አንተነህ ቸሬ
ገና በታዳጊነታቸው የጀመሩት ሰዎችን የመርዳት ተግባራቸው እስከሕይወታቸው ፍፃሜ ድረስ አብሯቸው ዘልቋል። 60 ዓመታትን ያስቆጠረው የበጎ አድራጎት ሥራቸው ከ250ሺ የሚበልጡ ዜጎችን የትምህርት፣ የጤናና የሰብዓዊ ድጋፍ እድል እንዲያገኙ አድርጓል። ብዙዎችን ባስደነገጠና ባስገረመ መልኩ ከአፄ ኃይለሥላሴ መኪና ስር ወድቀው የተቸገሩ ልጆች የሚማሩበት ትምህርት ቤት የሚገነባበት ቦታ እንዲሰጣቸው የጠየቁ ቆራጥ ሰው ናቸው። ሕይወታቸውን ሁሉ ለሌሎች አሳልፈው የሰጡ ታላቅ የአገር ባለውለታ ናቸው። ተማሪዎቻቸውና የሚያውቋቸው ሁሉ ‹‹ጋሽዬ›› እያሉ ይጠሯቸዋል … ታላቁ የበጎ አድራጎት ሰው አቶ አስፋው የምሩ!
አስፋው የተወለደው በ1925 ዓ.ም በቀድሞው ሸዋ ጠቅላይ ግዛት፣ ቡልጋ በተባለ አካባቢ ነው። ከአዲስ አበባ 120 ኪሎ ሜትር ከምትርቀው የትውልድ መንደሩ በእግር ተጉዞ ወደ አዲስ አበባ ሲመጣ ገና ታዳጊ ነበር። በኪሱ የያዘው ገንዘብ ደግሞ ሃምሳ ሳንቲም ብቻ! አዲስ አበባ እንደደረሰ አራዳ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ደጀ ሰላም ውስጥ ማደር ጀመረ። የዕለት ጉርሱን ለማግኘትም ደጀ ሰላም በር ላይ ምፅዋት ለመነ … ሌሎች ሥራዎችንም ሞከረ …
ከአንድ ዓመት በኋላ መልካም አጋጣሚ ተፈጥሮለት ከባለፀጋ ቤት በአገልጋይነት ተቀጠረ። ሥራውን እየሰራ በትርፍ ጊዜው እንዲማር ጠይቆ ተፈቀደለት። በትምህርቱ ያስመዘገበው ውጤትም አስፋው የብሩህ አእምሮ ባለቤት መሆኑን የሚመሰክር ነበር። የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በአጭር ጊዜ ከማጠናቀቁም በላይ፣ የስምንተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤቱ በጣም ከፍተኛ በመሆኑ በጀኔራል ዊንጌት ትምህርት ቤት የነፃ ትምህርት እድል አገኘ።
አስፋው ሁል ጊዜም አካባቢውን መቃኘት ይወድ ስለነበር በትምህርት ቤቱ አካባቢ አንድ ለየት ያለ ነገር አስተዋለ። እርሱ ከሚማርበት ትምህርት ቤት ውስጥ ከተማሪዎች የሚተርፈው ምግብ ሲቃጠልና ጉድጓድ ውስጥ ሲቀበር ተመለከተ። በሌላ አቅጣጫ ደግሞ በቅርብ ከሚገኝ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ብዙ ችግረኞች ምግብ ሲለምኑ አስተዋለ። ከትውልድ ቀዬው አዲስ አበባ እንደገባ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ያሳለፈው አጠቃላይ የጎዳና ሕይወቱ ትዝ አለው። አስፋው ሁኔታውን አመዛዝኖ በቀጥታ ወደ ትምህርት ቤቱ አስተዳዳሪ ሄዶ ትርፍራፊውን ምግብ እየሰበሰበ ምግብ ለሚለምኑት ልጆች ለመስጠት እንዲፈቀድለት ጠየቃቸው። አስተዳዳሪውም ፈቀዱለት። ከዚያ ቀን በኋላ ትርፍራፊውን ምግብ እየሰበሰበ ማደል ጀመረ።
ይሁን እንጂ ይህ ተግባሩ ብቻውን አላረካውም። የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች ከተመገቡ በኋላ ችግረኞች በግቢው ውስጥ የተለየ ቦታ ተዘጋጅቶላቸው የሚመገቡበት ሁኔታ እንዲመቻችላቸው የትምህርት ቤቱን አስተዳዳሪ ጠየቀ። አስተዳዳሪውም በሃሳቡ በመገረም ጥያቄውን ተቀበሉት። ችግረኞቹም መታወቂያ ተዘጋጅቶላቸው በሥርዓት ይመገቡ ጀመር።
የምግብ ችግራቸው የተቃለለላቸውና በድርጊቱም የተደነቁትና የተደሰቱት ልጆች በትርፍ ጊዜው እንዲያስተምራቸው ጠየቁት። ያልጠበቀው ጥያቄ ስለነበር ከትምህርት ቤት ጓደኞቹ ጋር ከተመካከረ በኋላ እርሱና ጓደኞቹ በጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን ግቢ ውስጥ በዛፍ ጥላ ሥር የማስተማር ሥራቸውን ጀመሩ። የሚሰጠው ትምህርት የተጀመረው በዚህ መልክ ነበር። አስፋው ይህንን ሁሉ ተግባር ሲያከናውን እርሱ ገና 9ኛ ክፍል ነበር። የአስፋው ጓደኞች ‹‹ከትምህርታችን ጋር እየተጋጨብን ነው … ጊዜያችንን እየተሻማብን ነው …›› ብለው ከማስተማሩ ሥራ አፈገፈጉ። ሰዎችን መርዳት ሰዋዊ ባህርይው የነበረው አስፋው ግን ወጣቶቹን ማስተማሩን ቀጠለ። በዚህም ምግባቸው የተማሪዎች ትርፍራፊ፣ መማሪያቸው የዛፍ ጥላ ሥር፣ አዳራቸው የአብያተ ክርስቲያን ታዛዎችና የመቃብር ስፍራዎች የሆኑ ወጣቶች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጨመረ።
አስፋው አሁንም ሌላ ችግር ገጠመው። ወጣቶቹን ሰብስቦ የሚያስተምርበት ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪዎች ሌላ አማራጭ እንዲፈልግ ነገሩት። አስፋው ብዙ አሰበ … ከብዙ ማሰላሰል በኋላ አንድ ሃሳብ መጣለት። ሃሳቡንም ለጓደኞቹ አካፈላቸው። ጓደኞቹ ግን ሃሳቡ የማይሞከር እንደሆነ ከመናገር አልፈው አንበሳውን አክላለሁ ብላ ተነፋፍታ ስለሞተችው እንቁራሪት እየተረቱ ቀለዱበት።
አስፋውን በቅርበት አውቃቸዋለሁ የሚሉ ሰው በፃፉት ማስታወሻቸው ላይ እንዲህ ብለዋል፡-
‹‹ … አስፋው የጓደኞቹን ተረት ወደ ጎን ትቶ ደብዳቤውን ጽፎ ላከ። ነገር ግን ለብዙ ጊዜ መልስ ሳያገኝ ቀረ። ከዕለታት በአንዱ ቀን የደብዳቤው ምላሽ ደረሰው። ያየውንና ያነበበውን ማመን አቃተው። ዓይኑን እየጠራረገ ደጋግሞ አነበበው። ደብዳቤው ‹… በአካባቢው ባዶ የመንግሥት ቦታ ካለ ይሰጠው …› የሚል መልእክት ይዟል።
አስፋውም በምላሹ ተደስቶ ደብዳቤውን ይዞ ላይ ታች ቢልም ሰሚ አላገኘም። ያሰበውን ሳይፈጽም የማያርፈው ወጣት አንድ ሃሳብ መጣለት። አሁን ግን ማንንም ማማከር አልፈለገም። አጋጣሚውን መጠበቅ ብቻ ያዘ። ጊዜው መድረሱን ሲረዳ፣ ተማሪዎቹን አሰልፎ በዋናው መንገድ ላይ ተገኘ። መኪናው ከዊንጌት ትምህርት ቤት ቀስ ብሎ እየወጣ ነበር። የእሱ ተማሪዎች እየጮኹ ይዘምራሉ። መኪናው ቀስ ብሎ እየሄደ ነው። መኪናው አጠገቡ እንደደረሰ አስፋው በድንገት ጎማው ሥር ተወርውሮ ወደቀ። ሹፌሩ በፍጥነት መኪናውን አቆመ። አስፋው ግን ብድግ ብሎ አቤቱታውን በከፍተኛ ድምጽ ማሰማቱን ቀጠለ። መኪናው ውስጥ ከኋላ አንድ ግርማ ሞገስ የተላበሱ ሰው ተቀምጠዋል። የወጣቱን ጩኸት ሲሰሙና ተማሪዎቹን ሲመለከቱ ከአንድ ወጣት ተማሪ የተፃፈላቸው ደብዳቤ ትዝ አላቸው። ሰውየው ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ነበሩ። ንጉሰ ነገሥቱ ‹መሬት ይሰጠው› የሚለውን የቀደመ ትዛዛቸውን አጽንተው በማዘጋጃ ቤት በኩል በአስቸኳይ እንዲፈጸም ድጋሚ ትዛዝ ሰጡ። ከቤተ ክርስቲያን አካባቢ የነበረበት ግፊትም ጋብ አለለት … ››
ጉዳዩ በአካባቢው መነጋገሪያ ሆነ። በርግጥ በወቅቱ እንደዚህ ዓይነት ተግባር መፈጸም የተለመደ የአቤቱታ አቀራረብ ዘዴ ቢሆንም ወቅቱ ‹‹የታኅሳስ ግርግር›› የሚባለው መንግሥትን የመገልበጥ ሙከራ ተደርጎ የከሸፈበት ወቅት በመሆኑ፣ የንጉሡ የክብር ዘበኛ ጠባቂዎች ጥንቃቄና ጥርጣሬ ከፍተኛ ስለነበር ነው፡ በዚያ ወቅት መሰል ተግባር መፈጸም አስደንጋጭም አደገኛም እንደነበር ቢታወቅም ሰብዓዊነት በደም ስሩ የገባው አስፋው ግን ደፍሮ አደረገው።
ንጉሰ ነገሥቱ የፈቀዱለትን ለማስፈፀም ከተንከራተተ በኋላ ማዘጋጃ ቤቱ የዊንጌት ትምህርት ቤትን አጥር ይዞ፣ የጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተ ክርስቲያንን አዋስኖ ስፋቱ 300 ካሬ ሜትር የሆነ ቦታ ሰጠው። የራሱን ትምህርት መማር፣ የሚመግባቸውንና የሚያስተምራቸውን ልጆች መከታተል እንዲሁም ማዘጋጃ ቤት እየተመላለሰ የመሬቱን ጉዳይ ማስፈፀም ቀላል ስላልሆነ በወቅቱ አስፋው ላይ ትልቅ ጫና ፈጥሮበት ነበር።
አስፋው የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቀቀ። በወቅቱ ሥራ መቀጠር አልያም የኮሌጅ/ ዩኒቨርሲቲ ትምህርትን መቀጠል ለዊንጌት ትምህርት ቤት ተማሪዎች የሚቀርቡ አማራጮች ነበሩ። አስፋው ‹‹ሁለቱንም አልፈልግም›› በማለት ትምህርት ቤቱንና ጓደኞቹን አስደነገጠ። ሥራ ከመቀጠርና የኮሌጅ ትምህርት ከመቀጠል ይልቅ ትምህርትን በማስፋፋት መሃይምነትንና ድህነትን መታገል እንዲሁም በተቻለው አቅም ሁሉ ማኅበረሰቡን ማገልገል ምርጫው መሆኑን አስታወቀ።
ለትምህርት ቤት ማሠሪያ የሚሆነውን ገንዘብ በተለያየ መንገድ (ከተማሪዎች ትርዒት፣ ከዊንጌት ትምህርት ቤት መምህራን መዋጮ …) ከሰበሰበ በኋላ በተሰጠው ቦታ ላይ ከተማሪዎቹ ጋር በመሆን ራሱ ጭቃ አቡክቶ፣ እንጨት ተሸክሞ፣ ግድግዳ አቁሞ፣ ማገር ማግሮና ቆርቆሮ አልብሶ በአንዱ ጥግ ለራሱ መኖሪያ የሚሆን አነስተኛ ቤት፤ በሌላኛው ጥግ ደግሞ ለተማሪዎቹ ማደሪያና መማሪያ የሚሆኑ ክፍሎችን ሠራ። በ1955 ዓ.ም ትምህርት ቤቱን ሰርቶ አጠናቀቀ።
የአስፋው የግል ሕይወቱም ሆነ የትምህርት ቤቱ ዋና ዓላማ ‹‹ትምህርትንና ሌሎች ማኅበራዊ አገልግሎቶችን በተቻለ አቅም ለተቸገሩ ወገኖች ማዳረስ›› የሚል ነው። ይህንን ዓላማ ለማሳካት ደግሞ ከልጅነት እስከ አዛውንትነት ያለውን እድሜውን ሁሉ ገብሯል።
ትምህርት ቤቱ የማስተማር አገልግሎትና የማኅበረሰብ ድጋፎችን አጣምሮ ስለሚሰራ አደረጃጀቱ ለየት ያለ ነው። ትምህርት ቤት ብቻ ነው እንዳይባል በመቶዎች የሚቆጠሩ ወላጅ አልባ ሕፃናት በትምህርት ቤቱ ውስጥ እየኖሩ ይማሩ ነበር። የወጣቶችና የሕፃናት ማሳደጊያ እንዲሁም የማኅበረሰብ ድጋፍ የሚደረግበት ተቋም ነው እንዳይባል ደግሞ ከአካባቢው ወደ ትምህርት ቤቱ እየመጡ የሚማሩ ችግረኛ ተማሪዎች ቁጥር ከወላጅ አልባ ሕፃናቱ ቁጥር በብዙ እጥፍ ይበልጣል።
የዚህ ዓይነት አደረጃጀት ትምህርት ቤቱን በትምህርት ሚኒስቴር መዝግቦና ቋሚ በጀት መድቦ ለማስተዳደር አስቸጋሪ አደረገው። በሌላ በኩል ሁኔታው ለአስፋው ትምህርት ቤቱን በራሱ መንገድ እንዲመራው ዕድል ፈጥሮለታል። ለአስፋው ዋና ችግር የሆነበት የበጀት ችግርንና የአስተዳደር ነፃነትን አቻችሎ መጓዝ ነበር።
ትምህርት ቤቱ ሥራውን የሚያከናውነው ከየፊናው በሚመጡ እርዳታዎች ነበር። በተለይ ከንጉሰ ነገሥቱ የተበረከተለት አምስት ሺ ብር፣ ብሔራዊ ሎተሪ መስሪያ ቤት ያደረገለት የ6ሺ 500 ብር ድጋፍ እንዲሁም ከዊንጌት ትምህርት ቤት ወዳጆቹ ያገኘው የሁለት ሺ ብር እርዳታ ተስፋውን ያለመለሙና ለቀጣይ ሥራ ያበረታቱት ነበሩ።
አስፋው ትምህርትን ለማስፋፋት የተከተለው መንገድ ‹‹ቅድሚያ ለትምህርት›› የሚል መርህ ነበር። በወቅቱ አስፋው ስለትምህርት ቤቱና አሰራሩ ሲናገር ‹‹ … የትምህርት ሚኒስቴርን መመሪያ ተከትዬ ክፍሎቹን ብሠራ ኖሮ የሚኖሩኝ ተማሪዎች ቁጥር 400 ብቻ ይሆን ነበር። እኔ ግን 2ሺህ 500 ተማሪዎች አሉኝ። ከእነዚህ ውስጥ 380 ያህሉ ትምህርት ቤቱ ውስጥ እየኖሩ የሚማሩ ወላጅ አልባ ወጣቶች ናቸው …›› ብሏል።
ትምህርት ቤቱ በ1955 ዓ.ም ከትምህርት ሚኒስቴር ዕውቅና ቢያገኝም፣ በሚከተለው የተለየ አደረጃጀት ምክንያት ሙሉ የበጀት ድጋፍ አያገኝም ነበር። መደበኛ በጀት ስላልነበረውም የረጅም ጊዜ ዕቅድ ለመንደፍ ይቸገር ነበር። ሆኖም ትምህርት ቤቱ እውቅና ካገኘ በኋላ የተማሪዎች ጥያቄ እየበዛ ስለነበር ትምህርት ቤቱም በተቻለው መጠን ተስፋፋ።
መጋቢት 21 ቀን 1958 ዓ.ም በትምህርት ቤቱ የተለየ ነገር ተከሰተ። ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ትምህርት ቤቱን ለመጎብኘት በድንገት ተገኙ። ከጉብኝታቸው በኋላም ‹‹በዚህ ተማሪ ቤት በጠቅላላው ደስ አሰኝቶናል። አስተማሪዎችና ተማሪዎች በርቱ፤ ላገር ጠቃሚ ትሆናላችሁ፤ እግዚአብሔር ይርዳችሁ›› የሚል አስተያየት ከጻፉ በኋላ በቃላቸው ‹‹ትምህርት ቤቱንም ‘አሠረ ሐዋርያት ትምህርት ቤት’ ብለነዋል›› አሉ።
‹‹ትምህርት ከድህነት ነፃ መውጫ መሣሪያ ነው›› የሚሉት አቶ አስፋው፤ ተማሪዎቻቸው ትምህርታቸውን በትጋት እንዲከታተሉ ያተጋሉ። አንድ ተማሪ በሁለት ትምህርቶች ዝቅተኛ ውጤት ካስመዘገበ ቤተሰቦቹን ጠርተው ያናግራሉ። ያለበለዚያም ራሳቸው ተማሪውን ይከታተላሉ። የአቶ አስፋው ለተማሪዎቹ ወላጆች ገንዘብ፣ አልባሳት እና ወተትና የመሣሠሉ ድጋፎችን ያደርጋሉ እንጂ የትምህርት፣ የመጻሕፍትና ሌሎች ክፍያዎችን አይጠየቁም። ተማሪዎቹም የአቶ አስፋውን አደራ ጠብቀው በየዓመቱ በስምተንኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ያስመዘግባሉ። ትምህርት ቤቱም ጥራት ያለው ትምህርት ከሚሰጥባቸው ትምህርት ቤቶች መካከል አንዱ እንደሆነም ተማሪዎቻቸው ይናገራሉ።
በ1950ዎቹ መጀመሪያ በዛፍ ጥላ ሥር የተጀመረው ይህ የማስተማር ተግባር ከ60 ዓመታት በላይ ቀጥሎ፣ 250ሺ ለሚሆኑ ወጣቶች የትምህርት ዕድል ከፍቷል። በ10ሺዎች የሚቆጠሩ የዝቅተኛው ማኅበረሰብ ክፍል አባላት (እናቶች፣ ሕፃናት፣ የጎዳና ተዳዳሪዎች) ደግሞ የተለየ ድጋፍ ተጠቃሚ ሆነዋል። አቶ አስፋውም ይህን ሁሉ ተማሪ አስተምረውና አግዘው ለቁም ነገር አብቅተዋል። ከትምህርት ቤቱ በተጨማሪ ገፈርሳ አካባቢ ክሊኒክ አቋቁመው አቅም የሌላቸው ነዋሪዎች እንዲገለገሉበትም አድርገዋል። አቶ አስፋው ለተማሪዎቻቸው አስተማሪ ብቻ ሳይሆኑ አባትም ጭምር ነበሩ። ለዚህም ነው ተማሪዎቻቸው ሁሉ ‹‹ጋሽዬ›› የሚሏቸው። ይህንን ያህል ቁጥር ያላቸውን ሰዎች ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ለሆነ ጊዜ ማስተማርና ድጋፍ ማድረግ የተቻለው ያለምንም ቋሚ በጀት መሆኑ ደግሞ እጅግ በጣም ያስገርማል።
አቶ አስፋው ካከናወኑትና በዋጋ ከማይተመን ተግባራቸው አንፃር የሚገባቸውን ያህል እውቅና አላገኙም። ‹‹ብዙ ሰው ስለስራቸው ያውቃል›› ለማለት አያስደፍርም። ይህም እርሳቸው የሚያከናውኑት የበጎ አድራጎት ተግባር እንዲታወቅና እንዲሞገሱ የሚፈልጉ ሰው ስላልነበሩ ሊሆን ይችላል። የቅርብ ወዳጆቻቸውም ‹‹አስፋው የምሩ የሚሠራውን ሥራ ‹እወቁልኝ› የማይል፤ ስለሚሰጠው አገልግሎት እንዲያመሰግኑት ፍላጎት የሌለውና ሥራውን መሥራት እንጂ በሠራተኝነቱ ስሙ እንዲነሳ የማይሻ ሰው ነው›› ይላሉ።
አቶ አስፋው ያቋቋሙትን ትምህርት ቤት የጎበኙትና በሥራቸውም መደሰታቸውን የተናገሩት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ፤ የ1962 ዓ.ም የቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ የትምህርት ዘርፍ ሽልማትን ለአቶ አስፋው አበርክተውላቸዋል። የሽልማቱ መጽሔቱ ላይ የሰፈረው ጽሁፍ እንዲህ ይነበባል፡-
‹‹… እኝህ በአገልግሎት ስሜት የተነሱ ትጉህ ኢትዮጵያዊ ይህንን ኃላፊነት በፈቃዳቸው ተሸክመው ሥራውን በሚመሩበት ጊዜ፤ ያላአንዳች ጥቅም ሰውነታቸውንና ዕውቀታቸውን በሙሉ ለኢትዮጵያውያን ተማሪዎች መስዋዕት አድርገው መድከማቸውን የማስተማር አገልግሎት ኮሚቴና ባላደራዎችም ተመልክተውታል። ይህንን የመሰለ አገልግሎት እፈጽማለሁ ብሎ ለሚነሳ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ይህ ምሳሌ ኃይልና ብርታትን የሚሰጥ መሆኑን ስለተገነዘበ፤ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የ1962 ዓ.ም የማስተማር አገልግሎት ሽልማት የወርቅ ኒሻንና የምስክር ወረቀት፣ ከ10ሺህ የኢትዮጵያ ብር ጋር ለአቶ አስፋው የምሩ እንዲሰጣቸው ወስኗል።››
ከዚህ በተጨማሪም በ1993 ዓ.ም ለሕፃናት መብት ታላቅ ተግባር ላከናወኑ ጀግኖች የሚሰጠውን የዓለም ሕፃናት ሽልማት (World Children’s Prize) አግኝተዋል። ለወላጆችና ሕፃናት መብት ላደረጉት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የዓለም አቀፍ ወዳጆች ማኅበር ሽልማትንም (The Global Friends Award) አሸናፊ መሆን ችለዋል። በዚህም ‹‹ሎሬት›› የሚል ማዕረግም አግኝተዋል፤ እርሳቸው ግን ‹‹ጋሽዬ›› የሚለው ይበቃኛል ብለው በሎሬትነቱ መጠራት ሳይፈልጉ ቀርተዋል። የኖቤል ሽልማት እጩ እንዲሆኑ የቀረበላቸውን ጥያቄም ሳይቀበሉት እንደቀሩ ታሪካቸው ያስረዳል። አቶ አስፋው ከወይዘሮ ሰናይት አክሊሉ ጋር ጋብቻ ፈፅመው ሦስት ልጆችን አፍርተዋል።
ላለፉት 60 ዓመታት ከ250ሺ በላይ ተማሪዎችን ያስተማሩትና በርካታ አቅመ ደካማዎችን በመርዳት ሀገራቸውን ያገለገሉት፤ የወላጅ አልባ ሕጻናትና የጎዳና ተዳዳሪዎች ተቆርቋሪ፣ የወጣቶች የቀለም አባት፣ የእናቶችና የልጃገረዶች አለኝታ፣ በድንገተኛ አደጋ ለተጎዱ ወገኖች ቀድሞ ደራሽ የነበሩት፤ ብዙዎች ‹‹ጋሽዬ›› እያሉ የሚጠሯቸው ‹‹የአንድ ብዙ›› የነበሩት ታላቁ የበጎ አድራጎት ሰው አቶ አስፋው የምሩ ሚያዝያ 29 ቀን 2013 ዓ.ም አርፈው ስርዓተ ቀብራቸው በብርሃናተ ዓለም ጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተክርስቲያን ተፈፅሟል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 9/2013