ታምራት ተስፋዬ
የሰው ልጅ ለምግብነት ከሚጠቀማቸው መካከል ዘይት አንዱና ዋነኛው ነው። በባህላዊም ሆነ በዘመናዊ መንገድ የሚዘጋጅ፣ ደሃውም ሆነ ሀብታሙ ለምግብነት የሚጠቀመው የምግብ አይነት ነው። ከምግብነት ባለፈም በኢንዱስትሪዎች፣ ለመዋቢያ ቅባቶች፣ ለመድኃኒት ለቀለሞችና ለሌሎችም የኢንዱስትሪ ምርቶች በግብአትነት ይውላል። ለተለያዩ የታሸጉ ምግቦች ዝግጅት ተፈላጊነቱ ጨምሯል።
መረጃዎች እንደሚያመላክቱት ፣ በአፍሪካ የምግብ ዘይት በተለይ የፓልም ዘይት ምርትን በማቅረብ ፣ናይጄሪያ፣ጋና፣ አይቮሪኮስት፣ ሴራሊዮንና ላይቤሪያን የመሳሰሉ አገራት በግምባር ቀደምትነት ይታወቃሉ። በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢንዶኔዢያና ማሌዢያና ህንድን ስማቸው ከቀዳሚዎቹ ተርታ ይጠቀሳል።
በአሁኑ ወቅትም በዓለም አቀፍ ደረጃ የምግብ ዘይት እጅግ ተፈላጊ ከሆኑ ግንባር ቀደም ምርቶች አንዱና ዋነኛው ነው። ዓለም አቀፍ ደረጃ የገበያ ድርሻም ከፍተኛ ነው። በዚህ ረገድ ጥናቶችን ዋቢ በማድረግ ቢዝነስ ዋየር፣ በሰራው ሃተታም ‹‹እኤአ በ2019 ዓለም አቀፍ የምግብ ዘይት ገበያ 96 ነጥብ 878 ቢሊዮን ዶላር ያስመዘገበ ሲሆን ይህ አሃዝም እኤአ በ2025 መጨረሻ ወደ 119 ነጥብ 571 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ይላል›› ሲል አስነብቧል።
ዋጋውም ቢሆን የዚያኑ ያህል እየጨመረ ይገኛል። በተለይ በዚህ ዓመት ባለፉት ለአስር ዓመታት ታይቶና ተሰምቶ የማያውቅ መልኩ ዋጋው ከፍ ብሏል። ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀርም የ62 በመቶ ጭማሪን አሳይቷል። ለዋጋው መጨመር ደግሞ የተለያዩ ምክንያቶች ተዘርዝረዋል።
‹‹መኒ ኮንትሮል››ላይ የወጣው መረጃ እንደሚያመላከተውም፣ በተለይም የምርቱ አቅራቢ በሆኑት ኢንዴኔዢያና፣ ማሌዢያ፣ አርጀንቲና ዩክሬንና ሩሲያ በመሳሰሉ አገራት ላይ የተከሰተ የአየር ጠባይ ለውጥ ለምርቱ ዋጋ መጨመር በምክንያትነት ቀርቧል። ሮይተርስም ፣ የዓለማችን ሁለተኛ ግዙፍ የፓልም ዘይት አቅራቢ በሆነችው ማሊዢያ የተከሰተው የሰራተኞች እጥረትም ለዘይት ምርቱ ዋጋ መሰቀል እንደ አንድ መንስኤ መሆኑን አስነብቧል።
በዓለም አቀፉ የምግብ የዘይት ኢንዱስትሪ ላይ የተለያዩ ትንታኔዎች በማስነበብ የሚታወቁ መገናኛ ብዙሃን፣ ባለሙያዎችና ተንታኞችም፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የምግብ ዘይት ፍላጎትም ሆነ ዋጋው ከመቀነስ ይልቅ እያደር የሚጨምር ስለመሆኑ በማስረዳት ላይ ተጠምደዋል። ይህም ለበርካታ አገራት ከባድ ራስ ምታት እንደሚሆኑ አፅእኖት ሰጥተውታል።
የኢትዮጵያ የምግብ ዘይት ፍላጎት ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በየዓመቱ በአማካኝ አስር በመቶ በላይ ጭማሪ እንደሚያሳይ የተለያዩ መረጃዎች ያመላክታሉ። አገሪቱ የዘይት ፍላጎቷን ማርካት አትቻል እንጂ በዓለም ላይ ካሉ ለጤና ተስማሚ የዘይት እህል አምራች ሀገሮች በግንባር ቀደምትነት ትጠቀሳለች።
በየአመቱም ከአራት እና አምስት መቶ ሜትሪክ ቶን በላይ ሰሊጥ፣ ከሶስት መቶ ሺ በላይ ኑግ፣ እንዲሁም ከሁለት መቶ ሃያ ሺ በላይ አኩሪ አተር ወደ ተለያዩ አገራት ትልካለች። የሚላከው የጥሬ የዘይት እህል የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ አገሪቱ የዘይት ምርቱን ከውጭ ለማስገባት ከምታወጣው ጋር ሲነፃፀርም ገቢው ከወጪው በእጥፍ ያንሳል።
የኢትዮጵያ መንግስትም ‹‹እንደ ሀገር ግዙፉ ጉድለታችን የዘይት አቅርቦትና ፍላጎት አለመመጣጠን ነው›› ሲል በተደጋጋሚ ተደምጧል። መረጃዎች እንደሚያመላክቱት በአሁኑ ወቅት በመቶዎች የሚቆጠሩ ድርጅቶች ከዱባይ፣ ከኔዘርላንድ፣ ከኢንዶኔዢያ፣ ቻይና እና ሌሎችም የምስራቅ አፍሪካ አገራት የተለያዩ የምግብ ዘይቶችን ወደ አገር ያስገባሉ።
በርካቶችም በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ዘይትን ለማቅረብ ተመዝግው ወደ ስራ ለመግባት በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ። ይሁንና የዘይት አቅርቦትና ፍላጎቱ መመጣጠን አልቻለም። ገበያው ላይም ከፍተኛ የዘይት እጥረት ተስተውሏል።
የአገር ውስጥ አምራቾች የዘይት ምርት አቅርቦት ድርሻ እጅግ ዝቅተኛ ነው። የተለያዩ መረጃዎችም የአገር ውስጥ አምራቾች አስተዋጽኦው ከፍላጎቱ አንፃር ከ40 በመቶ በላይ የሚሻገር እንዳልሆነ ያሳያሉ። ቀሪው የዘይት ምርት ፍላጎት የሚመጣው ከተለያዩ አገራት በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ተገዝቶ ነው።
የአገር ውስጥ የዘይት ፍላጎት ጥያቄን ለመመለስም በዓመት አማካኝ ከአራት እስከ አምስት መቶ ሚሊዮን ዶላር ወጪ ያወጣል። ወጪውም አገሪቱ ከውጭ ከምታስገባቸው እስከ 15 ቢሊዮን ወጪ የሚያስወጡ ምርቶች ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳል።
መረጃዎች እንደሚያሳዩትም፤ የኢትዮጵያ ዓመታዊ የምግብ ዘይት ፍላጎት በ2013 በጀት ዓመት 955 ሺ 600 ቶን ወይም በወር 79 ሺ 637 ቶን ደርሷል። በአሁኑ ጊዜ የቅባት እህሎችን ጨምቀው የሚያጣሩ 25 መካከለኛና መለስተኛ ኢንዱስትሪዎች ማምረት የተቻለው 4 ሺ 905 ቶን ሲሆን ከአጠቃላይ ከምግብ ዘይት ፍላጎት 6 ነጥብ 2 በመቶ ብቻ ነው።
በቅርቡ የፓልም የምግብ ዘይት ድፍድፍን በማጣራት ምርታቸውን ወደ ገበያ እያስገቡ የሚገኙ 5 ፋብሪካዎች በወር 26 ሺ 670 ቶን በማምረት ወደ ገበያ አስገብተዋል። በዚህም የዘይት ፍላጎት 40 ነጥብ 2 በመቶ መሸፈን ችለዋል። 30ዎቹ ፋብሪካዎች በድምሩ የፍላጎቱን 46 ነጥብ 4 በመቶ ሸፍነዋል።
መንግስት ከውጭ የሚገቡትን ምርቶች በአገር ውስጥ የመተካት ጽኑ ፍላጎት ያለው የለውጡ መንግስትም፣ በተለይ ለምግብ ዘይት የሚያወጣውን ከፍተኛ ወጪ ለማዳን የግሉ ዘርፍ ኢንቨስትመንት ተሳትፎ እጅግ ወሳኝ መሆኑን ተረድቷል።
አገር ውስጥ አምራቾን ምርትና ምርታማነታቸውን እንዲሻሽሉ አዳዲስ ኢንቨስተሮችም ዘርፉ ውስጥ እንዲሰማሩ የተለያየ ማበረታቻዎች በማዘጋጀት በሩን ክፍትና አሰራሩን ቀልጣፋ አድርጎ እየተጠባበቀ መሆኑ በተደጋጋሚ አሳውቋል።
ይህን ምቹ ሁኔታ ከግምት ያስገቡ የግሉ ዘርፍ ተዋናዮችም የተለያዩ ኢንቨስትመንቶችን ተግባራዊ ማድረግ ጀምረዋል። በግዙፉ ኢንቨስትመንት ለመሳተፍ ፋብሪካዎችን ገንብተው ወደ ስራ ገብተዋል። አንዳንድ ኩባንያዎቹ የምርት ሂደታቸውን በይፋ ያስጀመሩ ሲሆን አንዳንዶቹም በሂደት ላይ ይገኛሉ።
በዚህ ዓመት የምግብ ዘይት ኢንዱስትሪውን ከተቀላቀሉ ፋብሪካዎች መካከል ደግሞ ፊቤላ አንዱ ነው። በአራት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር ወጪ በአማራ ክልል ቡሬ ከተማ በ 30 ሄክታር መሬት ላይ የተገነባውና በጥር ወር መጀመሪያ የተመረቀው የዘይት ፋብሪካ በቀን 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሊትር ዘይት ማምረት ጀምሯል። 60 በመቶ የሀገሪቱን የዘይት ፍላጎት የመሸፈን አቅም አለው። ለምግብ ዘይት ይወጣ የነበረውን 30 በመቶ የውጭ ምንዛሪ የማስቀረት አቅም እንዳለው ተነግሮለታል። በሙሉ አቅሙ ማማረት ሲጀምርም ለ3 ሺ ሰዎች የስራ እድል ይፈጥራል።
ፋብሪካው ከተመረቀ በኋላ በፍጥነት ወደ ምርት ሂደት በመሸጋገሩም አበርክቶቱ በግልጽ መታየት ጀምሯል። የፊቤላ ኢንዱስትሪ ባለቤትና የቢኬጂ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ በላይነህ ክንዴ በሚያዚያ ወር መጀመሪያ ከአዲስ ዘመን ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹትም፣ ‹‹ፊቤላ ኢንዱስትሪ በመጀመሪያው ዙር የውጭ ምንዛሪ ተመድቦለት ባስገባው ጥሬ እቃ ተጠቅሞ 12 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሊትር የሚጠጋ ዘይት እና 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ተጓዳኝ ምርቶችን አምርቶ ለገበያ አቅርቧል››ማለታቸው አንዱ ማሳያ ነው።
በዚህ ዓመት ወደ ስራ የገባው ሌላኛው የምግብ ዘይት ፋብሪካ ‹‹ደብሊው ኤ›› ነው። በደብረ ማርቆስ ከተማ ከ5 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው ፋብሪካ፣ በሙሉ አቅም ማምረት ሲጀምር የተለያዩ የቅባት እህሎችን በመጠቀም በቀን የጥራት ደረጃውን የጠበቀ ከአንድ ሚሊዮን 350 ሺህ ሊትር በላይ ዘይት የማምረት አቅም አለው።
ፋብሪካው የአገሪቱን የዘይት ምርት ፍላጎት 40 በመቶውን የሚሸፍን እንደሆነ የገለጹት የደብሊው ኤ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ባለሀብት አቶ ወርቁ አይተነው ናቸው። በቀጣይ ጊዜያት በአቅሙ ልክ ማምረት ሲጀምር 60 በመቶ ሀገራዊ ፍላጎትን ይሸፍናል ነው ያሉት። ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ወደ ማምረት ሲገባ በአንድ ፈረቃ ብቻ ከ3 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል ይፈጠርላቸዋል።
‹‹የደብሊው ኤ›› ኢንዱስትሪያል የምግብ ዘይት ኮምፕሌክስ ምረቃ ላይ የተገኙት የፌዴራል ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበልም፣ የኢትዮጵያ የዘይት ምርት ፍላጎት ከፍተኛ ጭማሬን እያሳየ መሆኑንና የግሉ ዘርፍ ኢንቨስትመንት ይህን ጥያቄ መልስ በመስጠት ረገድ ልዩነት እንደሚፈጥር ነው የገለጹት።
ፋብሪካው የግብዓት እጥረት ካልገጠመው በስተቀር በቀን 18 ሺህ ኩንታል ጥሬ እቃ በመጠቀም በወር እስከ 33 ሺ ቶን የምግብ ዘይት የሚያመርት በመሆኑ ፍላጎቱን በእጅጉ ያሻሽላል ተብሎ ይጠበቃል። ‹‹በቅርቡ ወደ ስራ እየገቡ ያሉ ፋብሪካዎች ኢትዮጵያ የመሰረታዊ የፍጆታ እቃዎችን በሀገር ውስጥ የማምረት እቅዷን ስኬታማነት የሚያሳዩ ናቸው›› ብለዋል።
ከለውጡ በኋላ እንደ ዋነኛ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በተወሰደው በኢኮኖሚ ውስጥ የግል ባለሀብቱ በሰፊውና ያለ ገደብ የማሳተፍ ፣ቀስ በቀስም ኢኮኖሚው በግሉ ባለሀብት የሚመራበትን ሥርዓት ለመገንባት የሚደረግ ጥረት ማሳያ ስለመሆኑም ነው አጽእኖት የሰጡት። የምግብ ዘይት ኮምፕሌክስ ፋብሪካዎች በተለይም የፍጆታ እቃዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለኅብረተሰቡ ስለሚያቀርቡ የኑሮ ውድነቱን በማቃለል ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳላቸው ሳያስገነዝቡ አላለፉም።
የደብሊው ኤ ኢንዱስትሪያል የምግብ ዘይት ኮምፕሌክስ ኢትዮጵያ በለውጡ ማግስት ያስቀመጠችውን ወሳኝ የኢንዱስትሪ ልማት አቅጣጫ በግልጽ የሚያሳይ መሆኑን የመሰከሩት የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር ናቸው።
በተለይ የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚና የኢንዱስትሪ ትስስርን በግልጽ የሚያሳይ መሆኑን ያመላከቱት አቶ አገኘሁ፣ የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ምርታቸውን ተደራድረው እንዲሸጡ ያደርጋል፤ ምርታቸውን ለማሳደግም ይረዳል ነው ያሉት።
የፋብሪካዎቹ ወደ ኢንዱስትሪ መቀላቀል በኢትዮጵያ ያለውን የምግብ ዘይት እጥረትና የዋጋ ግሽበት እንደሚያረጋጋ አመላካች ምልክቶች አሉ። ሁለቱ ፋብሪካዎች በሙሉ አቅም ወደ ስራ ሲገቡ በድምሩ ከስድስት ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል የሚፈጥሩ መሆናቸውም የአገሪቱ ራስ ምታት የሆነውን የስራ እድል ፈጠራ በማገዝ ረገድም ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል።
ፋብሪካዎቹ የምግብ ዘይት ፍላጎት ጥያቄን ከመመለስ ባሻገር በአንድ ወገን የወጪ ንግዱን ሲያሻሽሉ በሌላ ወገን ደግሞ የገቢ ንግድ ሚዛንን እንደሚጠብቁም እርግጥ ነው። ፋብሪካዎቹ ዘይት ከማምረት ጎን ለጎን ቀደም ሲል ከውጭ አገራት የሚገቡና ከፍተኛ ወጪ የሚያስወጡ አትክልት ቅቤ፣ የዘይት ማያዥያ ጀሪካንን ጨምሮ በተረፈ ምርቱ ሌሎችን ምርቶች የሚያመርቱ መሆኑ ደግሞ አስፈላጊነታቸውን ይበልጥ ያገዝፈዋል።
ይሁንና የፋብሪካዎቹን ትሩፋት ለማጣጣም በሙሉ አቅማቸው እንዳያመርቱ ዋና ዋና ተግዳሮት ሊሆኑ የሚችሉ መሰናክሎችን ማስወገድ የግድ ይላል። በተለይም የኤሌክትሪክ አቅርቦትና ለግብዓት እንዲሁም ግብአትን ለማስመጣት የሚያስችል የውጭ ምንዛሬ እጥረት ቀዳሚ ሆኖ ይነሳል።
ምንም እንኳን መሰል ችግሮች ከመንግስት እይታ የተሰወሩ ናቸው ለማለት ባያስደፍርም የዘይት ኢንቨስትመንቱ ላይ ውጤታማ መሆን ከተፈለገ ግን የተደቀኑና የሚደቀኑ ተግዳሮቶችን ፈር ለማስያዝ የበለጠ ትኩረት መስጠት ግድ ይላል። ይህ የቤት ስራም ለነገ ተብሎ የሚቀመጥ አለመሆኑን ጠንቅቆ መረዳትን ይጠይቃል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 9/2013