የዛሬ 82 ዓመት የካቲት 12 ቀን 1929 ዓመተ ምህረት ፋሽስት ኢጣሊያ የአዲስ አበባ ህዝብ በገነተ ልኡል በተመንግሥት እንዲገኝ ጥሪ አስተላለፈ፡፡ በዕለቱም ለድሆች ምጽዋት እንደሚሰጥ አስታወቀ፡፡ የከተማዋ ህዝብም በጥሪው መሰረት በስፍራው ተገኘ፡፡ የፋሽስት ጣሊያን ጦር አዛዥ ጄነራል ሩዶልፍ ግራዚያኒም ንግግር ማድረግ ጀመረ፡፡
በመሀል ግን የቦንብ ፍንዳታ ተሰማ፡፡ ፋሽስት ጣሊያን ኢትዮጵያን መውረሩ የእግር እሳት የሆነባቸው ወጣቶቹ አብርሃም ደቦጭና ሞገስ አስገዶም የወረወሯቸው ቦምቦች ግራዚያኒን ሌሎች ጀነራሎችን አቆሰሉ፡፡ አንድ አብራሪ ተገደለ፡፡ከዚያ ወዲያ በኢትዮጵያውያን ላይ የተፈጸመውን ግፍ ለማመን የሚከብድ ሆነ፡፡
በስፍራው የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በግፍ ተጨፈጨፉ፡፡ ጭፍጨፋው መላ አዲስ አበባን ከማዳረሱም በተጨማሪ አብርሃም ደቦጭና ሞገስ አስገዶም ተደብቀውበታል የተባለው የደብረ ሊባኖስ ገዳም ድረስም የዘለቀ ነበር፡፡ በዚህ የግፍ ጭፍጨፋም በአጠቃላይ 30 ሺ የሚደርሱ ንጹሃን ኢትዮጵያውያን ተሰው፡፡ ጭፍጨፋው በጦር መሳሪያ ብቻ የተፈፀመ ሳይሆን እንደ አካፋ ያሉ የሥራ መሳሪያዎች ሁሉ ለእዚህ አሰቃቂ ድርጊት መጠቀሚያነት ውለዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን በፋሽስት ጣሊያን ጦር በማይጨውም ተጨፍጭፈዋል። ጣሊያን በዓድዋ በኢትዮጵያውያን የደረሰባትን ሽንፈት አጸፋ ለመመለስ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ታጥቃ ነው ኢትዮጵያን ለመውረር በድጋሚ የመጣችው፡፡ በዚህም ኋላቀር መሳሪያ ታጥቀው ጣሊያንን ማይጨው ላይ የገጠሙት ኢትዮጵያውያን የዓለም መንግስታት በከለከለው የመርዝ ጋዝ ጭምር ግፍ ተፈጽሞባቸዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን ግን በሁለቱም ወቅቶች በየቤታቸው በገባው ሀዘን አንገታቸውን አልደፉም፤ በቁጭት እየተነሳሱ የፋሽት ጣሊያንን ጦር በዱር በገደል በመዋጋትና መውጫ እና መግቢያ በማሳጣት ተደላድሎ እንዳይቀመጥ አድርገዋል፡፡
ምዕራባውያን አፍሪካን ተቀራምተው ለዓመታት በአህጉሪቱ ሀገሮች እንዳሻቸው እያደረጉ ቢኖሩም፣ ኢትዮጵያውያን ግን የፋሽስቶች እድሜ ከአምስት ዓመት እንዳይዘልቅ በማድረግ ፋሽስት ጣሊያንን በ1933 ጠራርገው አስወጡ፡፡
ይህ እና በዓድዋ ኢትዮጵያውያን ያስመዘገቧቸው አንጸባራቂ ድሎች ለሌሎች በቅኝ ግዛት ሲማቅቁ ለቆዩ የአፍሪካ ሀገሮች ጭምር ታላቅ ትምህርት የሰጠና ሁሌም ሲጠቀስ የኖረ እና የሚኖር ሆኑ፡፡
ኢትዮጵያውያን የውጭ ወራሪ ሀይልን እያንበረከኩ የሀገራቸውን ሉአላዊነት እያስጠበቁ የቆዩበትን ድንቅ ተግባር ሀገራቸውን ለማሳደግ ተግባር ሲያውሉት ቆይተዋል፡፡ የአሁኑ ትውልድም ይህንኑ ታሪክ በልማቱ ላይ በመድገም ማረጋገጥ ይኖርበታል፡፡
እንደሚታወቀው የሀገራችን ህዝብ ለዘመናት ሲናፍቀው የኖረውን የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ እውን ማድረግ የሚያስችል ለውጥ በሀገሪቱ መጥቷል፡፡ ይህን ለውጥ ተከትሎ በተለይ ለዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ወሳኝ የሆኑ ተግባሮች ተከናውነዋል፡፡ ከእነዚህ መካከልም ዜጎች እና የፓለቲካ ፓርቲዎች የመሰላቸውን አመለካከት የሚያራምዱበት ሁኔታ መፈጠሩ፣ የፓለቲካ እስረኞች መለቀቃቸው፣ በሀገሪቱ የነበረው የፓለቲካ ምህዳር መጥበብ በሀገር ቤት አላስቀምጥ ብሏቸው ኑራቸውን በባእድ ሀገር ለዓመታት ያደረጉ የተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎች እና የፓለቲካ ሰዎች እንዲሁም መሳሪያ አንስተው ጫካ የገቡትም መመለሳቸው ይጠቀሳሉ፡፡ በሀገሪቱ የዴሞክራሲ ስርአት፣ መልካም አስተዳደርና ፍትህ ለማስፈን ለሚደረገው ጥረት ጠቀሜታ እንዳላቸው የታመነባቸው ህጎችም እየተሻሻሉ ናቸው፡፡
ለውጡ በኢኮኖሚው መስክም የተለያዩ እርምጃዎች የተወሰዱበት ነው። በግብር አሰባሰብ ላይ የነበረው የተበላሸ አሰራር መፍትሄ እያገኘ ነው፤ በመንግሥት እጅ የሚገኙ የልማት ድርጅቶችን በከፊል በግሉ ዘርፍ እንዲያዙ እየተሰራም ይገኛል። የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ተጠናክሮ ቀጥሏል፤ ግንባታቸው የተጓተተ ፕሮጀክቶችን ለመጨረስ ርብርብ እየተደረገም ነው፡፡ እነዚህ በኢኮኖሚው ዘርፍ ከተከናወኑ ተግባሮች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
ይህ ትውልድ የአባቶቹን አኩሪ ታሪክ መዘከሩ እንዳለ ሆኖ፣ በአባቶቹ የተፈጠረለትን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ሀገሩን መጠበቅና ማልማት ይኖርበታል፡፡ ለዚህ ደግሞ የተፈጠረውን ለውጥ መጠበቅ የግድ ይሆናል፡፡ መንግስት ዴሞክራሲን በማስፈን ፣ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ እድገት ለማስቀጠል ትውልዱ የጀመራቸው ስራዎች ስኬታማ እንዲሆኑ ሃላፊነት አለበት፡፡
በህዝብ ተሳትፎ በሀገሪቱ እውን የሆነው ለውጥ ያልጣማቸው ወገኖች የሚሸርቡትን ሴራም ለመበጣጠስ ሃላፊነቱ የዚሁ ትውልድ ይሆናል፡፡ መንግሥት ከህዝብ ውጪ ብቻውን የሚያመጣው ለውጥ እንደሌለ ይታወቃል። ከዚህ አንጻር በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶች በመቀስቀስ ለውጡን ለማሰናከል የሚጥሩ ሀይሎችን ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ለማድረግ መንግሥት የሚወስዳቸውን እርምጃዎች በመደገፍ እና ለተግባራዊነታቸው በመስራት ሃላፊነቱን መወጣት ይኖርበታል፡፡
ሀገር በቅብብል ነው የምትጠበቀውና የምትለማው፡፡ ያለፉት ትውልዶች በአካልና ህይወት መስዋዕትነት ሉዓላዊ አገር አሰረክበውን አልፈዋል። የአሁኑ ትውልድ ይህን በደም የተዋጀ ሉዓላዊነትና ነጻነት የመጠበቅና የማልማት ሃላፊነት አለበት፡፡ ይህን ሃላፊነቱን ለመወጣት ደግሞ በሀገሪቱ እውን የሆነውን ለውጥ ማስቀጠል ይኖርበታል፡፡ ይህን በማድረግም የጀግኖችን ታሪክ መዘከር ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 12/2011