አለማችን በአየር ንብረት ለውጥ ተፅእኖ የድረሱልን ጥሪ ማሰማት ከጀመረች አመታት ተቆጥረዋል። በቀውሱ ምክንያት የሙቀት መጠኑ በእጅጉ ጨምራል። ግግር በረዶዎች እየቀለጡ ናቸው። የተለያዩ ከተሞች በተደጋጋሚ ጎርፍ እየተጥለቀለቁ ናቸው። ዜጎች በድርቅ ምክንያት የረሃብ ቸነፈር እየገረፋቸው ይገኛል።
የተለያዩ የዘርፉ ምሁራንም የአየር ንብረት ተፅእኖ አለማችን ውድ ዋጋ እንዳስከፈላትና በቀጣይ ጨምሮ እንደሚያስከፍላት በማስረዳት ላይ ተጠምደዋል። አሜሪካዊው ፕሮፌሰር ጃሬድ ዳይመንድ እእአ በ2005 ለንባብ ያበቁት ‹‹Collapse –:How Societies Choose to Fail or Succeed›› የተሰኘ መጽሐፉ ‹‹የተፈጥሮ ሀብቶቻቸውን በተገቢው መንገድ የማይዙና ጥቅም ላይ የማያውሉ ማህበረሰቦች ላልታሰበ ስርአተ ምህዳራዊ አጥፍቶ የመጥፋት አደጋ ይጋለጣሉ›› በማለት፣ ተፈጥሮን መንከባከብና በአግባቡ መጠቀም የህልውና ጉዳይ ስለመሆኑ አፅእኖት ሰጥተውታል።
ስመጥሩ የአፍሪካ ኒውስ ፀኃፊ ኪዚ አስላ፣ ‹‹Climate change is a major threat to global growth›› በሚል ባሰናዳችው ሀተታ፣ እኤአ በ2050 የአየር ንብረት ተፅእኖ 18 በመቶ የአለምን ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት ይነጥቃል፣ የእሲያ ኢኮኖሚ ደግሞ ከፍተኛው ድቀት ያስተናግዳል፣ የቻይና 24 በመቶ፣ የዩናይትድ እስቴትስ 10 በመቶ የአውሮፓውያን 11 በመቶ ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርታቸውን ይነጠቃሉ›› ስትል የቀውሱን አደገኛነት አስረድታለች።
የተለያዩ አለም አቀፍ ጥናቶችም የአየር ንብረት ተፅእኖ በኢኮኖሚ ላይ ከሚያሳድረው ጫና ማሳያዎች መካካል ሚሊየኖችን ከድህነት ጋር ማፋጠጡ ነው›› ይላሉ። በዚህ ረገድ የአለም ባንክ መረጃ፣ በተፅእኖው ምክንያት 132 ሚሊየን በላይ የሚሆኑ ዜጎች እኤአ በ2030 እጅግ አስከፊ ድህነት ውስጥ ሊገቡ እንደሚችሉ ይፋ አድርጓል።
በአየር ንብረት ለውጡ እሳት የበላቸውም ሆነ ቀጣዩ ቀውስ የሚያሰጋቸው የተለያዩ አገራትም የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል ልዩ ትኩረት ሰጥተው መስራትና አጀንዳውን የፖሊሲያቸው አካል አድርገው መንቀሳቀስ ጀምረዋል።
በአሁን ወቅትም ሁሉም በየፊናው የዓለም ስጋት ለሆነው የካርበን ክምችት መፍትሔ የሚለውን እያደረገ ይገኛል። የሚደረጉት ጥረቶች ይበል የሚያሰኙ ቢሆኑም፣ ካለው የካርበን ክምችት አንፃር ግን መሠራት ባለበት መጠን እየተሠራ ላለመሆኑ የዘርፉ ተመራማሪዎች ያስረዳሉ።
‹‹የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ከተፈለገ ከሁሉም በላይ ያለ ዛፍ አይታሰብም›› የሚሉ የዘርፉ ምሁራንም፣ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚደርሱ ጉዳቶችን በመቀነስ ረገድ የደን ሽፋኑን በከፍተኛ መጠን ማሳደግ ግድ እንደሚል ደጋግመው ይናገራሉ።
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለ ላለው ተፅዕኖ በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጭ ናት። ጊዜ እየቆጠረ የሚከሰተው ድርቅ የሚያሳድረውን ጫናም ሆነ የአየር ንብረት ለውጡን የሚቋቋም አቅምም የላትም። የደን ሀብትን ማብዛት የአየር ንብረት ለውጥ እያሳደረ ያለውን ተዕፅኖ ለመቋቋም ዓይነተኛ መፍትሔ ቢሆንም፣ ኢኮኖሚን ለማሳደግም ሆነ አመቺ የአየር ንብረትን ጠብቆ ለማቆየት የጎላ ሚና ያለው የኢትዮጵያ የደን ሀብት፣ ለበርካታ ዓመታት ሲመናመን ቆይቷል።
መጠነኛ የከባቢ አየር ለውጥን መቋቋም የማትችለው ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ቀርፃ ተግባራዊ ማድረግ ከጀመረች ዓመታት አልፈዋል። የደን ጭፍጨፋና መመናመንን መቀልበስና ደኖች የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለመደገፍ እንዲውሉ ለማስቻል ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶታል። የተመናመነ የደን ሀብቷን ከፍ ለማድረግ ዜጎቿን እያስተባበረች በየክረምቱ ችግኝ ትተክላለች።
ከዚህ ቀደም ሕዝቡ በራሱና በየአካባቢው በሚኖሩ መንግስታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ የግብርና ተቋማት አማካይነት የክረምትን ወቅት ተከትሎ ችግኝ የመትከል ልማድ የነበረው ቢሆንም በተለይ ባለፉት ሶስት አመታት፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ አነሳሽነት አረንጓዴ አሻራ ማሳረፍ በሚል ፕሮጀክት በቢሊየኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን የመትከል እንቅስቃሴ እየተካሄደ ይገኛል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩን አረንጓዴ አሻራ ብሄራዊ ጥሪ ሁሉን ገዢ ሃሳብ በመሆኑም በርካቶች ተቀብለው፣ ተቀባብለውታል። በተለይ ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም. በአገር አቀፍ ደረጃ የተከናወነው ‹‹የአረንጓዴ አሻራ ቀን›› ህንድ እ.ኤ.አ. በ2017፣ 1ነጥብ5 ሚሊዮን ዜጎቿን በማስተባበር በአንድ ቀን 66 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል በጊነስ ወርልድ ቡክ ያስመዘገበችው ክብረ ወሰን በኢትዮጵያ እንዲሰበር ያደረገ መሆኑ ይታወሳል።
አፈርን በንፋስም ሆነ በጎርፍ ከመከላት ከመከላከል አንስቶ፣ የአየር ጠባይ ሚዛንን በመጠበቁ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው የሚታመነውን ዛፎች ኅብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ በየአካባቢው ለመትከል የሚደረገው ጥረት ብዙዎችን አንቀሳቅሷል። እስካሁን በአገር አቀፍ ደረጃ የተካሄደው የችግኝ ተከላ መርሃ የፅድቀት ምጣኔም ከ80 በመቶ በላይ ሆኖ ታይቷል።
ኢትዮጵያም የኢኮኖሚ ዕድገቷን በዘላቂነት ለማስቀጠል የምታደርገው ግብ ግብ የተፈጥሮ ሀብትን በአግባቡ ጥቅም ላይ ከማዋል ጋር የተዛመደ ነው። የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂው የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋምና ዝቅተኛ የካርበን ልቀት መጠን እንዲኖር የሚያደርግ አብዮት ነው።
ስትራቴጂው በአንድ ጎን ልማትና ዕድገቷን የሚያፋጥንና ዘላቂነቱን አስተማማኝ የሚያደርግ አካባቢ እንደሚፈጥር ጥናቶች ይጠቁማሉ። ተፈጥሮን ከመንከባከብና ተጠቃሚ ከመሆን በተጨማሪ ለብክለትና ለውድመት ከሚዳርጉ አደጋዎች ጠብቆ ለማቆየት ሁነኛ መፍትሔ ያዘለ ሆኗል።
የተለያዩ የዘርፍ ምሁራን እና ጥናቶች እንደሚያመላክቱትም፣ ኢትዮጵያን ካሏት እምቅ የተፈጥሮ ሀብቶችና የመልሚያ ዕድሎች አንዱ የደን ሀብት ነው። የደን ሀብቶችን መጠበቅ፣ ማልማትና በዕቅድ ጥቅም ላይ ማዋል ኢኮኖሚያዊ፣ ስርዓተ-ምህዳራዊና ማሕበራዊ ጠቀሜታው የጎላ ነው።
የኢንዱስትሪ መስፋፋት፣ የደን መመናመንና የመሳሳሉት ዓለማችንን ለካርቦን ልቀት እየዳረጓት ባለበት በዚህ ዘመን ከዚህ ችግር ለመውጣት ሁነኛው መፍትሔ የችግኝ ተከላ እንደሆነ ነው። የችግኝ ተከላው ፋይዳም የወሰን ጥግ የለውም። ከሰው ልጅ ባለፈም የዱር እንስሳትና አራዊትንም ከመጥፋት ከመታደጉ በተጨማሪ በጎርፍ መጥለቅለቅ፣ የምግብ ዋስትናን ያለማረጋገጥ፣ አካባቢ ተኮር ግጭቶች እና የመሳሰሉ አሉታዊ ሁኔታዎችን የመከላከያ መንገዱ ነው።
የችግኝ ተከላው ከማንም በላይ በደን መመናመን ሳቢያ ክፉኛ እየታመመች ለምትገኘው ኢትዮጵያ ፍቱን መድሃኒት ነው። ደኖች ለአፈርና ውኃ ጥበቃ፣ የካርበን ልቀትን ለመምጠጥ፣ ለብዝኃ ሕይወት፣ ለመሬት ምርታማነትና ለሰው ልጅ ጤንነት፣ ለማኅበራዊ ኢኮኖሚው ከፍተኛ አበርክቶ አላቸው።
ደኖች በኢትዮጵያ አጠቃላይ ኢኮኖሚ ላይ ያላቸውን ጠቀሜታ ዕውን ለማድረግ የተቀረፀው ብሔራዊ የደን ዘርፍ ልማት ፕሮግራምም፣ ደኖችን መልሶ በማልማትና በማስፋፋት የአየር ንብረት ለውጡን ከመቋቋም ጎን ለጎን የሕዝቡን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት እንደሚያረጋግጥ የታመነበት ነው።
ኢትዮጵያ ካላት እምቅ አቅም አንፃር የደን ሃብት ውጤቶችን እዚሁ ማምረት ከፍ ሲልም ወደ ውጪ መላክ ሲገባት በደን ሀብት መመናመን ሳቢያ አገሪቱ የደን ውጤቶች ፍላጎት ማሟላት ስላልቻለች በየአመቱ በብዙ ሚሊዮን ዶላር ወጪ የእንጨት ውጤቶችን ታስገባለች።
ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ኢኮኖሚን ተግባራዊ በማድረግ ሂደት ለአረንጋዴ አሻራ ልዩ ትኩረት መስጠት ታዲያ የደን ውጤቶችን በማምረት የአገር ውስጥ ፍጆታን ከማሟላት ባለፈ ለተለያዩ አገራት እሴት የተጨመረባቸውን የእንጨት እንዲሁም ሌሎች የደን ምርት ውጤቶችን በመላክ የውጭ ምንዛሪ እንድታገኝ ያስችላታል። ከዚህ ተጠቃሚ ለመሆን ግን የዛፍ ችግኞችን መትከልና መንከባከብ ብቻ ሳይሆን የደን አያያዝንና አስተዳደርን በሰለጠነ መንገድ መተግበር ይጠበቃል።
በተፋሰሶች መራቆት፣ የአፈር መሸርሸር ምክንያት በቢሊዮን ቶን አፈር ተጠርጎ እንዳይወጣ፣ የእርሻ ምርታማነት እንዳይቀንስ፤ የወንዞች፣ ሀይቆች፣ ግድቦች በደለል እንዳይሞሉ ለመከላከልም ያስችላታል። እንደ ታንዛኒያ ኬንያ እና ደቡብ አፍሪካ የተፈጥሮ ደንን ዘመናዊ በሆነ መልኩ በማልማት የሳፋሪ/የቱሪስት መዳረሻዎች በማድረግ የውጭ ምንዛሬ እንድታገኝ ያግዛታል።
ኢትዮጵያም የኢኮኖሚ ዕድገቷን በዘላቂነት ለማስቀጠል የምታደርገው ግብ ግብ የተፈጥሮ ሀብትን በአግባቡ ጥቅም ላይ ከማዋል ጋር የተዛመደ እደመሆኑም በተለይ ለደን ልማት የሰጠችው ትኩረት ትልቅ ራእይን ያነገበ ነው። በአራት ዓመት ውስጥ 20 ቢሊዮን ችግኞች የመትከል ዕቅድ አለት።
ዘንድሮም ‹‹ኢትዮጵያን እናልብሳት›› በሚል መርሃ ግብር በአገር አቀፍ ደረጃ 6 ቢሊየን ችግኝ የሚተከል ሲሆን አንድ ቢሊየን ችግኝ ደግሞ ለጎረቤት አገራት ይሰጣል ተብላል። ጅቡቲ፣ ሶማሊያ፣ ኤርትራ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን እና ኬንያ የችግኝ ተቋዳሾች ከሚሆኑት መካከል ይገኙበታል።
ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በቢሊዬን የሚቆጠሩ ችግኞችን በአንድ ጀምበር በመትከል የራሷን አስተዋጾኦ ከማበርከቷም በተጨማሪ እንደ ሀገር ብቻ ሳይሆን ዓለምን ከካርቦን ልቀት ለመታደግ ለተያዘው ዓለም አቀፍ ጥረትም ጉልህ ፋይዳ አበርክታለች።
የተለያዩ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንና ሳይንቲስቶች ኢትዮጵያ ህዝቦቿን በማስተባባር የዓለምን ችግር ለመፍታት የራሷን ድርሻ እየተወጣች መሆኗ ሊያስመሰግናትና አስፈላጊው ድጋፍ ሊቸራት እንደሚገባ በመጠቆም እና በመወትወት ላይ ናቸው። በተለይ ለአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው ምእራባውያን አገራት እንደ ኢትዮጵያ ካሉ አገራት ጋር በቅርበት መስራት የግድ እንደሚላቸው አፅእኖት ሰጥተውታል።
አውጉስቶስ ሳንቶስ ሲልቫ እና ዋርነር ሆየር ‹‹How to ensure a green road ahead for Africa›› በሚል ኒውስ ብሬክ ላይ ባሰፈሩት ሀተታም፣ እ.ኤ.አ. በ2030 የግሪን ሃውስ ጋዝ ልቀት በ 55 በመቶ ልቀትን ለመቀነስ የተስማሙት የአውሮፓ አገራትም፣ እቅዳቸውን ዳር ለማድረስ ከሌሎች አገራት ጋር በቅርበት መስራት እንዳለባቸው አጽእኖት ሰጥተውታል።
በተለይም ከፍተኛ የካርበን መጠን ወደ ከባቢ አየር በመልቀቅ ለአየር ንብረት ተፅእኖ አስተዋፆኦ በመሆን ረገድ 4 በመቶ ድርሻ ብቻ ቢኖራትም በቀውሱ ዋነኛ ገፈጥ ቀማሽ መሆኗ ከሚገለፀው አፍሪካ ጋር ይበልጥ መቀራረብ እና አብሮ መስራት እንደሚያስፈልግ ነው ያሰመሩበት።
ይሕን እሳቤ በርካታ የዘርፉ ምሁራን እና ፀሃፍት ይጋሩታል። ከእነዚህ መካከል አንዷ የሆነችው Tariye Gbadegesi ‹‹A Green Africa Is the Key to a Greener World›› በሚል ርእስ ፎሬን ፖሊሲ ላይ ባሰፈረችው ሰፊ ሃተታ፣ ‹‹ዩናይትድ እስቴትስ የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል ረገድ ከአፍሪካ አገራት ጋር ይበልጥ መተሳሰር ካልቻለች፣ አለም አቀፍ የመሪነት ሚናዋ ከንቱ ይሆናል›› ብላለች።
ድጋፍን ከመጠባበቅ ይልቅ የዓለምን ችግር ለመፍታት የራሷን ድርሻ እየተወጣች የምትገኘው ኢትዮጵያ፣ በመጪው ክረምት ለ‹‹አረንጓዴ አሻራ›› ቀን ታሪካዊ አረንጓዴ አሻራን ለማሳረፍ እጇን ሰብስባለች። ዜጎቿም አሻራቸውን ለራሳቸው፣ ለአገራቸውና ለትውልድ አረንጓዴ ሕይወትና ውበት ለማስተላለፍ የሚችሉበትን መልካም ዕድል ለመቀጠም፣ ችግኝ ለመትከልና የተተከሉትንም ለመንከባበከብ አሰፍስፈዋል።
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ሰኔ 11/2013