በጅማ ከተማ የሚገኘው የአዌቱ ፓርክ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ያስቆጠረ ፣ በከተማዋ የሚገኝ ብቸኛው እድሜ ጠገብ ፓርክ ነው። ፓርኩ ለበርካታ ዓመታት ለአካባቢው ህዝብ እና ለጎብኚዎች የተለያዩ አገልግሎቶችን በመስጠት ይታወቃል። ካለፉት 15 ዓመታት ወዲህ ግን ተመልካችና አስታዋሽ አጥቶ የእድሳት እና ጥገና ስራ ባለመሰራቱ ከአገልግሎት ውጭ ሆኖ ቆይቷል። የመንግስት ለውጥ ከመጣ ወዲህ ግን ፓርኩ እድሳት ተደርጎለት ወደ ስራ እንዲገባ ከውሳኔ ላይ ተደርሶ የእድሳት ስራው ተጀምሯል ።
ቀደም ባሉት ጊዜያት ፓርኩ በመንግስት ይተዳደር የነበረ ቢሆንም መንግስት ፓርኩን ማደስ እና ለነዋሪዎች አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ ባለመቻሉ፤ የግል ባለሃብቶች ፓርኩን በኪራይ በመያዝ እንዲያድሱ እና አገልግሎት እንዲሰጡበት የከተማ አስተዳደሩና ባለሃብቶቹ ለአምስት ዓመት ውል ተፈራርመው ነው ወደ ስራ የተገባው። በዚሁ መሰረት የግል ባለሃብቶች ፓርኩን ከማደስ ጎን ለጎን አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ። የፓርኩን ስም ወደ ኦኤሲስ አዌቱ የጅማ መዝናኛ በሚል ተቀይሯል።
ፓርኩን በኪራይ በመያዝ በማደስ ላይ ከሚገኙ ባለሃብቶች መካከል አቶ መሃመድ አህመድ አንዱ ናቸው። አቶ መሃመድ እንደሚሉት ፓርኩ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ዕድሜ ያለው እጅግ ታሪካዊ ነው። ብዙ የሰርግ ስነ-ስርዓት ፣ ስብሰባዎች ፣ ታዋቂ አርቲስቶች የሙዚቃ ኮንሰርቶችን አስተናግዷል። እንዲሁም ሌሎች ብዙ ነገሮች ፓርኩ ውስጥ ለረጅም ጊዜ ተካሂደዋል። ከምንም በላይ በከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ጠንካራ ማህበራዊ ውህደት እንዲፈጠር ያደረገ ነው ። በቀን እስከ አስር የሰርግ ሰነ ስርዓቶች የተካሄዱበት ጊዜም ነበር ሲሉ የፓርኩን ባለውለተኛነት ይናገራሉ። ይሁን እንጂ በወቅቱ በነበረው የመንግስት አካል sትኩረት በማጣቱና በመዘንጋቱ ለህዝቡ የሚሰጠው አገልግሎት ተsርጧል። በዚህም የነዋሪው ልብ ተሰብሮ ቆይቷል።
‹‹ለፓርኩ ጥገና እና እድሳት ባለመካሄዱ እና በሌሎች ውስብስብ ችግሮች ምክንያት ተዘግቶ በቆየባቸው ዓመታት በፓርኩ ውስጥ ይካሄዱ የነበሩ የአርት ስራዎችም ተቋርጠዋል። አሁን ግን እድሳቱ በመደረጉ ምክንያት ተቋርጠው የነበሩ የጥበብ እና ሌሎች ስራዎችም ወደነበሩበት እንዲመለሱ ዕድል ይሰጣል›› ብለዋል።
አሁን ፓርኩ እየተጠናቀቀ በመሆኑ ዳግም የከተማዋ ወጣቶች እና ነዋሪዎች መገናኛ ቦታቸው እያደረጉ ነው።
የፓርኩን እድሳት 10 ሚሊየን ብር ገደማ በጀት የተያዘለት ሲሆን በአንድ ዓመት ውስጥ ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዞ የነበረ ሲሆን፤ በአራት ወር የእድሳቱ አብዛኛው ስራ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል። ፓርኩ ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ ሲገባ ከ100 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ይፈጥራል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ከ42 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የስራ እድል መፍጠሩን ተናግረዋል።
ፓርኩ ሙሉ ለሙሉ አገልግሎት ለመስጠት በዝግጅት ላይ ሲሆን በአሁኑ ወቅት የቀረው የህጻናት መጫወቻ ቁሳቁሶችን ማሟላት ነው። ይህንንም ከውጭ ሀገራት የማስመጣት ሂደት ላይ መሆኑን የተናገሩት አቶ መሃመድ በቀጣይ ጥቂት ወራት ውስጥ የህጻናት መጫወቻዎችን የመግጠም ስራ እንደሚሰራ ነው የተናገሩት።
ለፓርኩ እድሳት ባለማድረጉ ለህዝብ አገልግሎት ሳይሰጥ ለረጅም ጊዜ መቆየቱ ተገቢ አለመሆኑ ስለታመነበት እድሳት እና ጥገና እንዲደረግ ከስምምነት ላይ መደረሱን የተናገሩት የጅማ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ካሳሁን ዶብር ናቸው። በ2012 በጀት ዓመት የከተማ አስተዳደሩ የተወሰኑ የእድሳት ስራዎችን ሰርቷል። ቀሪው የእድሳት እና የጥገና ስራዎች ባለሃብቶች እንዲያለሙት መተላለፉንም ጠቁመዋል። ከእድሳትና ጥገና ስራ ጎን ለጎን ፓርኩ አገልግሎቶችን መስጠት መጀመሩንም ጠቅሰዋል።
የአዌቱ ፓርክ እድሳት የጅማ ከተማን ዝናዋን ወደነበረበት እንደሚመልሰው ተስፋ የተጣለበት ሲሆን ከተማዋን ውብ በማድረግ ጅማ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ቱሪስቶች ተመራጭ እንደሚያደርጋት ተስፋ ተጥሎበታል።
የፓርኩ ወደ ስራ መመለስ የከተማዋን ነዋሪዎች አስደስቷል። የጅማ ከተማ ነዋሪ አቶ ፈቃደ ወጉ ያካፈሉንም ይሄንኑ ደስታቸውን ነው። አዌቱ ፓርክ የከተማዋ ብቸኛዋ ፓርክ ናት። በፓርኩ ውስጥ ከልጅነት ዘመኑ ጀምሮ የማይረሱ ትዝታዎች አሳልፏል። ብዙ የሠርግ ሥነ ሥርዓቶችን ታድሟል፤ የተለያዩ የሙዚቃ ኮንሰርቶችን እና የውድድር ሥነ ሥርዓቶች ተካፍሏል። በጅማ የተወለዱ እና ያደጉ ሁሉ በዚህ ፓርክ ውስጥ ብዙ ትዝታ አላቸው። የፓርኩ መዘጋት እጅግ አሳዝኖት የቆየ ቢሆንም አሁን ወደ ነበረበት ክብሩ ለመመለስ እየተሰራ ያለው ስራ ደስታን ፈጥሮለታል።
ፓርኩ ዳግም መከፈቱ ለእኛ እና ለከተማችን ታላቅ ዜና ነው ። የፓርኩ መከፈት ለሁሉም ነዋሪ ደስታ ነው ብሏል። የሦስት ልጆች አባት የሆኑት አቶ ፈቃደ ልጆቻቸውን በዚህ ታሪካዊ ፓርክ ውስጥ እያዝናኑ መሆኑንም ተናግረዋል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ሰኔ 12/2013