መረጃ በማቀበል ብቻ አልተገደበም። በማሳወቅ፣ በማስተማር፣ በማዝናናት፤ አለፍ ሲል ደግሞ የቅርቡንም የሩቁንም ታሪክ ለትውልድ በማሸጋገር ሚናውን በመወጣት ላይ ይገኛል። በአማርኛ ቋንቋ የመጀመሪያው ጋዜጣ ሲታተም የነበረው ሥያሜና የአሁኑ መጠሪያው አንድ አልነበረም። ዕለታዊ ጋዜጣ ሆኖ በየቀኑ መታተም የጀመረውም ከጊዜ በኋላ ነው። የጋዜጣው የሥፋት መጠንም ለአያያዝ ምቹ አይደለም የሚለው ከአንባቢያን ይቀርብ የነበረው ቅሬታ አይዘነጋም። በቅርጽ፣ በይዘት፣ የህትመት ውጤቶቹን በተለያየ ቋንቋ በማቅረብ እና ሥርጭቱን በማስፋት በለውጥ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በአሁኑ ጊዜ በአማርኛ አዲስ ዘመን፣ በአፋን ኦሮሞ በሪሣ፣ በትግርኛ ወጋህታ፣ በሲዳምኛ በካልቾ እንዲሁም በውጭ ቋንቋዎች ዘ ኢትዮጵያን ሄራልድ በእንግሊዝኛ፣ ዓል ዓለም በአረብኛ ቋንቋዎች በድምሩ ስድስት ጋዜጦችንና አንድ በአማርኛ ቋንቋ የሚዘጋጅ ዘመን መጽሔት በማሣተም ስምንት አሥርት አመታትን ተጉዟል። ሰሞኑንም የምሥረታ በዓሉን ሲያከብር በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድና በሌሎችም ጭምር ድርጅቱ በራሱ ዐሻራ መሆኑ ተነግሮለታል። ድርጅቱ ታሪካዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ኩነቶችን ሰንዶ ትውልድ እንዲማርበት በማድረግ፣ ለጥናትና ምርምር የሚሆን ሥራዎችን በማቆየት ዘመን ተሻጋሪነቱ ነው ዐሻራ ያሰኘው። ይኸው አሻራ ለመሆን የበቃ ድርጅት ዐሻራ የሚል መጽሐፍ በማሳተም በህትመቱ ውስጥ ያለውን ሚና ከፍ አድርጎታል።
ድርጅቱ በህትመት ውጤቶቹ ሽፋን ከሚሰጣቸውና ከሚዳስሳቸው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ፖለቲካዊና ታሪካዊ ጉዳዮች መካከል የቱሪዝም ኢንዱስትሪው ይጠቀሳል። የሀገሪቱን ብዝሃ የቱሪዝም ሀብት የቅርቡም የሩቁም እንዲያውቀው፣ ከዘርፉም በሀገር ኢኮኖሚ ላይ አስተዋጽኦ ያለው ገቢ እንዲገኝ በማድረግ ረገድ ሚና መጫወቱም የ80 አመት ጉዞ ምስክር ነው። በራሱም እንደ ቱሪዝም መዳረሻ ቅርሶች ሁሉ ሀገር በቀል የሆነ 80 አመት ሳያቋርጥ በህትመት ዘርፍ ውስጥ የሚገኝ የሚዲያ ተቋም ለመሆን መብቃቱም ከተቋማዊ ኩራት አልፎ ሀገራዊ ፋይዳ አለው። በሀገሪቷ የህትመት ታሪክ ውስጥ ሚና ካላቸው የመገናኛ ብዙሃን መካከል ቀዳሚ ሆኖ መገኘቱ ትኩረትን ከመሳቡም በላይ እንደ ቱሪስት መዳረሻዎች ሁሉ ገቢ ሊያመነጭ እንደሚችልና እንዲህ ያለው አካሄድም ተቋሙ የበለጠ ጠንካራ ሆኖ እንዲቀጥል ያስችለዋል የሚሉ አስተያየቶች ተሰጥተዋል።
ሀሳቡን በማጠናከር አስተያየታቸውን የሰጡኝ የቱሪዝም ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ግርማ እንዳሉት በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ የቱሪዝም ኢንዱስትሪው በአብዛኛው በቤተሠብ ጥየቃና ከመዝናናት ጋር በተገናኘ ነው የሚሰራው። በሁለተኛ ደረጃ እየተሰራበት ያለው ከመዝናናት ወጣ ባለ በተለይም ለተለያዩ ኮንፈረንሶች ወደ ሀገር የሚመጡትን በመጠቀም ነው። በዚህ በኩልም በቱሪዝም ኢትዮጵያ ድርጅት ሥር የኢትዮጵያ ኮንቬንሽን የሚል ክፍል በማቋቋም እንቅስቃሴው ተጠናክሯል። ከነዚህ ውጭ የሆኑት በሌሎች ሀገሮች የተለመዱ በኢትዮጵያ ግን ገና ያልተጀመረ ብዙ ከቱሪዝም ኢንዱስትሪው ጋር የተያያዙ የቱሪዝም ዓይነቶች አሉ። ለአብነትም እንደፈረንሣይ፣ ስፔን ያሉ በአብዛኞቹ የአውሮፓ ሀገሮች ከግብርና ጋር የተያያዘ ቱሪዝም አላቸው። እንደ ወይን ልማት ያሉና በሌሎችም የሚታወቁባቸውን የእርሻ ሥራዎች በማስተዋወቅና በማስጎብኘት ይጠቀማሉ። ኢትዮጵያም በጤፍ እርሻና በሌሎችም የምትታወቅባቸውን የግብርና ሥራዎች በማስተዋወቅ መጠቀም ትችላለች። የስፖርት፣ የትምህርት ማዕከሎች፣ የአምራች ኢንዱስትሪዎች፣ የስፔስ (ጠፈር)፣ እንደ መንገድና መኖሪያ ቤቶች ያሉ መሠረተ ልማቶችና ሌሎችም በየቀኑ የሚወለዱ በርካታ የቱሪዝም ኢንዱስትሪዎች በዓለም ላይ ይገኛሉ። በኢትዮጵያ ግን ገና በሚባል ደረጃ ላይ የሚገኘው የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን መጠቀምም ያስፈልጋል። በኢትዮጵያ ከመዝናናት ባለፈ ኮንፈረንስና ቢዝነስ ቱሪዝም ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንና የስፖርት ቱሪዝም በጅምር ላይ እንደሆነ አስረድተዋል።በሌሎች ላይም ሥራዎች መጀመር እንዳለባቸው ገልፀዋል።
እንደ አቶ ስለሺ ማብራሪያ መገናኛ ብዙሃንም ከሚጎበኙ የቱሪዝም መዳረሻ ተቋማት መካከል ተጠቃሽ ናቸው። ነገር ግን አልተቃኙም። ወደፊት ግን በሀገር ውስጥ ሆነ ከውጭ በሚመጡ አካላት ሊጎበኝ የሚችል አንድ ሀብት ነው። ለጥናትና ምርምር፣ የሀገሪቱ የመገናኛብዙሃን ኢንዱስትሪ ያለበትን ደረጃ ለማወቅና የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ለሚፈልጉ ምቹ ማድረግ ይጠበቃል። በተለይም በህትመት መገናኛ ብዙሃን ውስጥ ረጅም ዓመታት ያስቆጠረ፣ የኢትዮጵያን ታሪክ በመዘከር፣ ልምድ ያላቸው ጋዜጠኞች ያሉትና ብዙ ባለሙያዎችንም በማፍራት አበርክቶ ያለው፣ ለሀገር አሻራ የሆነው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደ ቱሪዝም ሀብት ሊጎበኝና ሊታይ ይገባዋል። ነገር ግን እስከ ዛሬ ባለመሰራቱና ባለመለመዱ ጥቅም ላይ ሳይውል ቀርቷል።
ተቋሙ በምን መልኩ የቱሪዝም መዳረሻ ሊሆን እንደሚችልም አቶ ስለሺ ሲያብራሩ አንድ የሚዲያ ማዕከል በማቋቋም በውስጡም ተቋሙ ከምሥረታው ጀምሮ በማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ የሰነዳቸውን፣ በተለያየ ጊዜ ሀገሪቱን የመሩ መሪዎች አጀንዳቸው የተለያየ በመሆኑ ድርጅቱም በህትመት ውጤቶቹ የሚያሳትማቸው መረጃዎች፣መዝናኛዎችና ሌሎችም ርዕሰ ጉዳዮች እንደየወቅቱ ተለዋዋጭ በመሆናቸው በየወቅቱ የተሰጡ ሽፋኖችን የያዙትን መርጦ ትኩረትን በሚስብ መልኩ ለጎብኝዎች ማቅረብ ይችላል። ተማሪዎችም ከተሰነደው ዕውቀት ያገኛሉ፤ ይዝናናሉ። በኢትዮጵያ የህትመት ታሪክ ውስጥ መሠረት የተጣለበት መሆኑ ሲታወቅ የውጭ ቱሪስቶችም ይሳባሉ። የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሀገር ውስጥም በውጭም ቱሪስቶች የመጎብኘት አቅም እንዳለው አቶ ስለሺ ያምናሉ። የመገናኛ ብዙሃንን ጨምሮ ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው ግብዓት የሚሆኑ ተቋማትን በማስጎብኘት ውስንነት መኖሩንም ጠቁመዋል። በቱሪዝም ኢንዱስትሪው ከዚህ በፊት ባልተሰራባቸው ዘርፎች ለመሥራት የአስር አመት መሪ ዕቅድ መነደፉንም አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ያሉትን እሴቶች ለመጠቀም ምን መሥራት አለበት ለሚለው ጥያቄም አቶ ስለሺ ‹‹ይኼ ሀብት አለ። ወደጥቅም፣ ወደ ኢኮኖሚ መቀየር አለበት ብሎ ማንቃቱ ከእኛ ከቱሪዝም ተቋም ሥራ ይጠበቃል። ነገር ግን ከተቋሙ የሚጠበቀው ከምሥረታው ጀምሮ የሰራቸውን ሥራዎች ለህዝብ ተደራሽ ለማድረግ አነስተኛ ሙዚየም ማዘጋጀት አንዱ ሥራው ነው። የእርሱ ፈር ቀዳጅነት ሌሎችንም በማሰባሰብ አጠቃላይ የኢትዮጵያን የመገናኛ ብዙሃን ሊዘክር የሚችል ትልቅ ሙዚየም ሊቋቋም ይችላል።ተቋሙን ብራንድ (መለያ) እንዲኖረው ለማድረግ የ80 ዓመት ጉዞውን ሊያሳይ የሚችል የማስተዋወቂያ ድረ ገጽ ቢኖረው የበለጠ ይታወቃል። እንደ አስጎብኝ ድርጅቶች ያሉ ከቱሪዝም ጋር በተያያዘ ከሚሰሩ ተቋማት ጋርም ግንኙነት በመፍጠር ተቋማቱ ከሚያስጎበኙት ጋር አካተው ተቋሙን ማስጎብኘት ይችላሉ›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል። እንደ አንድ ኃላፊነት ያለው የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ተቋማቸው ቱሪዝም ኢትዮጵያ አብሮ በቅንጅት ሊሰራ እንደሚችልም ተናግረዋል።
ሀሳባቸውን በአድናቆት የጀመሩት ሌላው አስተያየት ሰጭ በመቀሌ ዩኒቨርስቲ የቅርስ ጥናት ትምህርት ክፍል መምህር ተባባሪ ፕሮፌሰር አየለ በከሬ ናቸው። የየእለቱን የህትመት ውጤት ያነባሉ። በተለይም አዲስ ዘመን ጋዜጣ በአንድ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ በስተደቡብ ያለውን የሚያስቀኝ ባህል ላይ ትኩረት ያደረገ ሥራዎች ያነቡ እንደነበርና ጽሁፉም እንደሚስባቸው አስታውሰዋል። መሿለኪያ በሚባለው አካባቢ ስለሚኖሩ ስለአካባቢያቸው የተባለውን ለማወቅ ይጓጉ እንደነበርም ወደኋላ መለስ ብለው አስታውሰዋል። የጽሁፍ ሥራዎች በካርቱን ስዕሎች ቢደገፍ ደግሞ የበለጠ ጥሩ እንደሚሆንና ለጽሁፉ ጉልበት እንደሚሰጠው ያምናሉ። የጋዜጣው ቅርጽ ለአንባቢ ምቹ መሆኑንም ወደውታል። እርሳቸው እንዳሉት ሰዎች ለንባብ የሚገፋፉት ዕውቀትና መረጃ አገኛለሁ በሚልና እግረ መንገድም ዘና ለማለት በመሆኑ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ያስተዋሉትንም ክፍተት ጠቁመዋል። በእርሳቸው እይታ በጋዜጣው ላይ የሚወጡትን የይዘት ስራዎች (መረጃ) የሚሻማ ማስታወቂያ መስተካከል ይኖርበታል። ድርጅቱ እንደ አንድ ዐሻራ ወይም ቅርስ መታየቱም ለጋዜጣው መሻሻል ወሳኝ ነው። ላለፉት 80 ዓመታት ድርጅቱ በህትመት ውጤቶቹ ያስተናገዳቸው የማይረሱና ሊታወሱ የሚገባቸውን በዘጋቢ ፊልም ለተደራሲው ማቅረብ ቢቻል የበለጠ ታሪካዊነቱና ዐሻራነቱ ይጎላል። ከቱሪዝሙ ጋርም አያይዘው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ከየት ወዴት የሚለውን በተለይም የጋዜጠኝነት ሙያ የደረሰበትን የዕድገት ደረጃ ለማሳየት ያለፉ ሥራዎቹን ሰንዶ ማቅረብ እንደሚገባው ነው ሀሳባቸውን ያካፈሉት።
ለአብነትም አፄ ኃይለሥላሴ ከሥልጣን ወርደው በቮልስዋገን መኪና ሲወሰዱና ሌሎችም አስደናቂ ታሪክ ያላቸውን ፎቶግራፎች በድርጅቱ ውስጥ ማየታቸውን የሚያስታውሱት ፕሮፌሰር አየለ፤ ይኼ አንድ የቱሪዝም ምንጭ እንደሆነ በመግለጽ እንዲህ ሰንዶ ያቆየውን ታሪክ ለእይታ የሚያቀርብበትን መንገድ ማመቻቸት እንዳለበት ተናግረዋል። እንዲህ ያሉ ለየት ያሉ ፎቶግራፎች፣ ከተመረጡ ጽሁፎች ጋር ቢካተቱ ሳቢ እንደሚሆኑ ለጎብኝዎች ማቅረብ የሚቻልበት ሰፊ የሆነ ሀብት እንዳለው ያስረዳሉ። ይኼ ደግሞ በዘጋቢ ፊልም ቢታገዝ የበለጠ ጥሩ እንደሚሆን ያስረዳሉ። ምንም እንኳን ዋጋውን የሚመጥን ሥራ ቢጠበቅም የህትመት ውጤቶቹን ከፍ ባለ ዋጋ ሽያጭ ላይ ማቅረብም ተፈላጊነቱ እንዲጨምር የራሱ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል። ሰው ጋዜጣ የመግዛት አቅም የለውም ተብሎ ቢታሰብም በኪራይ የሚያነብበትን አጋጣሚም መፍጠር እንደሚቻል ጠቁመዋል።ሌላው እንደ ሀሳብ ያነሱት አሁን በተለየ ሁኔታ በተሰራው መስቀል አደባባይን የስፖርት ማዘወተሪያ ብቻ ከሚሆን የንባብ ቦታም ቢካተትበትና የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ይህን አጋጣሚ ቢጠቀምበት የህትመት ውጤቶቹ የመጎብኘት ዕድል ያገኛሉ የሚል ነው።በኢትዮጵያ የህትመት ታሪክ በየዕለቱ የሚታተም ጋዜጣ ያለው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ነው። በመሆኑም ቱሪስቱን የበለጠ ይስባሉ የሚባሉ ቦታዎችን በመምረጥ በጋዜጣው ላይ ቦታ ሰጥቶ የማስተዋወቅ ኃላፊነት ወስዶ ቢሰራ ውጤታማ ሊሆን እንደሚችል፣ ድርጅቱ የቱሪዝም ኢንዱስትሪው ላይ እየሰራ እግረ መንገድም ራሱን በማስተዋወቅ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሊሆን እንደሚችል አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ያሳተመው 494 ገጽ ያላው ዐሻራ መጽሐፍ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ያደረጓቸው ንግግሮችና ከምክር ቤቱ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች የሰጧቸው ምላሾች የተካተቱባቸው ሲሆኑ፣ መሪዎችና ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎች የሚያደርጓቸው ንግግሮች እንዲህ በመጽሐፍ ተሰንደው መቅረባቸው ትውልዱ ያለፈውን፣ ያለበትንና የወደፊቱንም በማነፃፀር መረጃና ትምህርት ሊያገኝበት እንደሚችል መገመት ይቻላል።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትም እንዲህ ያለው ታሪክ ባለቤት መሆኑ የሚያስመሰግነውና በህትመት የመገናኛ ብዙሃን ውስጥ ቀዳሚ እንደመሆኑ የሚጠበቅ ተግባርም ነው። ድርጅቱ ከጋዜጦች የህትመት ሥራዎች በተጨማሪ መጽሐፍቶችንም በማሳተም እየተንቀሳቀሰ ሲሆን፤ ዐሻራን ጨምሮ በያዝነው በጀት ዓመት ሶስት መጽሐፍቶችን ለህትመት አብቅቷል። ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሰኔ 6/2013