ቅድስት ሰለሞን
መንታዎቹ ጉዳዮች መጣሁ መጣሁ እያሉ ነው፤ መምጣታቸው ለአብዛኞቻችን፤ ኸረ እንዲያም ለሁላችንም ማለት ይቻላል ተስፋን ሰንቀው ነው። ከመቼውም በላይ የቀረበው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ሲሆን፣ በሰላም ይጠናቀቅ ዘንድ የብዙዎቻችን ምኞትም ፍላጎት ጭምር ከሆነ ውሎ አድሯል። የመራጮች ምዝገባን የተረጋገጠ ቁጥር የማጣራት ሂደቱን ያጠናቀቀው የምርጫ ቦርድ ለ6ኛው አገራዊ ምርጫ የተመዘገቡ መራጮች ቁጥር 37 ነጥብ 4 ሚሊዮን የሚሆን ህዝብ መሆኑን እንደመግለጹ ይህም ህዝብ ለመምረጥ የሚያስችለውን ካርድ በሁነኛ ቦታ አስቀምጦ የቀኑን መድረስ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል።
ሌላው መንትያ ወንድሙ ደግሞ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ነው። የእስትንፋሳችን ያህል እየተጠነቀቅንለት ያለውና እዚህ ያለበት ደረጃ ያደረስነው የህዳሴ ግድባችን አይን አይኑን ስንመለከት እነሆ አስር ዓመት የደፈነ ሲሆን፣ የተንከባከብነው ግድብ ካደረሰው ፍሬ የምስራቹን ልንቀምስ ይኸው ጊዜው ከመቼውም በላይ ደርሷል፤ ይሁንና ይህን የመጀመሪያውን የምስራች የምንልለትን የሁለቱን ተርባይኖች ኤሌክትሪክ ማመነጨትን እንዳናጣጥም ከአፋችን ሊያስጥሉን በየአገሩ ደጅ የሚጠኑ ግለሰቦች በሏቸው ወይም ደግሞ ተቋማትም ሆኑ አገራትም በሏቸው በርክተዋል። ነገር ግን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ እንዳሉት፤ ያልተነቀነቀ ወንፊት ምርቱን ከግርዱ መለየት አይችልምና ኢትዮጵያም ምንም እንኳ ጎንታይዋ ቢበዛም መነቅነቋ ለጥንካሬ እየሆነ መምጣቱን መሬት ላይ እየታዩ ያሉ እውነታዎች ምስክሮች ናቸው።
ከቀናት በኋላ የሚደረገው ምርጫ 2013 ገና ለገና የማይተገበር መስሏቸው ‹‹እንዴ! ምርጫማ መካሄድ አለበት!›› ሲሉ፤ ምርጫው እንደሚካሄድ መንግስት እርግጠኛ ሆኖ ወደተግባር ሲገባ ደግሞ ‹‹በዚህ ሰዓት እንዴት ምርጫ ማካሄድ ይቻላል!›› በማለት ሲናገሩ የነበሩ አካላት ዛሬ ምርጫው ቀን ተቆርጦለት በጣት የሚቆጠር ቀን እየቀረውም እንኳ ኢትዮጵያ ላይ የሚያሳድሩትን ጫና ይበልጥ እንዲጠነክር ለማድረግ የተለያዩ አጀንዳዎችን በመፈለግ የተጠመዱ ይመስላል። እነዚህ አካላት ግን አንድ ነገር ሳያስገርማቸው የቀረ አይመስለኝም፤ ይኸውም ኢትዮጵያ እነርሱ በቀደዱት ቦይ አለመጉረፏን። በእርግጥም ደግሞ እነርሱ አንዱን ከአንዱ ለማናከስ ‹‹እኔ ነኝ›› ያለ አጀንዳ በየአጋጣሚው ማስቀመጣቸው ቢታወቅም፤ ህዝቡ ግን እንደ እላቂ ቁና ያረጀና የጎደፈውን አጀንዳቸውን አሸቀንጥሮ እየጣለው ዛሬ ላይ ደርሷል።
በእርግጥ የኢትዮጵያ ህዝብ እነርሱ እንደሚያስቡት አይነት አለመሆኑን አለመረዳታቸው እንደዜጋ ያናድዳል። ህዝቡ አዋቂ ነው፤ የቱ ላይ ቢስት ምን ሊከተል እንደሚችል ያውቃል። ያለፈውን የአባቱን ታሪክ አልዘነጋውም፤ በአገሩ ላይ በክፉ ለሚመጣ የትኛውም አካል ለምን የእናቱ ልጅ አይሆንም ጆሮ አይሰጠም፤ የአገሬ ህዝብ ውድቀትን ከሌሎቹ አገሮች አሳምሮ ተምሯል። በምዕራባውያኑም ሆነ በአሜሪካውያኑ ጫና ተደናቅፎ ለመውደቅ በጭራሽ አይሞኝም። ለዚህም ይመስላል ከመቼውም ጊዜ በላይ በአገሩ ጉዳይ ወጥ አቋምን እያሳየ የመጣው። እነርሱ እንደገመቱት በሚነፍሰው ነፋስ አለመገፋቱ፤ በአንደበታቸው አይናገሩት እንጂ ሳያስገርማቸው አልቀረም።
ምርጫና የህዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌት ያልኳቸው መንታ ጉዳዮች አይናቸው እያየ፣ ጆሯቸው እየሰማ በስኬት እንደሚጠናቀቁ እሙን ነው። ምክንያት ብትሉኝ፤ ለነገሩ ‹‹መጠርጠሩስ!›› ትሉኝ እንደሆን እንጂ ምክንያት እንደማትሉኝ እርግጠኛ ነኝ። ምርጫውም በሰላም እንዲጠናቀቅ፤ ግድቡም የታሰበው የውሃ መጠን እንዲሞላ የማይፈልግና የማይመኝ ብሎም የማይጸልይ ወይም ደግሞ ዱኣ የማያደርግ ኢትዮጵያዊ የለም ብዬ ነው። ይህ ቀናነትና የአንድነት መንፈስ ካለ ደግሞ የማናሳካው ነገር አይኖርም።
ይልቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ እንደገለጹት፤ ከቀናት በኋላ በምናካሂደው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ላይ አንድ በጎ ተግባር በመስራት በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ… እንዲሉ አበው እንድንተገብር ነው የዛሬው ዋና ትኩረቴ። ምንና ምን ለምትሉ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ በመስቀል አደባባይ የምረቃ ስነ ስርዓት ላይ እንደተናገሩት፤ ለመምረጥ የተዘጋጀው ህዝብ ወደ 40 ሚሊዮን ነው፤ ይህ ህዝብ ደግሞ እየመረጠ አንድ ችግኝ መትከል ቢችል ሁሌም አስገራሚ የሆኑ ነገሮችን ከወደ ባህር ማዶ ከመስማት ወደማሰማት እንሻገራለን።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህን ሲሉ በሚመሩት ህዝብ ላይ እምነት ስላላቸውም ጭምር ነው። የኢትዮጵያ እድገት የሚያቀጭጫቸው የሚመስላቸው ከባህር ማዶም በሉት በውስጣችንም ያሉ ጥቂቶች ሰላማችን የሚረብሻቸው፤ መስማማታችን የሚያቁነጠንጣቸው አካላት ምርጫ በምናካሂድበትም ቀን ‹‹አንዱ በአንዱ ላይ ይነሳል›› ብለው ሲጠብቁ እኛ ደግሞ በእስካሁኑ የምርጫ ሂደት ላይ ያልተደረገውንና ያልተሞከረውን ይልቁኑ ለአገራችን ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ አህጉራችንም ሆነ ለዓለማችን መልካም የሆነው የችግኝ ተከላውን ጉዳይ አጠንክረን ይዘን ብናሳካው አንድ ተዓምር መፍጠር ቻልን ማለት ነው።
ወዲህ ምርጫው ስኬታማ እንዳይሆን የሚያስቡ ህልመኞችን እናበሳጫቸዋለን፤ ወዲያ ደግሞ ማን ያውቃል ታሪክ እናስመዘግባለን። ከሁሉም በላይ የምንከተለው የሚጠቅመንን ችግኝ ስለሆነ እኛም ሆንን ልጆቻችን ከፍሬው እንበላለን፤ ለተቀረው ዓለምም እናቋድሳለን። እውነት እንነጋገር ከተባለ ይህ ቀላል ተግባር ነው፤ ደግሞም እናደርገዋለን።
ዶክተር ዐብይ እንዳሉት፤ በዚህ ዘመን ያለው ትልውድ ቀደም ሲል እያደረግን እንደመጣን ሁሉ ከቀናት በኋላም ለመምረጥ በምንወጣበት ጊዜ በነፍስ ወከፍ አንድ ችግኝ በመትከል አረንጓዴ ዐሻራችንን ለማሳረፍ እንደማንሰንፍ እርግጠኛ ነኝ። መሪያችን ዶክተር ዐብይ፣ ‹‹ከቀናት በኋላ ኢትዮጵያውያን በ6ኛው ብሔራዊ ምርጫ ድምፃችንን እንሰጣለን። ይህ ምርጫ በአገሪቱ የመጀመሪያ የሚሆን ነጻ እና ፍትሐዊ ምርጫ እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን። መላው ኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ መብቶቻችንን ለማስከበር ወደ ምርጫው በምንሄድበት ወቅት ቀኑን የዜግነት ግዴታችንን በመወጣት የትውልድ ማኅተም ለመተው እንድንጠቀምበት እጠይቃለሁ። በመጪው ሰኞ ውጡና ድምጽ ስጡ። አረንጓዴ ዐሻራችሁንም አስቀምጡ። ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነን ቀኑን ታሪካዊ የዴሞክራሲ ቀን እናድርገው!›› ነው ያሉት።
ታዲያ ምን ገዶን!! መቼም ዕለቱ ሰኞ ነው፤ ከቤት ደግሞ መውጣታችን አይቀርም። እግረ መንገዳችን አንድ ችግኝ ከመሬቱ ጋር በማዋደድ አረንጓዴ ዐሻራችንን ማሳረፍ፤ ብሎም ዴሞክራሲያዊ ቀን መሆኑን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በማሳየት ማረጋገጥ እንችላለን። እኛ ኢትዮጵያውያን እድገታችንና ልማታችን የሚያስቆጫቸው አካላት እንደሚያስቡን ወይም ደግሞ እንዲሆንብን እንደሚመኙት ዱላ ተማዘን የምንደባደብ ህዝቦች አለመሆናችንን ይልቁኑ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለውን ተግባር በማከናወን የዓለምን ህዝብ ለማስደነቅ እንትጋ፤ በዚህም ተግባራችን ለማያውቁን ይህን ያህል ራሷን ለመግለጥ የምትሞክረው ኢትዮጵያ ማነች ብለው ያለፈ ታሪካችንን እንዲመረምሩ፤ የዘነጉን ካሉ ደግሞ እንዲያስታውሱ፤ ደግመን ታሪክ ሰርተን እናስደምማቸው። ስድስተኛውን ምርጫ በዚህ ተግባራችን ዴሞክራሲያዊም ታሪካዊም እናድርገው። ሰላም ይብዛልን!
ቅድስት ሰለሞን
አዲስ ዘመን ሰኔ 11/2013