ግብርና ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መሰረት ከመሆኑም በላይ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለሚደረገው መዋቅራዊ ሽግግር ዋና አንቀሳቃሽ ሞተር ነው። የግብርና ዘርፍ ከጠቅላላ አገራዊ ምርት ጂዲፒ 40 በመቶ ድርሻ ሲኖረው አገሪቱ ከምታገኘው ዓመታዊ የውጭ ምንዛሪ 86 በመቶ ድርሻ የሚይዝ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ። በተጨማሪም 84 በመቶ የሚሆነው የአገሪቷ ህዝብ በግብርና ሥራ ላይ የተሰማራ በመሆኑ የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚ ዕድገት ለድህነት ቅነሳ ፋይዳው የጎላ ነው።
ኢትዮጵያ ምቹ የአየር ጸባይ ያላትና ለግብርናው ዘርፍ በተፈጥሮ የታደለች ከመሆኗም በላይ ዘርፉ ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠር የሚችል ነው። ይሁንና ኢትዮጵያ በተፈጥሮ የታደለችውን የውሃና የአፈር እንዲሁም ምቹ የአየር ንብረት ተጠቅማ የሚፈለገውን ውጤት ማስመዝገብ እንዳልቻለች ይነገራል። ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠር በሚችለው የግብርና ዘርፍ ምርትና ምርታማነቱ ተሻሽሎ ሀገሪቷ በምግብ ራሷን ባለመቻሏ ዛሬም ድረስ የምግብ ሸቀጣሸቀጥ ከውጭ ሀገር ይገባል።
ለዚህም ዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴን በመከተል እንዲሁም የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ አለመቻሉ በዋናት የሚጠቀስ ምክንያት እንደሆነ ባለሙያዎች ሲያነሱ ይደመጣል። ታድያ በአሁኑ ወቅት ግብርናን መሰረት ያደረገው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚን ለማሻሻል እና በምግብ ሰብል እራስን ለመቻል የግብርና ሜካናይዜሽን መጠቀም የግድ ሆኗል። የግብርና ምርቶችን በብዛትና በጥራት ለማምረት የሚያስችል እምቅ ሀብት ላላት ኢትዮጵያ በተለይም የግብርና ሜካናይዜሽን ምርትና ምርታማነትን ለማሻሻል ጠቀሜታው የጎላ ነው።
ለዘመናት ባህላዊ የአስተራረስ ዘዴን እየተከተለ ያለው የሀገሪቱ ግብርና ዘርፍ አዝጋሚ የሆነውን ዕድገት ትርጉም ባለው መንገድ መቀየር እንዲቻል የግብርና ሜካናይዜሽን ሥራ ተጀምሯል። ለዚህም በቀዳሚነት የሚጠቀሰው ኬኛ የእርሻ መሳሪያዎች ማምረቻና አጠቃላይ ንግድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር አንዱ ነው። ማህበሩ የተቋቋመበትን ዓላማ እና አጠቃላይ ለግብርናው ዘርፍ ምን አዲስ ነገር ይዞ መጣ በቀጣይስ ምን ይጠበቃል የሚሉ ጉዳዮችን አንስተን ለአንባቢ ለማጋራት ወደን የዕለቱ የስኬት እንግዳችን እንዲሆን ፈቅደናል።
በኦሮሚያ መንግሥት እና በግል ባለሀብት ጥምረት በ2010 ዓ.ም የተመሰረተው ኬኛ የእርሻ መሳሪያዎች ማምረቻና አጠቃላይ ንግድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በ50 ሚሊዮን ብር የተቋቋመ ስለመሆኑና የተቋቋመበት ዓላማም በሀገሪቷ ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረው ባህላዊ የአስተራረስ ዘዴ ለመቀየር በሚል እሳቤ መሆኑን የገለጹት የማህበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ፉሮ በቀታ ናቸው።
አቶ ፉሮ ሲያስረዱም የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት በማሳደግ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑና ሀገሪቷ በምግብ ሰብል እራስዋን እንድትችል ማድረግ የኩባንያው ቀዳሚ ዓላማ ነው። ምክንያቱም እስካሁን የተመጣበት በበሬ ማረስ ምርትና ምርታማነት ሊጨምርና ሊያሻሽል አልቻለም። አርሶ አደሩም ጊዜና ጉልበቱን ከመጨረስ ባለፈ የሚፈለገውን ያህል ውጤታማ ሲሆን አልታየም። ስለዚህ ይህን ሁኔታ መቀየር የሚያስችል አሰራርን በመዘርጋት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ድርጅቱ እንዲቋቋም ማድረግ ችሏል።
ድርጅቱ በዋናነት ራዕይ አድርጎ የተነሳው በሀገሪቱ ብሎም በምስራቅ አፍሪካ ታዋቂና ጥራቱን የተጠበቀ የእርሻ መሳሪያዎችን በማምረት ለተጠቃሚዎች ማቅረብ ነው። በአሁኑ ወቅትም ይህን ታላቅ ራዕይ ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛል። ድርጅቱ ሀገሪቷ በምግብ ሰብል እራሷን እንድትችል ለማድረግ በተለይም የእርሻ ስርዓቱን በማዘመን ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ያደርጋል። ምርትና ምርታማነት ሲጨምር ደግሞ በምግብ ሰብል እራስን መቻል ይቻላል ብሎ ያምናል።
እስካሁን ባለው ሂደትም ድርጅቱ የተለያዩ ተግባራትን ማከናወን ችሏል። ከእነዚህም መካከል በክልሉ መንግሥት ውሳኔ በዓለም የእርሻ መሳሪያዎች አምራችና ታዋቂ ከሆነው በአሜሪካ ከሚገኘው ጆኢንደር ኩባንያ ጋር ውል በመግባት የተለያዩ የእርሻ መሳሪያዎች እንዲገቡ አድርጓል። ወደ ሀገር ውስጥ ካስገባቸው የእርሻ መሳሪያዎች መካከልም 1ሺህ737 የሚደርሱ ትራክተሮች እና 80 አጭደው መውቃት የሚችሉ ኮምባይነር የእርሻ መሳሪያዎች ይገኙበታል።
የእርሻ መሳሪያዎቹም በዋናነት በኦሮሚያ ክልል በሜካናይዜሽን ለተደራጁ ሥራ አጥ ወጣቶች ተደራሽ ሲሆን በዚህም መሰረት ከ2ሺህ415 በላይ የሆኑ ወጣቶች የዚሁ ዕድል ተጠቃሚ ሆነዋል። ከዚህ በተጨማሪም ግንባር ቀደም ተብለው የተመረጡ 1ሺህ392 አርሶ አደሮችን የዕድሉ ባለቤት መሆን ችለዋል። ተግባራዊነቱም ከ30 እስከ 40 በመቶ የሚሆነውን የእርሻ መሳሪያዎች ዋጋ በባንክ መቆጠብ እንዲችሉና ቀሪውን ድርጅቱ በብድር በማድረግ አርሶ አደሮቹ የእርሻ መሳሪያዎች ባለቤት እንዲሆኑ አድርጓል። ከዚህ ባለፈም 53 ለሚደርሱ ቋሚና የኮንትራት ሠራተኞች የሥራ እድል ፈጥሯል።
በሜካናይዜሽን የተደራጁ ወጣቶችና አርሶ አደሮች የእርሻ መሳሪያዎቹን ተጠቅመው በማምረታቸው ምርትና ምርታማነታቸው አድጓል። ገቢያቸው ዕለት ከዕለት እየጨመረ መጥቷል። ከዚህ ባሻገርም በቴክኖሎጂ ሽግግር የላቀ ተጠቃሚ ሆነዋል። በተለይም የፈረስ ጉልበታቸው ከ100 በታች የሆኑ የትራክተር አካላትን ከውጭ በማስመጣት ሻሸመኔ በሚገኘው ማዕከል በድርጅቱ ሰራተኞች ተገጣጥሞ ለተጠቃሚዎች ተደራሽ በመሆኑ በርካቶች የዕድሉ ተጠቃሚ ከመሆን ባለፈ ለሌሎች የማስተዋወቅ ሥራ ተሰርቷል።
አቶ ፉሮ አያይዘውም ትራክተሮችን ጨምሮ የተለያዩ የእርሻ መሳሪያዎችን በሀገሪቱ የመገጣጠም ሥራ ቀጣይነት የሚኖረው ሥራ ይሆናል ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪም የመስመር መዝሪያ፣ የከብቶች መኖ ማሰሪያ፣ የመስኖ ሞተር ፓምፖችን በማስመጣት ለተጠቃሚዎች ተደራሽ ለማድረግ ድርጅቱ በእንቅስቃሴ ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የእርሻ መሳሪያዎች አካላትን በተለይም የፈረስ ጉልበታቸው ከ100 እና ከዛ በታች የሆኑ አካላትን እስካሁን ከውጭ ሀገር በማስመጣት በሀገር ውስጥ እየተገጣጠመ ያለ ሲሆን በቀጣይ እነዚህን አካላት በሀገር ውስጥ በማምረት ትራክተሮችን ሙሉ ለሙሉ በሀገር ውስጥ ለማምረት ታስቦ እየተሰራ ነው። ይህም የድርጅቱ አንኳር ጉዳይ በመሆኑ በቀጣይ ሀገሪቷ በምግብ ሰብል እራሷን እንድትችል ለማድረግ አይነተኛ ሚና ይጫወታል።
ድርጅቱ ዘመናዊ የእርሻ መሳሪያዎችን ከውጭ በማስመጣት በሀገር ውስጥ ተገጣጥመው ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እንዲሆኑ ሲያደርግ የተለያዩ ምቹ ሁኔታዎች ነበሩ። ከእነዚህም መካከል መንግሥት ዕቃዎቹን ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ የወሰነው ውሳኔ እና የሰጠው ፈቃድ ለተግባራዊነቱ ትልቅ አስተዋጽኦ የነበረው መሆኑን አቶ ፉሮ አንስተዋል። ከዚህም ባለፈ ለአርሶ አደሮችና ለወጣቶች ብድር የማመቻቸት ሥራ በመንግሥት በኩል የተመቻቸ በመሆኑ አርሶ አደሮቹ የእርሻ መሳሪያዎቹን በቀላሉ እያገኙ ነው ። አሁንም መንግሥት በተለይም የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ለግብርናው ዘርፍ በከፍተኛ ተነሳሽነት ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ በቁርጠኝነት እየሰራ ይገኛል።
ከክልሉ መንግሥት በተጨማሪም የኦሮሚያ ክልል ግብርናና የተፈጥሮ ሀብት ቢሮ፣ በፋይናንስ በኩልም ባንኮች ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ። የመርከብ ድርጅትም እንዲሁ በሚሰጠው የጭነት አገልግሎት እንዲሁም የጉምሩክ ኮሚሽን የኦሮሚያ ብድርና ቁጠባ እና ሌሎችም ከፍተኛ ትብብር ከሚያደርጉት መካከል ተጠቃሽ ናቸው። ድርጅቱ ተቋማቱ እያደረጉት ባለው ትብብርና ቅንጅት ውጤታማ ሥራዎችን በማከናወን በክልሉ ምርትና ምርታማነትን ትርጉም ባለው መንገድ ማሻሻል ችሏል። አርሶ አደሮችም ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ ችለዋል።
ድርጅቱ ምንም እንኳን በነበረው ጉዞ የገጠሙት ተግዳሮቶች ቢኖሩም በተለይም ሀገራዊ የሆነውና ትልቅ ማነቆ የሆነውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመቅረፍ መንግሥት ቅድሚያ ትኩረት ሰጥቶ እየተፈታ ሲሆን፤ ከኮረና ቫይረስ መከሰት ጋር ተያይዞም መሳሪያዎቹ ከሚመረቱበት ቦታ በፍጥነት አለመድረስ ችግሮች ነበሩ።
ኬኛ የእርሻ መሳሪያዎች ማምረቻና አጠቃላይ ንግድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር እስካሁን ባለው የሥራ እንቅስቃሴ በአብዛኛው ተደራሽ እየሆነ ያለው በኦሮሚያ ክልል ነው። በአማካኝ 99 በመቶ በሚባል ደረጃ የእርሻ ማምረቻ መሳሪያዎቹን እያቀረበ የሚገኘው በኦሮሚያ ክልል ቢሆንም ከ2012 ጀምሮ ግን እንደ ሀገር ከፍተኛ ፍላጎት እየታየ መምጣቱን ተከትሎ በመላው ሀገሪቱ ተደራሽ ለመሆን እየሰራ ነው። በሁሉም ክልሎች ተደራሽ መሆን ካልተቻለ ግን የሚፈለገው ውጤት እንደማይገኝ አቶ ፉሮ ይናገራሉ ።
ድርጅቱ ምንም እንኳን ከፍ ያለ ትርፍ ማግኘትን ዓላማው አድርጎ የተነሳ ድርጅት ባይሆንም የተሻለ ገቢ ለማግኘት በሚያደርገው ጥረት ካፒታሉ እያደገ መጥቷል ። ይሁንና ማህበረሰቡን በማገልገል አርሶ አደሩ ተጠቃሚ እንዲሆንና በምግብ ራስን ለመቻል እየሰራ ያለው ድርጅት ዓላማው ትልቅ ነው። በተለይም አነስተኛ ማሳ ያላቸውን አርሶ አደሮች ህይወት ለማሻሻልና ለመቀየር የሚረዳ መሆኑም ይታመናል።
ከመሬት ማለስለስ እስከ ምርት መሰብሰብና ማጓጓዝ ድረስ ባለው ሂደት ለአርሶ አደሮች እገዛ በማድረግ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ከፍተኛ ጥቅም የሚሰጠውን የግብርና ሜካናይዜሽን ለመጠቀም ግልፅ አቅጣጫ አስቀምጦ እየሰራ ነው። በዚሁ እንቅስቃሴም በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ ከውጭ የሚገባውን የግብርና ምርት በሀገር ውስጥ ለመተካትና ሰፊ የሥራ እድል ለማመቻቸት ትኩረት ተሰጥቷል።
ለአገሪቱ ሁለንተናዊ እድገት ወሳኝ የሆነውን ግብርና በማዘመን አርሶ አደሩ በፍጥነት በጥራትና በስፋት እንዲያለማ በተያዘው ግብ በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትሩ በተሰጠው አገራዊ አቅጣጫ መሰረት የሜካናይዜሽን ልማትን በኦሮሚያ ክልል ለማስፋፋት ጥረት እየተደረገ ይገኛል። በመሆኑም ዘርፉን ለመደገፍ በተለያየ አቅጣጫ ርብርብ እየተደረገ ሲሆን በተለይም ለአርሶ አደሩ ከቀረጥ ነፃ የሆኑ ዘመናዊ የእርሻ መሳሪያዎችን በማቅረብና ብድር በማመቻቸት ምርታማ እንዲሆን እየተሰራ ነው።
ድርጅቱ እያቀረበ ባለው የእርሻ መሳሪያ በርካታ ሥራ አጥ ወጣቶች ሥራ ከመፍጠር ባለፈ ሀብት መፍጠር ችለዋል። አርሶ አደሮችም ምርትና ምርታማነታቸው እየጨመረ የመጣ በመሆኑ በአሁኑ ወቅት ፍላጎቱ በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ መጥቷል። ፍላጎትና አቅርቦቱን ለማጣጣምም እየተሰራ እንደሆነ የጠቆሙት አቶ ፉሮ፤ የሜካናይዜሽን ሥራ ገና ያልተነካና ያልተሰራበት በመሆኑ ይህንንም አጠናክረን በመቀጠል በሀገሪቷ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በምግብ ራስን መቻል ይቻላል ሲሉ ተናግረዋል ።
ኬኛ የእርሻ መሳሪያዎች ማምረቻና አጠቃላይ ንግድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ከፍተኛውን ድርሻ ይዞ ያለው መንግሥት ሲሆን ሌሎች የግል ባለሀብቶችም በውስጡ ይገኛሉ። መንግሥትን በመወከል የሻሸመኔ ከተማ አስተዳደር ፤ ከግል ባለሀብት ደግሞ በሀገሪቷ ታዋቂ የሆነው ገደብ ኢንጂነሪንግ ባለድርሻ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል። በቀጣይም መንግሥት አሁን ላይ የያዘውን ድርሻ ይዞ ሌሎች ግለሰቦች እንዲሳተፉና ካፒታሉን ማሳደግ እንዲቻል ወደ ሼር ካምፓኒነት ለማሳደግ በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛል።
አርሶአደሩ በመካናይዜሽን እርሻ ጊዜና ጉልበቱን ቆጥቦ ምርታማ እንዲሆን ሰፊ ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው፤
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሰኔ 8/2013