ለከተሞች ፎረም ጅግጅጋ የሚገኘው የጋዜጠኞች ቡድን የተሰማራበት ተግባር ሊያከናውን ነበር ትናንት ማልዶ የተነሳው፡፡ ሆኖም ድንገት አንድ መረጃ ደረሰ፤ ይሄም፣ ቀዳማዊ እመቤት ዝናሽ ታያቸው ጅግጅጋ በመምጣት በጅግጅጋ ከተማ ትምህርት ቤት ለማስገንባት የመሰረት ድንጋይ እንደሚያኑሩ፤ የ8ኛው የከተሞች ቀን ፎረም ተሳታፊ ከተሞችን ኤግዚብሽን እንደሚጎበኙ ነበር፡፡ የቀዳማዊት እመቤቷን መምጣት የሰሙ የጅግጅጋና አካባቢዋ ነዋሪዎች እንዲሁም የፎረሙ ተሳታፊዎች ደስታ በተሞላበት ስሜት ነበር የተቀበሏቸው፡፡
ነዋሪዎች በባህላዊ ጭፈራ ጭምር አጅበው አስተናገዷቸው፡፡ በሚያስገነቡት “የአመጄ ዮጎል 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት” ስፍራ ሲደርሱ የህዝቡ ስሜት ልዩ ድባብ ነበረው፡፡ ሂደቱን በስፍራው ታድመው የሚከታተሉ የአካባቢው ነዋሪዎችና ሽማግሌዎችም ቀዳማዊ እመቤቷን “እናታችን” ሲሉ ነበር ሲጠሯቸውና ሲያመሰግኗቸው የተደመጠው፡፡ ሁነቱም ለዘመናት የተረሱ ህዝቦችን ያስታወሰ፤ የትምህርት ፍላጎቱን ተገንዝቦ ምላሽ የሰጠና ከልማቱ ባለፈም ለክልሉ ብሎም ለከተማው ሰላም፤ ለህዝቡም ወገን ወዳድነት ምስክር የሚሆን ስለመሆኑም ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡
“ክብርት እናታችን ዝናሽ ታያቸው እንኳን በሰላም መጣሽ፤ በቅርቡ ክልላችንና ከተማችን ብዙ ችግር የነበረበት ቢሆንም፤ የክልሉ ህዝብና አዲሱ የለውጥ አመራር ባደረገው ጥረት አሁን በተፈጠረው ሰላም በዚህ ሁኔታ እንድንቀበልሽ ፈጣሪ ስለረዳን አመሰግነዋለሁ”፤ በማለት የጅግጅጋ አካባቢ የአገር ሽማግሌዎችን ወክለው መልዕክት ያስተላለፉት ገራድ ኩርቢያ ናቸው፡፡ እርሳቸው እንዳሉት፤ ክልሉ ብዙ ጊዜ የተረሳ አካባቢ፤ የሶማሌ ህዝብም ትምህርት ሳያገኝ ብዙ ዓመታትን ያስቆጠረ ነው፡፡
ቀዳማዊ እመቤቷም አካባቢውን አስታውሰውና የአርብቶ አደሩን የትምህርት ፍላጎት ተገንዝበው በክልሉ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለመገንባት በያዙት ትልቅ ዓላማ በመካከላቸው በመገኘታቸው ደስታ ተሰምቷቸዋል፡፡ ምክንያቱም አካባቢው ትልቅ የትምህርት ፍላጎት ያለውና ለውጡ ከመጣም 27 ዓመት የተቆጠረ ቢሆንም እስካሁን በክልሉ ሁለት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ብቻ ነው ያሉት፡፡ በጅግጅጋ ያለው ብቸኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትም በሃይለስላሴ ዘመን የተገነባ ነው፡፡ “የሶማሌ ህዝብም ኢትዮጵያን የሚወድና ኢትዮጵያዊነቱንም በአፈሙዝ ሳይሆን አምኖ በፍላጎቱ በመቀበል እየሰራ ያለ ነው” ያሉት የአገር ሽማግሌው፤ በቅርቡ በክልሉ የተፈጠረው ችግር የክልሉን ሰላም ወዳድና ወንድሙን የሚናፍቅ ህዝብ ተግባር ሳይሆን የተቀናበረና ህዝቡን ለማፋጀት የተከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ ህዝብም ሆነ ቀዳማዊ እመቤቷ እንዲረዱት ጠይቀዋል፡፡ በዚህ ተግባርም እንደ ህዝብ ማዘናቸውን ገልጸዋል፡፡
“ቀዳማዊት እመቤት ያከናወኑት ተግባር ለሶማሌ ህዝብ ትልቅ ውለታ ነው፤ በቀጣይም ይሄንኑ ፍላጎታችንን እንደምታሟሉልን እምነት አለኝ፤” በማለትም፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ለሚያከናውኗቸው ተግባራት ጥንካሬ የቀዳማዊ እመቤቷ ጥንካሬም ጭምር መገለጫ መሆኑን በመጠቆምም፤ እርሳቸው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎን ሆነው እንደሚደገፏቸው ሁሉ የሶማሌ ክልል ህዝብም ከእርሳቸው ጎን ሆኖ እንደሚያግዛቸው በአካባቢው የአገር ሽማግሌዎች ስም ቃል ገብተዋል፡፡
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፋ ሙሐመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በመሩት የለውጥ ሂደት በኢትዮጵያ ውስጥ ከየትኛውም ክልል በላይ የተጠቀመው የሶማሌ ክልልና ህዝብ መሆኑን አስተውቀዋል፡፡” ሌሎች አካባቢዎች ብዙ ችግሮች እንዳሉ ቢታወቅም፤ በሶማሌ ክልል የነበረው ሁኔታ ግን በጣም የባሰ ነበር” ያሉት አቶ ሙስጠፋ ” አሁን ግን ያ ሁሉ ቀርቶለት ሰው በነጻነት ይናገራል፣ በነጻነት ይሰበሰባል፡፡ በክልሉ ግድያ በመቆሙና ማታ ወስዶ መግረፍ ባለመኖሩ ብቻ ህዝቡ እፎይ ብሏል፡፡ በዕለቱ በጅግጅጋ አካባቢ ያለው ድባብም በተለየ ሁኔታ ሰላማዊነትና ደስተኝነት ስሜትን መላበሱም የዚሁ ማሳያ ነው” ብለዋል፡፡ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት፤ በትምህርት መስክ የሶማሌ ክልል ወደኋላ የቀረ ነው፡፡ በመንግሥት የሚሰጡ መረጃዎችም ለስታስቲክስ ተብሎ የተደራሽነት ቁጥሩ ከፍ እንደሚል በህብረተሰቡም፣ የትምህርት አመራሮቹም ሆኑ ባለሙያዎቹም ያውቁታል፡፡
የክልሉ የትምህርት ሽፋን ከሌሎች ክልሎች ጋር ሲነጻጸር ጥሩ ባለመሆኑ፤ ይሄን ክፍተት ለመድፈንም ትክክለኛ ሽፋኑን ለማሳየት የሚያስችል ጥናት ተጀምሯል፡፡ የክልሉን የትምህርት ሽፋን ወደፊት ከማራመድ አንጻርም በቀዳማዊ እመቤቷ የሚገነባው ትምህርት ቤት ትልቅ አቅም ነው፡፡ ባለው ሁኔታም ትምህርት ቤቱ ለስድስትና ሰባት ቀበሌዎች የሚያገለግል ይሆናል፡፡ በዕለቱም ጅግጅጋ ከህዝቡ ጋር መገኘታቸው ለሶማሌ ክልል ትምህርት ቤት ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ ከማኖር በላይ፤ በክልሉ ሰላም የለም፣ ብሔር ብሔረሰቦች እየተጋደሉ ነው፣ ወዘተ. የሚባለው ወሬ እውነት እንዳልሆነ የሚያስረዳ ለሶማሌ ህዝብ ምስክር የሚሆን ነው፡፡
የአገር ሽማግሌዎችም ስሜት የሚናገረው ይሄንኑ እንደመሆኑ ለመልካም ተግባራቸው በክልሉ ህዝብና መንግሥት ስም አመስግነዋል፡፡ “እንኳን በደህና አገኘኋችሁ፣ እንኳን በሰላም ተገናኘን” በማለት ንግግራቸውን የጀመሩት ቀዳማዊ እመቤት ዝናሽ ታያቸው በበኩላቸው፤ “ዛሬ እዚህ የመጣሁበት ትልቁ አጀንዳዬ በቢሯችን በተቀመጠው አቅጣጫና ትምህርት ቤቶችን በየክልሎቹ የመገንባት እቅድ መሰረት ከእነዚህ ክልሎች አንዱ አድርጌ የሶማሌ ክልልን በመምረጤ ነው” ብለዋል፡፡
ትምህርት ቤት የማስገንባት ሀሳባቸው ምክንያትም በየክልሎች እምብዛም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ባለመኖራቸው በተለይ ወደገጠር አካባቢ ያሉ ተማሪዎች የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ብቻ ተምረው ሁለተኛ ደረጃ ላይ ሲደርሱ ትምህርታቸውን የሚያቆሙ መሆናቸው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ይሄንን ችግር ለመቅረፍ አስበው ከተለያዩ ድርጅቶችና ከውጭ አገራት ከሚያገኟቸው ገቢዎች ለመስራት አቅደው በዕለቱ በመካከላቸው እንደተገኙ በመጠቆምም፤ ለትምህርት ቤቱ ግንባታ 20 ሚሊዬን ብር መመደቡንና ግንባታውም በአንድ ዓመት ውስጥ ተሰርቶ እንዲያልቅ ቢሯቸው እቅድ መያዙን ገልጸዋል፡፡
“እናም በአንድ ዓመት ውስጥ ሰርታችሁ እንደምታስረክቡን በዚህ አጋጣሚ ልጠይቅ እወዳለሁ፡፡ ይሄ ትምህርት ቤት ተሰርቶና አልቆ ለምርቃት ተመልሼ እመጣለሁ፤ ምናልባትም ከዛም በፊት እመጣለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡ ስላገኘኋችሁ ደስ ብሎኛል፤” በማለት ስለተደረገላቸው አቀባለልም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
ወንድወሰን ሽመልስ
አዲስ ዘመን የካቲት 12/2011