ይዞታቸው ጥሩ ሆኖ ነገር ግን በእርጅና ምክንያት ገጽታቸው ተበላሽቶ፣የውስጣቸውም ንጽህና ተጓድሎ የሚያስቆጩ ጥቂት የማይባሉ ህንፃዎችን በከተሞች ውስጥ እንታዘባለን።በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ለህዝብ አገልግሎት መስጠታቸው ደግሞ ይበልጡን አስገራሚ ያደርገዋል።ከተሞች ገጽታቸው እየተለወጠ ባለበት በዚህ ወቅት እንዲህ ያሉ ህንፃዎች መኖራቸው ይበልጥኑ ባለቤት የላቸውም እንዴ የሚል ጥያቄ እንዲነሳ ያደርጋል።በእንክብካቤና ጥበቃ ጉድለት ለብልሽት የሚዳረግ ህንፃም ሆነ የተለያየ መገልገያ በአብዛኛው ባለቤት የሌለው እንደሆነም ይገመታል።ነገር ግን ባለቤት እያላቸው በግዴለሽነት፣ በአሰራር መንዛዛትና በተለያየ ምክንያት የሚጎዱ፣ከጥቅም ውጭ የሚሆኑም አይጠፉም።እንዲህ ያሉ ችግሮች በመንግሥት ወይንም በጋራ በሚተዳደሩ ንብረቶች ላይ ጎልቶ ይስተዋላል።
ከነአባባሉስ ‹‹ የፉክክር ቤት ሳይዘጋ ያድራል›› አይደል የሚባለው ።የእከሌ ሥራ ነው።የእከሌ ኃላፊነት ነው የሚሉ የተለመዱ አካሄዶች ጉዳታቸው ማመዘኑ ያረጁ ህንፃዎች ምስክር ናቸው።እነዚህ በፉክክርና በአሰራር ጉድለት ለጉዳት የሚዳረጉት ንብረትነታቸው የመንግሥት ቢሆንም የሚገለገልባቸው ደግሞ ህዝብ ነው።ለትውልድም እየተሸጋገሩ አገልግሎታቸው ቀጣይ ነው።ለአብነትም እንደ ጤና፣ ትምህርትና የተለያዩ የህዝብ ማህበራዊ አገልግሎት መስጫዎችን መጥቀስ ይቻላል።ምንም አንኳን ጥበቃው የአገልግሎት ሰጭው አካል ቢሆንም የተገልጋዩም ጭምር መሆን ይኖርበታል።በአሁኑ ጊዜ ለሰራተኛውም ሆነ ለተገልጋዩ ምቾት የሌላቸውን በመቀየር የህዝብ መገልገያ የሆኑ ተቋማትን ለማዘመን ጥረቶች ተጀምረዋል።
በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በየክፍለ ከተማው ያለውን እንቅስቃሴ መጥቀስ ይቻላል።ጥቂት ካልሆኑ በስተቀር አብዛኞቹ ክፍለ ከተሞች በአንድ ቦታ አገልግሎት መስጠት የሚያስችላቸውን ህንፃ ገንብተው ተደራሽ መሆን ከጀመሩ ሰነባብተዋል።ምድረ ግቢውንና ውስጡን በተለያየ ዕፅዋትና አበባ በማስዋብ ሳቢ የሆነ እይታ እንዲኖረውም ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው።እንዲህ ያሉ አሰራሮች ለተገልጋዩ ብቻ ሳይሆን አገልግሎት ሰጭ ሠራተኞችም በምቹ የሥራ ሁኔታ ውስጥ መሆናቸው የአገልጋይነት ስሜት እንዲኖራቸው ያስችላቸዋል።
ክፍለ ከተሞችን እንዲህ ለአብነት አነሳን እንጂ ሌሎችም የህዝብ አገልግሎት መስጫ ተቋማት በተመሳሳይ ዘምነው ተደራሽ እንዲሆኑ ያለፉ ክፍተቶችን የሚያርም ሥራ በአዲስ አበባ ከተማ በየክፍለ ከተሞች ይበል የሚያስብሉ እርምጃዎች በመወሰድ ላይ ይገኛል።የህዝብ አገልግሎት መስጫ ተቋማት በወቅቱ እንዲጠገኑና እንዲታደሱ፣ ግንባታም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ እንዲገነባና የማስፋፊያ ሥራም እንዲሰራ በአጠቃላይ ተቋማት በሚሰጡት አገልግሎት ብቻ ሳይሆን፣ከተማዋን የሚመጥኑ ገጽታቸውና ይዞታቸው ጥሩ የሆኑ ህንፃዎች እንዲኖሩ ለማድረግ፣ በተመሳሳይም በውስጣቸው ያሉ የቢሮ መገልገያዎች አብረው እንዲዘምኑ ተከታትሎ የሚሰራ በየክፍለ ከተሞቹ የመንግሥት ህንፃና ንብረት አስተዳደር ተቋቁሟል።
በአራዳ ክፍለ ከተማ ተገኝተን የጽህፈት ቤቱን እንቅስቃሴ እና የተሰሩ ሥራዎችን በተመለከተ የአራዳ ክፍለ ከተማ መንግሥት ህንፃና ንብረት አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ ከሆኑት አቶ ዘውዱ በቀለ ጋር ቆይታ አድርገናል።
እንደ አቶ ዘውዱ ገለጻ ጽህፈት ቤቱ በ2011ዓ.ም በአዋጅ የተቋቋመ ሲሆን፣በዋናነት ቀልጣፋና ዘመናዊ አገልግሎት ለመሥጠት እንዲቻል የመንግሥት ህንፃዎችና ንብረቶች በአግባቡ ተይዘው ጥቅም ላይ እንዲውሉና አገልግሎቱም እንዲዘምን ለማስቻል ክትትልና ቁጥጥር የሚያደርግ አካል ነው።ጽህፈት ቤቱ ከመቋቋሙ በፊት ከህንፃ ግንባታ ጀምሮ በንብረት ግዥ ላይ ያለው አሰራር ወጥ ባለመሆኑ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ይባክን እንደነበር ተደርሶበታል።ከደመወዝ ውጭ ያለው የሥራ ማስኬጃ በአብዛኛው ግዥ ላይ ነው የሚውለው።በጀት በመመደብ ብቻ የዕቃው አስፈላጊነት ሳይረጋገጥ በየዓመቱ ግዥ ይፈጸማል።ወጨው ከፍተኛ ሆኖ ጥቅሙ ግን አነስተኛ ነው።የህንፃ ግንባታውም በተመሳሳይ ትኩረት አልተሰጠውም።
በአሁኑ ጊዜ የከተማ አስተዳደሩ የአገልግሎት መስጫዎች አብዛኞቹ በኪራይ ቤት ውስጥ ነው የሚገኙት።ይህን ማስተካከል ይገባል።ጽህፈት ቤቱ እነዚህን ሁሉ ታሳቢ ባደረገ መልኩ ነው የተደራጀው።ጽህፈት ቤቱ ከተቋቋመ ጀምሮ የተለያዩ ተግባራት አከናውኗል።ከዚህ አንዱ በግንባታ ዘርፍ የሚከናወነው ሲሆን፣በኪራይ ቤት ውስጥ በተበታተነ ሁኔታ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት በአንድ ቦታ በቅልጥፍናና በዘመናዊ አሰራር የአንድ ማዕከል አገልግሎት በመስጠት ተደራሽ እንዲሆኑ በከተማ አስተዳደሩ ደረጃ በተያዘ ዕቅድ በከተማዋ በሁለት አቅጣጫዎች ግንባታዎች እንዲከናወኑ የቅድመ ዝግጅት ሥራ ተጠናቅቋል፡አንደኛው ግንባታ በከተማዋ 22 ተብሎ በሚጠራው አካባቢ 64 ሄክታር ላይ ግንባታው የሚከናወን ሲሆን ብዛት ያላቸው ተቋማት እንዲኖሩት ታሳቢ ያደረገ ነው።ሁለተኛው ተክለሃይማኖት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገነባ ሲሆን፣ የዲዛይን ሥራው በመከናወን ላይ ይገኛል።ግንባታቸውም በ2014ዓ. ም ይጀመራል።በአገልግሎት ላይ ያሉት ህንፃዎችም ጠባብ በሆነ ቦታ ላይና በወረዳ አስተዳደር 103 ሠራተኞችን ታሳቢ ተደርጎ ነው የተገነባው።በአሁኑ ጊዜ ግን የወረዳ አስተዳደር ሰራተኛ ቁጥር ወደ 400 ከፍ ያለ መዋቅር ነው ያለው።የአዲስ አበባ ከተማ ዕድገት ደግሞ በጣም እየተፋጠነ ነው።በከተማዋ በተለያየ ኢንቨስትመንት የተሰማራው ባለሀብት በሚያመነጨው ሀብት ልክ በዘመናዊ ህንፃ ውስጥ ቀልጣፋ አገልግሎት ማግኘት ይኖርበታል።የሥራ አካባቢው ለተገልጋዩም ሆነ ለአገልጋዩ ሳቢ መሆን ይኖርበታል። የህንፃ ጥገና ፣ እድሳትና ማስፋፊያም እንዲሁ በወቅቱ እንዲከናወኑ ካስፈለገ የሚመራ አካል ያስፈልጋል።በዘፈቀደም መከናወን የለባቸውም።እስከዛሬ በነበረው አሰራር የግንባታ ፣ የጥገና፣ የዕድሳትና ማስፋፊያ ሥራዎች በጥናት ላይ የተመሰረቱ ባለመሆናቸው በዘርፉ የበዛ ክፍተት ይስተዋል ነበር።ከሁለት ዓመት በፊት ተቋቁሞ ወደ ሥራ የገባው ጽህፈት ቤት በግንባታው ዘርፍ የፍሳሽ፣የኤሌክትሪክ፣የግንባታና የተለያየ ሙያ ያላቸውን በመያዝ ተደራጅቶ ሥራውን በማከናወን የነበረውን ክፍተት መሠረት ባደረገ ከፍተኛ ሀብት የሚፈስበትን ግንባታ ለማስቀረት ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል።በዚሁ መሠረት ጽህፈት ቤቱ ማስፋፊያና አዲስ ግንባታም ሲያስፈልግ ለግንባታ የሚሆን ቦታ ለይቶ፣አስፈቅዶና አዘጋጅቶ ለግንባታ ክፍል ያቀርባል።ከጽህፈት ቤቱ ዕውቅና ውጭ ማንኛውም የመንግሥት ተቋም በራሱ የሚያከናውነው ነገር አይኖረውም።
በማዕከል እንዲሰራ ያስፈለገበት ዋናው ምክንያት ብክነትን ለማስቀረት ብቻ ሳይሆን የተሻለ ግንባታም ለማከናወን ሲባል ነው።በክፍለ ከተማው ውስጥ ከሚገኙ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት መካከል ለአገልግሎት ምቹ ያልሆነ ካጋጠመና በኪራይ ቤት ውስጥ እንዲሰራ ከታመነበትም አስፈላጊነቱን አረጋግጦ ፈቃድ ለሚሰጠው አካል የሚያሳውቀው፣በጀትም አስፈቅዶ ኪራዩ እንዲከናወን የሚያደርገው ጽህፈት ቤቱ ነው።በተጨማሪም አስፈላጊ ግብአቶችን ያሟላል።ጽህፈት ቤቱ በንብረት አያያዝ ላይም እንዲሁ ተገቢውን ትኩረት በመስጠት ቀልጣፋና አስፈላጊ የሆነ የንብረት ግዥ እንዲፈጸም ያደርጋል።ጽህፈት ቤቱ በዚህ መልኩ 10 ጤና ጣቢያዎች፣30 ትምህርት ቤቶች፣10 የወረዳ አስተዳደሮችና አንድ የፖሊስ መምሪያ ተቋማት እድሳትና ጥገና ሲያስፈልጋቸው በጽህፈት ቤቱ ሥር የተደራጀው የመሐንዲስ ክፍል በሚያደርገው ክትትልና ድጋፍ ሥራው ይታያሉ።ህንፃዎቹ ውጫዊና ውስጣዊ ይዘታቸው ከታየ በኋላ በመሐንዲሶቹ ውሳኔ መሠረት ጥገናው ወይንም ዕድሳቱ ከፍተኛም ሆነ መጠነኛ ይከናወናል።ባለሙያዎቹ አስፈላጊነቱን ካላመኑበትም ባለበት ይዞታ እንዲቀጥል ይደረጋል።በባለሙያዎች እገዛ መከናወኑ አላስፈላጊ የሆነ ወጪን ለመቀነስና ብክነትን ለማስቀረት ሲሆን፣የጥገና ወይንም የእድሳት ጥያቄው በተቋማት ሊቀርብ ይችላል።ነገር ግን ጽህፈት ቤቱ በራሱ በሚያደርገው ዳሰሳ ይከናወናል።ሥራዎች ከተለዩ በኋላም አስፈላጊው በጀት ተይዞላቸው የሚከናወኑ በመሆናቸው በወቅቱ የግንባታ ክፍል እንዲያውቀው ይደረጋል።
የህንፃው ደህንነት እንዲጠበቅ የሚደረገው ከአጥሩ ጀምሮ በመሆኑ ማራኪና ሳቢ እንዲሆን የግቢውን አፀድ ሁሉ ታሳቢ ያደረገ ሥራ ነው የሚሰራው።ለአብነትም ጽህፈት ቤቱ የሚገኝበት አራዳ ክፍለ ከተማ ከመግቢያው በር ጀምሮ በየክፍሉ አረንጓዴ ልማትን ማዕከል ባደረገ አገልጋይንና ተገልጋይን የሚስብ ሥራ መሰራቱንና ተሞክሮውንም ወደ ጤና፣ትምህርትቤቶችና የተለያዩ የህዝብ መገልገያዎች የማስፋት ሥራ መጠናከሩን የጽህፈት ቤት ኃላፊው አስረድተዋል።
አሁን ካለው የከተማዋ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የሚራመድ የዘመነ አገልግሎት ለመስጠት ረዘም ያለ ጊዜ የሚወስድ ቢሆንም ሥራዎች ተጀምረዋል ያሉት አቶ ዘውዱ፤በክፍለ ከተማው በሚገኙ 10ሩም ወረዳዎች ባለሰባት ወለል (ፎቅ) ህንፃዎች ለመገንባት የመሬት ልየታ ሥራ መከናወኑንም ጠቁመዋል።
እርሳቸው እንዳሉት የግንባታ ፍላጎት እየጨመረ ነው።ለአብነትም አራዳ ክፍለ ከተማ ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች ቁጥር እስከ 1ሺህ 200 ይደርሳል።በመዋቅሩ ግን እስከ 1800 ይደርሳል።በመሆኑም ተጨማሪ የሥራ ክፍሎች ያስፈልጋሉ።ያለውን ነባራዊ ሁኔታ እየለዩ የማስተካከል ሥራ ይከናወናል።
ጽህፈት ቤቱ የግንባታ፣ የዕድሳት፣ የጥገናና የማስፋፊያ ሥራዎችን በምን ያህል ቅልጥፍና እንደሚያከናውንም አቶ ዘውዱ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ጽህፈት ቤቱ በተቻለው መጠን የተቀላጠፈ ሥራ ይሰራል።ነገር ግን ቅድመ ሁኔታዎች መዘጋጀት አለባቸው።በየዓመቱ ዕቀድ ይቀርባል ፤ በጀት ይያዛል።ይሄ ከተሟላ ሥራዎች በወቅቱ ይከናወናሉ።በዚሁ መሠረትም በአራዳ ክፍለ ከተማ ባለፈው ዓመት ለ30 ትምህርት ቤቶች የዕድሳትና የጥገና ሥራ አከናውኗል።ትምህርት ቤቶቹ ለረጅም ጊዜ ያለጥገና በመቆየታቸው በገንዘብ፣ በጊዜና በሥራ ዋጋ አስከፍለዋል።በወቅቱ ተከናውኖ ቢሆን ኖሮ ግን ችግሩ አሁን ላይ አይነሳም ነበር።በነበረው አሰራር ህንፃዎች ይገነባሉ እንጂ የሚያስተዳድራቸው አልነበረም።ባለቤት መፈጠሩ እንዲህ ያሉ ችግሮችን ለማስወገድ ይረዳል።
ጽህፈት ቤቱ በተጨማሪ ጤና ጣቢያዎችንና የወረዳ አስተዳደሮችን በተለይም ለሌሎች ወረዳዎች ሞዴል ይሆናሉ ተብሎ የታሰቡ ወረዳዎች የማደስና የማስተካከል ሥራ ሰርቷል።በልዩ ሁኔታ የተሰሩት ሶስት ወረዳዎች ከዕድሳት ባለፈ ለተገልጋይ ምቹ መሆናቸው ግምት ውስጥ ገብቷል።በቀጣይ ተሞክሮውን በማስፋት የተጠናከረ ተግባር ይከናወናል።በወቅቱ እድሳትና ጥገና ማድረግ ለህንፃዎች ዋጋ መጨመር የራሱ አስተዋጽኦ ስለሚኖረው ጽህፈት ቤቱ ይህንም ታሳቢ ያደረገ ሥራ ነው የሚያከናወነው።የአገልግሎት መስጫ ተቋማት በውስጣቸው የሰራተኛው መዝናኛ፣ የስፖርት ማዘወተሪያና የህፃናት ማቆያ እንዲኖራቸው በማድረግ ረገድም ጽህፈት ቤቱ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል።
እንደ አቶ ዘውዱ ማብራሪያ ጽህፈት ቤቱ ጎን ለጎን የንብረት ግዥና አያያዝ ሥርዓቱ በምን ደረጃ ላይ እንደሆነና ክፍተቶቹንም ለይቶ አሰራሩን ለማዘመን በጽህፈት ቤቱ ባደራጀው ዳይሬክቶሬት እና ኦዲት ክፍል እያከናወነ ባለው ተግባርም በሥልጠና በታገዘ ከአግባቡ ወጭ የሆነውንና ያልሆነውን ንብረት የመለየትና የማስወገድ ሥራ እየሰራ ነው።ጽህፈት ቤቱ በዚህ ሥራ መለየት የቻለው አብዛኛው የመንግሥት ንብረት በግዥ ሥርዓት ላይ ነው ያተኮረው።የተገዛው ንብረት ለታለመለት ዓላማ ስለማዋሉ የሚከታተል አካል ባለመኖሩ የሚባክነው ንብረት የበዛ ነው።ጽህፈት ቤቱ ከመቋቋሙ በፊት የንብረት አስተዳደር በፋይናንስ ሥር የተደራጀ በመሆኑ ትኩረት ሳያገኝ ቆይቷል።የወረቀት ሥራዎች በቴክኖሎጂ የመተካት በ2017ዓ.ም የመካከለኛ ዘመን ዕቅድ የንብረት አያያዝን ለማዘመን ነው የታቀደው።የሚወገዱ ንብረቶችን በወቅቱ በማስወገድ፣ግዥም ባግባቡ እንዲከናወን፣በሥራ ላይ ያሉትም በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውሉ በጽህፈት ቤቱ በኩል ተከናውኗል።
በከተማ አስተዳደሩ ሥር በሚገኙ ክፍለ ከተሞች የተደራጀው የመንግሥት ህንፃና ንብረት አስተዳደር ጽህፈት ቤት የጀመረውን የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ህንፃዎችና የውስጥ አገልግሎታቸውን የማዘመን ሥራ ከግብ ለማድረስ ለሥራው የሚያግዙ ግብአቶችና ባለሙያዎች ተሟልተው ሥራ ካልተሰራ የክፍሉ መቋቋም በራሱ ግብ እንዳልሆነ ግንዛቤ ሊያዝ ይገባል።ከአራዳ ክፍለ ከተማ የመንግሥት ህንፃና ንብረት አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ ጋር በነበረን ቆይታ ክፍላቸው ተንቀሳቅሶ የሚሰራበት የተሽከርካሪ እጥረት አለበት።ሌሎችም ሊፈቱ የሚገባቸው ነገሮችን አንስተዋል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሰኔ 8/2013