ወቅቱን ሳስበው የሰላም ዋጋ ስንት ነው ብዬ እንድጠይቅ ያደርገኛል። ምክንያቱም ሰላም በብር ሳይሆን በአስተሳሰብና በሥራ የሚገኝ ነው። ሰላም መልካም ነገሮችን ለሌላም ማድረግ ነው። ሰላም ለእኔ ብቻ ለሌላም ይትረፈው የሚባል አየር ነው። በእርግጥ አየርም ቢሆን በኮሮና ምክንያት በክፍያ የሆነባቸው አገራት አሉ። እኛ ጋ ብዙም ባይታይም። እናም ሰላም ከአየርም በላይ ነው። ስለዚህ ይህንን ተመን አውጥቶ መንቀሳቀስ ካልተቻለ በክፍያ እንኳን የማናገኝበት ብዙ ነገር ይፈጠራል። ታዲያ ምን ይሁን ካላችሁ መልሱ አንድና አንድ ነው በግለሰብ ደረጃ ተነስተን ማህበረሰብ ሆነን ለእርሱ ህልውና ዘብ መቆም ነው።
አገራት በተለይ ውጪዎች እኛን በብዙ ነገር ይፈልጉናል። አንድም ሀብታችንን ለመዝረፍ፣ አንድም ቂማቸውን ለመወጣት ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በእኛ ለመዳን የማይቆፍሩት ድንጋይ የለም። ለዚህ ደግሞ የእኛ የእርስ በእርስ መጣላት ጥቅሙ የትየለሌ ነው። እኛ ስንጣላ የፈለጉትን በዝብዘው ያወጣሉ። እኛ ስንጣላ ደካማ መንግስት እንድንመሰርት መስመራቸውን ይዘረጋሉ። እኛ ስንጣላ የወደፊት በእኛ ላይ ሆነው የሚያዙበትን መደላደል ይፈጥራሉ። እኛ ስንጣላ ከእኛው ሰው ገዝተው እኛኑ በእኛው ወደ ጥልቁ ጉድጓድ ይከቱናል። ስለዚህም ዛሬ ቆም ብሎ የማሰቢያችን ጊዜ እንደሆነ ማመን ይገባናል።
አሁን ጎረቤቶቻችንን የመደገፋቸው ምስጢር፣ ከእኛ የሚወጡ ሰዎችን በርቱ የማለቱ ነገር፣ በሰው ላይ ሰብዓዊ እረገጣ እያደረጋችሁ ነው ብሎ የመክሰሱ ጉዳይ ምንም የተለየ ምክንያት የለውም። አንድና አንድ እኛን አሸማቆ እንደፈለጋቸው የማድረጉ እርምጃ ነው። ይህ ደግሞ መቼም እንደማይሆን በመተባበር ክንድ ልናሳያቸው ያስፈልጋል። ይህ የሚሆነውም ሰላማዊ ነገሮችን በማድረግ ብቻ ነው። ከእነዚህ መካከል ደግሞ ዛሬ የምናከናውነው አገራዊ ምርጫ አንዱ ነው። ለዚህ ምርጫ ሰላማዊ ሆኖ መጠናቀቅ እያንዳንዱ ዜጋ ሀላፊነት አለበት። ምክንያቱም ምርጫውን ተገን አድርገው ሊወጉን ያሰፈሰፉ ብዙ ጠላቶች አሉብንና።
ብዙዎችን አሳስቦ ስጋት ውስጥ የከተተውም ይኸው ከምርጫው ባሻገር ያለው የሰላም ጉዳይ ይመስለኛል። ነገር ግን ከህዝብ የሚሸሸግ ምንም ነገር ስለማይኖር ለየት ያለ ነገር ከታየ በቅርብ ላሉ የጸጥታ አካላት ማሳወቅና ችግሩ ወዲያው እንዲፈታ ማድረግ የሁላችንንም ርብርብ ይጠይቃል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የሚናፈሱ በርካታ ወሬዎችን ወደጎን መተውም ተገቢ ነው። ለአብነት የዘንድሮ ምርጫ ረብሻ ሊኖርበት ይችላል የሚሉ ጉዳዮች ይነገራሉ። ግን ርባናቢስ ወሬዎች ናቸው። ይህ እንደሌሎቹ ምርጫዎች የጥቂት ፖለቲካ ፓርቲዎች ምርጫ አይደለም፤ህዝቡ የእኔ ነው ብሎ የተቀበለው እና ለምርጫውም ሰላማዊነት ዘብ የሚቆምለት ህዝባዊ ምርጫ ነው።ህዝብ እያለ ማን ሊረብሽ ይችላል? እናም የማይጠቅሙ ወሬዎችን ወደጎን በመተው የነገ ተስፋችንን ማለምለም ይገባል።
ይህ ምርጫ ከእስከዛሬው ብዙ የሚለዩት ነገሮች ያሉበትና የነገ እጣችንን የሚወስን እንደሆነ ማመን ይጠበቅብናል። ለዚህ ደግሞ ጠበቃውና የሰላም ዘቡ ራሱ ህዝቡ በመሆን ነገውን ማስተካከል አለበት። ማንም አጀንዳውን ከፍቶ የፈለገውን እንዲተነፍስበት መፍቀድ የለበትም። ስጋት ይሆናል የሚለውንም ማቅለልና ሰላምና አንድነትን ማጠንከር ከህዝቡ ይጠበቃል። ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ የራሱንም ሆነ የአገሩን የወደፊት እጣ ፋንታ እንዳያስቀምጥ የሚፈልጉ አካላት ከአገርም ውስጥ ከውጪ አካላት እንዳሉ እሙን ነው። ለዚህም በማሳያነት የምናነሳቸው እንደ አሸባሪው ህውሓት አይነት አጭበርባሪዎችን ነው።
በራሳቸው በአካሄዱት ምርጫ ህዝቡን መያዝ ስላልቻሉ ከአገር ጠል አገራት ጋር የማይወዳጁበት ምክንያት አለ ተብሎ መታሰብ የለበትም። ሰላማዊ ምርጫም እንዲከናወን ዝም ብለው ይፈቅዳሉ ብዬ አላምንም። በቻሉት ሁሉ ውስጥ ለውስጥ የሚሰሩት ሥራ ይኖራል። ለዚህ ደግሞ ምንም እንኳን ስልጣን የተሰጠው አካል በቂ ዝግጅት ያደረገ ቢሆንም ከህዝብ በላይ አይሆንምና ለምርጫው ሰላማዊነት ህዝቡ ራሱ ዋስ ጠበቃ መሆን ይኖርበታል። ከጸጥታ አካሉ በላይ ህዝቡ ችግሮች አይፈጠሩም ብሎ መንቀሳቀስ አለበትና ይህንን ሀላፊነቱን መወጣቱን ሊያተኩርበት ይገባል።
ህዝቡ ከሰላም ማስከበሩ በተጨማሪ የነገ ሰላሙን የሚያረጋግጥበትን ምርጫ በድምጹ ማድረግም አለበት። ማንም በእርሱ ጉዳይ እንዲወስን እድል ሊሰጥ አይገባም። ወሳኝነቱን በተግባር በወሰደው ካርድ ማረጋገጥ አለበት። በባህላችን እንደሚባለው ‹‹ ማን ይናገር የነበረ ማን ያርዳ የቀበረ›› ነውና አሁን አገራችንን ከአለችበት ችግር ሊያወጣ የሚችለውን ምርጫ ባለበትና በተረዳበት ልክ ይሆነኛል የሚለውን መርጦ ችግሮቹን መቅበር ይኖርበታል። ሁሉ
ነገር በጊዜው ነው መከናወን ያለበት። ጊዜው ካለፈ ድምጹም ሆነ ተስፋው ዋጋ ያጣል። ስለዚህም በስጋት ውስጥ ሆኖ ማሳለፍ በመተው ለድምጼ ዋጋ ሰጥቼ ችግሬን ልፍታ ማለት መጀመር አለበት። ለዚህ ደግሞ ዛሬ ወሳኝ ጊዜ ነው። እኛ ለእኛ የምንሰራባትና የአገራችንንም ሆነ የወደፊት ተስፋችንን የምናለመልምባት እንቁዋ ቀን ነች። ዛሬ የውጪ ሀይሉ አገራችን ላይ ጫና በፈጠረበት በዚህ ጊዜ ለእኛ እኛ ብቻነን መቆም ያለብን። እነርሱ ልማታችን እንዳይረጋገጥ፣ እድገታችን እንዳይቀጥል፣ ዘላለም ተቀላቢ ሆነን እንድንኖር ብዙ የሚሸርቡት ሴራ አላቸው። ለዚህ ደግሞ የመጀመሪያው ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዳይጠናቀቅ ማድረግ አንዱ ነው። ህዙቡ ድምጽ ለመስጠት እንዳይወጣ ማሸበርም ሌላው ጉዳይ ነው። ስለዚህም ይህንን አውቆ መንቀሳቀስ የዛሬ ሳይሆን የአሁን ሥራችን ይሁን።
ከጉንጭ አልፋ ንግግራችን ወጥተን እኛ የአባቶቻችን ልጆች ነን የምንልበት ጊዜ ላይ ነንና ይህንን በተግባር እናረጋግጥ። ምክንያቱም የአባቶች ልጅ መሆን በተግባር አይበገሬ መሆን ነው። የአባቶች ልጅ መሆን እራስን ሰላም አድርጎ ለሌሎች ሰላም ዘብ መቆም ነው፤ የአባቶቻችን ልጆች መሆን ሌሎችን ቀልበን ኖረን እንዴት እኛ ተቀላቢ እንሆናለን ብሎ በቁጭት መነሳት ነው። ለዚህ ደግሞ ብዙ ማሳያዎች አሉን የህዳሴ ግድቡ ብቻ ይህንን ወኔያችንን ያረጋግጥልናልና በምርጫውም እንድገመው ማለት እፈልጋለሁ።
ጠላቶቻችን እኛ ስንጠነክር፤ ስንለማና ራሳችንን ስንችል ያማቸዋል። ምክንያቱም በምንም መጥተው ሊገዙን አይችሉም። አንድነታችንንም መናድ ይሳናቸዋል። ዛሬ በየአቅጣጫው የሚሮጡትም በዚህ ምክንያት ነው። አንዳንድ ግጭቶች በውስጣችን ቢኖሩም በአገር ጉዳይ ላይ አንድ ሆነን ለልማት መነሳታችን ከምንም በላይ አበሳጭቷቸዋል። እነርሱ ማናቸው እያሉ መጠየቁንም ተያይዘውታል። ስለዚህም ከምርጫው ባሻገርም የሀገራችንን ሰላምና ድህንነት በማስጠበቅ በኩል ዜግነት ግዴታችንን ልንወጣ ይገባል።
ገንዘብ ካለ በሰማይ መንገድ አለ እንደሚባለው ሀያል ስንሆን ከእኛ ጋር ለመስራት የማይቋምጥ አይኖርም። ለዚህ ደግሞ ጊዜው ሩቅ አይሆንም። ከእኛ የሚጠበቀው ህብረት ሀይል መሆኑን ማመንና በሥራ ማሳየት እንዲሁም እንደአባቶቻችን አንድነት ሀይልም ሀያልም እንድንሆን ሰርተን ማሳየት ብቻ ነው። ሰላም!!!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሰኔ 14/2013