ግብፅ ለዘመናት ያለተቀናቃኝ ተቆጣጥራው የኖረችው ቀጣናዊ ስትራቴጂካዊና ጂኦፖለቲካዊ ሚና ከእጇ ሊወጣ አንድ ሀሙስ ነው የቀረው ። ይሄ ሟርት አይደለም። እየሆነ ያለ ተጨባጭ ሀቅ እንጂ። ይሄን ልቧ ስለሚያውቅ ነው በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጥርሷን የምታፋጨው ጸጉሯን የምትነጨው። ፊቷን የምትፈጀው። እስራኤል እንደ ሀገር ከቆመችበት እኤአ ከ1948 ዓም ጀምሮ ግብጽ መጀመሪያ በጠላትነት ኋላ ላይ በአጋርነት የምዕራባውያንንና የእስራኤልን ደህንነትና ጥቅም እያስከበረች አለች። ምንም እንኳ ፍልስጤሞችና አረቦች እንደ ክህደት ቢቆጥሩትም።
ግብጽ ከአንዴም ሁለቴ ከቀጣናው ሀገራት ጋር አብራ እስራኤል ላይ ጦርነት ከፍታ አሳፋሪ ሽንፈት ተከናንባ ተዋርዳለች። ይህ ሽንፈት ዛሬ ድረስ የዜጋዋን ቅስም እንደሰበረ ፤ የአረብ ብሔርተኝነት አቀንቃኝነቷ ላይ ጥላ እንዳጠላ አለ። ከዚህ ንብርብር ብሔራዊ ውርደት በኋላ ግብጽ ሳትወድ ተገዳ ከእስራኤል ጋር የሰላም ስምምነት ተፈራረመች። በተለይ ካለፉት 50 ዓመታት ወዲህ ግብጽ ከጠላትነት ወደ እስራኤልና ምዕራባውያን ስትራቴጂካዊ አጋርነት ተሸጋግራለች። ለዚህ ውለታዋ በየዓመቱ ከአሜሪካ ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ እርዳታ ይጎርፍላታል ። አሁን ላይ በየዓመቱ እስከ አራት ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ድጋፍ ይደረግላታል ። በአሜሪካ ፊትአውራሪነት በዓለማቀፍ ደረጃ ዲፕሎማሲያዊና ፓለቲካዊ እገዛ ታገኛለች ። አሜሪካ እንዳሻት ቁጭ ብድግ ከምታደርጋቸው የገንዘብ ተቋማት በእሷ”ዋስትና” ከዓለማቀፉ የገንዘብ ተቋም/IMF/ና የዓለም ባንክ በአነስተኛ ወለድ ብድርና እርዳታ ትቀላውጣለች። በዚህ ልዋጭ አፏ ተይዟል ። እስራኤል ሰፈራውን ብታስፋፋ፤ እንዳዚያ ሰሞኑ የተከታታይ 11 ቀናት እንዳሻት ቦንብ ብታዘንብ ፤ ከተሞችን ወደፍርስራሽነት ብትቀይር “አንተም ተው፣ አንቺም ተይ፤” ከማለት ያለፈ እንደ ስድስት ቀኑም ሆነ ከዚያ በፊት እንዳደረገችው ጦር አታዘምትም። አሸማጋይ ሆናለች።
ይሁንና አሜሪካ ስለ እስራኤል ሀሳቧን ግብጽ ላይ ጥላ እጇን አጣጥፋ አልተቀመጠችም። በምታደርግላት ኢኮኖሚያዊ ድጋፍ እስራኤል ከበለጸጉ ሀገራት ተርታ እየተሰለፈች ነው ። የመካከለኛው ምስራቅ ልዕለ ኃያል ሆናለች ። የባር ላን ዩኒቨርሲቲ ስትራቴጂካዊ ጥናት ይፋ እንዳደረገው ሰሞነኛ መረጃ ፤ የእስራኤል የሀገር ውስጥ ጥቅል ምርት/GDP/ ግብጽን በ14 ፣ ኢራንን በስምንት ፣ ሊባኖስን በስድስት ፣ ሳውዲ አረብያን በሁለት እጥፍ ይከነዳቸዋል። በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፣ በሰው ሰራሽ ክህሎት/AI/በአቪየሽንና ባዮቴክኖሎጂ የደረሰችበት ደረጃ ቢጠሯት አትሰማም። ለጥናትና ለምርምር የጅዲፒዋን አምስት በመቶ መመደቧ መዳረሻዋን አበክሮ ያመላክተናል ። የውጭ ምንዛሬ መጠባበቂያዋ እንግሊዝን በልጦ ከዓለም 13ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። ዘጠኝ ሚሊዮን ብቻ ሕዝብ ላላት ሀገር ይህ አስገራሚ ስኬት ነው ይላል የባር ላን ዩኒቨርሲቲ ጥናት።
እስራኤል ከጎረቤት አረብ ሀገራት ጋር በወታደራዊ አቋሟ እናነጻጽር ብንል የሰማይና የምድር ያህል ሆኖ እናገኘዋለን ። እኤአ በ1967 ዓም እስራኤል የአረብ ሀገራትን ወረራ በስድስት ቀን ድል አድርጋለች። ዛሬ ላይ ይሄን መሠል ጦርነት በሰዓታት ማጠናቀቅ ትችላለች ይላል ከፍ ብሎ የተጠቀሰው ዩኒቨርሲቲ ጥናት። ዓመታዊ ወታደራዊ በጀቷ አስር እጥፍ የሕዝብ ብዛት ካላት ኢራን በላይ ሲሆን በጦር መሳሪያ በብዛትም ሆነ በጥራት እንዲሁ ብልጫ አላት ። በተለይ አየር ኃይሏ ተወዳዳሪ የለውም ። በቀጣናው የኒውክሌር የጦር መሳሪያ የታጠቀች ብቸኛ ሀገርም ናት። 100 የኒውክሌር ተተኳሽ/warheads/ እንዳላት ይነገራል። ይህ ከኒውክሌር አንጻር እጅግ ግዙፍ ትጥቅ እንደሆነ ልብ ይሏል። ሀገር አልባ ከሆነችው ፤ ከአምስት ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ካላት ፍልስጤም ጋር ስትነጻጸር ደግሞ ልዩነቱ የትየለሌ ነው። ኢኮኖሚያዊ ልዩነቱ እንዳለ ሆኖ ወታደራዊ ቁመናዋ ግን ለአቅመ ንጽጽር አይበቃም ። ሰሞነኛውን ለ11 ቀናት የዘለቀውን የእስራኤል ጥቃት በአብነት ብንወሰድ አንድ እስራኤላዊ በሞተ ቁጥር ከ20 እስከ 30 የሚደርሱ ፍልስጤማውያን ይገደላሉ። ከተመሰረተች ገና የ73 ዓመት አረጋዊ የሆነችው እስራኤል በዚህ ደረጃ ኢኮኖሚዋ መበልጸጉና ወታደራዊ አቅሟ መፈርጠሙ ከፍልስጤም ጋር ለመደራደርና ሰጥቶ ለመቀበል የሚያስገድዳት ነገር እንደሌለ ያመለክታል ይላል የCNN ተወዳጅ ሳምንታዊ ፕሮግራም የGPS አዘጋጅና የWashington Post አምደኛ ፋሪድ ዘካሪያ፤ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ በፍልስጤማውያን ግፍ ስትነግድ ለኖረችው ግብፅ ይህ የእስራኤል “ስኬት” ረፍት ይነሳታል።
አዎ ! እስራኤል ከፍልስጤማውያን ጋርም ሆነ ከጎረቤት አረብ ሀገራት ጋር እንድትደራደር የሚያስገድዳት ነገር። ምን አልባት ሊያስገድዳት የሚችለው ነገር የሞራል ልዕልና ብቻ ነው። ለዚህ ደግሞ ግብፅ ያን ያህል አታስፈልጋትም። እስራኤል በአሜሪካና በምዕራባውያን አግባቢነትና የእጅ አዙር ጫና ከሱዳን፣ ሳውዲ፣ ከዩናይትድ አረብ ኤሚሬትስ፣ ከባህሬን፣ ከኩየት፣ ከኳታር ፣ ወዘተረፈ ሀገራት ጋር አብሮ ለመስራትና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለመጀመር በመስማማት ላይ መሆኗ የግብጽን ጅኦፖለቲካዊ ማዕከልነት ክፉኛ ይሸረሽረዋል። ይህ ደግሞ ከአሜሪካ ጋር ያላትን ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ወደ ታክቲካዊ አጋርነት ደረጃ ዝቅ ያደርገዋል። አሜሪካ ለግብፅ የምታደርገው ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ እርዳታ ከእስራኤል ጥቅም፣ ህልውናና ደህንነት አንጻር ስለሆነ በሒደት እየቀነሰ ይሔዳል።
እስራኤል በይፋ እንደ ሀገር ከተመሰረተች እ ኤ አ ከ1948 አንስቶ በመቶዎች የሚቆጠር ግን የከሸፉ የሰላም፣ የእርቅ ወይይቶችና ድርድሮች በአሜሪካ፣ በፈረንሳይ፣ በእንግሊዝ፣ በተባበሩት መንግስታት ፣ በአረብ ሊግ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በአውሮፓ ሕብረት አነሳሽነትና ሸምጋይነት ተከናውነዋል። ሁለት ክፍለ ዘመኖችን ማለትም 20ኛውን ተሻግሮ 21ኛውን የተያያዘ የጅኦ ፓለቲካ ጨዋታ እያሉ ይሳለቁበታል። ጠብ የሚል ነገር ያጡበት ልሒቃን። የጨዋታውን ሕግ የሚያውቁት አሜሪካ እና እስራኤል ብቻ ናቸው። ተጫዋችም ዳኛም እነሱ ናቸው። ከ1970ው (እ አ አ) የሮጀርስ የሰላም እቅድ አንስቶ በዚያ የትራምፕ ዘመን ዶናልድ ትራምፕ አምቹ ጃሪድ ኩሽነር አጋፋሪት የተዘጋጀውና ትራምፕ የ” ክፍለ ዘመኑ የሰላም እቅድ“ ሲል ያሞካሸው ይጠቀሳል።
ይህ የሰላም እቅድ ከጅምሩ ባለድርሻ አካላትን በተለይ ፍልስጤማውያንን፣ የአውሮፓ ሕብረትን ፣ የአረብ ሊግን ያላሳተፈ ስለነበር ገና የህትመት ቀለሙ ሳይደርቅ ፣ ከዋይታሀወስ እግሩን ሳያነሳ የፍልስጤም ነፃ አውጭ ድርጅት/ፒ ኤል ኦ/ ሊቀ መንበር ሞሀመድ አባዝና በዚህ ዓመት በሞት የተለዩት ዋና ተደራዳሪው ሳይብ ኤራካት እሳት ለብሰው እሳት ጎርሰው አውግዘውታል።
አንዳንዶችም የሰላም እቅዱን ከአፓርታይድ የባንቱስታን አገዛዝ ጋር አመሳስለውታል። ይሁንና የአረቡ ዓለም እንደ ትላንቱ ዛሬም በአንድነት መቆም ባለመቻሉ፣ እነ ሳውዲ አረቢያም ከኢራን ጥቃት የምትጠብቃቸውን አሜሪካንን ላለማስከፋት፣ ግብፅም በየዓመቱ ከአሜሪካ የምታገኘው በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ እርጥባን እንዳታጣ ከሁሉም በላይ የታላቁን የሕዳሴ ግድብ ሦስትዮሽ ድርድር ላይ ጫና በማድረግ እንድታግዛት የፍልስጤማውያንን ህልውና አደጋ ላይ እንደጣለ ስለሚነገርለት የትራምፕ የመካከለኛው ምስራቅ ኢፍትሐዊ የሰላም እቅድ ትንፍ አላለችም። ለተከታታይ 11 ቀናት ፍልስጤማውያን ቦንብ ሲዘንብባቸው የአረቦች ቃፊር ነኝ የምትለው ግብጽ እምጥ ትግባ ስምጥ ያየ የለም። እስራኤል ሲበቃት ግን አይኗን በጥሬ ጨው ታጥባ በአሸማጋይነት ብቅ ብላለች።
በአሜሪካ ሪፐብሊካንም ሆኑ ዴሞክራቶች ወደ ስልጣን ይምጡ የእስራኤል ነገር የውጭ ጉዳይ፣ የደህንነትና የኢኮኖሚ ፓሊሲያቸው ማጠንጠኛ ነው። እድሜ የአይሁድ ደም ላለባቸው ትሪሊየነሮች፣ ቢሊየነሮች፣ ሚሊየነሮች፣ ሳይንቲስቶች፣ አርቲስቶች፣ ተዋንያኖች፣ ጋዜጠኞች፣ ቀኝ ዘመም ክርስቲያኖች፣ ጠንካራና ተፅዕኖ ፈጣሪ የአይሁድ ማህበረሰብ ማህበራት፣ ወዘተረፈ አሜሪካ፣ ምዕራባውያንና ተቋሞቻቸው የእስራኤልን ጥቅም ለማስከበር አያንቀላፉም። እስራኤል እንደ ሀገር ከቆመችበት ዘመን አንስቶ በተለይ አሜሪካ የምታደርገው ወታደራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፓለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ በቀጣናው ጠንካራ ወሳኝ ኃይል ሆና እንድትወጣ አስችሏል። በተቀራኒው የአረቡ አለምም ሆነ ፍልስጤማውያን አንድ እንዳይሆኑ በፊት ለፊትም ሆነ በጀርባ ሌት ተቀን ትሰራለች።
ጋዛ በሀማስ የተቀረው ፍልስጤም በፒኤለኦ ይተዳደራል። እነዚህ የፍልስጤም ድርጅቶች ለአንድ አላማ የቆሙ እስከማይመስል ድረስ አይን ለአይን አይተያዩም። አልፎ አልፎም በጦር መሳሪያ የታገዘ ግጭት ውስጥ እስከመግባት ደርሰዋል። ከፍልስጤም ጎን የቆሙ አረብ ሀገራትም በአንድነት መቆም ባለመቻላቸው የፍልስጤማውያን ጉዳይ ከድጡ ወደ ማጡ ሆኗል። እስራኤል ከዓመት ዓመት በፍልስጥኤማውያን መሬት ሰፈራን እያስፋፋች፤ የ5ሚሊዮን ፍልስጤማውያን ፍዳ እየበዛ ከመሄዱ ባሻገር ራሱን የቻለ ሀገርና መንግሥት የመሆን ህልማቸውም እየመከነ ይገኛል። ዛሬ ዛሬ የፍልስጤም ጉዳይ ከዓለማቀፍ ፓለቲካዊ ርዕሰ ጉዳይነት ወደ እስራኤል የውስጥ ጉዳይነት እየኮሰመነ ነው። በእስራኤል ፍልስጤም ጉዳይ የግብጽ ሚና እየተዳከመ የመጣው በዚህ ምክንያት ነው። የግብጽ ጀምበር እያዘቀዘቀች ያለችው ለዚህ ነው።
ግብጽ እስከ ቅርብ ዓመታት ድረስ የእስልምና ስልጣኔ፣ ትምህርትና የእስላማዊ ፓለቲካ ማዕከል ነበረች። እስላማዊ ዩኒቨርስቲዎቿ ብቸኞች ነበሩ። ሙስሊም ብራዘርሁድን አይነት በአረቡ ዓለም ተፅዕኖ እስከመፍጠር የደረሰ የግብረ ሰናይና የእስላማዊ ፓለቲካ አደረጃጀት ጠንሳሽ ነበረች ። በአረብ ሊግ ምስረታም ሆነ በአመራርነት ከፍ ያለ ድርሻ እንዲኖራት ያደረገውም ይህ የከረመ ስንቅ ነው። ምንም እንኳ ሊጉ በእርስ በርስ ክፍፍልና በልዩነት ቢታወቅም ግብጽ እንዳሻት የምትዘውረውና የምትጠቀምበት የትሮይ ፈረሷ ነው። ሰሞኑን በኳታር ዶሀ የ22 አባል ሀገራቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ተሰብስበው የመንግሥታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ጣልቃ እንዲገባ ጥሪ ማድረጉ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው። ሆኖም የእነ ቱርክ ፣ ማሌዥያ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ኤምሬትስ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት የግብጽን ፓለቲካዊና ማህበራዊ ሚና እያደበዘዘው ይገኛል።
እንደ መውጫ
ግብፅ የሕዳሴውን ግድብ ጉዳይ በድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አጠቃቀም ታሪክ ታይቶም ተሰምቶም በማያውቅ ሁኔታ አንድ ጊዜ ወደ ነጩ ቤተ መንግሥት፤ ሲያሻት ወደ መንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት፤ ሰሞኑን ደግሞ ወደ አረብ ሊግ በማንሸራሸር ከአፍሪካ መዳፍ ፈልቅቃ በማውጣት አለማቀፋዊና የአረብ ሀገራት ጉዳይ ለማድረግ እየማሰነች ያለችው ከፍ ብሎ ለመጥቀስ እንደተሞከረው ከእስራኤልና ከአረቡ ዓለም አንጻር ያላትን ጅኦፓለቲካዊ ስፍራ በመጠቀም ነው። ይህን ስፍራዋን በቀጣይ ጥቂት ዓመታት ከማጣቷ ባሻገር ለናይል ወንዝ 86 በመቶውን ውሃ የምታበረክተው ኢትዮጵያ ምክንያታዊና ፍትሐዊ ተጠቃሚ የሚያደርጋትን የሕዳሴ ግድብ በማጠናቀቅ ላይ መሆኗ በሰሜንና ምስራቅ አፍሪካ ጅኦፓለቲካዊ አሰላለፍ ላይ ነጮች እንደሚሉት መሬት አርዳዊ /seismic/ለውጥ ያመጣል። የኢትዮጵያን ስትራቴጂካዊና ጅኦፓለቲካዊ ስፍራም በእጅጉ ከፍ ያደርገዋል። ግብጽ ለዘመናት ኢትዮጵያ ገና ተረጋግታና በልጽጋ አባይንና ገባሮቹን ትጠቀማለች በሚል ጠንካራ ሀገረ መንግሥት እንዳይኖራት፣ ከድህነት አረንቋ እንዳትወጣና ሰላሟ ታውኮ እንዳትረጋጋ ሌት ተቀን ስታሴር ኖራለች ። በተወሰነ ደረጃም ተሳክቶለታል። ይሁንና የሕዳሴው ግድብ ሁለተኛ የውሃ ሙሊት ሲጠናቀቅ የግብጽ ኢትዮጵያን የማተራመስ አጀንዳ አብሮ ይከተታል። ይቋጫል። የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ልማት ብቻ ሳይሆን በቀጣይ የሰላም ዋስትና ጭምር የሚሆነው ለዚህ ነው። እንደ ዜጋ ሀገራችን እንዲህ ባለ የሞት ሽረት ትንቅንቅ መሆኗን ተገንዝበን በአንድነት ከሀገራችንና ከሕዝባችን ጎን ልንቆም ይገባል። ግድቡ የኔ ነው!
እንደጀመርን እንጨርሰዋለን! ኢትዮጵያ ትቅደም!
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ሰኔ 13/2013