
በፋንታነሽ ክንዴ –
አስራኤል ጋዛ ሰርጥ በሚገኙ የሀማስ ይዞታዎች ላይ የአየር ጥቃት መፈጸሟን አስታውቃለች። የአየር ጥቃቱ ከጋዛ ሰርጥ ተቀጣጣይ ነገሮችን ይዘው ወደ ግዛቴ ለተለቀቁ ፊኛዎች ምላሽ ነው ማለቷን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ማክሰኞ ጠዋት በርከት ያሉ ፊኛዎች ከጋዛ ወደ አስራኤል ተለቀው በተለያዩ ቦታዎች ላይ የእሳት ቃጠሎ ማስነሳታቸውን የእስራኤል የእሳት አደጋ መከላከያ አገልግሎት አስታውቋል።
ይህን ተከትሎ እስራኤል በወሰደችው እርምጃ ዛሬ ረቡዕ ከንጋት በፊት ጋዛ ከተማ ውስጥ ፍንዳታዎች ሲሰሙ እንደነበር ተዘግቧል።
ባለፈው ግንቦት ወር በሁለቱ ወገኖች መካከል በተካሄደው የ 11 ቀናት ውጊያ በተኩስ አቁም ከተጠናቀቀ በኋላ የተከሰተ የመጀመሪያው ግጭት መሆኑን የቢቢሲ ዘገባ አመልክቷል። ይህ ጥቃት የተፈጸመው ማክሰኞ ዕለት በወረራ ስር ባለችው ምሥራቅ ኢየሩሳሌም ውስጥ አክራሪ አይሁዶች ሰልፍ ካካሄዱ በኋላ ጋዛን ከሚያስተዳድረው ታጣቂ ቡድን ከሀማስ በኩል ማስፈራሪያ መሰንዘሩን ተከትሎ እንደሆነ ታውቋል፡፡
የአስራኤል መከላከያ ኃይል ጥቃቱን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ላይ የጦር ጀቶቹ ካን ዩኒስ እና ጋዛ ከተማ ውስጥ በሀማስ የሚተዳደሩ ወታደራዊ ሰፈሮች ላይ ድብደባ መፈጸሙን አስታውቋል።
መከላከያ ኃይሉ እነዚህ ወታደራዊ ሰፈሮች ኢላማ የሆኑት “የሽብር ተግባራት” ስለሚካሄድባቸው እንደሆነ የገለጸ ሲሆን፤ ከጋዛ ሰርጥ በቀጠለው የሽብር ተግባር ምክንያት ድጋሚ ወደ ጦርነት መግባትን ጨምሮ ተመጣጣኝ የሆነ አጸፋ ለመመለስ ዝግጁ መሆኑን ይፋ አድርጓል።
ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በተፈጸመው የአየር ጥቃት በሰው ህይወት ላይ የደረሰ ጉዳት መኖር አለመኖሩን የሚያመለክት መረጃ አለመኖሩን የቢቢሲ ዘገባ ያመለክታል፡፡
ጥቃቱን ተከትሎ የሀማስ ቃል አቀባይ በትዊተር ገጹ ላይ ባሰፈረው መልዕክት ፍልስጤማውያን መብታቸውንና ኢየሩሳሌም ውስጥ ያሉ ቅዱስ ቦታዎችን ለመከላከል የጀግንነት ተጋድሏቸውን ይቀጥላሉ ብሏል።
የአስራኤል የእሳት አደጋ መከላከያ አገልግሎት በበኩሉ ቀደም ሲል ከጋዛ በኩል የተለቀቁት ተቀጣጣይ ፊኛዎች በደቡባዊ እስራኤል ውስጥ ያሉ ማህበረሰቦች ይዞታ በሆኑ መስኮች ላይ ቢያንስ 20 የእሳት አደጋዎችን ማስከተሉን አስታውቋል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ታጣቂዎች በጋዛ ድንበር ላይ የሚቃጠሉ ነዳጅ እና ፈንጂ መሳሪያዎች የሚሸከሙ ኮንቴነሮችን የያዙ ፊኛዎችን እና ካቶችን በተደጋጋሚ እንደሚልኩ ቢቢሲ በዘገባው አስታውሷል፡፡
መሳሪያዎቹ በእስራኤል ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ የእሳት አደጋዎችን ያስነሱ ሲሆን፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሄክታር ደን እና የእርሻ መሬቶችን እንዲቃጠሉ ማድረጋቸውንም አመልክቷል፡፡
የአየር ድብደባው የቤንጃሚን ኔታንያሁን የ12 ዓመታት የስልጣን ዘመናቸውን እንዲያበቃ በማድረግ ጥምር መንግስት በመመስረት እሁድ እለት ስልጣኑን በተረከበው አዲሱ የእስራኤል መንግስት ስር የተከናወነ የመጀመሪያ እርምጃ መሆኑ ታውቋል፡፡
አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናፍታሊ ቤኔት የእስራኤልን ፖለቲካ በሙሉ የሚያካትት የስምንት ፓርቲዎችን ጥምረት የሚመሩ ሲሆን፣ የቀኝ ክንፍ ብሔርተኛ መሆናቸው ይነገርላቸዋል፡፡
ከሳምንታት በፊት በሁለቱ ወገኖች መካከል ተከስቶ በነበረው ግጭት በጋዛ ከተገደሉት ውስጥ ቢያንስ 128 የሚሆኑት ሰላማዊ ዜጎች መሆናቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በጋዛ ከ16ሺ በላይ ቤቶች፣ 58 ትምህርት ቤቶችና ማሠልጠኛ ማዕከላት፣ ዘጠኝ ሆስፒታሎች፣ 19 ክሊኒኮች እና አስፈላጊ መሠረተ ልማቶች በግጭቱ ወድመዋል ወይም ተጎድተዋል የሚል መረጃ ማውጣቱን ቢቢሲ አስታውሷል፡፡ እስራኤል የወሰደችው የአየር ጥቃት ሁልጊዜም በቋፍ ላይ ያለውን የእስራኤል ሀማስ አለመግባባት እንዳያባብሰው ስጋት መፍጠሩ ታውቋል፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 10/2013