ሀገር ቤት የሚነገር የይባላል ወግ፤
ሰውዬው ብርቱ አራሽ ነው ይባላል። ይባላል መባሉ ልብ ይባልልኝ። ይሄ ብርቱ ገበሬ ያለመታደል ሆኖ የትዳሩ ጉዳይ እንደ ግብርናው የአዝመራ ውጤት አጓጊና ፍሬው የተንዠረገገ ሊሆንለት አልቻለም። ምክንያቱ ደግሞ ሚሽቲት ሆዬ አንደበቷ ነበልባል እሳት ይሉት ብጤ ስለሆነበት ነበር። ማልዶ ወደ ግብርናው የሚወጣው የአደረ አፉን በቁርስ አሟሽቶ ሳይሆን “በጦር ምላሷ እየተሸቀሸቀ” ነበር። ውሎውን ከውኖ ሲመለስም የሚጠብቀው ያው እንደ ጎሞራ እሳት የሚፈነዳው ስድቧ ነበር። ጎተራው ሙሉ ቢሆንም ማዕዱ ግን ሁሌም አዋይ እንደራቀው፤ የሚጎናጸፋቸው አልባሳት ቢትረፈረፉለትም ሁሌም በሚስቱ ጠባይ ምክንያት ራቁትነት እንደተሰማው መኖሩ አንገሽግሾታል።
“የውጭ አልጋ የቤት ቀጋ” አንዲሉ ያቺ አለብላቢት ምላሳም ሚስቱ ክፉ ባህርይዋን ቤቷ ውስጥ ቆልፋበት ስለምትወጣ ውጭ ውጭውን “መልአክ” ለመሰኘት ተውኔቱን የምትከውነው በማስመሰል ረቂቅ ጥበብ ተክና ነበር። በዚህ ተቃርኖ በተሞላበት የሚስቱ ባህርይ ግራ የተጋባው አባወራ እጅጉን መቸገሩ አልቀረም። ጾምና ጸሎቱን ሳይዘነጋ ወዳጆቹ የባህርይውን ድክመት እንዲነግሩት ብዙ ቢደክምም ከደግነቱ በስተቀር ይህንን አሻሽል ሊሉት አልቻሉም።
ምናልባትም ችግሩ ከጤንነቴ ጉድለት ይሆንን በማለትም “ሰውነቱን ለሐኪሞች አስፈተሸ” – ምንም ለውጥ አልተገኘም። ስለዚህም “ግራ የገባው የወርቄ ልጅ” አንዳለ ዓመታት ነጎዱ። ሚስት በምላሷ እንደበጠበችው፣ የእርሱም ሞራል በግርፋቱ ሰንበር እንደቆሰለ ድንገት የሞት ጽዋ ደጃፋቸውን አንኳኩቶ በመግባት ሚስቲት በተፈጥሯዊ ሞት ግባ መሬቷ ተፈጸመ።
አያ ባልም ሰልስቷን፣ ሰባቷን፣ አርባዋንና ሙት ዓመቷን በአግባቡ እየዘከረ ከኖረ በኋላ በቅርብ ወዳጆቹ ውትወታ ውሃ አጣጭ በማግኘቱ ድርብርብ ሃዘን ያወረዛው ቤቱ ሞቅ ደመቅ ማለት ጀመረ። ይህቺ ሁለተኛይቱ ሚስቱ የመጀመሪያዋ ሚስት ተቃራኒ ነበረች ብሎ ከመደምደም ይልቅ በአጭሩ “ክንፍ ነሳት” እንጂ የመላእክት ባህርይ የምትጋራ ነች ማለት ይቻላል። ሲወጣ ጌታዬ፣ ሲገባ ጌታዬ፣ ልሙትልህ፣ ልቀበርልህ እያለች በእውነተኛ ፍቅር ድል ነስታ ማረከችው። ትዳሩ መሞቅ ብቻም ሳይሆን የአባወራነቱ ክብር ጨምሮ በአዋዋሉም ሆነ በተግባሩ “ነዎሩ!” እየተባለ በምሳሌነት መሞገስ ጀመረ።
በዚህ ደስታ መካከል ድንገት አንድ ቀን ብድግ ብሎ ያቺን “ንጽሕት ርግብ” ሚስቱን ያለምንም ጥፋቷ በዱላ ይነርታት ገባ። “አጋሩ እህት ዓለም” የመደብደቧ ምሥጢርና ጥፋቷ እንቆቅልሽ ቢሆንባት ጉዷን ጎረቤት እንዳይሰማው በመጠንቀቅ በለሆሳስ ድምጽ “አይዋ ምን በደልኩህ፤ አጥፍቼም እንደሆን ማረኝ!?” እያለች በአቦ፣ በሥላሴ መማጸኑን ተያያዘችው።
ይሄን ጊዜ ባል በድብደባ የዛለውን ክንዱን እያፍታት “እስከ ዛሬ ዓመታቶቼ ባክነው ስንገበገብና ስቃጠል የት ነበርሽ!?” ብሎ እርፍ። መቼም ጥንታዊ ሀገራዊ ወግ ነውና በተረት ጨዋታ መካከል አድማጭ አደብ ገዝቶ በርጋታ ያደምጣል እንጂ “አንዲህ ለምን ተባለ? ይሄማ ሰብዓዊነትን የሚዳፈር፣ የወንድ ጀብደኝነትን የሚያጎላና የሴትን ክብር የሚጋፋ ተረት ነው! ወዘተ” እየተባለ ተረተኛው ሊሞግት አይገባም። ምክንያቱም “ሥነ ቃሉ” ይባላል ስለሆነና ተረት በባህርይው እንዴት? ለምን? ተብሎ ስለማይጠየቅ ለመሟገት በር አይከፍትም። ለማንኛውም “ተረቴን መልሱ፤ አፌን በዳቦ አብሱ” በማለት ልዳስሰው ወደ ፈለግሁት “ኮምጣጣ” ወጌ እዘልቃለሁ።
”የፈሰሰ ውሃ ባይታፈስም…‘
አንድ የሀገራችን ብርቱ ገጣሚ “ልክ እንደ ዘጠና ደቂቃው የእግር ኳስ ጨዋታ ሁሉ ምናለበት ፈጣሪ የባከ ጊዜያችንን የሚያካክስ ዕድሜ ቢመርቅልን” የሚል ተወዳጅ ቅኔ መቀኘቱን አስታውሳለሁ። የላይኛው የሀገር ቤት ወግና የገጣሚው አባባል ትዝ ሊለኝ የቻለው ሰኔ 3 ቀን 2013 ዓ.ም የጠቅላይ ሚኒስትሩን የልማት ስኬት የሚያሳየው ዶኪዩመንተሪ ፊልም በዋልታ ቴሌቪዥን ከተላለፈ በኋላና ሰሞኑን የመስቀል አደባባዩና የቸርችል ጎዳና መሰል ታላላቅ ፕሮጀክቶችን የሀገሪቱ ባለስልጣናት እየተጣደፉ ሲመርቁ መሰንበታቸውን ሳስተውል ነው። ልማቶቹ በሙሉ መቼ ተጀምረው እንዴት እንደተጠናቀቁ ለማሰላሰልም ፋታ የሚሰጥ አልሆነም።
ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ ከውጭ ባዕዳን ጠላቶችና ከውስጥ መሠሪ ባንዳዎች ጋር የሀገር ማዳኑ ፍልሚያ በተጧጧፈበትና እዛም እዚህም የሚገነፍሉ ሀገራዊ ችግሮች ወጥረውን እያለ በሺህዎች የሚቆጠሩ ፕሮጀክቶች በስኬት ተጠናቀው ተመረቁ ማለት ከተአምራትም በላይ የሚያስደንቅ ዜና ብቻም ሳይሆን ህሊናውን ለሚያዳምጥ ወገን መንግሥት ያስፈጸማቸውና በመጠናቀቅ ላይ ያሉት ፕሮጀክቶች ጥራትና ብዛት “አጃኢብ” አሰኝቶ እጅን በአፍ ላይ የሚያስጭንም ጭምር ነው።
በመላው ሀገሪቱ ለቁጥር የሚታክቱ ፕሮጀክቶች መመረቃቸው ያጥወላወላቸው አንዳንድ ወገኖች ከፖለቲካ “ትርፍ” ጋር አያይዘው ቢተቹ፣ ወይንም እያንኳሰሱ ቢያጥላሉ መብታቸው መሆኑ ባይካድም የጤንነታቸውን ሁኔታ ቢያስመረምሩ ይበጅ ይመስለናል። ለመሆኑ ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ውስጥ የሀገሪቱ ሀብት በወሮበሎችና በህሊና ቢስ መሪዎች ሲቦጠቦጥና ግዙፍ ፕሮጀክቶች ሲመክኑ እየተመለከትን ቆሽታችን ሲያር ዛሬ ጥብጣቡን ለመቁረጥ የሚሽቀዳደሙ አንዳንዶች “የት ነበሩ!?” ብለን በዱላ ሳይሆን በፍቅር ብንጠይቃቸው ተገቢ ሳይሆን ይቀራል?
መቼም በከንቱ በባከኑብን ለሦስት ዐሠርት ጥቂት ፈሪ ዓመታት ውስጥ ምንም ሥራ አልተሰራም ማለት እንዳልሆነ አጠንክሮ ማስታወስ ያስፈልጋል። መንገድ ተገንብቷል። አዎን። ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተገንብተዋል። ማን ይክዳል። ሌሎች በርካታ ግዙፍ ፕሮጀክቶችም ልክ እንደ ሙት በድን መታሰቢያ ሐውልት የመሠረት ድንጊያ እየቆመላቸው የተሸፈኑባቸው ቀያይ ግምጃዎች ሲገለጡ ማየታችንንም አንክድም።
ክፋቱ የሥርዓቱ ዋነኛ መዘውሮች ሀገሪቱን መዝረፍ ብቻም ሳይሆን ባዶ አጥንቷን እስከ መጋጥ ደርሰው የከርሰ ምድሩንና የገጸ ምድሩን በረከቷን ሙጥጥ አድርገው በማኘክ ምስኪን ኢትዮጵያን ራቁት ማስቀረታቸው ነው። ትንሽ “የልማት ቆሎ” እያሳዩ “በጎተራ ሙሉ የሚተመን ሃብት” ሲዘርፉና ሲሞጨልፉ፣ ከእነርሱም አልፎ ተርፎ ለልጆቻቸው፣ ለልጅ ልጆቻቸው፣ ለቅምጦቻቸውና ለቤተሰቦቻቸው ሲያደላድሉ መኖራቸው የአደባባይ ምሥጢር ነበር። አንድ የሀገራችን ጎምቱ ፖለቲከኛ እነዚህን “የሀገር ቅንቅኖች” የገለጹበት አባባል በጥሩ ሁኔታ ይወክላቸዋል። “የጠሉትን ሀገርና ሕዝብ እየመሩና እያስመረሩ የኖሩ የክፍለ ዘመናችን የጭካኔ መገለጫዎች።” ለመሆኑ ሚሊዮኖችን እየናቁ በቢሊዮን የሚገመት የሀገር ንብረት ወደ ውጭ እያሸሹ የባዕዳንን ባንኮች ሲያጨናንቁ ህሊናቸው ምን ብሏቸው ነበር። ዳሩ የህሊናን ክብርና ሞጋች ድምጽ መች አድምጠው!
ያለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ የኀዘን ማቃቸውን ሳይለውጡ መኖር ብቻም ሳይሆን ዓመታቱ ባክነው ከዕድሜያችን ላይ ተገንጥለው እንደረገፉ አበቦች ጭምር የሚቆጠሩ ናቸው። ባለፉት ሦስት ዓመታት በብዙ ሀገራዊ ተግዳሮት ውስጥ እያለፍን የተከናወኑት የልማት ስኬቶች ያለ ምንም ማጋነን ለመገመት እስከሚያዳግት ድረስ የሚያስደንቁና የጠቅላይ ሚኒስትሩን የጭንቅላት ምጥቀት አጉልተው የሚያሳዩ ናቸው።
ከሽብርተኝነት የተሻለ ሌላ መገለጫ ቢኖር እንኳን የህወሓት ክፋትና የሸር ጥግ እንዲህ ነው ተብሎ ዳርቻ የሚበጅለት አይሆንም። ዛሬ ሥራ ላይ እየዋለ ያለው ሀገራዊ በጀት ያኔም እንዲሁ ለፕሮጀክቶች እየተባለ ይበጀት ነበር። ዛሬ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን አስመርቀው የሚመረቁ ባለሙያዎችም እዚያው በመስክ ላይ ነበሩ። የዛሬዎቹ ጎምቱ ሹማምንትም ያኔም እንደ ገዘፉ በአንቱታና በፍርሃት መንገድ ይለቀቅላቸው ነበር። ለመሆኑ እንዳይናገሩ አፋቸውን የሸበበው ምን ነበር። የዛሬን መሰል ስራ እንዳይሰሩስ የፍርሃት ቆፈን ያፈሰሰባቸው አዚም እንደምን የበረታ ነበር። እንጠይቃቸው። ካነበቡ መልሱን ይስጡን፤ ካልመሰላቸውም እንደለመዱት እውነታውን ገፍትረው ይለፉ።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በዚያ ወልጋዳ የጠማሞች ምህዳር ውስጥ እንኳን እየኖሩ የሠሩትን ግዙፍ ስራዎች ለመመስከር እንደ ባህር አሸዋ የበዛ ምስክር ማቅረብ ይቻላል። አንዳንዶች እንደሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀን እረፍት፣ የሌት እንቅልፍ ሳይበግራቸው “ቃላቸውን ለመጠበቅ የሚተጉት” ሕዝቡን በምርጫ አማለው ሥልጣናቸውን አጥልቀው ለመትከል ስለፈለጉ አይደለም። ነው ብለው የሚከራከሩ ካሉም “እንኳን!” ብሎ ንቆ ማለፉ የበለጠ የተሻለ ይሆናል።
በከንቱ ለባከኑብን ሃያ ሰባት ዓመታት ምክንያት የሆነውን “የከንቱዎች ወንጀል ደጋግሞ መተረኩ” አግባብ ባይሆንም በቁጭት ተነሳስቶ ለተሻለ ተግባር ሊያነቃቃ ስለሚችል ማስታወሱ አይከፋም። በሦስት አሠርት ቢሊዮኖች የሚሰላው የሀገሪቱ ሀብት የተዘረፈው በስውር ሳይሆን በጠራራ ፀሐይ ነበር። “ያኔ ዝም አይነቅዝም!” እያሉ በመተረት ዓይናቸውን በፍርሃት እራፊ ይሸፍኑ የነበሩ አንዳንድ የመንግሥት ሹሞች ዛሬ የዓይናቸውን ቅርፊት ከላያቸው ላይ ገፈው ንሰሃቸውን በተግባር ከማደስ ይልቅ ጥግ ይዘው የመንግሥትን አካሄድ ሲተቹ ማስተዋል ይበልጥ ህሊናን ያቆስላል። ከዕድሜያችን ላይ ዕድሜ እየተቀረፈ ሲወድቅ እንዳላዩ ሲያዩ የነበሩ ወይንም እነርሱም የዘረፋው ተካፋይ በመሆን “ሌባ ሲባሉ ሌባ እያሉ” ንጹሐንን ለመከራ ሲዳርጉ መኖራቸው በታሪክም በፈጣሪ ዙፋን ፊትም “ቅጽበታዊ ፍርድ” ባሰጣቸው ነበር።
እንደ ባለሀገሩ አባወራ ዱላ አንስተን “የት ነበራችሁ?” በማለት ራእያቸውንና ስኬታቸውን አንደበድብም። እንሞክርም ብንል “ሰይጣን ራሱ ባገጠጠ ጥርሱ እየገለፈጠ ይስቅብናል።” በአጭር ጊዜ ውስጥ ያየነው ሀገራዊ ልማት ልባችንን በሀሴት፣ ተስፋችንን በብሩህ ብርሃን አፍክቶልናልና “ትናንትን ለመካስ” ዛሬ ላይ የጀገናችሁትን ሁሉ እናመሰግናለን። ትናንትን እያዛጉ አልፈው ዛሬም እንቅልፍ እንቅልፍ እያላቸው “እንዴት ይቻላል?” የሚሉ የእግር ሙቅ እስረኞች የባለ ራእዩ መሪ ራእያችሁ ይሁን ብለንም እናበረታታቸዋለን። ትናንትን በፍልሚያ፣ ዛሬን ከተግዳሮት በላይ ከፍ ብላችሁ ከፍታን የምትመኙልን አቃጆች፣ አስፈጻሚዎችና ፈጻሚዎች ምስጋናችን ይድረሳችሁ። እስከ ዛሬ የት ነበራችሁ ብለን በግንጣይ ለበቅ ወይንም በትችት ጅራፍ አንገርፋችሁም። ለባከነው ዕድሜያችንም ሙሾ እያወረድን ደረት አንደቃም። ይልቁንስ በቀረችን አጭር ዕድሜ እጅ ለእጅ ተያይዘን፣ ልብ ለልብ ተናበን የዘላለሟን ሀገር ወደ ከፍታ ለማውጣት አብረናችሁ እንተጋለን። ለእስካሁኑ ስኬታችሁ “ገለቶማ!”፣ ለነገው ውጥን ደግሞ አደራ! ኢትዮጵያ ታፍራ ተከብራ ትግነንልን፤ ህዝባችንም በክብር ከፍ ይበልልን። ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ሰኔ 9/2013