ቤቶችና ሁለት ፋካልቲዎች ማደጉን ተከትሎ በህክምናና ጤና ሳይንስ ዙሪያ ብቻ በምሁራን ይሰሩ የነበሩ ምርምሮችን ሲሰጥ የነበረው የማህበረሰብ አገልግሎት ለማህበረሰቡ ተደራሽ እንዲሆን ጥሩ አጋጣሚን ፈጥሯል።
በዚህ አግባብ ምሳሌ ሊሆኑ የሚችሉ ምርምሮችና የማህበረሰብ አገልግሎቶች በርከት እያሉ እንዲመጡ ሆኗል። በዚህ አግባብ ለ67 ዓመታት የተሰሩ ምርምሮችንም ስንቃኝ በመጀመሪያዎቹ አርባ እና ሃምሳ ዓመት ይሰሩ የነበሩ ምርምሮች በመምህራኑ በጎ ፈቃድና ፍላጎት ላይ የተመሰረቱ ነበሩ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ምርምሮች የሚሰሩት በትኩረት አቅጣጫዎች ተለይተው በተቀመጡ በተለዩ የምርምር አጀንዳዎች ሊሆን ስለሚገባው፤ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምርምር የትኩረት አቅጣጫዎችን የዛሬ አስር ዓመት ገደማ ለይቶ፣ ምሁራኑ የምርምር ስራዎቻቸውን እየሰሩ ይገኛሉ፡፡
አምስት ዓመታትን ወደፊት
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት በሀገር አቀፍ ብቻም ሳይሆን በአለም ዓቀፍ ደረጃ ተጽእኖ ፈጣሪ የሆኑ ትላልቅ የምርምር ሥራዎችን ለመስራት እቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በ2013 ዓ.ም ብቻ ከ700 በላይ የሚሆኑ ምርምሮች በአለም ዓቀፍ ደረጃ ማሳተም መቻሉን ከተቋሙ ያገኘናቸው መረጃዎች ያመላክታሉ። ይሕም ዩኒቨርሲቲው በአፍሪካ ከሚገኙ 1ሺህ 250 በላይ ዩኒቨርሲቲዎች 20ኛ ደረጃን፣ ከኢትዮጵያ ደግሞ ሁለተኛ ደረጃ ላይ እንዲቀመጥ አስችሎታል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አስራት አጸደወይን እንዳብራሩት፤ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በ2007 ዓ.ም ባወጣው የምርምር፣ የቴክንሎጂ ሽግግር፣ የማህበረሰብ አገልግሎት መመሪያና የምርምር አጀንዳዎች በርካታ ውጤቶችን ማስመዝገብ ችሏል። ተቋሙ በሀገር አቀፍ ደረጃ የምርምር ዩኒቨርሲቲ ተብሎ ከመለየቱ ጋር ተያይዞ የአስር አመት ስትራቴጂክ እቅድ አዘጋጅቶ ወደ ፊት ሊያስፈነጥሩት የሚችሉ ትልልቅ ሃሳቦችን በመቀመር ወደ ስራ መግባቱን ያመላክታሉ፡፡ ይሕን ለማሳካት በተለይ የምርምር፣ የማህበረሰብ አገልግሎት፣ የቴክኞሎጂ ሽግግርና በሳይንስ ዘርፍ በሚቀጥሉት አመታት ብዙ መስራት እንደሚጠበቅም ይናገራሉ፡፡
በዚህ ደረጃ ላይ የሚገኘው ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለምርምር የሰጠውን ልዩ ትኩረት መሰረት ያደረገ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ሀገር አቀፍ ምርምሮችን ማድረግ የሚያስችለውን ፕሮግራም ማዘጋጀቱን ያስታወቁት የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበራዊ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ቢኒያም ተክሉ ናቸው። ዶክተር ቢኒያም እንደሚሉት ዩኒቨርሲቲው በቀጣይ አመት ተግባራዊ የሚያደርገው ይሕ ፕሮጀክት የሶስተኛ ዲግሪ ትምህርትን ከምርምር ጋር በማጣመር፤ አንጋፋ ተመራማሪዎችን በማቀፍ በጋራ የሚተገበር ይሆናል። ለዚህ ደግሞ በሀገር አቀፍ ደረጃ ጠቃሚ በሆኑ አጀንዳዎች ላይ ምርምሮችን ለመስራት 20 አዳዲስ የምርምር ቡድኖች ተዋቅረዋል። ቡድኖች ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገባቸው ጉዳዮች ላይ ራሳቸውን ችለው ምርምሮችን እንዲያደርጉ ታሳቢ ተደርገው የተዋቀሩ ናቸው፡
ከፕሮጀክቱ ተጠባቂ ቱሩፋቶች
የምርምር ቡድኖቹ በ2014 ዓ.ም ወደ ተግባር እንደሚገቡ ያስገነዘቡት ዶክተር ቢኒያም፣ ይሄም ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ትላልቅ የምርምር ስራዎችን መስራት እንደሚያስችለው ያብራራሉ። “በትግበራው የምርምር ውጤቶች ብቻ አይጠበቁም” ያሉት ዶክተር ቢኒያም፤ የሚሰሩ ምርምሮች የሚፈለገውን ጥራትና ደረጃ እንዲያሟሉ ይደረጋል። ምርምሩን ማድረግ የሚያስችል በቂ የበጀት ድጎማ ይደረግላቸዋል፡፡ የፒኤች.ዲ ተማሪዎች ከሌሎች ትልልቅ ልምድ ካላቸው ተመራማሪዎች ጋር በማሰራት የአቅምና ልምድ ልውውጥ እንዲቀስሙ ይመቻቻል፤ መሰል ትስስሮችም ዩኒቨርሲቲው በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ትልልቅ የምርምር ስራዎችን እንዲሰራ ያስችሉታል በማለት ያብራሩ ሲሆን፤ በሀገር አቀፍ ደረጃም በጣም ጠቃሚ በሆኑ አጀንዳዎች ላይ የተለያዩ ምርምሮችን በመስራት ሀገሪቱ ወደምትፈልገው አቅጣጫ እንድትጓዝ አቅም የሚፈጥር መሆኑንም ይገልጻሉ፡፡
“በተጨማሪም ለፒኤች.ዲ (ሶስተኛ ዲግሪ) ምርምር የሚመደበው በጀት አነስተኛ በመሆኑ ተማሪዎች ጥራት ያለው ምርምር ለማካሄድ ይቸገራሉ “ያሉት ዶክተር ቢኒያም፤ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ፅህፈት ቤት ከአካዳሚክ ቢሮው ጋር በመቀናጀት የምርምሩንና የድህረ ምረቃ ትምህርቱን በአንድ ላይ በማስተሳሰር ጥሩ ምርምር ተሰርቶ ጥሩ መማር ማስተማር ማካሄድ እንዲቻል በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግ ለመግባባት ተችሏል።
በዚህ መሰረትም ፕሮጀክቱ ሊቀረጽ መቻሉን ነው ያመላከቱት። “በመሆኑም ችግሩን ለመቅረፍና ጥራቱን ለማሻሻል ከአንጋፋ ተመራማሪዎች ስር ሆነው የምርምር በጀት ተመድቦላቸው እንዲሰሩ ማድረግን አላማ ያደረገ ስለመሆኑም ነው ያስገነዘቡት። በመሆኑም የተዋቀሩት አዳዲስ የምርምር ቡድኖች በአንጋፋ ተመራማሪዎች የሚመራና የሶስተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን እንዲሁም ፖስት ዶክተራል ተማሪዎችን በማካተት በየኮሌጁ የተቋቋሙ ናቸው። ለምርምር ቡድኖቹ የምርምር በጀት ተመድቦላቸው ሰፊ፣ ችግር ፈቺና ጥራት ያለው ምርምር መስራት እንዲችሉ ሲሆን፤ በዚሁ መልኩም መዋቀራቸውን ነው ያስገነዘቡት፡፡
በመጨረሻም ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በቀጣዮቹ አስር ዓመታት በአፍሪካ ከሚገኙ ምርጥ 10 ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ ለመሆን እቅድ ይዞ እየሰራ መሆኑን ሲሆን፤ ለጥናትና ምርምር ተግባር የተለየ ትኩረት በመስጠት፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ጠቃሚ በሆኑ አጀንዳዎች ላይ ትኩረት በማድረግ፤ ትላልቅ ምርምሮችን በማከናወን፤ ይሕን ትልሙን ለማሳካት ፕሮጀክቱ ተግባራዊ መደረጉ፤ በተግባርም ውጤት ማምጣት የሚያስችል ስለመሆኑ ዶክተር ቢኒያም ተናግረዋል።
ዳንኤል ዘነበ
አዲስ ዘመን ሰኔ 14/2013