ለእስከዛሬው የኢትዮጵያ ታላቅነትና ገናናነት የአገር መከላከያ ሚና ትልቁን ስፍራ ይይዛል። አሁን አሁን አንዳንድ ደስ የማይሉ ነገሮች ቢያጋጥሙም (እንደ ግለሰቦች ከዲሲፕሊን ያፈነገጠ ተግባር ቆጥረን ልናልፋቸው የሚገቡ)፣ ይህ ወደ ፊትም የሚቀጥል ስለ መሆኑ መጠራጠር አይቻልም።
ኢትዮጵያ በአለም አቀፉ መድረክ እውቅናን፣ ዝናን፤ በሰላም ማስከበርና ማስጠበቁም ሰፈር ድልን፤ በተሳተፈችባቸው ወታደራዊ ተግባራት ሁሉ ስኬትን ስታስመዘግብ ኖራለች። ይህ ሁሉ የሆነው በጀግናው የሰራዊታችን፤ መከላከያችን ከፍተኛ መስዋእትነት ስለመሆኑ ሁሉም ያውቃል። የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ሁሴን ኦባማ እዚህ ኢትዮጵያ በመጡ ጊዜ በብሄራዊ ቤተመንግስት ቆይታቸው ወቅት ባደረጉት ንግግራቸው ደግመው ደጋግመው ያረጋገጡት፤ “ታፍ” ሲሉም የገለፁት እውነት ቢኖር ይኸው የመከላከያ ሰራዊታችን ዘመን ተሻጋሪ ጀግንነት ነው።
በሁሉም ዘንድ እንደሚታወቀው፣ ኢትዮጵያን ለመጎንተል፤ ከፍ ሲልም ለማዋረድ፣ ከዛም ሲያልፍ ለማፍረስና ለመቆጣጠር ያልሞከረ የለም። አንዳንዶቹም በአንድ ሽንፈት አላምን ብለው እንደ ውሀ ቀጂ በመመላለስ የሽንፈት ፅዋቸውን ሲጎነጩ ኖረዋል። ከእነዚህ የሽንፈት ፅዋ ተጎንጪዎች መካከልም አንዷ የአሉላ አባ ነጋ ክርን ደጋግሞ ያሻት፤ እያገላበጠም የቆላት ግብፅ ነች። ጣሊያንን በተመለከተ አድዋ ይናገር እንደሚባለው፤ ይህንን የግብፅን ጉዳይ በተመለከተም ጉራእ እና ጉንዲት ይናገሩ ብለን እናልፋለን።
የዛሬው ጽሑፍ መነሻ የታላቁ ህዳሴ ግድባችንን ማእከል ያደረገው፤ ወቅታዊው የኢትዮጵያና የግብፅ ጉዳይ ሲሆን እሱም “Ethiopian Military Buildup around Renaissance Dam” በሚል ርእስ ባለፈው ሰኞ ጁን 7, 2021 በራሳቸው በግብፆች ጋዜጣ (https:// english.aawsat.com ድረ-ገፅም ላይ ያገኙታል) ላይ ለንባብ የበቃ ፅሁፍ ነው።
ጽሑፉ ለንባብ የበቃበት አቢይ ምክንያት በቅርቡ የኢትዮጵያ አየር ኃይል አዛዥ ሜጀር ጀነራል ይልማ መርዳሳ በቅርቡ የሰራዊቱን አባላት ሲመርቁና የሽልማት ስነ-ስርአት ሲካሄድ የተናገሩትና ያስተላለፉት መልእክት ነው።
በስነ ስርአቱ ላይ ሜጀር ጀነራል ይልማ መርዳሳ በተለያዩ አገራዊና ወታደራዊ ጉዳዮች ላይ ንግግር ያደረጉ ሲሆን፤ በተለይም ለህዳሴው ግድብ ልዩ ትኩረት በመስጠት በግድቡ ላይ የሚቃጣ ማንኛውንም ጥቃት ለመከላከል አየር ኃይሉ ዝግጁ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው መልዕክት አስተላልፈዋል።
በዚሁ ማስጠንቀቂያ ንግግራቸው ውስጥ ከፍ ብሎ የተነሳው አቢይ ነጥብ የሚከተለውን ይመስል ነበር። ‹‹በህዳሴው ጉዳይ ላይ ምንም አይነት ወለም ዘለም እንደሌለ፣ ኃይላቸው ከመቼውም ጊዜ በላይ ሌት ተቀን በተጠንቀቅ ላይ እንደሆነ፤ የህዳሴውን ግድብ መንካት አይደለም በአካባቢው እንኳን ዞር የሚል አውሮፕላን ሊኖር እንደማይችል፤ ሲንቀሳቀስ ከተገኘም እዛው ፀጥ እንደሚደረግ›› ወዘተ በመጥቀስ የአየር ኃይሉን ዝግጁነት ተናግረዋል ።
ይህ የጀነራሉ ንግግር ወዲያውኑ፣ በተለይም በተለያዩ የግብፅ መገናኛ ብዙሀን በተለያየ መልኩ የተናፈሰ ሲሆን በጋዜጠኛ Asharq Al-Awsat አማካኝነትም በትኩረት በመተንተን ጉዳዩ ትኩረት እንዲያገኝ ለማድረግ ሞክረዋል።
የጀነራሉን ንግግር ተከትለው በተናፈሱት በእነዚህ መገናኛ አውታሮች ፕሮፓጋንዳ ጎልቶ ይወጣ የነበረው ድምፅና ይተላለፍ የነበረው መልእክት ኢትዮጵያ ግብፅን ልትመታ ዝግጅቷን ጨርሳ በመዛት ላይ ነች፤ ግብፅ አፀፋውን መውሰድ ሲገባት እጇን አጣጥፋ ቁጭ ብላለች። ይህ ደግሞ የግብፅን ህዝብ ያስጠቃል፤ ጥቅሙንም ያሳጣል በሚል መልእክት ሊጠቃለል የሚችል ሲሆን፤ የጋዜጣውም ሆነ የአንባቢያንኑ አስተያየት የግብፅን መንግስት፣ በተለይም አልሲሲን የሚያወግዝና በአስቸኳይም ከኢትዮጵያ በኩል ለተላለፈው መልእክት ምላሽ እንዲሰጥ የሚገፋፋ ነበር።
በፅሁፉ ላይ እንደ ሰፈረው የማህበራዊ ሚዲያዎች ተጨናንቀው ሰንብተዋል፣ የአገሪቱ የስራ ሀላፊዎች ደግሞ ድምፃቸውን አጥፍተዋል፤ በጋዜጣው ዝግጅት ክፍል በኩል የመንግስትን አቋም ለህዝቡ እንዲያስረዱ ቢጠየቁም ፍቃደኛ ባለመሆን ከምንም አይነት ምላሽ መስጠት ተቆጥበዋል።
እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ መንግስትም ሆነ ሰራዊቱ የማይመለከተውን ሲጠይቅ፣ የራሱ ያልሆነውን ሲመኝ ታይቶም ሆነ ተሰምቶ አይታወቅም። መጠየቅም ሆነ መመኘት አይደለም በማንም ጉዳይ ጣልቃ ገባ ተብሎ የታማ እንኳ ስለመሆኑ ምንም አይነት መረጃም ሆነ ማስረጃ የለም። ይሁን እንጂ ሁሌም ተንኳሽ፣ ያለ አቅሙ የሚንጠራራ ሀይል አያጣም። ከእነዚህም አንዷ ግብፅ ነች።
ግብፅ ሁሌም፣ በተለይም ከህዳሴው ግድባችን መጀመር በኋላ ጮክ ብላ ስትናገር ሰው ይሰማኛል ብላ እንኳ አስባ የምታውቅ አይመስልም። እፍረት የሚባል አታውቅም፤ ይሉኝታ የለም። አቅምን ማወቅ ብሎ ነገር አይታሰብም። ብቻ ሁሌም መጮህ ነው።
የግብፅን ጩኸት ከሌሎቹ ለየት የሚያደርገው በኢትዮጵያ ውስጥ አይደለም መከላከያ ሰራዊት ወፍ እንኳን ያለ እስከማይመስል ድረስ መፎከሯ ነው።
የወቅቱን ሁኔታ በተለይም ከወደ ግብፅ ያለውን ያዙኝ ልቀቁኝ በቅርብ የሚከታተል አድማጭ/ተመልካችም ሆነ አንባቢ አሳምሮ እንደሚያውቀው ግብፅ ሁሌም ስትፎክር “ድምጥማጣቸውን ነው የማጠፋው፣ በአንድ “በተን” (የኮምፒውተር ቁልፍ) ነው የምንደመስሳቸው፤ አንድ ውሀ ይነኩና” ወዘተ ወዘተ ነው የምትለው። እዚህ አበሻ አገር አይደለም ጦር ቁንጫ እንኳን ያለ እስከማይመስል ድረስ ነው ንግግሯ ሁሉ። ደስ የሚለው ነገር የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ሂደትና አሰራሩ እንደ ግብፅ ሁሉ የገበቴ ውሀ ይመስል የሚዋልል ሆኖ አለመገኘቱ ነው።
ባጭሩ ለማለት የፈለግነው የሰሞኑ የአየር ሃይላችን አዛዥ ሜጀር ጀነራል ይልማ መርዳሳን የ”አትንኩን!!!” ማስጠንቀቂያ ተከትሎ ከወደ ግብፅ አካባቢ የሚሰማው የፍርሀት ድምፅም ሆነ የሚታየው መርበድበድ ምንጩ እራሳቸው እንጂ ኢትዮጵያ አይደለችም። ኢትዮጵያ እንደ ምንጊዜውም ሁሉ “አትንኩኝ፤ ከነካችሁኝ ግን አይማረኝ . . .” አለች እንጂ ማንም ላይ አልደረሰችም። እራሷ ግብፅም እንደምታውቀው ሰው ላይ የመድረስ ታሪክም የላትም። ስለዚህ መፍትሄው አለመድረስ ነው እንጂ እደርስብሀለሁ፤ ግን እንዳትነካኝ ይሉ ነገር በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እድሜ ጠገብ ታሪክ ውስጥ የለም።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ሰኔ 7/2013