ምህረት ሞገስ
እማማ ውብዓለም አተኩሮ ላያቸው እንደስማቸው ውብ ናቸው። ‹‹ መልከ ጥፉን በስም ይደግፉ›› የሚለው አባባል እማማ ውብዓለምን በፍፁም አይመለከታቸውም። እሳቸው ስያሜን ዓመለወርቅ አስብለው አመለጥፉ እንደሚሆኑት ዓይነት አይደሉም። እንደስማቸው ውብ ብቻ ሳይሆን ልዩ፣ ድንቅ፣ ታይተው እና ተሰምተው የማይጠገቡ … በሚል ብቻ የማይታለፉ ወይዘሮ ናቸው።
አተኩሮ ላያቸው ብቻ አይደለም፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ድንገት ያየቻቸው ሴትም ሆነች የተመለከታቸው ወንድ ሁለቱም ልባቸው መደንገጡ አይቀርም። እማማ ውብዓለምን በተለይ ወንዶች ሲያዩዋቸው ከጥቂቶቹ በስተቀር የብዙዎቹ ልብ ልውጣ እያለ ማንቁርታቸውን ይተናነቃል። ሴትም ብትሆን እንደወንዶቹ ልቧ እስኪሰወር ባትማልልም ለእማማ ውብዓለም መደንገጧ አይቀርም።
መልከ መልካም እና ደርባባዋ እመቤት ፤ ላያቸው በሙሉ የዋህነት የተሞላው ፈገግታቸው ልብ ያቀልጣል። ትንሽ ትልቅ ብለው አያበላልጡም፤ አይንቁም። ሰው ደግሞ ተለምዶ ነውና አረመኔውም ቢሆን፤ ያከበረውን ይወዳል። እማማ ግርማቸው ቢያስፈራም አጎንብሰው የሕፃን ልጅ ቆሻሻ ለመጥረግ አይጠየፉም። ሲበዛ ሥራ ይወዳሉ፤ እርሳቸው ሥራ ወዳድ በመሆናቸው ሌሎችን ሰነፍ እያሉ አያጥላሉም፤ አያጣጥሉም። በሰው ሥራ እየገቡ አቃቂር በማውጣት አይበጣጠሱም። የተለያዩ የተራራቁትን ሁሉ እያቀራረቡ ‹‹ወገኔ ዘመዴ ከመንደርህ አትራቅ፤ አትራራቁ›› እያሉ ያሰባስባሉ፤ ይመክራሉ። ይህ ባህሪያቸው በውበታቸው ላይ ተደርቦ ትንሹም ትልቁም በሩቅም ሆነ በቅርብ ያያቸው ሁሉ እንዲወዳቸው ተገዷል።
አስደሳች ተግባራቸው ተደማምሮ እማማ ውብዓለም ሰው ሳይሆኑ መልዓክ ናቸው ብለው ያመኑ ስለእርሳቸውም የሚከራከሩ ጥቂት አይደሉም። ታዲያ ምን ያደርጋል? ልጆቻቸው በተለይ ግማሾቹ መልክ ብቻ ሳይሆን ግብራቸውም አስቀያሚ ነው። የእማማ ውብዓለም ተቃራኒ ናቸው። ታዲያ ሰዎች የእማማ ውብዓለምን አስቀያሚ ልጆች እያዩ ይህችን የመሰለች ወይዘሮ እነዚህን የመሰሉ አስቀያሚ ልጆች ለምን ወለደች? ብለው ይጠይቃሉ። እንግዲህ ምን ይደረጋል ሁሉም ራሱን የመሰለ አይወልድ!
በእማማ ውብዓለም ፍቅር ተጠምደው ለሊት እና ቀን ስለእሳቸው ብቻ ከሚናገሩ፣ ከሚያስቡ እና ከሚከራከሩት መካከል አቶ ጌታቸው እና አቶ ወልዱ ዋንኞቹ ናቸው። ሁለቱም እማማ ውብዓለምን ከልባቸው ይወዳሉ። ነገር ግን ቅናት አይሉት ምቀኝነት ብቻ ምክንያት ሳይኖራቸው ለገላጋይ የሚያስቸግር ፀብ ለመፍጠር ዳር ዳር ይላሉ። ይሄ አካሄዳቸው የአቶ ጌታቸው እና የአቶ ወልዱን ሚስትና ልጆችም አስጨንቋቸዋል። ያው ‹‹ዝሆኖች ሲጣሉ ሳሩ ይጎዳል› ይባል አይደል። የእነዚህ የእማማ ውብዓለም ወዳጆች መጋጨታቸው ሁለቱንም ቤተሰብ እንዳያጫርስ አስግቷል።
መቼም ከስጋት ማን ያመልጣል? አንዳንዱ ከመሬት ተነስቶ የሥጋት መንፈስ ይፀናወተዋል። ምንም በሌለበት ጭው ባለ ሜዳ ላይ ‹‹አውሬ መጥቷል ›› ብሎ የሚፈረጥጥ አይጠፋም። እኩለ ለሊት ላይ ድመት ጣራ ላይ ስትዘል ‹‹ሌባ ጣራውን ነቅሎ ቤት ገባ›› ብለው እሪታቸውን እንዳቀለጡት የጎረቤታችን ሴት ወይዘሮ ትንሹን ነገር ከትልቅ ጉዳይ ጋር እያዛመደ የሚበረግገው ብዙ ነው። የጎረቤታችን ሴት ወይዘሮ በራቸው ከተንኳኳ መድረሻ ይጠፋቸዋል። እርሳቸውን ‹‹እንደሰረቀ ሰው ለምን ይፈራሉ?›› ብሎ ደፍሮ እውነቱን ፊት ለፊት አውጥቶ ለነገራቸው እና ለጠየቃቸው ፤ደግሞ ‹‹አልፈራሁም›› ለማለት፤ እያፈጠጡ ምን ማለትህ ነው? እያሉ ያጨናንቃሉ። ያው መቼም እውነቱን የሚናገር አይወደድም አይደል። እርሳቸውም አፍጥጠው ፍርሐታቸውን ክደው ጠዋት አልፈራም ብለው ማታ ፍርሐታቸውን በአደባባይ ያሳያሉ።
እማማ ውብዓለም ግን ከኛዋ ጎረቤት ወይዘሮ በእጅጉ ይለያሉ። እውነቱን የሚነግራቸውን ይወዳሉ። ነገር ግን ሰዎች የልጆቻቸውን ነውረኛ ድርጊት ለእርሳቸው ከመንገር ይልቅ ውስጥ ውስጡን ያሟቸዋል። ‹‹ ያው እርሷማ የተለየች ፍጥረት ነበረች። የሰው ነገር የሚጨንቃት፤ ለሰው ኖራ ስለሰው መሞት የምትፈልግ ናት። ምነው ልጆቿ እንደዚህ ከፉ?›› ይባባላሉ። እማማ ውብዓለም ደግሞ ሃሳባቸው ትልቅ ነው። ህልማቸው እርሳቸው ብቻ ሳይሆኑ ጎረቤታቸው ዘመድ አዝማድ ሁሉ እንዲመቸው ነው። ሁሉንም ለማስደሰት ይጥራሉ። ነገር ግን በጉያቸው የያዟቸው ልጆች የእርሳቸውን በጎ ተግባር በተቃራኒው ጥላሸት እንዲቀባ ያደርጋሉ። ስግብግቦች ናቸው፤ ሰው አይወዱም። የሚያስቡት ስለእነርሱ በልቶ ጠግቦ ማደር ብቻ ነው። ነገ የተራበው ጎረቤት ቤታቸውን ሰብሮ እነርሱን አጥፍቶ ያከማቹትን እህል እንደሚዘርፍ አይገምቱም። አንዳንዴ የእማማ ውብዓለም ልጆች አስቀያሚ ተግባር ሰዎች እማማ ውብአለምንም እንዲጠሉ እያደረገ ነው። አንዳንዶች ግን አጥፊ ልጆቿን ትተን እንደእርሷ ያሉ በጎ ልጆቿን እና እርሷን እንመልከት ይላሉ።
እማማ ውብአለም አጥፊዎቹ ልጆች ብቻ ሳይሆኑ የልጅ ልጆቻቸው ሕፃናቶቹ ሳይቀሩ እያጠፉ ሰዎችን እያስቀየሙ ነው። በተቃራኒው ልክ እንደእማማ ውብዓለም መልክ እና ተግባር ከምርጥ ስብዕና ጋር ተዳምሮ የተቸሩ ባይሆኑም ለእማማ ውብዓለም ልፋት ዋጋ የሚሰጡ እንደእማማ ውብዓለም ለሰዎች ለማሰብ የሚሞክሩ ቸር ልጆች እና የልጅ ልጆች ቢኖሩም ሰዎች የሚታዩዋቸው የእማማ ውብዓለም አጥፊ ልጆች እና የልጅ ልጆች ብቻ ናቸው።
ውሎ ሲያድር ምንም እንኳ የእማማ ውብዓለም ውበት ዕድሜ እያጠወለገው ቢቀንስም መልካቸው አልጠፋም፤ ተግባራቸው ደግሞ በየቀኑ የሚፈጥሩት እና የሚሠሩት አዲስ ሥራ ስለእርሳቸው መልካምነት እና ስለተግባራቸው ትልቅነት ለማሰብ ያስገድዳል። ሆኖም ግን ሰዎች የእማማ ውብዓለምን ተግባር እያደነቁ መውደዳቸውን ከመቀጠል ይልቅ፤ በልጆቻቸው አመካኝተው መወነጃጀል እና ማጥላላትን ተግባራቸው አደረጉት።
አቶ ጌታቸው እንደስማቸው ይገለጻሉ። ሁሌም የጌትነት ስሜት ይሰማቸዋል፤ ሲያሻቸው ያደንቃሉ፤ ሲፈልጉ ተገልብጠው ያጣጥላሉ። እንደወጉ ቢሆን ከአቶ ወልዱ ይልቅ አቶ ጌታቸው ለእማማ ውብዓለም የልጅነት ጓደኛ አብሮ አደግና የቅርብ ጎረቤት ናቸው። ‹‹አወቅኩሽ ናቅኩሽ›› በሚል ስሜት ይሁን በሌላ ብቻ በሆነው ባልሆነው የእማማ ውብዓለምን ስም የራሳቸው መድመቂያ የሆኑትን ወይዘሮ እንደቀድሞ በደግ አያነሱም። በየጊዜው በክፋት ማነሳሳታቸውን ደጋግመውታል። አቶ ወልዱ ግን ምንም እንኳ የእማማ ውብዓለም የቅርብ ጎረቤት ባይሆኑም እማማ ውብዓለም ላይ ፊታቸውን አያዞሩም። ‹‹የማምናትና የምወዳት ለሰዎች ባላት ክብር፤ አገር ወዳድ በመሆኗና ተግባሯም ይሄንኑ ስለሚያሳይ ነው።›› ይላሉ።
አቶ ጌታቸው በበኩላቸው ማሳመን የራስን የተሻለ አጀንዳ መያዝ እና ያንን ለማሳወቅ መጣር ብሎ ነገር አያውቁም። እማማ ውብዓለም እንዲወደዱ አያደርጉም። ሥራቸው ማጥላላት እና መናቅ፤ በስሜት ተነድተው ሌላውንም በስሜት ለመንዳት መጣር፤ መገለጫቸው ነው። እሳቸው የሚያስከትለውን አደጋ መገመት አለመቻል፤ የገዛ ወገናቸውን የእማማ ውብዓለምንም ስም ማጥፋት ልምድ አድርገውታል። ልክ እንደ አቶ ጌታቸው አይነትም ብዙዎች ናቸው። ማር የማይጥማቸው፣ አይተው ከማመን ይልቅ ልባቸው የጠቆረ ፣ በክፉ ሃሳብና በጥላቻ የታወሩ ክፉዎች። አንድ ሰው ለእነርሱም ሆነ ለሌሎች ብሎ ምንም ዓይነት መልካም ነገር ቢሠራ አይታያቸውም። መልካሙን ለማየት ያልተፈጠሩ እንደሚባሉት ዓይነት ናቸው።
በሌላ በኩል ከአቶ ጌታቸው ጋር የሚቀራረቡ፤ እኔ ካላመስኩት ተቆልቶ አይበስልም። እኔ ካላቦካሁት ተጠፍጥፎ አይጋገርም። ብለው የሚየምኑ በርካታ ናቸው። እነዚህ ሰዎች ከእነርሱ ውጪ ሌላው ሰው ለአገር እና ለህዝብ ያስባል የሚል እምነት የላቸውም። ሁሌም እውነትን መናገር ዳገታቸው ነው። እውነታውን ለማየት አልታደሉም። ማንንም የሚመዝኑት አይተው ሳይሆን እነርሱ ቀድመው በሚያስቡት ልክ ነው። እውነቱን አይተው ለመምረጥ አይጥሩም። ምርጫቸው እና ቅስቀሳቸው ምክንያታዊ ሳይሆን ስሜታዊነትን የተከተለ ነው።
ደፍሮ ስለስሜታዊነታቸው የሚናገር ከተገኘ ደግሞ የእንደዚህ ዓይነቶቹ የብዙዎች ጠላት ይሆናል። ምክንያቱም ስሜታዊነትን ብዙዎች ይከተሉታል። ይህ በምርጫ ጊዜ ሲሆን ደግሞ አደገኛ ነው። ምርጫ ቀልድ አይደለም። የአገር ቀጣይ ዕጣ ፈንታን መወሰኛ፤ የትውልድ መንገድን ማስመሪያ ነው። ስለዚህ መምረጥ ያለውን እውነት አይቶና አገናዝቦ ነው። መናገር፣ መደገፍም ሆነ መቃወም ከምክንያት ጋር የተቆራኘ መሆን አለበት። ከእውነተኛ ምክንያት ጋር ከተቆራኘ ዛሬ ደጋፊ ነገ ተቃዋሚ የሚኮንበት ዕድል ጠባብ ይሆናል።
እርግጥ ነው! ሁል ጊዜ ደጋፊ ወይም ተቃዋሚ መሆን አይጠበቅም። በምክንያት መደገፍ እና መቃወም ይቻላል። ነገር ግን ትናንት ሲወዱት የነበረን ሰው ያለተጨባጭ እና እውነተኛ ምክንያት ዛሬ ላይ ማውገዝ ጤነኛነት አይመስልም። የሰውየው ጥሩነት መገለጫው እና መመረጫው የያዘው አቅጣጫ መልካም እና አገርን የሚገነባ መሆኑ ነው። በጭፍን መደገፍም ሆነ መቃወም አያዋጣም። አይንና ልብን ከፍቶ ያለውን እውነት ማረጋገጥ የሚገባውን መርጦ መሸለም፤ የማይገባውን ባለመምረጥ መቅጣት ትክክል ነው። ከዚህ ውጪ በቅዠት ውስጥ እየዋዠቁ መብትን በአግባቡ አለመጠቀም መልካም አይደለም።
‹‹በልቶ ሆዱ ያልሞላ ሃሳቡ እና ህልሙ ምግብ ብቻ ነው።›› ይባላል። እንደዚህ ዓይነት ሰው የቀረበው ሁሉ ምግብ ይመስለዋል። የሚያስበው ስለሆድ በመሆኑ፤ ‹‹ ያበላኝ ይሆን›› ብሎ ለሆዱ አድሮ ለአገር ጥቅም ሳይሆን ለእርሱ ሆድ ብቻ ይሠራል ብሎ ያመነበትን መምረጥ ያስተዛዝባል። ስለስብዕና ግንባታ ስለቀጣይ የአገሪቱ ተስፋ እና ስለቀጣዩ ትውልድ ማሰብ ይገባል።
አገር የሚለወጠው በፓርቲዎች አቅጣጫ ብቻ አይደለም። በትጋት የሚሠራ ሰው ቁጥር ከፍ ሲልም ጭምር እንጂ። በእርግጥ በሞያው የተካነ ዜጋ ምርጥ አቅጣጫ ሲቀመጥለት የውስን ግለሰቦች ብቻ ሳይሆን ተደማምሮ የአገር ስኬት ይረጋገጣል። ነገር ግን ከባድ ጥፋቶች ብቁ ነኝ በሚሉ ባለሞያዎች እየተከሰቱ የተወላገደ አቅጣጫ ተቀምጦ መተራመስ ከተፈጠረ፤ አገር ከማደግ ይልቅ ቁልቁል ትወርዳለች። ከላይ ብቻ ሳይሆን ከታችም ያለው ባለሞያ ለህዝብ አስቦ ስለህዝብ ካልሠራ፤ የላይኛው ብርቱ ክብርና ሞገስ የሚገባው ምርጥ የኢትዮጵያ ልጅ ቢሆንም፤ እንደእማማ ውብዓለም ለጊዜው ቢደነቅም፣ እየተሰደበ ያለግብሩ በሌሎች ስሜታዊያን ይገፋል። በተለይ አጥር እያጠሩ አናስገባም ከሚሉና ከሚስገበገቡ እንደ እና እማማ ውብዓለም ልጆች ዓይነት የሚታከሉ ከሆነ የቤታቸውን ጓዳ እና ጎድጓዳ ለሌሎች እያሳዩ የሚንጎዳጎዱ ከበዙ መዘዙ ብዙ ይሆናል። አዎ! እኛም እንዲህ እንላለን ‹‹ከጊዜያዊ የራስ ጥቅም ይልቅ አገር ትቅደም፤ እውነቱን፣ሀቁን ጠልቀን ለማየት ልባችንን ፣ ዓይናችንን እንክፈት። ሰላም!
አዲስ ዘመን ሰኔ 10/2013