ከእናት ሆድ ጀምሮ እስከ ሽምግልና ድረስ የሚዘልቀው ዘመናችን በተለያዩ የእድሜ ክፍሎች ውስጥ ይመደባል። ጽንስ ከመሆን ጀምሮ፣ ጨቅላ ህጻን፣ ህጻን፣ ታዳጊ፣ ወጣት፣ ጎልማሳ፣ ሽማግሌ እና አዛውንት ተብሎ ይገለጻል። ሁሉም ሰው በሁሉም የእድሜ ደረጃዎች ላይ የመድረስ እድል ላይኖረው ቢችልም በዙሪያችን ግን ከየምድቡ የሆኑ ሰዎች ያሉ ሲሆን፤ ሁሉም የእድሜ ክፍሎች የየራሳቸው ብርቱ የሆነ መገለጫ አላቸው። በዚህ ጽሁፍ ስለ ፈጣኑ የእድሜ ክፍል እናያለን። ወደ አዋቂነት በሚደረገው መንደርደር ላይ ብቻም እናተኩራለን፤ ከአካላዊ ለውጥ ይልቅ ከፍተኛ ሥነ-ልቦናዊ ተጽእኖ ያለበትን የእድሜ ክፍልም ለይተን እንመልከታለን።
ውሳኔ ለመወሰን ዝግጁ የምንሆንበት፤ በወሰንነው ውሳኔ ጥቅሙንም ሆነ ጉዳቱን ለመቀበል የምንዘጋጅበት፤ ከወቅቶች ሁሉ አስቸጋሪው ፈጣኑ የእድሜ ወቅት ነው። ከታዳጊነት የመጨረሻዎቹ አመታት ጀምሮ እስከ ጎልማሳነት የመጀመሪያዎቹ አመታት ውስጥ ባሉት ጊዜያት ውስጥ ያለውን የእድሜ ክፍል ዛሬ እንመለከታለን። አንባቢው በዚህ የእድሜ ክልል ውስጥ ያለ ከሆነ መልእክቱ በቀጥታ የሚደርሰው ሲሆን፤ ሌሎቻችን ደግሞ እነርሱን ለመረዳትና ለመርዳት እንድንችል ያግዘናል። መንደርደሪያ ታሪካችን ወደ አንድ ቢሮዋን ኩሽና ያደረገች በጭስ የጨነበሰች የሃያ ዘጠኝ አመት ወጣት ሴት ጋር ይወስደናል።
የእድሜዋ ቁጥር በወጣትነት ውስጥ እንድትመደብ ያደርጋታል። ወጣትነት ውስጥ ያለው ውስጣዊ ግፊት ሁሉ በውስጧ ሲብላላም የነበረ ነው። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን አጠናቃ ወደ ዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ወስዳ ክረምቱን ዘመድ በመጠየቅ ለማሳለፍ ከአዲስ አበባ ወደ አሶሳ ታቀናለች። አሶሳ የክረምት የእረፍት ጊዜዋ ወቅት የተዋወቀችው ወጣት ጋር ግንኙነት ትጀምራለች። ግንኙነቱም ያልታሰበ እርግዝና እንዲፈጠር ምክንያት ይሆናታል። ከጥብቅ ሃይማኖታዊ ቤተሰብ ያደገችው ወጣቷ የጀመረችው የስህተት መንገድ ጽንስን እስከ መጸነስ መድረሱ ያስደነግጣታል። ጽንሱን ማስወረድ ህይወት ያለውን ፍጡር ለሞት መዳረግ መሆኑን በመረዳት ተጨነቀች። በመጨረሻም የሚመጣውን ሁሉ ለመቀበል ዝግጁ ሆነች።
ሁኔታውን አዲስ አበባ ያለው ቤተሰቧ ጋር መጥታም አስረዳች። አባት በሁኔታው አዝነው ልጃቸው ላይ ጨክነው ከቤት እንድትወጣ ይወስናሉ። ወጣቷም መከፈል የሚገባውን ዋጋ ሁሉ ከፍላ ልጇን ለማሳደግ ህልም ታደርጋለች። ያለጊዜው የመጣው እርግዝና ትምህርቷን መነሻ አድርጋ እደርስበታለሁ ብላ ያለመችውን ህልም የቀየረው ሆነ። በደቂቃዎች ውስጥ በሚፈጠር የስሜት ማእበል ውስጥ በደቂቃዎች ውስጥ የማይፈታን ህልም ይዞ መጣ። የአሶሳው ወጣት፤ ለአንድ ክረምት በፍቅር አብረው የከነፉት በሌላ የህይወት አቅጣጫ ከሀገር ወጥቶ ኑሮን ለማቅናት በደላሎች መንደር ሲያንዣብብ ቆይቶ የስደትን መንገድ ይዞታል። የተከፈለ ልብ ይዞ ስደት። ክፋዩ ልብ ወደ ልጁ፤ ክፋዩ ልብ ወደ ወጣቷ፤ ሌላ ክፋዩ ልብ በስደት ጉዞ ስለሚገጥሙት ያልታወቁ ቀናት እያሰበ ነው። በየቦታው የተበታተነው ልብ ተሰብስቦ በአንድ ጎጆ ውስጥ አብሮ ለመተንፈስ ስንት አመታትን ይፈልግ ይሆን? የሚለውን ጥያቄ በእርግጠኝነት የሚመልስ የለም። ሰላሰኛ አመቷ ወደ ቁጥር ውስጥ ሊገባ ጥቂት ወራት የሚቀሯት ወጣት ግን በጥቂት አመታት ውስጥ በህይወቷ ውስጥ በሆነው ለውጥ እየተገረመች ነገን አሻግራ የምታይበት ልጇ ውስጥ እያየች በጭስ ውስጥ አሻግራ በስደት ጉዞ ላይ ያለውን የልቧን ክፋይ እያየች ቀናትን ትቆጥራለች።
በወጣቷ ውስጥ የሆነው ፈጣን ለውጦች ከፈጣኑ የእድሜዋ ክፍል ጋር ይገናኛሉ። በፈጣኑ ለውጥ አስተናጋጅ የእድሜ ክፍል ውስጥ በቤተሰብ ዙሪያ ከነበረው ህይወት ወደ ውጭ መውጣትን የሚጠይቅ ነው። የሁለተኛ ደረጃ ተማሪው ወደ ኮሌጅና ዩኒቨርሲቲ ሲሄድ ለውጪው አለም ይበልጥ ተጋላጭ ይሆናል። በመነሻ ታሪካችን ያገኘናት ወጣት ተጋላጭነት የጀመረው ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት መጠናቀቅ ቅጽበት ውስጥ ሆኖ ነው። ወደ ኮሌጅ/ዩኒቨርሲቲ የደረሱ ወጣቶች አዲስ አካባቢን የማወቅ ከአዳዲስ ሰዎች ጋር የመገናኘት እድላቸውን ይፈጥራል። ወቅቱ ነገሮችን በትኩረትና በዓላማ ውስጥ እያዩ የማይኬድበት ከሆነ የህይወት አቅጣጫን ለውጥ ሊያመጣ ይችላል። የመነሻ ታሪካችን ወጣት አይነት ታሪክ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚገጥማቸው ጥቂት አይደሉም። አሁን ባለንበት ዘመን ችግሩ አሳሳቢ በሚባል ደረጃ ላይም የሚገኝ ሆኗል። የሁለተኛ ደረጃና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ውርጃን እንደ ቀላል ቆጥረው በረጅም ጊዜ በህይወታቸው ላይ ጠባሳን እየተው ሲሄዱ እናስተውላለን። ፈጣኑ የለውጥ እድሜ ክፍል ለዚህ አይነቱ አደጋ ተጋላጭ ያደርጋል።
በዚህ ክፍል ውስጥ የፈጣኑ እድሜ ባህሪያት እና በፈጣኑ እድሜ ውስጥ እንዴት ህይወትን እንምራ የሚለውን እንመለከታለን። በእድሜው ውስጥ ላሉት በአደራ መልክ ከእድሜ ውጭ ላሉት በዙሪያቸው ስላሉት ሰዎች ብለው በበለጠ አደራ።
የፈጣኑ እድሜ ባህሪያት፣
እያንዳንዱ የእድሜ ክፍል የራሱ የሆኑ ባህሪያት አሉት። የሚከተሉት የፈጣኑ እድሜ ክፍል ባህሪያት ናቸው።
1. ውሳኔን ጠያቂነት
ውሳኔን መወሰን መቻል በማንኛውም የእድሜ ክፍል ውስጥ የሚገኝ ነው። በፈጣኑ የእድሜ ክፍል ውስጥ በአጠቃላይ የህይወት አቅጣጫን የሚወስኑ ውሳኔዎች ይወሰናሉ። ከሁለተኛ ደረጃ ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚመደብ ተማሪ የሚማረውን ትምህርት ወይንም የሚማርበትን የትምህርት ክፍል መወሰንን ይጠይቀዋል፣ የእጮኝነት ጥያቄ የሚመጣበት ወይንም የሚቀርብበት እድሉ ሰፊ ስለሆነ ለነገ የትዳር ህይወት ማሰብን የሚጠይቅበት ነው፣ ከትምህርት ቀጥሎ ወደ ሥራው አለም መግባት ሲታሰብ ስራ በማመልከትና ከአንድ ተቋም ወደ ሌላ ተቋም በሚደረግ ሽግግር ውሳኔ ይወሰናል፣ እጮኝነት አድጎ ወደ ትዳር የሚመጣውም በአብዛኛው በዚህ የእድሜ ክፍል ውስጥ የመሆን እድሉ ሰፊ ነው፤ ትዳርን ተከትሎ የልጅ አባት ወይንም እናት መሆንም እንዲሁ ወዘተ። ወደ ኮሌጅና ዩኒቨርሲቲ የማይሄድ ደግሞ ወደ ሥራው አለም ገብቶ ትምህርት በማታ ወይንም በርቀት ለመማር ጥረት ማድረግም በዚሁ የእድሜ ክፍል ነው። በአጭሩ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚማሩትን ትምህርት፣ የነገ የትዳር አጋር የሚሆን እጮኛን መምረጥ፣ የወደዱትን ስራ ለማግኘት ጥረት ማድረግ፣ ወደ ትዳር መግባት እና ልጅን ማሳደግ መጀመር የፈጣኑ የእድሜ ክፍል ውሳኔ በፍጥነት ተከሳቾች ናቸው። በዚህ ሁሉ ውስጥ ውሳኔ አለ። ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የሚደረግ የህይወት ልዩ ውሳኔዎች።
2. ለፈተና ተጋላጭነት
ፈጣኑ እድሜ የሚፈልገውን ውሳኔዎች በጥራት መወሰን የሚከለክል የፈተና ተጋላጭነት በዚሁ የእድሜ ክፍል ውስጥ ይገኛል። ወጣትነት ውስጥ ባለው ጾታዊ የስሜት ፍላጎት፣ ደስታንም ሆነ ንዴትን መጋራት ያለመቻል ስሜታዊነት፣ ሁሉንም በመፈለግ የሚገለጽ የውስጥ ግፊት፣ ለብዙ ነገሮች ራስን ተጋላጭ ማድረግ፣ እጮኝነት ህይወት ትርጉሙን አጥቶ መለስተኛ ትዳር ሆኖ አባትና እናት በእኩል ሃላፊነት ዝግጁ ባልሆኑበት ሁኔታ የሚወለድ ልጅ ሃላፊነት፣ በስደት ህይወት ውስጥ የህይወትን ስኬት ጠቅልሎ በመጨመር ባልተገባ ተስፋ ውስጥ ሆኖ እግርን ለስደት ማንሳት ወዘተ ውስጥ የፈተና አይነቶች አሉ።
ሕይወት ያለው ሰው ሁሉ ለፈተና ተጋላጭ ቢሆንም በፈጣኑ የእድሜ ክልል ውስጥ የሚኖረው ተጋላጭነት ግን ከሁሉም የእድሜ ክፍሎች ቀዳሚውን ይይዛል። ህጻናት፣ ታዳጊዎች፣ ጎልማሶች እንዲሁም አዛውንት ካለባቸው የፈተና ተጋላጭነት የበዛው በፈጣኑ የእድሜ ክፍል ውስጥ የሚገኘው ነው ብንል የተሳሳትን አንሆንም።
3. ምክርን አለመስማት፣
የህይወት ጉዞ ውስጥ የሚሰጠው ውሳኔ ለፍሬ የሚያበቃ ይሆን ዘንድ ብረት በብረት እንደሚሞረድ አንዱ ሰው ሌላኛውን ይሞርዳል። የቀደሙቱ አዲሶቹን እየመከሩ መንገድን እየጠቆሙ አቅጣጫን በማሳየት ያገለግላሉ። ምክር ታላቅ ስራን የምትሰራው ሰውን በማቅናት እና በትክክለኛው ጎዳና በመምራት ውስጥ ስታገለግል ነው።
ፈጣኑ የእድሜ ክፍል በበረከቱ ውሳኔዎች የተሞላ ቢሆንም ለውሳኔዎች ግን የሌሎችን ምክር ሰምቶ ውሳኔን ለመቃኘት ከመሞከር የራስን ሃሳብ ፍጹም አድርጎ የመውሰድ አጋጣሚ በፈጣኑ እድሜ ውስጥ የሚገኙ መገለጫ ሊባል የሚችል ነው። ምክርን አለመስማት ዘግይቶም ቢሆን የሚሰማና ለጸጸት የሚዳርግ ሆኖ ይገኛል።
ምክርን አለመስማት ጎጂ ሆኖ እንደሚገኝ ሁሉ የማይሆን ምክርን መስማትም እንዲሁ ጎጂ ነው። ፈጣኑ እድሜ ምክርን ባለመስማት ብቻ ሳይሆን ለይቶ ለመስማት በመሞከርም ይገለጻል።
የጠቢቡ ሰለሞን የጥበብ ገለጻዎች ውስጥ ምክርን ሃብት ማድረግ ለህይወት ያለው ፋይዳ ላይ ያተኩራል። በእድሜ የገፉ ሰዎች በምክራቸው ውስጥ ጣል የሚያደርጉት ምክርን ባለመስማት የተሳሳቱበትን ወቅት ምስክርነት ይገኝበታል፤ ከእነርሱ ስህተት መጪው እንዲማርበት። ስንቶቻችን ግን በአስተውሎት እናደምጣለን የሚለውን ጥያቄ መጠየቅ ግን ግድ ይለናል።
በፈጣኑ እድሜ ውስጥ ህይወትን እንዴት እንምራ?
የፈጣኑ እድሜ ባህሪያትን የተረዳ ሰው ህይወትን በፈጣኑ እድሜ ውስጥ እንዴት መምራት እንዳለበት ሲያስብ ባህሪያቱን ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርበታል። ሦስቱ ቁልፍ የፈጣኑ የእድሜ ክፍልን ባህሪያትን መነሻ በማድረግ ጥያቄውን እንመልስ።
በፈጣኑ እድሜ ውስጥ ህይወትን ለመምራት፣
1. ጥራት ላለው ውሳኔ ትኩረት እንስጥ፣
እያንዳንዱ ቀን ውስጥ ውሳኔ አለ። መኪና የሚያሽከረክር ሰው በእያንዳንዱ ቅጽበት ውስጥ ውሳኔን ያሳልፋል። ፍሬን ለመያዝ፣ ፍጥነት ለመጨመር፣ የመኪና ጥሩምባ ለመጠቀም/ክላክስ ለማድረግ ወዘተ ውሳኔ ይወስናል። የመኪና አሽከርካሪ የሚወስነው ውሳኔ መወሰን ከሚገባው ጊዜ ከዘገየ ውጤቱ አሰቃቂ አደጋ ሊሆን ይችላል። ምንአልባት ከአደጋዎች ሁሉ የከፋ የሆነው የሰውን ህይወት የሚነጥቅ አደጋ።
በህይወት ጉዞ ውስጥ ጥራት ያለው ውሳኔ መወሰን ማለት ትክክለኛውን ውሳኔ በትክክለኛው ጊዜ መወሰን ማለት ነው። በከፍተኛ ፍጥነት ላይ ሆኖ በፍጥነት እስከመጨረሻ ፍሬን መያዝ መገልበጥን ሊያመጣ ይችላል፤ ፍሬን መያዝ ሲገባ አለመያዝ ደግሞ ህይወትንም ሊያጠፋ ይችላል። ስለሆነም ትክክለኛውን ጊዜና የፍሬን አያያዙን መጠን መወሰን ይጠይቃል። ውሳኔ መወሰኑ ብቻ ሳይሆን መወሰን ባለበት ጊዜና ሁኔታ ውስጥ መወሰኑ የግድ ይላል የሚለውን በጥሞና ማሰቡ ተገቢ ነው።
ጥራት ላለው ውሳኔ ለመወሰን ውሳኔ ስለምንወስንበት ነገር ማወቅ፣ መረጃን መያዝ፣ ልብን ማዳመጥ፣ የሰዎችን ምክር መስማት፣ ውሳኔው ከሌሎች የህይወታችን ውሳኔዎች ጋር ያላቸውን ቁርኝት መረዳት ከሁሉም በላይ ውሳኔው በራሳችን ላይ ብቻም ሳይሆን በሌሎች ላይ ያለውን ተጽእኖ በመረዳት ቢሆን ይመከራል።
2. ለፈተና ዝግጁ ሆኖ መኖር፣
ፈተናን በገዛ እጅ መጥራት እና ፈተናውን አሻግሮ ተመልክቶ ለፈተና ዝግጁ የሆነን ህይወት መኖር ይለያያል። በህይወት ውስጥ ብዙ ሊመጡ የሚችሉ የየራሳቸው ባህሪ ያላቸው የፈተና አይነቶች አሉ። አንዲት ወጣት ሴት የሚደርስበት የፈተና አይነትን ለመረዳት በጥሞና ማሰብ ብቻ ነው የሚጠይቀው። ፈተናው በተለያዩ አይነት ምስክርነት በብዙ መድረኮች ሲነገር የሚደመጥ ስለሆነ።
በኮሌጅና ዩኒቨርሲቲ ውስጥ፣ በሥራው አለም ውስጥ፣ በእጮኛነትም ሆነ በትዳር እንዲሁም ልጅን በማሳደግ፤ በአጠቃላይ ኑሮን አሸንፎ በመኖር ውስጥ ያሉ ፈተናዎችን ዘርዝሮ ማወቅ ተገቢ ነው። ፈተናዎቹን በስም አውቆ ለእያንዳንዱ ፈተና ዝግጁ የሆነ ቢመጣ እንዳመጣጡ የሚመልስ አቅምን ይዞ መገኘት አስፈላጊ ነው።
ፈተናን በመሸሽ ብቻ ማሸነፍ አይቻልም፤ ሲመጣ ለማስተናገድም ዝግጁ በመሆን እንጂ። መፍትሄነት የሚወጣው በፈተና ውስጥ አልፎ በመገኘት ነው። የዛሬ ተፈታኝ ለነገው ህያው አቅም ሆኖ ለመገኘት የዛሬውን ፈተና በዝግጁነት ገጥሞ የሚረታ መሆን አለበት።
በፈጣኑ የእድሜ ክፍል ውስጥ የበዙ ፈተናዎች በመኖራቸው ተሸናፊነትን ማዳበር ሳይሆን ለፈተናዎች እየተዘጋጁና እየረቱ በማለፍ እንደ እድል መቁጠር ይገባል።
3. ምክርን ገንዘብ ማድረግ፣
ግለ-መካሪ ለእያንዳንዱ ሰው አስፊላጊ ነው። በህይወት ያለ ሰው ሁሉ ግለ-መካሪ ያስፈልገዋል። እጮኛን በመያዝ፣ በትምህርት ዘርፍ ምርጫ፣ በተቋም ውስጥ ስለሚኖር ኑሮ፣ በግል የራስን ስራ ስለመጀመር፣ የባህሪ ለውጥ ስለማምጣት፣ ስለ ልጆች አስተዳደግ ወዘተ ምክርን ገንዘብ ማድረግ ያስፈልጋል።
በእኛ ኢትዮጵያዊያን የማህበራዊ ህይወት በገጠሪቱ የሀገራችን ክፍል እስከአሁን የዘለቀ፣ ከጎረቤት ጋር ቡና አብሮ የመጠጣት ጠንካራ ባህል አለ። ቡናን አብሮ በመጠጣት ማህበራዊ ህይወት ውስጥ በነገር ነገር የአንዱ ጉዳይ ይነሳና ሌሎች አስተያየት በመስጠት ኢ-መደበኛ በሆነ መንገድ ምክክር ይደረጋል፤ በጋራ እውቀትን የመጋራት መድረክም ይሆናል። በማህበራዊ ህይወት ጠንካራ የሆኑ ሰዎች ከሌሎች የተሻለ የውስጥ ሰላም እንዳለቸው ብዙ ጥናቶች ያሳያሉ። የዚህ ዋናው ምክንያቱ በማህበራዊ ህይወት ውስጥ ያለው ምክክር አቅጣጫን ተላሚና ሸክምን ለመጋራት የሚያስችል በመሆኑ ነው – ምክርን የመቀባበል መድረክ።
ምክርን ገንዘብ ስለማድረግ ስናስብ አንድ ሰው የሌሎች ሰዎች ምክር ያስፈልጉታል ሲባል ውሳኔን ይወስኑለታል ማለት አይደለም። ውሳኔ ለባለቤቱ የተተወ ሲሆን ምክርን መስጠት ግን ምክር የተፈለገበት ሰው ሃላፊነት ነው። በአንድ ጉዳይ ከተለያዩ ሰዎች ምክርን መጠየቅ ጉዳዩን በተለያየ አቅጣጫ ለመመልከት እድልን የሚሰጥ ነው። በተለያየ አቅጣጫ የተሰጠው ምክር ጥራት ያለው ውሳኔን ለመወሰን በእርግጥ የሚረዳ ነው። ጥራት ያለው ውሳኔ ለህይወት ጉዞ ወሳኝ በመሆኑ የሌሎችን ምክር ለራስ ጥቅም መሆኑን በመረዳት የመስማት እድል መስጠት ይገባል።
ፈጣኑ የእድሜ ክፍል የበረከቱ ውሳኔዎችን መወሰንን የሚጠይቅ እንደመሆኑ የሌሎችን ምክር ለመስማት ተገቢ የሆነውን ትኩረት መስጠት ይገባል። ለመምከር የሚመጡትን በጉርምስና ስሜት ገፍቶ ከመመለስ በደስታ ማድመጥ መቻል የአስተዋፅኦ አድራጊነት ጉዞን ለመንደርደር ያስችላል።
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
አዲስ ዘመን ሰኔ 12/2013