ኢትዮጵያ 14 የቅመማ ቅመም ዓይነቶችን ታመርታለች። ሰባቱ ደግሞ በየዓመቱ በቋሚነት ወደ ውጭ የምትልካቸው በውጭው ገበያም እጅግ ተፈላጊ መሆናቸውን ከኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን የገበያ መረጃና ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል። በተለይ እርድና ኮረሪማ ዋነኞቹ ተፈላጊዎች ናቸው። ከዚህ አንፃር አሁን ላይ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ገበያ ዋጋቸው ጭማሪ ማሳየቱንም ያመለክታል።
በባለስልጣኑ የገበያ መረጃና ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክቶር አቶ ኸይሩ ኑሩ እንደገለጹልን በዘንድሮ በጀት ዓመት 11 ወራት ውስጥም ከታቀደው 98 ነጥብ 76 ቶን ኮረሪማ ወደ ውጭ ተልኳል። ከዚህም 511 ሺህ 776 የአሜሪካ ዶላር ተገኝቷል። ይሄ ገቢ ከአምናው ጋር ሲነፃፀር በእጅጉ የተሻለ ሆኖ ተገኝቷል። የተገኘው የኮረሪማ ሽያጭ ገቢ አንድ ኪሎ ኮረሪማ 5 ከ 20 የአሜሪካ ዶላር ሲሆን ይሄ ሲመነዘር 215 ብር ገደማ ይደርሳል። አሁን ላይ የኮረሪማ ምርት በውጪም ሆነ በሀገር ውስጥ ገበያ እጅግ ተፈላጊ እየሆነ ነው። በዋጋም ቢሆን ከፊቶቹ ዓመታት ጋር ሲነጻጸር ዕድገት አሳይቷል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ ምርቱ በሀገር ውስጥና በውጭ ተፈላጊ እንዲሆንና ዋጋውም እንዲጨምር ካደረጉት ጉዳዮች መካከል የሕብረተሰቡ የምግብ አጠቃቀም ባህል እየተቀየረ መምጣት፣ ከውጪው ዓለም ጋር ያለው የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶች መጠናከር መሆኑ ይጠቀሳል። ዛሬ ላይ ኮረሪማን የሚገዙት 14 የውጭ ሀገራት መሆናቸውንና ቁጥራቸው መጨመሩ ማሳያ ነው። እነዚህ ቅመማ ቅመም ከሚገዙት ሀገራት ውስጥ አብዛኛዎቹ የኢሽያ ሀገራት ናቸው። ህንዶች፣ ፓኪስታን፣ የአውሮፓ ሀገሮች ይገኙበታል። የአረብ ሀገሮችም ምርቱን ይወስዳሉ። በአጠቃላይ በሀገራችን የሚመረቱት የቅመማ ቅመም ዓይነቶች 14 ቢሆኑም በየዓመቱ ሳያቋርጡ በተከታታይ ወደ ሀገራቱ የሚላኩት ግን ሰባት ናቸው።ከሰባቱ አንዱ ዘንድሮ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት የቻለው ኮረሪማ ነው። ዛሬ ላይ ዓለም አቀፋዊነትና ሀገራችን ያላት የውጭ ግንኙነት እየሰፋ በመምጣቱ ጭምር ከውጪ የሚመጣው የምርቱ ተጠቃሚ ቁጥር እየጨመረ መጥቷል። ከዋጋ አንፃርም ቢሆን በውጪም ሆነ በሀገር ውስጥ ገበያ ከፍተኛ ጭማሪ ያሳየበት ሁኔታ አለ። በተለይ በውጭ ገበያ ያለው ፍላጎት ከጊዜ ጊዜ በመጨመር በጣም ሰፊ እየሆነ ነው። አንዳንድ የውጭና የሀገር ውስጥ ገበያን በእኩልነት የሚያነጻጽሩ ህብረተሰብ ክፍሎች አሉ። ሆኖም የሀገር ውስጥና የውጭ ገበያ እኩል አይደለም። የዓለም ግብይት ስርዓቶች የሚያሳዩት የሀገር ውስጥ ዋጋና ወደ ውጭ የሚላከው ነው። ለአብነት የሀገር ውስጥ ቡና ዋጋ ለውጭ ከሚላከው በላይ ነው።
ከቅመማ ቅመም ውስጥም በርበሬን ጨምሮ ኮረሪማም የዋጋው ሁኔታ ተመሳሳይ ነው። ሆኖም መንግስት የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት የሚያደርጋቸው አንዳንድ የጎንዮሽ ማበረታቻ ድጋፎች አሉ። ለምሳሌ ወደ ውጭ የሚላኩት የውጪ ምንዛሪ ለማግኘት ሲባል በመላክ ሂደት የሚፈፅሙት የተጨማሪ እሴት ታክስ ክፍያ የለባቸውም። በመሆኑም የአንድ ኪሎ ኮረሪማ ዋጋ በአማካኝ 520 አካባቢ ነው የሚሸጠው። በእርግጥ ከዚህ ዋጋ በላይ የሚሸጡ አንዳንድ ሀገሮች አሉ። ደንበኝነት የፈጠሩት ደግሞ በኪሎ ከ300 ብር በላይ የሚሸጡበትም ሁኔታ አለ። ዞሮ ዞሮ አማካኝ መሸጫ ዋጋው ሲወሰድ 5 ብር ከ25 አያልፍም። ይሄ አማካኝ ዋጋ ካለ ከአምስት ብር በታች እንዲሁም በላይም የሚሸጥ ኮረሪማ መኖሩንም መመልከት ይቻላል።
የሀገር ውስጥ ኮረሪማ መሸጫ ዋጋ ከፍ ማለቱ በአሉታዊ ጎኑ ትርጉም አይሰጠውም። የሀገር ውስጥ የኢኮኖሚ መነቃቃት አንዱ አካል ነው ተብሎ ነው የሚወሰደው። ሆኖም የእኛ ምርት ሳይበቃ ቀርቶ ከውጪ የሚመጣ ከሆነ እንደ መድሃኒትና ነዳጅ ሀገር የማይጎዳበት ሁኔታ አይኖርም። ሆኖም ይሄ እንዳይሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል። አሁን ላይ ቀድሞ ምርታማነቱን በመጨመር ችግሩ የሚፈታበትም ስርዓት ተቀምጦ እየተሰራ ይገኛል። ለዚህም ኮረሪማን ጨምሮ ወደ ውጪ የሚላኩት ቅመማ ቅመሞች ቤንች ማጂ ዞን ተፋሰስን ይዘው በብዛት ይመረታል።
አርሶ አደሩም የቅመማ ቅመም ምርት ጥቅም እንዳለው ስላወቀ አብዝቶ በማምረቱ በአቅርቦትም እየጨመረ መጥቷል። በእርግጥ ኮረሪማን ጨምሮ ውድ የሚባሉት ቅመማ ቅመሞች ራሱን የቻለ ማሳ የሚፈልጉ ናቸው። በተለይ ጠባብ መሬት ባላቸው አካባቢዎች ፣ከሌሎች ቋሚ ሰብሎች እርሻ ጋር በተጓዳኝ አብረው ሊሰሩ የሚችሉ ናቸው። ለነዚህ በተለይም ተፈላጊ ለሆኑት ለሰባቱ ምርቶች እንደ ኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ከአምና ጀምሮ የግብይት ስርዓት ተፈጥሮላቸዋል ። መመሪያ ወጥቶ እንዲፀድቅ ወደ ግብርና ሚኒስቴር የተላከበት ሁኔታም አለ። ይሄ በቀጣይ ዓመት ስራ ላይ ይውላል ተብሎ ይታሰባል። ይሄው መስክ ከዚህ በፊት የግብይት ስርዓት እንዳልነበረው ዳሬክተሩ ያስታውሳሉ።
የግብይት ስርዓቱ አንዱ ፋይዳ የምርቱን ጥራት ማስጠበቅ ነው። ለምሳሌ ወደ ውጭ በሚላክ ቡና ላይ ከማሳ እስከ ኢንዱስትሪ በጥራት እንዲመረትና እንዲዘጋጅ ክትትልና ቁጥጥር የሚደረግ ሲሆን አርሶ አደሩን በማሰልጠንም ሆነ አስገዳጅ በሆኑ የህግ ማዕቀፎች የጥራት ቁጥጥር ይደረግበታል። ለምሳሌ በርበሬ ወደ ውጪ አውሮፓ ሀገር ከተላከ በኋላ ተመልሶ የመጣበት የአፍላቶክሲን በአጠቃላይ የአያያዝ ችግር ነበር። በእርጥበት ምክንያት የሚመጣው ሻጋታ ወደ መርዛማነት የሚቀየርበት አጋጣሚ ነበር። ይሄ ለሀገር ውስጥ ፍጆታ እንኳን ቢውልና ቢቀርብ በሕብረተሰቡ ጤና ላይ ጉዳት ያስከትላል። ሲመለስም እንዲቃጠል የሚደረገውም ለዚህ ነው። በአሁኑ ወቅት በሀገራችን የገበያ ጉድለቱን የሚከላከል ህግ ወጥቷል። ወደ ፊት ተግባራዊ ይሆናል ተብሎም ይጠበቃል።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሰኔ 7/2013