ዘንድሮ በተለይም ካለፉት ሁለት ወራት ጀምሮ በሀገሪቷ የሚገኙ የወተት ላሞች የነጠፉ በሚመስል መልኩ ከፍተኛ የወተት እጥረት ተከስቶ ሰንብቷል። ግብርና ሚኒስቴርም ለእጥረቱ ምክንያት የሚታለቡ ላሞች ቁጥር ማነስ መሆኑን ይጠቅሳል። በዋነኛነትም በወተት ልማቱ አርሶ አደሩ ተደራጅቶና ጠንካራ አቅም ፈጥሮ በስፋት አለመግባቱን በምክንያትነት ያነሳል።አነስተኛ ቁጥር ያላቸው አርሶ አደሮች በቁጥቁጥ አነስተኛ መጠን ያለው ወተት በማቅረባቸው ችግሩ መፈጠሩን ነው የሚያስረዳው። በወተት ልማቱ ያሉት ባለሃብቶችም ከሁለት በመቶ የሚበልጡ አይደሉም። በዚያ ላይ ደግሞ የከብት መኖ እጥረትና የዋጋ ውድነት ለወተት እጥረቱ ተጠቃሽ ምክንያት ሆኗል።
የመኖ እጥረት የተከሰተውም እንደ ሰሊጥና ኑግ የመሳሰሉ የቅባት እህሎችም ሆኑ ለዱቄት ፋብሪካ ግብዓት የሚሆኑ ስንዴና አጃ በጥሪያቸው ወደ ውጭ ሀገር በመላካቸው ምክንያት ፋብሪካዎች ለመኖ የሚውል ተረፈ ምርት ሊያቀርቡ አልቻሉም። በተዘዋዋሪም ሆነ በቀጥታ ለወተት ልማት መስፋት ህልውና የሆኑ ግብዓቶች ላይ እስከ ሦስት ደረጃ የተጣለው ቀረጥ አለመነሳትም ሌላው ምክንያት ሆኖ ይጠቀሳል። ነጋዴውና ተጠቃሚው ወተት በሞኖፖል ከአርሶ አደሩ ቀጥታ እንዲወስድ መደረጉና በዚህም ምክንያት ለዋነኛው ተጠቃሚና ለአከፋፋይ ለነጋዴ ተደራሽ ያለመሆኑ በቅሬታ ይቀርባል። ያልተገባ ጥቅም ፈላጊ በሆኑ ነጋዴዎች የተፈጠረ ደባ እንደሆነም ይነገራል። ይህም የመንግስት ቁጥጥርና ክትትል ማነስ ውጤት መሆኑን ይጠቁማል።
የዋጋው መናር ከእጥረቱ በላይ አሻቅቦ ከርሟል። መውጣት እንጂ መውረድ ፈፅሞ የሚታሰብ አይመስልም። እጥረቱ በዚህ በያዝነው በሰኔ ወር ትንሽ የተሻሻለ ቢመስልም ዋጋው ግን ዛሬም ዕለት ከዕለት ከማሻቀብ አልተመለሰም።ባሳለፍነው ግንቦት ወር ከፍተኛ የወተት እጥረት ተከስቷል በመባሉ አዲስ አበባ ላይ ግማሽ ሊትር የላስቲክ ወተት በተለያዩ መደብሮች ከ20 እስከ 25 ብር እየገዙ ለተጠቃሚው ሕብረተሰብ ከ20 እስከ 35 ብር ይሸጣሉ። በዚያው ልክ በተለይም ካፍቴሪያዎች አንድ ስኒ ወተት በተጋነነ ዋጋ በመሸጥ ላይ ይገኛሉ።
‹‹ባለፈው ወር በየሱቁና በየሱፐር ማርኬቱ ወተት አናገኝም ነበር። መች መጥቶ መች እንደሚያልቅ ባይታወቅም ማልደን ብንወጣም አልቋል ነው የምንባለው›› ሲሉ አስተያየታቸውን ከሰጡን ተጠቃሚዎች መካከል ግቢ ገብርኤል ቤተክርስቲን አጠገብ ከሚገኘው የወተት ማከፋፈያ ሲገበያዩ ያገኘናቸው ወይዘሮ ሻሼ ዳባ አንዷ ናቸው። ወይዘሮዋ ወተት የሚፈልጉት የልብ ድካም ስላለባቸውና ለዚሁ በሽታ ሐኪም ወተት እንዲጠጡ ስለታዘዙና የአንድ ዓመት ህጻን ልጃቸውም ወተት በቋሚነት የሚያስፈልጋት በመሆኑ ወተት ለመግዛት ይገደዳሉ ። ይሁን እንጂ በተለይ በግንቦት ወር ወተቱን እንደ ልብ ቀርቶ አንድ ቀን እንኳን ማግኘት ባለመቻላቸው ሲቸገሩ ከርመዋል ።
ሆኖም ሰኔ ወር አቅርቦቱ ተሻሽሏል። በግል ማከፋፈያዎችና በአንዳንድ መደብሮች መታየት ጀምሯል። ዋጋው ግን ከአስራ አምስት ብር ተነስቶ 22 ብር በመድረሱ በየቀኑ ገዝቶ ለመጠቀም እጅግ ችግር ሆኖባቸዋል። በየዕለቱ ወተት ለልጃቸው ማቅረብ አስፈላጊ ቢሆንም ከዋጋው መወደድና ከአቅማቸው ጋር ተያይዞ ስላልሆነላቸው አንዳንዴ ብቻ ወተት ለመግዛት መገደዳቸውን ይናገራሉ።
ሌላው አባድር ሱፐር ማርኬት ግማሽ ሌትር ወተት ሲገዙ ያገኘናቸው የቀድሞ ወታደር አስማረ ዘውዴ እንደሰጡን አስተያየት ዕድሜያቸው ቢገፋም የጉልበት ሥራ በመሥራት ይተዳደራሉ። በሚያገኙት ገንዘብም ገዝተው የሚመገቡት ወተት በዳቦ መሆኑን ይናገራሉ። ወተት አዘውትረው የሚጠቀሙት የጨጓራ ህመም ስላለባቸው ጭምር ነው። ጠቀም ያለ ሥራ ካገኙ ከራሳቸው አልፎ ለልጅ ልጆቻቸውም ወተት ገዝተው የሚገቡበት ጊዜ አለ። ባለፉት ሳምንታት ግን ወተት በየመደብሩ ስላልነበረ ከተለመደው አመጋገባቸው እርቀዋል ። ‹‹በገበያ ላይ ለወተት መጥፋት መንስኤው የመኖ እጥረት ነው›› የሚለውን ምክንያት አይቀበሉትም። ሁከት ፈጣሪዎች መንግሥትና ሕብረተሰቡን ለማጨናነቅ የፈጠሩት ደባ ነው ባይ ናቸው። አሁን ላይ አቅርቦቱ ቢሻሻልም የዋጋው ውድነት ከአቅማቸው በላይ መሆኑም ከሌላው የኑሮ ውድነት ጋር ተያይዞ ምሬታቸውን አባብሶታል ።
‹‹ የሥራዬ ቦታ አራት ኪሎ አካባቢ በመሆኑና ማልጄ ከቤት ስለምወጣ ሻይ አልጠጣም። ቁርስ የምጠቀመው በአካባቢው ያሉ ካፌዎች ነው ›› ያሉን አቶ ዩሱፍ ኑር ከዚህ በፊት በ15 ብር ይጠጡት የነበረውን አንድ ስኒ ወተት ዛሬ 24 ብር ለመጠጣት መገደዳቸውን ነግረውናል። ዋጋው ቀነስ ባለበት ካፍቴሪያ ሄደው እንደሚጠቀሙ የነገሩኝ ደግሞ አንድ ስኒ ወተት በ22 ብር ሲጠጡ ያገኘናቸው አቶ መንግስቱ ስሜ ናቸው።
የአሜንና የቅድስተ ማርያም ካፌ ባለቤቶች በየፊናቸው እንዳሉን ካፌያቸው ወተትን ከማክያቶና በሻይ መልክ ብቻውን ከመሸጥ አንስቶ ለኬክና ጣፋጭ ምግቦች መሥሪያ ይፈልገዋል። ሆኖም አሁንም እጥረት በመኖሩ ሥራውን ማካሄድ እየተቸገሩ ነው። ግንቦት ላይ ደንበኞች ወተት ጠይቀው ብዙ ጊዜ አያገኙም። በመጥፋቱ ካፌያቸው ሊዘጋ የደረሰበትም ጊዜ እንደነበር ይናገራሉ። አሁን ላይ አቅርቦቱ ቢሻሻልም ቀድሞ ከማማ አከፋፋዮች 30 ብር ይገዙት የነበረውን አንድ ሊትር ወተት አሁን ላይ 42 ብር ለመግዛት ተገድደዋል። እሱ ደግሞ አንድ ስኒ የሻይ ወተት 24 ብር በመሸጥ ላይ ናቸው።ከዚህ በላይ ጭማሪ ማድረግ ህዝብን ማማረር ይሆናል በሚል አነስተኛ ትርፍ እያገኙ ለመነገድ መገደዳቸውን ይናገራሉ። በአሁኑ ወቅት ግን ሁሉም ነገር የዋጋ ጭማሪ እያስከተለና የኑሮ ውድነቱ ሽቅብ እየወጣ በመሆኑ ነግዶ ማደር አስቸጋሪ እየሆነ መሆኑን ይጠቅሳሉ።
‹‹በማያባራው የኑሮ ውድነት ሁሉም ተያይዞ ሊያልቅ ነው። በተለይ አማራጭ የሌለው ተጠቃሚ ያሳዝነኛል›› ያሉን በአባድር ሱፐርማርኬት በሱፐርቫይዘር የሚሰሩት ወይዘሮ ዘይኔባ ሀሰን የወተት እጥረትና ውድነቱ መንግስት ቁጥጥርና ክትትል ባለማድረጉ የመጣ ነው ሲሉ ግምታቸውን ይናገራሉ ።
የማማ ወተትም ሆነ አብዛኞቹ ሌሎቹ የሚመጡት ከአዲስ አበባ 130 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከምትገኘው ደብረብርሃን ከተማ መሆኑን ያስታወሱት ሱፐርቫይዘሯ እጥረቱ የተከሰተው ደብረብርሃን ላይ ያለ የአንድ ግዙፍ ካምፓኒ ባለቤት ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በኤጀንቶች አማካኝነት የሚከፋፈለውን ወተት በሙሉ ስለተቆጣጠረው እንደሆነም ይናገራሉ። ለእነሱ የሚያከፋፍሏቸው ባለ ፋብሪካዎችና ወኪሎች ከደብረ ብርሃን አርሶ አደሩ ያቀረበውን ወተት በዱቤ ገዝተው ያቀርቡላቸውና ብሩን ከእነሱ ከተቀበሉ በኋላ ይከፍሉ እንደነበርም ያስታውሳሉ። ሆኖም ባለካምፓኒው ጥሬ ገንዘብ ከፍሎ ሁሉንም በመውሰዱ እጥረቱ መከሰቱንም ይጠቅሳሉ።
እንደ ሱፐርቫይዘሯ ገለጻ እጥረቱ ከመከሰቱ በፊት በየቀኑ ከ200 እስከ 300 ሊትር የማማ ወተት ይቀርብላቸው ነበር። አሁን በሳምንት ሁለቴ 50 ሊትር እንኳን አያገኙም። አቅርቦት የሌለበትም ቀን ብዙ ነው። በዚህም ደንበኞቻቸው እየተመለሱ ነው። ቀድሞ እሳቸው ለህፃን ልጆቻቸው የላስቲክ ወተት ያጠጡ ነበር። አሁን ግን እጥረት በመኖሩ ስላልቻሉ የቆርቆሮ ዱቄት ወተት ለማጠጣት ተገድደዋል። ‹‹እኔ አማራጭ ስላለኝ ለልጄ የቆርቆሮ ወተት ባጠጣም አማራጭ የሌላቸው ለልጆቻቸው ምን ያጠጣሉ ?›› ሲሉም ይጠይቃሉ። ‹‹ውድነቱም ከእጥረቱ ጋር ተያይዞ የመጣነው›› ይላሉ።
ከዚህ ቀደም 15 ብር ሲሸጥ የነበረ ግማሽ ሊትር ወተት አሁን ላይ 22 ብር መሸጡም አማራጭ ለሌላቸው ተጠቃሚዎች ሌላ ፈተና መሆኑንም ይጠቅሳሉ።ልጅ አዝለው መጥተው ሳንቲም ሲጎላቸው ለሚደነግጡ ተጠቃሚዎች ከኪሳቸው የሚሞሉበትም ጊዜ እንዳለም ይናገራሉ። አቅርቦት እጥረት በመኖሩ አንድ ሊትር ወተት 50 ብር እናደርጋለን የሚሉ እንዳሉም መታዘብ ችለዋል።
ፋብሪካ 500 ሺ የነበረው ወርሀዊ ገቢው አሁን ላይ ወደ 150 ሺህ ብር ማሽቆልቆሉንና የእሳቸው ሱፐር ማርኬትም እጥረት ሲኖር ችዝ፣ ሞዜረላ፣ ፍሌቨር፣ እርጎና ሌሎች አቅርቦቶችን ስለሚነካ ገቢያቸው ወጪያቸውን መሸፈን እያቃተው መምጣቱንና መንግሥት ይሄን ችግር ተገንዝቦ በወተት ገበያው ጠንካራ ቁጥጥርና ክትትል ከማድረግ ጀምሮ እርምጃ እንዲወስድ ይጠይቃሉ።
በሰሜን ሸዋ ዞን አንጎለላ ወረዳ ነዋሪው አርሶ አደር ጫኔ ወንድምአገኘሁ እንደሚሉት ከእርሻ ሥራቸው ጎን ለጎን ባሏቸው የወተት ላሞች ኑሯቸውን ይደጉማሉ። ከሁለት ዓመት በፊት በተለይ በጾም ወራቶች ያመርቱት የነበረው ወተት እስከ መደፋት ይደርስ ነበር። ከሁለት ዓመት ጀምሮ ግን የጾም ቀናቶችን ጨምሮ እቤታቸው ድረስ እየመጡ የሚረከቧቸው በማግኘታቸው ምርታቸው መባከኑ ቀርቷል።ዳጎስ ያለ ገቢም እያገኙበት ነው። በቅርቡም ከአካባቢው አርሶ አደሮች ጋር በመመካከር ሰብሰብ ብለው በመደራጀት ምርታቸውን ወደ ደብረብርሃን ከተማ በመውሰድ ግዙፍ የወተት ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች ለማቅረብ ሀሳብ አላቸው። ወደፊት ትልቅ መኪና በመግዛትም ከደብረ ብርሃን 130 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ለምትገኘውና ወተት በይበልጥ ለሚፈለግባት አዲስ አበባ ነዋሪዎች የማቅረብ የረጅም ጊዜ ዕቅድ እንዳላቸውም ነግረውናል። ዞኑ ለምለም በመሆኑ ሣር ቢጠቀሙም የከብት መኖ ውድነት መኖሩን ግን ሳይገልጹ አላለፉም ።
በግብርና ሚኒስቴር የወተት ሀብት ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አስመላሽ በርሄ እንደነገሩን በኢትዮጵያ ካሉት 61 ሚሊዮን ከብቶች ውስጥ 20 ሚሊዮኑ በአርሶ አደሩ የተያዙ ከብቶች ናቸው። ታላቢዎቹ ከብቶች ከሰባት ሚሊዮን አይበልጡም። ከእነዚህም መካከል አንድ ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮኑ ብቻ ወተት ይሰጣሉ። ከዚህም እንደ ሀገር በዓመት አራት ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ሊትር ወተት ይመረታል። ከሚመረተው 98 በመቶው ከአነስተኛ አርሶ አደር የሚሰበሰብ ነው። በወተት ልማት ላይ የተሰማሩት ባለሀብቶች ሁለት በመቶ ብቻ ናቸው። ይሄ ለእጥረቱ አንዱ መንስኤ ነው።
እንደ ዳይሬክተሩ ሁለተኛው ለእጥረቱ ምክንያት የሆነው ጉዳይ የከብት መኖ እጥረት ነው።ደላቢ ከብቶችና የወተት ላም በተለይ የመኖ ፍጆታቸው ከፍተኛ ነው።የመኖ እጥረቱ ሊከሰት የቻለው እንደ ሰሊጥና ኑግ እንዲሁም ስንዴ ያሉት ግብዓቶች በጥሬው ወደ ውጪ በመላካቸው ነው። በዚህ የተነሳ ለመኖነት የሚውለው ተረፈ ምርት በሀገር ውስጥ ሊመረት አልቻለም።በመሆኑም ሀገር ውስጥ አቀነባብረው ወደ ውጭ የሚልኩትና ተረፈ ምርቱን ለከብት መኖ የሚያቀርቡ ጥቂት ፋብሪካዎች ቢኖሩም ተጠቃሚው ብዙ በመሆኑ መኖው ተደራሽ መሆን ባለመቻሉ እጥረቱ ተከስቷል።
ሦስተኛው እነዚህ ተረፈ ምርታቸው ለመኖ አገልግሎት ሊውል የሚገባው ግን ደግሞ በጥሬው ወደ ውጭ የሚላኩ ግብዓቶች ለመላክ በሚያደርጉት ሂደት ቀድሞ በነበረው አሰራር በሦስት ደረጃ ቀረጥ ይጣልባቸዋል። የዚህ ቀረጥ ጫና ደግሞ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መጨረሻ ላይ በወተት ምርቱ ላይ ያርፋል።ከሚመረተው ወተት ከሚገኘው ትርፍ 80 በመቶው ለመኖ በሚውል ወጪ የሚሸፈንበት ሆኗል።
ዳይሬክተሩ መፍትሄውን አስመልክተው የዋጋ ውድነቱንና የአቅርቦቱን ችግር መቅረፍ የሚቻለው አርሶ አደሩ በማህበር ተደራጅቶ በሰፊው ወደ ማምረት እንዲገባ በማድረግ ነው።ለገበያም በዚህ መልኩ ማቅረብ ይጠበቅበታል። የተሻሻሉ የወተት ላሞችን መያዝ መቻል አለበት። መንግሥት በበኩሉ ቀረጥ ማንሳትና ጠንከር ያለ ቁጥጥርና ክትትል ማድረግ አለበት። የሚበረታታበት ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ ምርትና ምርታማነቱን በማሳደግ ከሀገር አልፎ ወተት ወደ ውጪ መላክ ይችላል።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሰኔ 10/2013