የአንድ ወጣት ምርታማነት የሀገር ምርታማነት ነው። የአንድ ወጣት ስኬት የሀገር ስኬት ነው። የአንድ ወጣት ውድቀት የአገር ውድቀት ነው። የአንድ አገር ሀብት ሰላምና እድገት የሚለካው በሀገሪቷ ብሄራዊ ግምጃ ቤት ባለው ሀብት አይደለም። ይልቁንም ምን ያህል የአገሪቷ ህዝቦች ያመርታሉ የሚለው ነገር ነው። የሀገሪቷ ምርት፣ እድገት፣ ሰላም፣ ጥረትና የዜጎች ጥቅል ምርታማነት የዜጎች ሰላማዊነት ነው። የኢትዮጵያ ወጣቶች የሰላም የበጎ ፈቃደኛ ማህበር ከአዲስ አበባ ወጣቶችና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ ጋር በመተባበር ‹‹ምክንያታዊ ወጣት ለሰላማዊ ምርጫ›› በሚል በአገር አቀፍ ደረጃ ለሚካሄደው ስድስተኛው ምርጫ የመራጮች ትምህርትና የስነዜጋ ስልጠና ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ሰጥቷል። በዚህ ስልጠና ላይ የተገኙ ተማሪ ወጣቶች ምክንያታዊነትን በማሳደግ ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል። በተጨማሪም በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ የኢትዮጵያን አቋም በማህበራዊ ሚዲያ በማሰራጨት የበኩላቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ለዝግጅት ክፍሉ አስተያየት የሰጡ ወጣቶች ተናግረዋል።
ወጣት ሲሳይነሽ ቃውት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሶስተኛ ዓመት የፍልስፍና ተማሪ ስትሆን በምክንያታዊ ወጣቶች ዙሪያ የተሰጠው ስልጠና የአመለካከት ለውጥ ማምጣት የሚችል መሆኑን ትናገራለች። ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲጠናቀቅ ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንዳለበት በመጥቀስ ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ ወጣቱ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረግ እንዳለበት ታሳስባለች። ለህዳሴ ግድቡ ከተማሪነት ጀምራ እያዋጣች ስትሆን በቀጣይም በማንኛውም መንገድ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን ትገልፃለች።
ወጣት ነግያ ጋዲሴ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፐብሊክ አድምንስትሬሽን የመጀመሪያ አመት ተማሪ ነው። እሱ እንደሚናገረው፤ ‹‹ምክንያታዊ ወጣት ለሰላማዊ ምርጫ›› በሚል የተሰጠው ስልጠና የአመለካከት ለውጥ ያመጣል። ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በሰላም እንዲጠናቀቅ ብዙ ነገሮች ይጠበቃሉ። በተለይ ሰላማዊ እንቅስቃሴዎች እንዲኖሩ ወጣቱ ትኩረት ሰጥቶ መስራት አለበት። ምርጫው ሰላማዊ እንዲሆን እያንዳንዱ ሰው ምርጫው ከመካሄዱ በፊት ሰላማዊ ድባብ የሚፈጥሩ ጉዳዮች ላይ መወያየት ያስፈልጋል። ወጣቱም ምርጫው እስኪጠናቀቅ በጋራና በትብብር ሊሰራ ይገባል። ከምርጫው በኋላ ወጣቱ የህዝብን አብላጫ ድምፅ ያገኘውን አካል በመቀበል አገሪቱ ሰላማዊ ሽግግር እንዲኖራት ማድረግ አለበት። ከተመረጠው ፓርቲ ጎን በመሆን ለአገሪቱ እድገት መስራትም ይጠበቅበታል።
በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ የኢትዮጵያን አቋም ወጣቱ በማህበራዊ ሚዲያ ማሰራጨት እንዳለበት የሚናገረው ወጣት ነግያ፣ ግብፅና ሱዳን በማህበራዊ ሚዲያዎቻቸው የተዛባ መረጃ በመስጠት ጫና ለመፍጠር የሚሞክሩትን ለመቀልበስ ወጣቱ በማህበራዊ ሚዲያ በኩል ዘመቻ ሊያደርግ እንደሚገባ ያስረዳል። በግድቡ ዙሪያ ከመንግስት የሚወጡ መረጃዎችን በመከታተል ማሰራጨትና አቋም መያዝ እንደሚገባም ወጣት ነግያ ይናገራል።
ሌላኛዋ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪ ወጣት ሮዛ አያናው እንደምትናገረው፤ በተለያዩ አገራት ውስጥ በወጣቱ ሀይል ብጥብጥና ሁከቶች ይነሳሉ። ለዚህም በወጣቱ ላይ ስራዎች መሰራት አለባቸው። አገር የሚያፈርሱትም የሚቀጥሉትም ወጣቶች ናቸው። ወጣቱ እየጎለመሰ ሲሄድ አገር ወደ መምራት የሚሸጋገር በመሆኑ ስለ ሰላም ማውራት ያለበት ወጣቱ ነው።
ግጭቶች በተነሱባቸው አካባቢዎች ተሳትፎ የሚያደርጉ ወጣቶች ምክንያታዊ ያልሆኑና በአግባቡ ማገናዘብ የማይችሉ ናቸው። ምክንያታዊ ለመሆንና የፖለቲካ ሀሳቦችን ለመረዳት የግንዛቤ ማስጨበጫዎች አስፈላጊ ናቸው። አብዛኛው ወጣት የፖለቲካ ሀሳቦችን ሳይረዳ የሚነዳበት ሁኔታ ይስተዋላል። የፖለቲካ መሪዎች የሚከተሉትን ርዕዮተ-አለም ማወቅ የግድ ይላል። ሁሉም ብሄሩን ሳይሆን አንድ ያደረገውን አገራዊ ማንነት ብቻ በመመልከት ከእርስ በርስ ግጭት መቆጠብ ያስፈልጋልም ነው የምትለው ወጣት ሮዛ።
እንደ ሮዛ አስተያየት የአገር አንድነትን ለመመለስ ወጣቱ በአንድነት ተባብሮ ሰላም የማምጣት ግዴታ አለበት። በተጨማሪም በምርጫ ወቅት ችግሮች እንዳይፈጠሩ ወጣቱ ላይ መሰራት እንዳለበት ትጠቅሳለች። በታላቁ የህዳሴ ግድብ የወጣቱ ሚና መሆን ያለበት በጉልበትም ሆነ በፋይናንስ የበኩሉን እየተወጣ በማህበራዊ ሚዲያው ደግሞ የኢትዮጵያን አቋም እያንፀባረቀ መንቀሳቀስ አለበት። በየሄዱበት ቦታ ለኢትዮጵያ ይሄን አደርጋለሁ እያሉ ማስተዋወቅ፤ የግድቡን ስራዎች ማስተባበር አለባቸው። አብዛኛው ወጣት ማህበራዊ ሚዲያዎችን የሚጠቀም ሲሆን በማህራዊ ሚዲያዎቹ ስለ ግድቡ መረጃዎችን ማሰራጨት እንደ ግዴታ ሊቆጠር ይገባልም ስትል ትናገራለች።
ወጣት መልካሙ ተስፋ እንደሚናገረው ደግሞ፤ “ምክንያታዊ ወጣት ለሰላማዊ ምርጫ” በሚል የተዘጋጀው ስልጠና ግንዛቤ ከማስጨበጥ ባለፈ ከምክንያታዊነት ጋር የተያያዘ በመሆኑ ለውጥ ያመጣል። አሁን በአገሪቱ እንደሚታየው በምክንያታዊነት አለማሰብ እየሰፋ ነው። አስተሳሰብን ሰፋ አድርጎ አለማስቀመጥን ለመቅረፍ ስራዎች በድፍረት አልተገባባቸውም ነበር። ስልጠናው ቀጣይነት ኖሮት አድማሱን አስፍቶ ክልሎች ድረስ ቢዳረስ ለውጥ ማምጣት ይቻላል። በአስተሳሰብ ደረጃ ሁሉም እኩል እንዲሆን በአገር አቀፍ ደረጃ መሰራት አለበት።
ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በሰላም እንዲጠናቀቅ ለማድረግ ወጣቱ ለሰላም መቆም አለበት የሚለው ወጣት መልካሙ፤ ቀደም ሲል የተካሄዱ ብዙዎቹን ሁነቶች ብንመለከት በሰላም እንጂ በጦርነት የተፈቱ ችግሮች የሉም። በጦርነትና በግጭት የሚገኝ አንዳችም ነገር የለም። በቅርቡ የተፈጠሩ ሁነቶች ቢታዩ ከተገኘው ይልቅ የከሰረው ይበዛል። ስለዚህ ምክንያታዊ ሆኖ መንቀሳቀስ የግድ ሰላም ለማምጣት አስፈላጊ ነው። በዘንድሮውም አገራዊ ምርጫ ሁሉም ይጠቅመኛል የሚለውን ፓርቲ በመምረጥ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለበት ያመለክታል።
እንደ ወጣት መልካሙ አባባል፤ በማህበራዊ ሚዲያ የሚለቀቁ የተዛቡ መረጃዎች ሰዎችን እያገዳደሉ መሆናቸው በብዛት ተስተውሏል። ማህበራዊ ሚዲያን ለበጎ ነገር በመጠቀም ለአገር አንድነት ማዋል ያስፈልጋል። በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ ግብፅ በማኅበራዊ ሚዲያቸው የተሳሳቱ መረጃዎችን እያሰራጩ ጫና መፍጠር ይፈልጋሉ። በኢትዮጵያ ውስጥ ግን በዘር ተከፋፍሎ ሲሟገት የሚውለው ይበረክታል። በማህበራዊ ሚዲያ ወጣቱ ስለ ግድቡ የሚያወራበት መንገድ የለውም። ወጣቱ በነቃ አስተሳሰብ በመራመድ አገሩን መጠበቅ አለበት። ቀደም ብለው የነበሩ ታሪኮችን እንደ መማሪያ በመውሰድ ነገን ማስተካከል ይገባል። ጥሩ ነገሮችን ይዞ ወደ ፊት መራመድ ከወጣቱ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ወጣቶች የሰላም የበጎ ፈቃደኛ ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ዮሀንስ ጣሰው እንደሚናገረው፤ ወጣቶች ምክንያታዊ ከመሆናቸው በፊት ወጣትነት ምን ማለት እንደሆነ ሊረዱት ይገባል። ወጣትነት ትልቅ ሰብዓዊ ሀብት እንደመሆኑ የተለያዩ ውጤታማ ስራዎችን የሚሰራበት የእድሜ ዘመንም ነው። ወጣትነት የማይመለስ፣ የማይካድ እንዲሁም እምቅ አቅም የለም ተብሎ የማይዋሽበት የእድሜ ክልል ነው። ወጣትነት የጉብዝና ወቅት መሆኑን አውቀው ነጋቸውን ዛሬ ላይ የሚሰሩበት እድላቸው መሆኑን ማወቅ አለባቸው። ፖለቲካዊ ጉዳይ ለወጣቱ አንድ ራሱን የቻለ ጉዳይ ነው።
ወጣትነት ሀይልና ብቃትን የያዘ ነገር እንደመሆኑ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ በተለይ በምርጫ በቀጥታ መንገድ ካልመረጡና ካልተመረጡ ነገ ከእነሱ አቅምና ችሎታ ባነሰው ሰው ለመመራት ይገደዳሉ። ይሄ ደግሞ ወደ ግጭት ይመራል። ስለዚህ የሚፈልጉትንና የሚወዱትን አመራርና ፓርቲ ድምፅ በመስጠት መምረጥ አለባቸው። በዚህም ፖለቲካዊ ተሳትፏቸውን ማሳደግ፣ ማህበራዊ መስተጋብራቸውን ማላቅ ከወጣቶች የሚጠበቅ ነው። ቆም ብሎ ማሰብ፣ እርስ በርስ መደማመጥ፣ እነሱ የሚፈልጉት እንዳለ ሌላውም ወጣት የራሱ ፍላጎት እንዳለው መረዳት፤ የውይይት ባህልንም ማዳበር ይገባል። የውይይት ባህል ሲዳብር ሁሉንም ነገር ወደ ጠረጴዛ በማምጣት እልባት እንዲያገኙ ማድረግ ይቻላል። ፍርድ ቤትና ሶስተኛ ወገን ጣልቃ ሳይገባ ለመግባባት በር ይከፍታል። በስድስተኛው ምርጫ ወጣቱ ካርዱን እንጂ ህይወቱን ሊሰጥ አይገባም በማለት ያስረዳል።
እንደ አቶ ዮሀንስ ገለፃ፤ በአገሪቱ የፖለቲካ ህይወት ውስጥ ፍራቻ አለ። ህብረተሰቡም ፖለቲካ ውስጥ መግባትን ስለሚፈራ ወጣቱ የተስተካከለ አመለካከት እንዳይኖረው አድርጓል። በዚህም ፖለቲካ ፓርቲዎች ወጣቱን በቀላሉ እንዲጠቀሙበት አድርጓል። የጥፋት ሀይሎች ለሚፈልጉት የጥፋት አጀንዳ የሚጠቀሙበት ወጣቶች ያላቸውን ብቃትና አቅም ስለሚረዱ ነው። ትልቁ መሰረታዊ ችግር የወጣቱን ያልተመለሱ ጥያቄዎች በመያዝ ፖለቲከኞች እየተጠቀሙበት ይገኛሉ። ለምሳሌ ስራ እጥነትን፣ በሁኔታዎች ተስፋ መቁረጥንና ወጣቱ ነገ እሰራዋለሁ ብሎ የሚያስብበትን መንገድ በቀላሉ እንደሚያገኘው አድርገው የሚያጭበረብሩት ወገኖች አሉ።
የወጣቱን ደካማ ጎኖች በመጠቀም ብጥብጥ እንዲነሳ ሁኔታዎች ይመቻቹለታል። ያልተመለሰ የወጣቱ ፍላጎት እስካለ ድረስ ሁል ጊዜ ግጭት አለ። አንደኛው ፖለቲካ ፓርቲ ከሌላው ፖለቲካ ፓርቲ ጋር ተነጋግሮና ተግባብቶ ለመመለስ መስራት ካልቻለ ጥያቄዎች ወደ ግጭት ሊያመሩ ይችላሉ። ስለዚህ አለመቻቻል በራሱ ግጭት የሚፈጥር ነገር ነው። ዋናው ችግር ፖለቲከኞች በጠረጴዛ ዙሪያ አለማውራታቸው ነው። ወጣቱ በጥቅሙ በኩል ከመጡበት በቀላሉ ወደ ግጭት ሊገባ ይችላል።
በታላቁ የህዳሴ ግድብ ዙሪያ ያሉትን ጉዳዮች ለመመልከት እንዲቻል ቀደም ብሎ የግድቡ ግንባታ በሃሳብ ደረጃ የነበረ ነው። በሁሉም ስርዓት ውስጥ ያለፉ ወጣቶች ስለ ግድቡ ተመሳሳይ የሆነ አላማ አላቸው። አሁንም ያለው ወጣት የግድቡን ጉዳይ በልቡ ያኖረ ነው። በተጨማሪም በተግባር ተሳትፎ እያደረገ የሚገኝ ነው። አሁን ያለውን ወጣት ቀደም ብሎ ከነበረው ወጣት ልዩ የሚያደርገው ሌሎች ሲመኙና ሲያዝኑ የነበሩለትን በቀጥታ ወደ ተግባር ይዞ የገባ በመሆኑ ነው። አሁን ያለው ወጣት የሌሎች አገራትን ዜጎች በአግባቡ እያስተናገደ የሚገኝና የህዳሴ ግድብን በሚመለከት የወጣቱ ተሳትፎ እስከ ፍፃሜው የሚደርስ ሲሆን በግድቡ ግንባታ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት ወጣት ባለሙያዎች እንደመሆናቸው ውጤቱ በቅርቡ እንደሚታይ ያመለክታል።
‹‹በማህበራዊ ሚዲያው በኩል በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ የሚናፈሱ ወሬዎች ወጣቱ ሊቀለብሳቸው ይገባል›› የሚለው አቶ ዮሀንስ፤ ማህበራዊ ሚዲያ ማህበራዊነትን ለማሳደግ እንጂ ለማፍረስ ከመጠቀም መቆጠብ ያስፈልጋል። ሌሎች አገራት ማህበራዊ ሚዲያን ወጣቱ በአግባቡ እንዲጠቀም በማድረግ ወደ አሸናፊነት እየመጡ ናቸው። በማህበራዊ ሚዲያ በኩል ደጋፊ ባለመኖሩ የሚሸነፉ ሰዎች እንዳሉም መታወቅ አለበት። የማህበራዊ ሚዲያው ሀይል በቀላል የሚታይ አደለም። በጣም ከፍተኛ የሆነ ተፅዕኖ የሚያመጣና የሰውን አስተሳሰብ ቀይሮ ወደ ተለያዩ ውሳኔዎች የሚያስኬድ ነው። ሰላም ለማስፈን ወይም ወደ ጦርነት ለማምራት ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑንም ይጠቅሳል።
በአሁን ወቅት ግን ጉዳዩ እኔን እስካልነካኝ ድረስ በምን አገባኝ መንፈስ የሚንቀሳቀሱ አሉ። አሁን ላይ ቆም ብሎ በማሰብ የሚፈጠሩ ጉዳዮች ይመለከቱናል ማለት ይገባል። ያሉትን አማራጮች በመጠቀም የአገሪቱን ስምና መልካም ገፅታ መገንባት ያስፈልጋል። ኢትዮጵያ መነሳት ያለባት በበጎ ጎን ሲሆን በውስጧ የያዘችው እምቅ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ሀብት ጥቅም ላይ እንዲውል መደረግ አለበት። አገሪቱ በአፍሪካ ቀንድ ያላትን ተሰሚነት በመጠቀም ለበጎ ስራዎች እንድታውለው የወጣቱ ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑንም አቶ ዮሀንስ ያብራራል።
መርድ ክፍሉ
አዲስ ዘመን ሰኔ 11/2013