የስብዕና ልህቀትና የአስተሳሰብ ለውጥን በመደበኛ ትምህርት ብቻ ማሳካት አይቻልም። ከመደበኛ ትምህርት በተጨማሪ በህብረተሰቡ የአስተሳሰብ ለውጥ ላይ የሚሰሩ ማዕከላት እገዛ ያስፈልጋል። የጋራ ጥረት ለውጤት ያበቃል። በአስተሳሰብ ለውጥ ላይ የሚሰሩ ሥራዎች ተከታታይነት ከሌላቸው የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣት አያስችልም። ምክንያቱም ደግሞ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ያማከለ መሆን ስላለበት ነው። ሃሳብ የመጀመሪያው የሃብት ምንጭና የአንድ ሀገር ዕድገት መለኪያ ሲሆን ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራበትና ጥቅም ላይ ሊውል ይገባል። አሁን ባለው የዓለም ነባራዊ ሁኔታ በማህበረሰብ ደረጃ ቀናና የበለጸገ አስተሳሰብ ማምጣት ለፍትሃዊ ዕድገት ቁልፍ መሳሪያ በመሆኑ በአስተሳሰብ ላይ ብዙ መስራትና የመወያያ መድረኮችን ማበራከት ያስፈልጋል። ወደ ግለሰብ፣ ቤተሰብና ማህበረሰብ በማውረድ ሁሉም ኃላፊነቱን እንዲወጣ ማድረግም ይገባል።
ድንበር ተሻጋሪ በጎ ፈቃደኝት ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየተለመደ የመጣ ተግባር ነው። ነገር ግን የታሰበውን ያክል ወጣቶች ተሳትፎ እያደረጉበት አለመሆኑ ይነገራል። በተለይ የኮቪድ 19 ወረርሽን ወደ አገሪቱ ከገባ በኋላ ወጣቶች በአካባቢያቸው ተደራጅተው አቅም ለሌላቸው ሰዎች ድጋፍ ማድረግ ጀምረዋል። የተወሰኑት ደግሞ በማህበር በመደራጀት እውቅና አግኝተው ዘላቂ የሆኑ ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛሉ። በጎዳና ላይ የሚገኙ ህፃናትን ማንሳትና አቅም የሌላቸውን ተማሪዎች መርዳት በበጎ ፈቃኞች እየተሰራ ይገኛል። ይህንን ሥራ ማዕከል ከፍተው ድጋፍ የሚያደርጉም እየተበራከቱ ነው። ለዛሬ መነሻውን ኦሳህና ከተማ አድርጎ በተወሰኑ ከተሞች በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኘውን ብርቱ ተስፋ የህፃናት ማዕከልን እንቃኛለን። ከማዕከሉ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ መድህን ስዩም ጋር ቆይታ አድርገናል። መልካም ንባብ።
የማዕከሉ ራዕይ ህልሙ ቅዠት፣ ተስፋው መና የሆነበትን ትውልድ፤ ከጎዳና ማንሳትና ተስፋን በመዝራት ህልምን ማልማት ላይ ያተኮረ ነው። እንደ ተልዕኮ ይዞ የሚንቀሳቀሰው ደግሞ ወላጅ እና አቅም በማጣት ምክንያት የተጎዱ ህጻናትን በመደገፍ ከትምህርት ገበታቸው እንዳይጎሉ ማድረግ፤ ህጻናት ከጎዳና በማንሳት ወደ ቤተሰቦቻቸው መቀላቀል፤ እንዲሁም ቤተሰብ ለሌላቸው ማቆያ ማዘጋጀት፤ አቅመ ደካማ ቤተሰቦችን በመደገፍ ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረግ፤ እንዲሁም በአገሪቱ የመረዳዳትን ባህል ማሳደግን ነው።
የማዕከሉ አመሰራረትና
ያከናወናቸው ተግባራት
ማዕከሉ 2005 ዓ.ም ላይ ሁለት ህፃናትን በመያዝ በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች ክልል ሆሳእና ከተማ ተመሰረተ። ሥራው ሲጀመር የማህበሩ አባላት ገና ተማሪዎች ነበሩ። አጠቃላይ ሥራው በአስራ ሰባት አባላት የተጀመረ ሲሆን በወቅቱ አባቱ በሞት የተለየው አንድ ህፃን እና ከጎዳና ላይ የተገኘ ህፃንን በመያዝ ሥራው ተጀመረ። በአሁኑ ወቅት ህፃናቱ የሶስተኛ ክፍል ተማሪዎች ሆነዋል። ልጆቹ በተደረገላቸው ድጋፍ ትምህርታቸውም ላይ ጎበዞች ለመሆን በቅተዋል። የማዕከሉ እንቅስቃሴ ከዓመት ዓመት እያደገ 2010 ዓ.ም ላይ ከትምህርት ቤት ክበባት ወደ ህጋዊ ማዕከልነት እንዲያድግ ተደረገ።
2010 ዓ.ም ላይ አጠቃላይ ወጪያቸውን በመቻል 35 ህፃናትን መደገፍ ተጀመረ። ልጆቹን በግልና በመንግሥት ትምህርት ቤቶች እንዲማሩ ሥራዎች ተሰርተዋል። በቋሚነት ከሚረዱ ህፃናት ውጪ የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ የሚደረግላቸውም ነበሩ። እነዚህ ህፃናት በመማሪያ ቁሳቁስ እጥረት ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ ለማድረግ ሥራዎች ተከናውነዋል። በማንኛውም ምክንያት ህፃናት ከትምህርት ውጪ ጎዳና ላይ እንዳይውሉ ማዕከሉ አላማ አድርጎ እየሰራ መሆኑም ልዩ ያደርገዋል።
ህፃናት ኑሯቸውን በጎዳና ላይ እንዳያደርጉ ማዕከሉ ጠንክሮ የሰራ ሲሆን ህፃናት ወደ ጎዳና እንዳይወጡ በመከላከልና ጎዳና ላይ የወጡትን ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲመለሱ በማድረግ ረገድ ሥራዎች ተሰርተዋል። ማዕከሉ አገር በቀል እንደመሆኑ ከየአካባቢው ህብረተሰብ ጋር በትብብር ይሰራል። በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባ ከተማ ላይ ማስተባበሪያ ቢሮ ተከፍቶ በአርባ ምንጭ፣ በኦሳእና፣ በሀመር፣ በድሬዳዋ፣ በመተሐራና በቱሉ ቦሎ አካባቢ ተመሳሳይ የበጎነት ሥራ እየተከናወነ ይገኛል። ቀድሞ በተጀመረባቸው አካባቢዎች ማዕከል ተከፍቷል። በማዕከሉ ውስጥ በጎዳና ላይ የሚገኙ ህፃናትን በማንሳት ቤተሰቦቻቸው እስኪገኙ ድረስ ይቆያሉ። ቤተሰባቸው ያልተገኙ ህፃናት ማዕከሉ ውስጥ እንዲኖሩ ይደረጋል።
እስካሁን በማዕከሉ ወደ 2ሺህ 200 ህፃናት እየተደገፉ ይገኛሉ። በቀጣይ ይህን ቁጥር ወደ 10ሺህ ለማሳደግ ይሰራል። በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ ተፈናቃዮችን የመደገፍና የመጎብኘት እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው። የኮቪድ ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ ማዕከላት በሚገኙባቸው አካባቢዎች ከዞን አስተዳደሮች ጋር በመተባበር አራት ወራትን በወሰደ ጊዜ ውስጥ ሙሉ ህፃናት ከጎዳና ላይ ማንሳት ተችሏል። ምንም እንኳን እንቅስቃሴው ውጤት የታየበት ቢሆንም ክፍተቶችም ነበሩበት። በየአካባቢዎቹ የሚታዩትን ችግሮች በተቻለ አቅም ለመቀነስ እንጂ ለማጥፋት ሙሉ አቅም የለም። ሆኖም በትንሽ ጊዜ ውስጥ የህጻናቱን ህይወት መታደግ ተችሏል።
በዚህ ወረርሽኙ ተስፋፍቶ በሚገኝበት ወቅትም ቢሆንም ቀደም ብሎ ከአመለካከትም አንፃር ከባድ ሁኔታዎች ተፈጥረው ነበር። በወቅቱ ሁሉንም ህፃናት በማእከል ውስጥ በማቆየት ጤናቸው እንዲጠበቅና ከማንም ሰው ጋር ንክኪ እንዳይኖራቸው ተደርገዋል። ይህ እንቅስቃሴ ሁለት ጥቅሞች ነበሩት። በጎዳና ላይ የሚገኙ ህፃናት በወረርሽኙ የመያዝ እድላቸው ሰፊ ነው። ወደ ሌላም ሰው የማስተላለፋቸው እድልም በተመሳሳይና ሰፊ ነው። በሁለቱም አቅጣጫ ያለውን ሁኔታ ለመቀነስ ጥረት ተደርጓል።
የማዕከሉ የገቢ ምንጭ መጀመሪያ አካባቢ ጫማ በማፅዳት ሆሳእና ከተማ ውስጥ ይሰራ ነበር። የማዕከሉ መስራች አባላት ቤተሰቦቻቸው ከሚሰጧቸው በማጠራቀም ያዋጡም ነበር። በተጨማሪም አባላቱ ትምህርት በሚማሩበት ወቅት ለትራንስፖርት የሚሰጣቸውን ለእርዳታ ያውሉት ነበር። ከጊዜ በኋላ ወጪዎች እያደጉ ሲመጡ አገር ውስጥ ስፖንሰሮች መጠየቅና ድጋፍ ማድረግ ተጀመረ። በሌላ በኩልም የአባላቱ ቤተሰቦች አስፈላጊውን ድጋፍ ከማድረጋቸውም በላይ ሌሎችም ሰዎች እንዲደግፉ ያደርጉ ነበር። ማዕከሉ የትኩረት አቅጣጫው ባለመልቀቅ ህፃናት ላይ አተኩሮ እየሰራ ሲሆን፤ ‹‹የአገርን ሰው በአገር ልጅ መርዳት›› የሚለውም እንደ መሪ ሀሳብ ተይዞ እየተሰራበት ይገኛል።
ማህበሩ የውጭ ጣልቃ ገብነቶችን የማያስተናግድ ሲሆን ሁሉንም ሥራዎች ያከናወነው ህብረተሰቡን በማስተባበርና ድጋፍ እንዲያደርጉ በማድረግ ነው። የመርዳት ባህል ባለማደጉ እንጂ በሁሉም ሰው ውስጥ የመርዳት ፍላጎት አለ። በጎ ማድረግ ሰፊ ነገር በመሆኑ ለምሳሌ የአረጋውያንን ቤት መጠገን፣ ከአረጋውያን ጋር በዓላትን ማክበር፣ በከተሞች ላይ የፅዳት ሥራ ማከናወን፤ እንዲሁም በሌሎች ሥራዎች ላይ ተሳትፎ እያደረገ ይገኛል።
በአሁኑ ጊዜ ከኬጂ-1 እስከ 1ኛ ክፍል ድረስ በማዕከሉ ስር የትምህርት ቤት አገልግሎት እና በሆሳእና ከተማ ከትምህርት ገበታ በመጉደል የሚመጣውን ጎዳናዊነትን ከመከላከል በተጨማሪ የጎዳና ህጻናትን ከጎዳና በማንሳት የአእምሮው ለውጥ ትምህርት በመስጠት የማቀላቀል እና የማቆየት ሥራ በመስራት ላይ ነው። ይህም እንቅስቃሴ ጅምሩ ጥሩ በሚባል መልኩ ከሆሳእና በስቲያ በአርባ ምንጭ እንዲሁም በድሬዳዋ እየተሰራ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ማስተባበሪያ ቢሮውን አዲስ አበባ በማድረግ ከሆሳእና ከተማ አርባምንጭና ድሬዳዋ በተጨማሪ ቱሉ ቦሎ፣ ቻግኒ፣ ሐመር እና ደሴ እንቅስቃሴ ለማድረግ በዝግጅት ላይም ይገኛል።
የማዕከሉ የህጋዊ ሰውነት ጉዞ ሲታይ ደግሞ ከ2005 ዓ.ም እስከ 2006 ዓ.ም በትምህርት ቤት ክበብነት፤ ከ2007 ዓ.ም እስከ 2009 ዓ.ም በቀበሌ ፈቃድ፤ ከ2010 ዓ.ም እስከ 2011 ዓ.ም በዞን ፈቃድ፤ ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ በፌዴራል ፈቃድ በመንቀሳቀስ ላይ ነው። ይህም ማለት የገንዘብ እንቅስቃሴ እና አስተዳደራዊ ጉዳዮች በወጭ ኦዲተር እንዲሁም የመንግሥት እና በበጎ ፈቃደኛ ተጠሪዎች ክትትልና ግምገማ የሚደረግበት ማዕከል ነው ማለት ነው።
የህብረተሰቡ አቀባበል
የድጋፍ ሥራዎች ከተጀ መሩ በኋላ የህብረተሰቡ አቀባበል ከአካባቢ አካባቢ ይለያያል። ጥሩ እንቅስቃሴ ያለው በአዲስ አበባ ውስጥ ነው። ከአዲስ አበባ ውጪ የግንዛቤ ሥራዎች ያስፈልጋሉ። በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ድጋፍ ለማሰባሰብና ሰውን ለመርዳት ምቹ ያልሆኑ ቦታዎች አሉ። ነገር ግን እንደ አጠቃላይ ሲታይ በሁሉም ቦታዎች እንደ ግለሰብ ድጋፍ የሚያደርጉ ሰዎች በብዛት አሉ። በተጨማሪም ከደመወዛቸው ጭምር በየወሩ የሚያዋጡ ሰዎች አሉ። በመንግሥት ደረጃም ተመሳሳይ ድጋፎች የሚደረጉ ሲሆን በተለይ አመራሮች ባላቸው አቅም ሁሉ ከማዕከሉ ጎን መሆናቸውን አሳይተዋል። በሁሉም ደረጃ ስለ “ድጋፍ” የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች አስፈላጊ መሆናቸው ታምኖበት እየተሰራ ይገኛል።
በማዕከሉ ያጋጠሙ ችግሮች
ገና የበጎ አድራጎት ሥራ ሲጀመር እንቅፋት የሚሆኑ በርካታ ጉዳዮች አሉ። የገንዘብ እጥረት፣ ማህበረሰቡ በራሱ “ለምን እንደዚህ አይነት ስራ ፈታችሁ ትሰራላችሁ?” በማለት አባላቱን መውቀስ፤ እንዲሁም በኮሮና ወረርሽን ወቅት የራስን ጤንነት አጋልጦ ለሌላው መስራት አስቸጋሪ ነበር። ምንም አይነት ጥቅም በማይገኝበት ለምን እራስን አደጋ ላይ ጥሎ መስራት አስፈለገ? የሚሉ አስተያየቶች መኖር፤ በአንዳንድ አካባቢዎች ከመንግሥት አካላት ጋር ጥሩ የሚባል ግንኙነቶች አለመኖር ተጠቃሸ ናቸው። በአዲስ አበባ አካባቢ ድጋፍ ማድረግ የሚበረታታ ሥራ ሲሆን በሌሎች ከተሞች ግን የሚፈለገውን ያህል አይደለም። ከሁሉም አስቸጋሪ የነበረው በህፃናት ህይወት ውስጥ ለውጥ ማምጣት የሚችሉ ሰዎች ፍላጎት አለማሳየታቸው ነው። አቅምና አድል ያላቸው ሰዎች ለተቸገሩ ሰዎች ህይወት መሳካት ሲባል እጃቸውን ቢዘረጉ ሁኔታዎችን መቀየር ይችላሉ።
የማዕከሉ ቀጣይ እቅድ
ማዕከሉ የአጭር፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ እቅዶችን ይዞ እየሰራ የሚገኝ ተቋም ሲሆን፤ የአጭር ጊዜ እቅዱ ለ10ሺህ ህፃናት የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረግ ነው። ማዕከሉ እንቅስቃሴ በሚያደርግባቸው አካባቢዎች ጥናት ተካሂዷል። አሁን ግብዓት የማሰባሰብ ሥራዎች በመከናወን ላይ ናቸው። ይህ ሥራ በ2014 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የሚከናወን ይሆናል። ማንኛውም ተማሪ የመማሪያ ቁሳቁስ አጥቶ ትምህርት እንዳያቋርጥ ታስቦ ነው ሥራው የተጀመረው።
የማዕከሉ የመካከለኛ ጊዜ እቅዱ 2ሺህ 600 ህፃናትን ጠቅልሎ የሚይዝ የማዕከል ግንባታ ማከናወን ነው። ግንባታውን ለማከናወን የቦታ መረጣ ተጠናቆ ወደ ግንባታ ሂደት እየተገባ ይገኛል። የማዕከል ግንባታውን በተመለከተ ሰራተኛና ማህበራዊ ሚኒስቴር ድጋፍ እንደሚያደርግለት ቃል ተገብቷል፤ ይህንኑ ተሞክሮም ወደ በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች በማሻገር በክልሉ የሚገኙ የጎዳና ተዳዳሪ ህፃናትን ለመሰብሰብ እቅድ ተይዟል። ይህ ተግባር በበኩሉ ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረጉ ፍልሰቶችን ይቀንሳል ተብሎ ይታመናል። የማዕከሉ የረጅም ጊዜ እቅድ ደግሞ በአገር አቀፍ ደረጃ በጎዳና ላይ የሚገኙ ህፃናትን ማንሳትና ጎዳና የመንቀሳቀሻ ስፍራ እንጂ የሰው ልጅ መኖሪያ አለመሆኑን በተግባር ለማሳየት መሆኑን ከማእከሉ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
መርድ ክፍሉ
አዲስ ዘመን ሰኔ 11/2013