አቶ ታምሩ ታደሰ ይባላሉ። ‹‹ታምሩ ታደሰ ኃላፊነቱ የተወሰነ ቡና አቅራቢና ላኪ ድርጅት›› ባለቤትና መሥራች ናቸው። ድርጅቱን የመሰረቱት በአምስት ሚሊዮን ብር ቢሆንም የወራት ዕድሜ ባስቆጠረ አጭር ጊዜ ካፒታላቸው ወደ 30 ሚሊዮን ብር ማደግ ችሏል። ተወልደው ያደጉት በሲዳማ ክልል በንሣ ወረዳ ቀጠና በምትባል ቀበሌ ውስጥ ነው። ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ በኢትዮጵያ በተካሄደው የምርጥ ቡና ቅምሻ ውድድር በተለያዩ ማጣራቶች 90 ነጥብ 6 ውጤት አምጥተው አንደኛ በመውጣት አሸንፈዋል። አቶ ታደሰ ወደ ቡና ንግዱ ሲያመሩ አርአያ ያደረጉት አንድም አቅራቢና ላኪ አልነበራቸውም። አርሶ አደሩ አባታቸውም የቡና ማሳ አልነበራቸውም። እንዴት ቢባል ተወልደው ያደጉባት የሲዳማ ክልል በንሣ ወረዳ ቀጠና ቀበሌ የአየር ሁኔታዋ እጅግ ደጋማ ስለሆነ ቡና አይበቅልምና ነው። በእርግጥ ሲዳማ ላይ ቡና ተለምዷል፤ ይጠጣል፤ ይወደዳል። በዚህ ላይ በክልሉ ቡና አብቃይ አካባቢዎች ይኖሩ የነበሩት ሰፋፊ የቡና እርሻ የነበራቸው አጎታቸው፣ የቅርብ ዘመዶቻቸውና ጓደኞቻቸው በቡና ዘርፉ የተሰማሩ እንደነበሩ ያውቃሉ፡፡ ሆኖም በዘርፉ የተሰማሩት የእነርሱ እንቅስቃሴ ስቧቸው ሳይሆን፣ ቡናው በዕውቀት መደገፍ አለበት የሚል ተሰጥኦ ጠርቷቸው መሆኑን ነው የሚናገሩት።
ይሄ ፍላጎታቸው ፈጥኖ ከውስጣቸው ባይወጣም ገና የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ ሳሉ ሆድ ሆዳቸውን ይበላቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። እስከ 10ኛ ክፍል ያለውን ትምህርታቸውን እዛው ተወልደው ባደጉባት ቀጠና ቀበሌ እስኪያጠናቅቁ ሀሳቡ አልተለያቸውም። በየሄዱበት የሚያይዋቸው ብዙዎቹ በቡና ማብቀል፣ ማቅረብና መላክ ስራ የተሰማሩ የቀበሌው፣ የወረዳውና የክልሉ አርሶ አደሮች ፊደል ያልቆጠሩ መሆናቸውን ያሰላስሉ ነበር። በወኪል በመሥራታቸው ብዙ ውጤታማ ላለመሆናቸው ምክንያቱ አለመማራቸው ነው የሚል ዕምነት እንዳሳደረባቸውም አይዘነጉትም። በእርግጥ ይሄ ዕውነታ በውስጣቸው ሲብላላ ቆይቶ በወቅቱ ትምህርቴን ስጨርስ ብገባበት ስኬታማ እሆንበታለሁ የሚል ሀሳብ በአእምሯቸው ማቃጨሉ ትዝ አይላቸውም።
የዛሬው እንግዳችን አቶ ታምሩ ስለ ቡና በውስጣቸው የሚብላላ ሀሳብ ቢኖርም ፊታቸውን ግን ከትምህርታቸው አልመለሱም። የ11ኛ እና የ12ኛ ክፍልን እንዲሁም የከፍተኛ ትምህርታቸውን በሀዋሳ ከተማ ውስጥ ተምረው አጠናቀቁ። ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በኤሌክትሪካል ኢንጅነሪንግ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን ያዙ። በዚህ ዲግሪም ወደ ደብርብርሃንዩኒቨርሲቲ በመሻገር ሁለት ዓመት በመምህርነት አገልግለዋል። ከዚህ በኋላ የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን በኮንትሮል ኢንጅነሪንግ መማር የሚያስችላቸውን ዕድል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አምስት ኪሎ ካምፓስ በማግኘት ገቡ።
ወደ ቡና ንግዱ ዘርፍ የተሰማሩትም በዚህ መካከል ነው። ትምህርታቸውን እየተማሩ በትርፍ ጊዚያቸው አብዝተው አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በቡና ስራ ከተሰማሩና ከሚቀራረቧቸው ጓደኞቻቸው ጋር በመሄድ አንዳንድ ስራዎችን መስራት ጀመሩ። ለራሳቸው እስኪገርማቸው ቀልባቸው ወደ ቡናው እየተሰበሰበ መጣ። የሦስተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን የመማር ሀሳብ ሰንቀው የነበረ ቢሆንም ቡናው ላይ የመስራት ፍላጎታቸው ገንፍሎ በመውጣቱ ገና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ሳይጨርሱ ‹‹ዱካሌዋቃዮ ቡና ላኪ››በተሰኘ ካንፓኒ ውስጥ ለመቀጠር ወሰኑ። ተቀጥሮ የመስራት ፍላጎታቸው ከፍተኛ ስለነበረም ከትምህርታቸው ጎን ለጎን ሥራውን መሥራት ጀመሩ። ጎን ለጎንም ሁለተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን በማጠናቀቃቸው የሦስተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን ለመቀጠል ዳግም ወደ ዩኒቨርሲቲ ላይመለሱ ለራሳቸው በመማል ተጠቃልለው ወደ ካምፓኒው ገቡ። በኩባንያው ውስጥ በጉዳይ አስፈፃሚነት ነበር የገቡት። እዛም በተለያየ የስራ ደረጃ ለአምስት ዓመታት አገልግለዋል። እየተማሩ ያካበቱት ልምድ፣ ራሱ የቀለም ትምህርቱ ለቡና ሥራው አስተዋጾ ማድረጉ ተደማምሮ ውጤታማ ሥራ ለመሥራት አብቅቷቸዋል።
አቶ ታምሩ እንዳጫወቱን በተለይ ሽያጭ ላይ በሚሰሩበት ጊዜ ከውጭ ከሚመጡ ደንበኞች ጋር ጥሩ ግንኙነት የነበራቸው መሆኑና ሽያጭ መልመዳቸው ሥራውን አቅልሎላቸዋል። እናም እነዚህን ታሳቢ በማድረግ አይከብደኝም ብለው በማሰብ በ2010 ይሰሩበት የነበረውን ‹‹ዱካሌ ዋቃዮ ቡና ላኪ›› ካምፓኒ ለቅቀው በቀጥታ ወደ ቡናው ባይገቡም ከቻይና ወደ ሀገር ውስጥ አንዳንድ ዕቃዎችን እያስገቡ ወደ መሸጥ አቀኑ። ጎን ለጎንም በትንሹም ቢሆን የራሳቸውን ቡና ወደ ውጭ በመላክ ሲሸጡም ቆይተዋል። በዚህ መካከል ቡናውን በዕውቀት ያውም በቀጥተኛ ዕውቀት ታግዘው ለመሥራት በማሰብ ሁሉንም ሥራቸውን እርግፍ አድርገው አቆሙ። ትኩረታቸውን ቡና እና ቡና ላይ ብቻ በማድረግ ወደ ትምህርት ቤት ገብተውም የምርጥ ቡና ቅምሻን ትምህርት ቀሰሙ። በመስኩም የመጀመርያ ዲግሪ ያዙ። ይሄም ሳይበቃቸው ቡና ላይ ያተኮሩ የተለያዩ በዓለም ዙሪያ ያሉ መጽሐፍቶችን በማገላበጥ ስለ ቡና አስፈላጊ ነው ያሉትን በሙሉ ሲያነብቡ ቆዩ። አቶ ታምሩ ከዚህ በኋላ ነው ሙሉ በሙሉ ወደ ቡናው ዘርፍ መግባት እንዳለባቸው ያመኑትና የራሳቸውን ቡና ወደ ማዘጋጀት የገቡት።
‹‹ ዘንድሮ ወደ ቡናው መስኩ ገብቼ በዚሁ ዓመት ያውም በጥቂት ወራት ውስጥ ስኬታማ እሆናለሁ፤ የሀገሬንም ስም አስጠራለሁ›› ብለው አላሰቡም። ብቻ ባላቸው 2 ነጥብ 5 ሄክታር ማሳቸውና ከአንድ እስከ አምስት ሄክታር ማሳ ካላቸው የሲዳማ ቡና አብቃይ አርሶ አደሮች ቡና እየተረከቡ ዝግጅታቸውን አጧጧፉ። ዳጎስ ባለ ዋጋ ምርታቸውን የሚረከባቸው ያገኙት አርሶ አደሮች ምርጥ ምርጡን ቡና ይዘው ወደ እርሳቸው መጉረፍ ጀመሩ። ቀይ ቀይዋን ብቻ ወስደው ያልበሰለውን ለቅመው በመመለስ የቡና ዝግጅት ጥራትን መጠበቁንም ተያያዙት። ዝግጅቱ በትውልድ ቀያቸው በነሣ ወረዳ ቀጠና ገጠር ቀበሌ ውስጥ ነው። ቡናው ከዚህ ቦታ በተከራዩት ማበጠሪያ ተበጥሮና ተዘጋጅቶ ጭምር ሲመጣ የሚቀመጥበት 300 ካሬ መጋዘን ደግሞ ከተማ ውስጥ አላቸው።
የቡና አቅራቢና ላኪው አቶ ታምሩ እንዲህ ያማረ ዝግጅት ባደረጉበት በሁለተኛው የምርጥ ቡና ቅምሻ ውድድር የተሳተፉት በታጠበና ባልታጠበ ሁለት የቡና ዓይነት እንደነበርም አጫውተውናል። አንደኛው አናኤሮብክ ይባላል። የዚህ ቡና አዘገጃጀት አሁን የመጣ አዲስ ነው።
ወደ አዘገጃጀቱ ሲገባ እሸቱ ቡና በበርሜል ውስጥ እንዲንሳፈፍ ይደረጋል። ከላይ የተንሳፈፈው ይነሳል። ወደ ውስጥ የገባውና ፍሬ ያለው ቡና በርሜል ውስጥ ይጨመርና ምንም ኦክስጅን ከውጪ በማይገባበት ሁኔታ በርሜሉ ይዘጋል። ሁለተኛ የተሳተፉበት ያልታጠበ ቡና ነው። ይሄ ቡና አርሶ አደሩ እንዳመጣው እንዲንሳፈፍ ይደረጋል። 24 ሰዓት አልጋ ላይ ቆይቶ እርጥበቱ ይለካና ወደ መጋዘን ይገባል። ለውድድሩ ከሁለቱም ተወስዶ ነው አቅራቢውም፣ አርሶ አደሩም ላኪውም ከተሳተፉበትና እንደ ሀገር ከቀረበው 1ሺህ 848 የቡና ናሙና ጋር የተደመረው። ናሙናው የተወሰደው አቶ ታምሩ ካቀረቡት አጠቃላይ ቡና ነው። ወደ 32 በሚደርሱ ቡና ቀማሾችም ተቀምሷል። ዘንድሮ ተፎካካሪውም ብዙ ነበር። ያም ሆነ ይህ መጨረሻ 40 ናሙና ተመረጠ። አቶ ታምሩ ያስደሰታቸው ደግሞ በተመረጡት አርባዎቹ መካከል ሁለቱም ቡና መግባቱ ነው። እነዚህ 40 ዎቹ ናሙናዎች ተወስደው ወደ ስድስት ሀገሮች የተላኩበት ነበር። ቻይና፣ ጃፓን፣ ደቡብ ኮርያ፣ አሜሪካ፣ ኖርዌይ ከሀገሮቹ ይጠቀሳሉ።
ከተወዳደሩበት ሁለት የቡና ዓይነቶች አናኤሮብክ የተሰኘው ቡና 90 ነጥብ 6 ውጤት በማምጣት አንደኛ ሆኖ አሸነፈ። ሁለተኛው የተወዳደሩበት ቡና ደግሞ አምስተኛ አሸናፊ ሆኗል። ይሄ እራሱ አንደኛ ከወጣውና ዋነኛ አሸናፊ ከሆነው ቡና ብዙም የማይራራቅ 90 ነጥብ 1 ነው ያመጣው። አምስቱም አሸናዎች ፕሬዚዴንሻል የተሰኘ ደረጃ ውስጥ የገቡ በመሆናቸው አምስተኛ የወጣው ቡናቸው ቀላል ግምት የሚሰጠው እንዳልሆነም አቶ ታምሩ ነግረውናል። በሽያጭ ከሚያስገኘው ገቢ አንፃርም ቢሆን ትልቅ ዋጋ ያለው ነው። በአጠቃላይ በዚህ ውድድር የሚገኘው የውጪው ቡና ሽያጭ ዋጋ ከሀገር ውስጥም ሆነ ቀድሞ ከነበረው ጋር ሲነፃፀር እጅግ የተለየ ነው። አምና ከተሸጠበት ዘንድሮ የሚሸጥበት እጅግ ጨምሯል። አንድ ኪሎ ቡና እስከ 450 ዶላር ድረስ የሚሸጥበት ሁኔታ ይኖራል ብለው ይገምታሉ። በኢትዮጵያ ብር አንድ ኪሎ ቡና 20 ሺህ ብር ይሸጣል የሚል ዕምነት አላቸው።
‹‹ውጪ የሚሸጥበት ዋጋ በፍፁም ከመደበኛ ዋጋ ጋር የሚገናኝ አይደለም›› ብለውናል ውድድሩ ከዋጋ አንፃር ያመጣውን ከፍተኛ ለውጥ ሲገልፁ። ለአብነት እንዳነሱት እሳቸው አናኤሮብክ የተሰኘውንና አሁን አሸናፊ የሆኑበትን ተፈጥሮአዊ (ኦርጋኒክ) ቡና ሸጥኩበት የሚሉት ከፍተኛ ዋጋ በኪሎ ከ500 እስከ 600 ብር ነው። ለድርጅታቸው ሲያቀርቡ የነበረውም በዚህ ዋጋ ነው። አሁን ላይ በዓመት ከ25 እስከ 30 ኮንቴይነር ቡና ወደ ውጪ እየላኩ ይገኛሉ። ከውድድሩ በፊት ይሄን ቡና በኪሎ ከ500 እስከ 600 ብር ባለው ዋጋ መሸጣቸውንም ያስታውሳሉ ።
እንደ አቶ ታምሩ ማብራሪያ፤ ከዚህ ቀደም ውድድሩ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለ መግባቱ አርሶ አደሩ ለረጅም ጊዜ ትልቅ ዋጋ ቀርቶ በተመጣጣኝ ዋጋ እንኳን የቡና ምርቱን የመሸጥ ዕድል ማግኘት ሳይችል ቆይቷል። ይሄ ለውጥ የመጣውና ገቢ የተገኘው የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን በአዋጅ ተቋቁሞ ወደ ሥራ ከገባ በኋላ በተሰራው ሥራና በተፈጠረው መነሳሳት ነው።
ባለስልጣኑ ላኪና አቅራቢውን በማስተሳሰር ብድር የሚያገኙበትን ሁኔታ በማመቻቸት እያገዛቸው ይገኛል። ቡና ላይ ብዙ ዕውቀት ያላቸው ሰዎች ያደረጉት አስተዋጾም ከፍተኛ ነው። በእርግጥ ከጠዓምና ጥራት አንፃርም ከሌሎች ሀገሮች ጋር ሲነፃፀር የኢትዮጵያ ቡና ላይ የሚደርስ የለም። እንዲህም ሆኖ አሁን ላይ ውጤታማ መሆን የቻለው መንግስት ትኩረት ስለሰጠውና የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣንን የመሰለ ባለቤት አግኝቶ ጥራቱና ገበያው ላይ ስለተሰራበት ነው። ቀድሞ ያለው አሰራር እንኳን የተሻለ ጥቅም ማግኘት ሊያስችል በዘርፉ ለመሰማራት የሚጋብዝ አልነበረም። ዛሬ ላይ ሆነው ሲያስቡት ቡናው በዕውቀት መደገፍ አለበት ከሚለው የፀና አቋማቸው ባሻገር እሳቸውም ቢሆን ወደ ዘርፉ ለመግባት ፈራ ተባ እያሉ የዘገዩበት ምክንያት ምን እልባት ይሄው ሊሆን ይችላል የሚል ጥርጣሬ የላቸውም። አሁን ላይ በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ ወደ ዘርፉ ገብተዋል። ካፒታላቸው ከአምስት ሚሊዮን ተነስቶ 30 ሚሊዮን ደርሷል። ገቢያቸው በፍጥነት እያደገ መጥቷል። ዘንድሮ ድርጅታቸው ከሁለት ሚሊዮን ዶላር በላይ ኮንትራት ያለው መሆኑ ማሳያ ነው። እስከ አሁን ወደ 800 ሺህ ዶላር ማስገባቱንም ይጠቀሳሉ። ገና በቅርቡ የሚገባ አንድ ሚሊዮን ዶላር አለው። በአሁኑ ሰዓት ኮንቲነር እየጠበቀ መገኘቱን የገለፁት አቶ ታምሩ ይሄ በሁለተኛው ዙር ውድድር አንደኛ ወጥተው በማሸነፋቸው የሸጡት መሆኑንም አበክረው ይናገራሉ።
በተከፈተው ትልቅ የገበያ በር ቻይና፣ ሆንግ ኮንግ፣ በተወሰነ መልኩ አሜሪካ ለገበያ የቀረበውን አይጨምርም። በቅርቡ ገበያው ይሰፋል። አንደኛ የወጣውን ቡና ጃፓን ወስዶ የመሸጥ ዕቅድ አላቸው።
በዚህ በር ሁሉም በቡና አብቃይነት የተሰማራ አርሶ አደር ተነቃቅቶ እየሰራ ይገኛል። ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠርም ሚናው የጎላ ነው። በሥራቸው ሰባት ቋሚና 64 ጊዜያዊ ሠራተኞች አሏቸው። አሸናፊ የሆኑበት ሁለተኛው ውድድር ይዞት ከመጣው ብዙ ዕድሎች አንዱ የነዚህን የቡና ሳይት ሠራተኞች ቁጥር መጨመር ነው።
ቋሚና ጊዜያዊ ሠራተኞቻቸውን ቁጥር በእጥፍ ለመጨመር ማስታወቂያ አውጥተው ቅጥር እያከናወኑ ይገኛሉ። ካፒታላቸውንም በሚፈለገው ደረጃ እንደሚያሳድግላቸው በእርግጠኝነት ይናገራሉ። ለድርጅታቸው የሚያመጣው ክብሩም፣ ብራንዱም ከፍተኛ ነው ባይናቸው። ይሄ ስም ይዞት የሚመጣው ከፍተኛ የውጭ ገበያ በቃላት የሚነገር አይደለም። በዚህ ጊዜ ደግሞ አዳዲስ የሰው ኃይል መጨመሩ ግድ ነው በማለት ሀሳቡን ያጠናክራሉ። የውጪ ምንዛሪ በማምጣትም ድርሻው የጎላ መሆኑንም አጫውተውናል። ሆኖም በንብረትና ቤት ዋስትና ላይ የሚያተኩሩት ባንኮች ብድር አሰጣጥ ላይ አሰራራቸውን ማሻሻል እንዳለባቸው ይመክራሉ። እስከ መሥርያ ሳይት ቦታ ድረስ በመምጣት ቀርበው ሥራውን በማየት ብድር ቢሰጡ ተመራጭ ነው ባይ ናቸው። መንግስትና ባንኮች በተለይ ከላኪው ጋር ቀርበው መሥራት አለባቸው። የቡና ማበጠሪያ ችግሩን ለመፍታት ለሌሎች ኢንዱስትሪዎች እንደሚደረገው ሁሉ ቡና አምራቹን አንድ ቦታ ላይ ሰብሰብ አድርጎ ኢንዱስትሪ ፓርክ ቢሰጥ፤ በአጠቃላይ ወርቅ ላይ እንዳለው ቡና ላይ ቢሰራ ብዙ ሀገሮችን ከድህነት ያወጣ እንደ መሆኑ ብዙ ለውጥ ማምጣት ይቻላል። ሀገራችን አሁን ላይ እየገጠማት ካለው ብርቱ የውጭ ምንዛሪ ችግርም ይታደጋል በማለት ጽሑፋችንን ቋጨን።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሰኔ 12/2013