እኛ ኢትዮጵያውያን የብዙ አኩሪ ታሪክ፣ ባህልና ትውፊት ባለቤት ነን። ከዓለም ቀድመን በጥበብ የተራቀቅን ህዝብ ለመሆናችን የትናንት አባቶቻችን የእጅ አሻራዎች ዛሬም ከማይነጥፍ ውበታቸው ጋር እዚህም እዚያም ቁመው ይመሰክራሉ። አኩሪ ድላችንም በማይነጥፍ የታሪኮቻችንም መዛግብት ተጽፈው ይገኛሉ።
ትናንት አባቶቻችን ለቅኝ ግዛት ሳይንበረከኩ ከዳርዳር እስከ ዳር እጅ ለእጅ ተያይዘው በህብረት ጠላትን በተባበረ ክንድ በመመከት በሰሩት አኩሪ ታሪክ የጥቁር ህዝብ የነጻነት ቀንዲል፣ የኩራት ምንጭ ለመሆን በቅተናል። በዚህም እኛ ኢትዮጵያውያን አንገታችንን ሳንደፋ በዓለም አደባባይ ቀና ብለን የምንሄድ፤ ትናንትም ዛሬም ነጻ የሆንን ህዝቦች መሆን ችለናል። ህዝቡም ደግና እንግዳ ተቀባይ ነገር ግን አትንኩኝ ባይ ሞገደኛ መሆኑን ዓለም ይመሰክራል።
ታዲያ የዚህች አገር ከፍታ የእግር እሳት የሆነባቸው ፋሺስቶች ጥንትም ዛሬም ይህቺን አገር ለማውደም ቀን ከሌሊት የማይፈነቅሉት ድንጋይ፤ የማይለኩሱት እሳት የለም። እነዚህ ፋሺስቶች በሚጎነጉኑት ሴራ ትውልዱ የትናንት አኩሪ ድሉንና ታሪኩን እንዳያውቅ ተደርጎ ወደፊት መራመድ ተስኖት እርስ በእርስ ሲናቆር ይስተዋላል።
በዚህም ትውልዱ ከትናንት በጎውን ወስዶ ጠማማውን አርቆ አገርን ከፍ ማድረግ ሲገባው አንዱ የሰራውን አንዱ እየናደ ጉዟችን የእንቧይ ካብ ሆኖብናል። በትውልድ ቅብብሎሽ አገርን ወደ ከፍታው ማማ ማውጣት ሲገባት ከነበርንበት የጥበብ ማማ፣ የሞራል ልዕልና፣ አኩሪ ድልና ታሪክ ወርደን በተቃራኒው ዛሬ ላይ እጃችን ለልመና መዝርጋታችንም የአገሪቱ መጥፎ ታሪክ ሆኖ በዓለም በጥቁር ቀለም መፃፉም የሚካድ አይደለም ። እጅ ለእጅ ተያይዞ ጠላትን በመከተበት እጁ ወንድም ወንድሙን መውጋት ከጀመረ ዓመታት መቆጠር ጀምሯል።
የዛሬ 40 እና 50 ዓመት ኢትዮጵያ ስትረዳቸው የነበሩ አገራት፤ ዛሬ ላይ የት እንደደረሱ መናገር ለቀባሪ ማርዳት ነው። እነዚህ አገራት ከኋላችን ተነስተው ዛሬ ላይ በስልጣኔ ጫፍ ሲደርሱ የኛ ጉዟችን ወደኋላ ሆኗል። እንደእኔ ኢትዮጵያውያን ከትናንት ከፍታችን ወርደን ከዓለም ኋላ የቀረነው፣ ምጽዋት ጠባቂ ለመሆን እና አሁንም በቅርብ ወንድም በወንድሙ ላይ ለመነሳት ያበቃው ትናንት አባቶቻችን የሰሩትን መልካምም ይሁን ክፉ ስራ የጋራ አድርጎ በጎውን ወስዶ ጠማማውን አርቆ አገርን ማስቀጠል ስላልቻልን ነው ባይነኝ።
እኛ ኢትዮጵያውያን ሰው ለሰራው ስራ ተገቢውን ክብርና ምስጋና ከመስጠት ይልቅ የተሰራውን ስራ አቃቂር ማውጣትና ስህተት መፈለግ ይቀናናል። የራሳችንን ምሁራን ከማድነቅና ተገቢውን ክብር ከመስጠት ይልቅ ባህር ተሻግረን ነጭ ማምለክ ተጠናውቶናል። ለምሳሌ ስንቶቻችን ነን? ‹‹ቴክኖሎጂን ተጠቅመው ደመና ማዝነብ ጀምረናል›› ብለው በተናገሩ ማግስት ዝናብ ሲጥል ዝናቡ የእግዜሩ ነው ወይስ የመንግስት እያልን የምናፌዝ? ይህ የሚያሳየው እኛ አንችልም ከሚል ስሜት የመነጨና ነጭ አምላኪ ስለሆን ነው። ነገር ግን መንግስት ቴክኖሎጂውን ተግባር ላይ አውሎ አሳይቶናል።
ሌላው ቀርቶ እኛ ኢትዮጵያውያን የአንዱ ወንድማችን ውድቀት ሊያስቆጨን እና የራሳችን ውድቀት ያህል ሊሰማን ሲገባ አፋችን አይናገረው እንጂ በወንድማችን ውድቀት ውስጣችን የሚደሰት እኩዮች ነን። ለአብነት አንድ ተማሪ የአንድን ጥያቄ መልስ ተሳሳተ እንበል። ይህ ተማሪ ጥያቄውን ለምን እንደተሳሳተ ምክንያቱን አውቆ ለቀጣይ መሰል ስህተትን ላለመስራት መጣር ሲገባው አብሮት የሚማረውን ጓደኛውን ‹‹የጥያቄውን መልሱን አገኘኸው ወይስ አላገኘኸውም›› ብሎ ይጠይቃል። ጓደኛው ‹‹መልሱን አግኝቼዋለሁ›› ካለው እርሱ መልሱን ባለማግኘቱ ወይም ባለማወቁ ሳይናደድ ጓደኛው መልሱን ስላገኘው እርር ድብን ይላል።
እንዲሁም አንድ ነጋዴ ቅጣት ተጥሎበት የከፈለው ገንዘብ ሳይሆን የሚያንገበግበው ሌሎች ሳይቀጡ እንዴት እኔ ብቻዬን እቀጣለሁ የሚለው ነው ይበልጥ የሚያንገበግበው። ስለዚህ እኛ ኢትዮጵያውያን የወንድማችን ውድቀት ደስታችን፤ ስኬቱ የእግር እሳታችን የሆነብን ምቀኞች ነን ብል መሳደብም ማጋነንም አይመስለኝም።
በጥቅሉ እኛ ኢትዮጵያውያን ከጎናችን ያለውን ወንድማችን ወይም እህታችንን ለሰራው(ችው) ስራ ተገቢውን ክብርና ምስጋና ላለመስጠት የምንሄድበት የሴራ መንገድ እንደ አገር ውድቀት፤ እንደግል ክሽፈት አስከትሎብናል። በዚህም በራሳችን ዜጎች የማንኮራ የውጭ አምላኪ ሆነናል። በዚህ የሴራና የምቀኝነት ጎዟችን ተጠላልፈን እንደ ኤሊ እያዘገምን ከጎጥ አስተሳሰብ ሳንወጣ ዓለም ስንትና ስንት እጥፍ በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂና በዲሞክራሲ እርቆን ረቆ ሄዷል።
ስለዚህ ከሴራና ከምቀኝነት ወጥተን ወንድማችን ወይም እህታችን ለሰራው (ችው) ስራ ተገቢውን ክብርና ምስጋና መስጠት ያስፈልጋል። ከዚህ አንጻር ከሰሞኑ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው በትምህርት ዘርፍ ላበረከቱት አስተዋጽዖ ትምህርት ሚኒስቴር እውቅና እና ምስጋና መስጠቱ ይበል የሚያስብል ነው። ምክንያቱም የሰሩ ሰዎችን ለሰሩት ስራ ክብርና ምስጋና መስጠት መለመድ አለበት። እንደአገርም ልምድ ሊሆን ይገባል።
የጋራ መኖሪያ ቤት ህንጻ በሚጠፋበት አገር፤ ተስፋ የተጣለባቸው የስኳር ኮርፖሬሽኖች ስንትና ስንት ወጪ ወጥቶባቸው በመከኑበት አገር፤ የገበሬውን ምርትና ምርታማነት ያሳድጋሉ ተብለው ተስፋ የተጣለባቸው የማዳበሪያ ፋብሪካዎች የውሃ ሽታ በሆኑበት አገር …ወዘተ እኚህ ቀዳማዊት እመቤት የባለቤታቸውን የመጽሃፍ ሽያጭ ወጪ በማድረግ በሁለት ዓመት ውስጥ በሁሉም ክልሎች 20 ትምህርት ቤቶች ግንባታቸው ተጠናቆ 16ቱን ማስመረቃቸው በእውነቱ ትልቅ ደስታን ይፈጥራል።
ስለዚህ በተለይ የፕሮጀክት አፈፃፀም አፈር ድሜ በበላበት እንደእኛ ባለ አገር በሁለት ዓመት 20 ትምህርት ቤቶችን ገንብቶ (በአማካኝ አንድ ትምህርት ቤት 60 ቀናት ባልሞላ ጊዜ) መጨረስ ተአምር ካልተባለ ሌላ ምን ሊባል ይችላል። ከዚህ ባሻገር ቀዳማዊት እመቤቷ ተጠናቀው ስራ ላይ ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች በተጨማሪ 8 አዳዲስ ትምህርት ቤቶችንና የአይነስውራን አዳሪ ትምህርት ቤት ግንባታዎችን በማጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ ማድረስ እሳቸው ባይሆኑ የሚሳካ ነበርን? የሚያስብል ነው።
እንዲሁም ቀዳማዊት እመቤቷ ከትምህርት ቤት ግንባታ ባሻገር ዩኒፎርም፣ ደብተር፣ ቦርሳ፣ በተለይ ለአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች የዊልቸር ድጋፍ እና ሌሎች ልዩ ልዩ ድጋፎችን እያደረጉ ይገኛሉ። ስለዚህ ትምህርት ሚኒስቴር ለጀግኒት ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ለጥረትና ልፋታቸው ዕውቅና መስጠቱ ይበል የሚያስብለው ነው። ሌሎች ባለስልጣናት የቀዳማዊት እመቤቷን ፈለግ በመከተል ለትውልድ የሚተላለፍ አሻራችሁን ማስቀመጥ ይገባችኋል እላለሁ።
በአጠቃላይ ህዝብና መንግስትን የሚዘርፉ አያሌ የቀን ጅብ ባሉባት አገር እንደ ጀግኒት ያለ ለትውልድ የሚያስብ ዜጋ ቢበራከቱልን አገራችን የትና የት በደረሰች ነበር። ስለዚህ ሰው በሰራው ስራ ልክ ክብር ለሚገባው ክብር መስጠት ተገቢ ነው። ለኚህ ቀዳማዊት እመቤት በዚህ አጭር ጊዜ ለሰሩት ስራ ምስጋናና ክብር ቢያንስባቸው እንጂ አይበዛባቸውም።
ስለዚህ በየዘመኑ ታሪክ ለሚሰሩ ጀግኖቻችንን የሚገባቸውን ክብርና ምስጋና በመስጠት የነገ አገር ተረካቢ ዜጎች የነዚህን አገር ወዳድ ወገኖች መልካም አርአያቸውን ተከትለው እንዲያድጉ ማድረግ ያስፈልጋል። ሰላም!
ከራማአ ማዶ
አዲስ ዘመን ግንቦት 6 ቀን 2013 ዓ.ም