ግንቦት 30 ቀን 1933፤ ከፊት ገጹ ላይ ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በአውቶሞቢል ሆነው በአጀብ የሚሄዱበት ምስል ተሰይሟል። ይኸውም አርበ ጠባብ ቁመቱ 42፣ ስፋቱ ደግሞ 31 ሴንቲ ሜትር የሆነው ከራስጌው ላይ “አዲስ ዘመን” የሚል ሎጎ በጉልህ የታተመበት ብሔራዊ ጋዜጣ ነው። ባሰለፍነው ሳምንት 80ኛ አመቱን የደፈነው አዲስ ዘመን ጋዜጣ።
“አዲስ ዘመን ጋዜጣ” አዲስ ዘመን የሚለውን ሥያሜ ያገኘበትን ምክንያት በጋዜጣው የመጀመሪያው እትም ላይ ሲብራራ እንዲህ ተብሏል፤ “ይህ አዲስ ዘመን ተብሎ የተሰየመው ጋዜጣ ከዛሬ ጀምሮ ወደፊት ለመላው ለኢትዮጵያ ሕዝብ የረዳትነቱን ሥራ ይሠራ ዘንድ ተመሠረተ።”
የጋዜጣው ምሥረታ ኢትዮጵያ በ928 ወረራ ፈጽሞባት የነበረውን ፋሽስት ጣልያን ድል ማድረጓን ተከትሎ ንጉሠ ነገሥቱ ከስደት ወደ መንበራቸው ሲመለሱ ከከወኗቸው ቀዳሚ ተግባራት መካከል ተጠቃሹ ነው። ሥያሜውም የተወሰደው አፄ ኃይለሥላሴ ካደረጉት ንግግር ሲሆን፣ ይህም “ከማናቸውም አስቀድሞ ለሁላችሁ ልነግራችሁና ልትረዱት የምፈልገው ይህ ቀን ለአዲሲቱ ኢትዮጵያ የአዲስ ዘመን መክፈቻ መሆኑን ነው። በዚሁ በአዲሱ ዘመን ሁላችንም መፈጸም ያለብን አዲስ ሥራ ይጀመራል” የሚል ነበር።
ጋዜጣው መጀመሪያ ይታተም የነበረው በየሳምንቱ ሲሆን፣ ከ15 ዓመታት በኋላ ግን ወደ እለታዊ ጋዜጣነት ተሸጋግሮ እስከዚህ ጊዜ ድረስ መረጃን ተደራሽ በማድረግ በቀዳሚነት እየሰራ ያለ አንጋፋ ጋዜጣ ነው።
በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኀን ታሪክ ይልቁንም በኅትመት በኩል ሥማቸው ከሚነሳ ቀደምት ከሆኑና ሦስት መንግሥታትን ዘልቀው ካለፉ መካከል አንዱ የሆነው አዲስ ዘመን ጋዜጣ፤ በሀገሪቱ ብዙ ዘመናትን የተሻገረ ተወዳዳሪ ጋዜጣም የለውም።
የሕዝብን ጥያቄና ጉዳይ እንዲሁም ስጋት ለሚመለከታቸው አካላት በማቅረብ፣ ለፖሊሲ አውጪዎች የሚረዱ ሐሳቦችን በማቅረብ፣ የሕዝብን ጉዳይ አጀንዳ አድርጎ እያነሳ ለሕዝብ የሚያስፈልገውን ሲያነሳና ችግሮችንም ከእነ መፍትሄያቸው እያመላከተ አሁን ላለበት ደረጃ ደርሷል።ሁነቶችን በዜና፣ በሀተታ እና በትንታኔ በመዘገብና በፎቶዎች ጭምር በማስደገፍ መረጃዎችን በመሰነድ 80 አመታትን ተጉዟል።
እንደነ ጳውሎስ ኞኞ፣ በዓሉ ግርማ፣ ብርሀኑ ዘሪሁን፣ …ስበሐት ገብረ እዚአብሔርን የመሳሰሉ ድንቅ የሥነ ጽሁፍ ሰዎችን በማሳተፍ ጋዜጣው ለኪነ ጥበቡም ዘርፍም ጭምር ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
ጋዜጣው ከንጉሳዊ ስርአቱ በመቀጠል በመጡት የደርግ እና የኢህአዴግ መንግስታትም ሁነቶችን በመዘገብ፣ በእቅድ ስራዎቹም የተለያዩ ፓለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ዜናዎችን ሀተታዎችንና ትንታኔዎችን በማቅረብ መረጃዎችን ለህዝብ አድርሷል።በኢህአዴግ ዘመንም እንዲሁ ይህን ሃላፊነቱን ተወጥቷል።
ጋዜጣው ይህን ያህል እድሜ ሲያስቆጥር ነገሮች አልጋ ባልጋ ሆነውለት ግን አልነበረም።በደርግ ወቅት ነጻነቱን ሲጻረር የቆየው የቅድመ ምርመራ/ሳንሱር/ እስረኛ ነበር።የመንግስት ባለስልጣናትና የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ፈተናዎቹ ነበሩ።በኢህዲግ ዘመን ደግሞ ቅድመ ምርመራ ቀርቶ በተወሰነ መልኩ ነጻነቱን ቢያገኝም፣ ከፖለቲካና ከባለስልጣናት ጣልቃ ገብነት ነጻ ሊወጣ አልቻለም ነበር።
ይሁንና በየዘመናቱ ያጋጠሙትን ጫናዎች በዘዴ በማለፍ የህዝብን የመረጃ ጥማት ለማርካት ሰርቷል።ጋዜጣው የህዝብን የልብ ትርታ በማዳመጥ በሰራቸው ስራዎቹም ይበልጥ ተነባቢነትን በማግኘት የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዘመን የተባለበት ወቅት ላይ ደርሶ እንደነበርም ይጠቀሳል።
አዲስ ዘመን ጋዜጣ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ከሚያሳትማቸው ጋዜጦችና መጽሄት አንጋፋው ነው።ድርጅቱ ዘኢትዮጵያን ሄራልድ፣ በሪሳ ጋዜጣ፣ ዘመን መጽሔት፣ አልዓለም ጋዜጣን ሲያሳትም አመታትን ተሻግሯል።በቅርቡ ደግሞ በትግሪኛ ቋንቋ የሚዘጋጀውን ወጋኅታ እና በሲዳምኛ ቋንቋ የሚዘጋጀውን በካልቾ ጋዜጣን ለአንባብያን እያቀረበ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የዛሬ ሶስት አመት የመጣውን ሀገራዊ ለውጥ ተከትሎ እያካሄደ ባለው የሪፎርም ስራ ውስጥ እያለፈ ሲሆን፣ አዲስ ዘመን ጋዜጣም ይበልጥ ተነባቢነት እያገኘ በመጣበት ወቅት ላይ ይገኛል።በርካቶች የመረጃ ምንጭ እያረጉት ይገኛሉ።ድርጅቱ በፈጠራቸው የተለያዩ የኦንላይን አማራጮች በኩል ዘገባዎቹና መረጃዎቹ የሚነበቡበት ሁኔታም ተፈጥሮለታል።
አዲሱ ገረመው
አዲስ ዘመን ሰኔ 6/2013