ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ ለውጡን ተከትሎ በመአድን ዘርፉ በተሰሩ ሀገር አቀፍ የሪፎርም ስራዎች መአድን የማምረት አቅምን በመጨመር ከዘርፉ የሚገኘውን የውጪ ምንዛሬ ማሳደግ ተችሏል። በተለይ ደግሞ ህግ-ወጥ ንግድን በመከላከል ለብሄራዊ ባንክ የሚቀርበው የወርቅ መአድን መጠን ከፍ በማለቱ ከመአድኑ የወጪ ንግድ የሚገኘው ገቢ እየተሻሻለ እንደመጣ ከመአድንና ነዳጅ ሚኒስቴር የወጡ መረጃዎች ያሳያሉ።
ወርቅ ለብሄራዊ ባንክ ቀርቦ የውጪ ምንዛሬ እንዲያስገኝ በማድረግ ረገድ ግምባር ቀደም ሚና ከተጫወቱ ክልሎች ውስጥ አንዱ የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ሲሆን ባለፉት ሦስት ዓመታት በባህላዊ የወርቅ አምራች ማህበራት አማካኝነት 777 ነጥብ 792 ኪ.ግ ወርቅ አምርቶ ለብሔራዊ ባንክ ገቢ አድርጓል። በክልሉ በሦስት ዓመት ውስጥ በባህላዊ ጌጣጌጥ አምራች ማህበራት 36 ነጥብ 24 ቶን /Blue Agate, Aquamarine, quartz, Amazonite, flourite/ ለላኪዎች እንዲቀርብ ከክልሉ መአድንና ኢነርጂ ኤጀንሲ የተገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በማዕድን ስራዎች ላይ የማዕድን መመሪያና ደንብ ማውጣትና ማሻሻል ስራዎች መከናወናቸውና ከላኪዎች ጋር በቅንጅት መሰራቱ ደግሞ የጌጣጌጥ ማዕድናት በከፍተኛ ደረጃ እንዲመረት አድርጓል፤ ለመጣው ውጤትም ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል። በሌላ በኩል በነዚህ ሦስት ዓመታት ከማዕድን ሮያሊቲና ከሌሎች ገቢዎች 140 ነጥብ 92 ሚሊዮን ብር ገቢ በዘርፉ መሰብሰብ የተቻለ ሲሆን 59 ሺ 442 ለሚሆኑ ዜጎች የስራ አድል እንደተፈጠረም እነዚሁ መረጃዎች ያመላክታሉ።
በሌላ በኩል የክልሉን የማዕድን ሀብት በዓይነትና በመጠን በጥናት እየለዩ በዘርፉ የሚደረገውን ኢንቨስትመንት ለማሳደግ 943 ካሬ ኪሎሜትር በሚሸፍን ቦታ ላይ የወርቅ፤ የጌጣጌጥና የኢንዱስትሪ ማዕድናት አለኝታ ጥናት በተለይ በዘንድሮ ዓመት ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ከኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ጋር በመቀናጀት ማከናወን በመቻሉ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉንና የማዕድን ምርት መጠንን ከማሳደግ አንፃር 10 ሚሊዮን ሚትር ኪዩብ ድንጋይና አሸዋ የኮንስትራክሽን ማዕድናት እንዲመረቱ መደረጉን መረጃዎቹ ይጠቁማሉ።
የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል መአድንና ኢነርጂ ኤጀንሲ የመአድን ዘርፍ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ እያሱ ማሞ እንደሚገልፁት ክልሉ በዘንድሮው በጀት ዓመት መጀመሪያ 10 ቶን /ዳግም በመከለስ ደግሞ 15/ ቶን /Blue Agate, Aquamarine, quartz, እና Amazonite/ የጌጣጌጥ መአድናትን አምርቶ በላኪዎች አማካኝነት ለውጪ ገበያ ለማቅረብ ያቀደ ሲሆን የበጀት ዓመቱ ሳይጠናቀቅ በአስራ አንድ ወራት ውስጥ 24 ቶን የጌጣጌጥ መአድን አቅርቧል። ከዚህም 96 ሺ የአሜሪካን ዶላር ገቢ ተገኝቷል። ይህ ከአምናው በጀት ጋር ሲዋዳደር አምና በዚህ ግዜ የተመረተው የጌጣጌጥ መአድን 10 ታቅዶ ከእቅድ በታች 3 ቶን ብቻ ነበር።
በዩኒቨርሲቲዎች በኩል በተደረጉ ጥናቶች አዳዲስ ግኝቶች መኖራቸውና፣ በርካታ ወጣቶችም በዚህ የጌጣጌጥ ማምረት ስራ በስፋት መሰማራታቸው እንዲሁም ወጣት የስራ እድል የተፈጠረላቸውን ከባለሃብቶች ሀገር የማስተሳሰር ስራ መሰራቱ ለምርቱ አፈፃፀም ከፍተኛነት ጉልህ ሚና ተጫውቷል።
ክልሉ በዚህ በጀት ዓመት ከአጠቃላይ የመአድን ዘርፍ 50 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ እቅድ ይዞም የነበረ ሲሆን በአስራ አንድ ወራት ውስጥ 56 ሚሊዮን ብር መሰብሰብ ችሏል። አስከበጀት ዓመቱ ማገባደጃ ድረስም ተጨማሪ ገንዘብ ይሰበሰባል ተብሎ ይጠበቃል። ይህ አፈፃፀም ከአምናው በጀት ጋር ሲነፃፀር በዚህ ግዜ የ8 ሚሊዮን ብር ብልጫ አለው።
በተመሳሳይ በበጀት ዓመቱ 400 ኪሎግራም የወርቅ መአድን ለብሄራዊ ባንክ ለማቅረብ እቅድ ተይዞ በአስራ አንድ ወራት ውስጥ 263 ኪሎግራም ወርቅ ለብሄራዊ ባንክ ማቅረብ ተችሏል። ይህም 65 ከመቶ ያህሉ ወርቅ ለብሄራዊ ባንክ መቅረቡን ያሳያል። ከአምናው በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀርም የዘንድሮው በዚህ ግዜ የ26 ኪሎግራም ወርቅ ጭማሬ አሳይቷል። በሁለት የወርቅ ማውጫ ወረዳዎች ላይ የእሳት አደጋ መከሰቱ እንጂ አፈፃፀሙ ከዚህም በላይ መሆን ይችል ነበር። በቀጣዩ ወር ለብሄራዊ ባንክ የሚጠበቀውን ያህል የወርቅ መጠን ከቀረበው አፈፃፀሙ ከእቅድ በላይ እንደሚሆን ይጠበቃል።
ዳይሬክተሩ እንደሚሉት ኤጀንሲው ከላይ በተሰጠው አቅጣጫ መሰረት በበጀት ዓመቱ በመአድን ዘርፍ 30 ሺ ለሚሆኑ ወጣቶች ግዚያዊ የስራ እድል ለመፍጠር አቅዶ እስካሁን ድረስ በአስራ አንድ ወራት ውስጥ 17 ሺ 881 ለሚሆኑ ወጣቶች የስራ እድል መፍጠር ችሏል። ከዚህ ውስጥም 4 ሺ 576ቱ ሴቶች ናቸው። ይህም ከአፈፃፀም አንፃር 60 ከመቶ ነው። አስካሁን ባለው ሂደትም አፈፃፀሙ ዝቅተኛ ነው።
አብዛኛዎቹ ወጣቶች በኮንስትራክሽን ማአድናት ዘርፍ ላይ መሰማራታቸውና ይህ ዘርፍ በሲሚንቶ ምክንያት መቀዝቀዙና ከአደራጅ መስሪያ ቤት በኩል የቅንጅት ችግር መኖር ለአፈፃፀሙ ዝቀተኛ መሆን በምክንያትነት ይጠቀሳሉ። ከዚህ በመነሳት ችግሩን ለመፍታት ኤጀንሲው ከአደራጁ መስሪያ ቤት ጋር በጋራ እየሰራ ይገኛል።
በሌላ በኩል በክልሉ በርካታ መአድናት ቢኖሩም በሚፈለገው ልክ አቅም ባላቸው ባለሞያዎች በቂ ጥናቶች ባለመካሄዳቸው መአድናቱን አምርቶ ጥቅም ላይ በማዋል ከዘርፉ በበቂ ሁኔታ የውጪ ምንዛሬ ማግኘት አልተቻለም። በመአድን ማውጫ አካባቢዎችም በቂ የመሰረተ ልማት አቅርቦት የለም። የክልሉ መንግሥትም በነዚህ አካባቢዎች ላይ መንገዶችን የመገንባት አቅሙ ውስን ነው። ይህም ባለሃብቶች እንደልብ ገብተው እንዲሰሩ አላስቻለም። ከነዚህ ችግር በመነሳትና ባለሃብቶችም ጥርጣሬና ስጋት ያለባቸው በመሆኑ መንግሥት ዋስትና ሰጥቷቸው ያለቸውን ገንዘብ ኢንቨስት እንዲያድርጉ እገዛ ሊያደርግ ይገባል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሰኔ 14/2013