ሀገራችን ባለፉት ዓመታት በተለይ አዲስ አበባ ግንባታ በከፍተኛ ሁኔታ እንደ አሸን እየፈላበት በሚል ስትጠራ ቆይታለች። በእርግጥም በርካታ የመንግሥትና የግል የግንባታ ፕሮጀክቶች በስፋት መካሄዳቸው ሲታሰብ ይህ ትክክለኛ ምልከታ ነው። መንግሥት ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ጨምሮ በርካታ የመሰረተ ልማትና የመሳሰሉት የግንባታ ፕሮጀክቶችን፣ የግሉም ዘርፍ እንዲሁ የተፈጠረለትን ምቹ ሁኔታ ተከትሎ በሆቴል ፣በኢንዱስትሪ በሪልስቴትና በመሳሰሉት የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች በስፋት ገንብቷል።
ግንባታዎቹ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይም ትርጉም ያለው ለውጥ አምጥተዋል። ይህም ለውጥ የኮንስትራክሽን ዘርፉ በአጠቃላይ ሀገር ውስጥ ምርት ውስጥ ባሳየው ለውጥ እንዲሁም የሥራ ዕድል በመፍጠር በኩል ባበረከተው አስተዋጽኦም ይገለጻል።
በአንጻሩ ሀገሪቱ የግንባታ ፕሮጀክት በከፍተኛ ሁኔታ የሚጓተትባት ሆናም ነው የቆየችው። ህዝብና ሀገር እንደ ዓይናቸው ብሌን የሚጠብቁት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ሳይቀር በፕሮጀክት ቀበኞች ተፈትኖ ለመጓተት ተዳርጓል። ኑሯቸው ከእጅ ወደ አፍ የሆነው ዜጎች ከአፋቸው እየከፈሉ በማዋጣት ግንባታውን እያካሄዱ የሚገኙትን ይህን ግድብ ጨምሮ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ለውጥ ያመጣሉ ተብለው የሚታሰቡ በርካታ ፕሮጀክቶች በዚህ የፕሮጀክት መጓተት ተፈትነዋል።
በ2010 ወደ ስልጣን የመጣው መንግሥት የለውጥ አመራር ባይደርስላቸው ኖሮ እንደ ማዳበሪያ ፕሮጀክቱ እነዚህም ፕሮጀክቶች ውሃ ብልቷቸው አጨብጭበን በቀረንም ነበር። የለውጥ አመራሩ ቅድሚያ ትኩረት ከሆኑት መካከል እነዚህን የተጓተቱ ፕሮጀክቶችን መታደግ ነበር። መንግሥት እነዚህን ፕሮጀክቶች ለመታደግ ሲል አዳዲስ ፕሮጀክቶችን አልጀምርም ብሎ ጭምር ነበር ለፕሮጀክቶቹ ትኩረት ሰጥቶ ወደ ሥራ የገባው። ፕሮጀክቶቹ የተመደበላቸው በጀት በቀበኞች ክፉኛ የተሟጠጠባቸው፣ ግንባታቸው እልፍም ያላለላቸው፣ በፕሮጀክት ስም ዘረፋ ሲፈጸምባቸው የነበሩ ናቸው።
የለውጡ አመራር በቅድሚያ የሠራው የእነዚህን የፕሮጀክቶች ችግር መለየት ላይ ነበር። ከዚያም ተቋራጮችን ጭምር በመቀየር፣ ከፍተኛ በጀት በመመደብ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቁ ለማደረግ ችሏል። የቅርብ ክትትልና ቁጥጥር ተደርጎባቸዋል።
ይህን ተከትሎም ፕሮጀክቶቹ ላይ ለውጥ ማምጣት ተችሏል። ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ ከአስሩ የስኳር ፕሮጀክቶች በደቡብ ኦሞ የሚገኝ አንድ የስኳር ፋብሪካ ወደ ሥራ ከገባ ቆይቷል፤ የጣና በለስ ቁጥር አንዱ ደግሞ በቅርቡ ወደ ሥራ ገብቷል።
በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ ከፍተኛ ለውጥ እየታየ ነው። ግንባታው ከ80 በመቶ በላይ የደረሰ ሲሆን፣ በዚህ የክረምት ወቅት በሁለት ዩኒቶቹ ኃይል ማመንጨት በመጀመር ብርሃን ይፈነጥቃል፤ ሁለተኛው የውሃ ሙሌትም በዚሁ ክረምት ይፈጸማል። ፕሮጀክቱን እዚህ ደረጃ ማድረስ የተቻለው ከቀማኞች መዳፍ በማውጣትና እነሱ ያስከተሉትን ኪሳራ ቆጥሮ በመክፈል ነው። እነዚህ ከተጓተቱና ለውጥ እንዲመጣባቸው ከተደረጉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ጥቂቶቹ ናቸው።
ሌሎች መስመር ውስጥ የነበሩ የኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች ፣ የመንገድና ሌሎች መሰረተ ልማት ግንባታዎች ከለውጡ ወዲህ ባሉት ዓመታት እየተጠናቀቁ ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል።
የለውጡ መንግሥት የተጓተቱ ፕሮጀክቶችን እና ሌሎች የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በማስጨረስ ላይ ብቻ አልነበረም ሲሠራ የቆየው። ሌሎች በርካታ ግዙፍ ፕሮጀክቶችንም አቅዶ አስገንብቶ አስመርቋል፤ በግንባታ ላይ የሚገኙ ግዙፍ ፕሮጀክቶችም አሉ፤ ግንባታቸው ተጠናቆ ምረቃ የሚጠብቁም እንዳሉ ይታወቃል ።
ለዚህም የሀገሪቱን ዋና ከተማ ፣ የአፍሪካ ህብረትና የዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ የሆነችውን አዲስ አበባን እንደ ስሟ አዲስ አበባ ሊያደርጓት የሚችሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች በአብነት ይጠቀሳሉ። አንድነት ፓርክ ፣ የወዳጅነት ፓርክ፣ የእንጦጦ ፓርክ የለውጡ መንግስት ጀምሮ ያስጨረሳቸው አዳዲስ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ናቸው። ሰሞኑን የተመረቀው የመስቀል አደባባይ ፕሮጀክትም ሌላው ሊጠቀስ የሚገባው ነው። እነዚህ ፕሮጀክቶች የከተማዋንም የሀገሪቱንም ገጽታ በወሳኝ መልኩ የሚቀይሩ፣የቱሪስቶችን ቆይታ የሚያራዝሙ ፣የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን በወሳኝ መልኩ የሚቀይሩ ሥራዎች ናቸው።
መንግሥት በገበታ ለሸገር ተሞክሮው ላይ በመመስረት ባለሀብቶች መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን በማስተባበር የጀመራቸው የጎርጎራ፣ የወንጪና ኮይሻ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች፣በእነዚህ ሦስት ዓመታት ተመርቀው ወደ ሥራ የገቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮችና የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ በሀገሪቱ የተያዙ እቅዶችን ለማሳካት የሚያስችሉት በግሉ ዘርፍ እዚህም እዚያም በምግብ ዘይት ኢንዱስትሪዎች እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያስመረቃቸውን ጨምሮ ግንባታቸው የተጠናቀቀና እየተፋጠኑ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች፣ በየክልሉ እየተመረቁ ያሉ የመሰረተ ልማት፣ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ገና እጅ ውስጥ ይገኛሉ።
በሀገሪቱ ፕሮጀክቶች የሚታዩና የሚዳሰሱ እንዲሆኑ ተደርገዋል። በሪፖርት ብቻ እዚህ መቶኛ ላይ ደርሰዋል በሚል የሚገለጹ አይደሉም። ለይስሙላ ተመርቀው የተዘጋባቸው ፕሮጀክቶችም አይደሉም፤ ተጠናቀው አገልግሎት የጀመሩ እንጂ።
አንድነት ፣የወዳጅነት እና እንጦጦ ፓርኮች እየተጎበኙ ሀብትም እያመነጩ ናቸው። እኛ የለመድነው የፕሮጀክቶች አፈጻጸም በመቶኛ እየተገለጸ የተስፋ እንጀራ መብላትን ነበር፤ መሬት ላይ የሌለ አፈጻጸም፤ መንግሥት አሁን ከዚያ ዓይነቱ አሠራር ሀገሪቱን አውጥቷል።
ሁሉም በእነዚህ የለውጡ መንግሥት አጭር የሦስት ዓመት ዕድሜ ነው የተሠሩት። የመጀመሪያውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ እናውቃለን፤ ሁለተኛውንም እንዲሁ። በመጀመሪያ ተመዘገበ የሚባል ውጤት ብዙም አልታየም፤ ኢኮኖሚውን ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር የታቀደው የውሃ ሽታ ሆኖ ቀርቷል፤ ከሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ከሁለት ዓመት በላይ ሥራ ላይ ዋለ በተባለለት ጊዜም የታዩ ለውጦች አሉ ብሎ መናገር ያስቸግራል። ከእነዚህ ዓመታት አኳያ እንዲሁም ካለፉት ሦስት ዓመታት አኳያ ሲታይ ያለፉት ሦስት ዓመታት አፈጻጸም ዕድሜው አይገልጻቸውም። የለውጡ መንግሥት ከኖረው ዕድሜ በላይ ሥራዎች ተሠርተዋል።
ፕሮጀክቶቹ የተፈጸሙት ደግሞ አስቻይ ሁኔታዎች ብዙም በሌሉበት ሁኔታ ውስጥ ነው። ሆን ተብሎ ፕሮጀክቶችን ለማስተጓጎል ዘመቻ እየተደረገ ባለበት ሁኔታ ውስጥ ነው። ሰላምና መረጋጋት ቢኖር ምን ያህል ውጤታማ ሥራ መሥራት እንደሚቻል ያመላከተ ሥራም ነው የተሠራው።
ዋናው ነገር ከልብ ካለቀሱ ዕንባ አይገድም ነው ነገሩ። ምንም ያህል ያደሩ ብዙ ችግሮች ያሉባቸው ግዙፍና ሌሎች ፕሮጀክቶች ቢኖሩም፣ ሌሎች በርካታ የህዝብ ጥያቄዎችን መመለስ የግድ ቢሆንም፣ በመንግሥት በኩል ቁርጠኝነቱ ካለ ህዝብና መንግሥት የሰጠን አደራ መፈጸም ላይ ከተሠራ ፕሮጀክቶችን በአጭር ጊዜ መፈጸም እንደሚቻል በተጨባጭ ማሳየት ተችሏል።
በሀገራችን የሰዎችን ብርታትና ጥንካሬ ለመግለጽ ግምት ይሰጣል። አንድ ሰው በብዙ ሰዎች ሲገመት ይስተዋላል። አንዳንድ ሰዎችም እከሌ ተብለው ሲጠሩ የሃምሳ ሰው ግምት ፣የአስር ሰው ግምት ወዘተ ብለው ራሳቸውን ሲገልጹ ይሰማል። ህብረተሰቡም ጠንካራ ሰው ሲመለከት አሁን እሱ/ እሷ እንደ አንድ ሰው ይቆጠራሉ ብለው ራሳቸውን በመጠየቅ ጠንካራ ሰዎችን በብዙ ሰዎች የሚመነዝሩም ይስተዋላሉ። ለእዚህ ምስክርነት የሚሰጡም አሉ። እኔ በእነዚህ ሦስት ዓመታት በመንግሥት የተከናወኑ ተግባሮችን በዚሁ መንገድ እመለከታቸለሁ። የሦስት ዓመት ሥራዎች ብቻ ብዬ አልገልጻቸውም። የአምስት ዓመትና ከዚያም በላይ ዓመታት ሥራዎች ግምት ነው የምሰጣቸው።
ዘካርያስ ዶቢ
አዲስ ዘመን ሰኔ 13 ቀን 2012 ዓ.ም