በሀገራችን የፕሮጀክት አፈጻፀም ችግር ማሳያ ተደርገው ሲነሱ ከቆዩ ሜጋ ፕሮጀክቶች መካከል ጣና በለስ የስኳር ፕሮጀክት ተጠቃሽ ነው፡፡ በመጀመሪያው እድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን ግንባታቸው ከተጀመሩት አሥር ስኳር ፕሮጀክቶች አንዱ ነው፡፡ ከስምንት ዓመታት በፊት በአጠቃላይ በ75 ሺህ ሔክታር መሬት ላይ የተጀመረ ሲሆን፤ በወቅቱ ሦስት ስኳር ፋብሪካዎችን ለመገንባት ታቅዶ ነበር እንቅስቃሴው የተጀመረው፡፡ እነዚህም ጣና በለስ ቁጥር 1 ስኳር ፋብሪካ፣ ጣና በለስ ቁጥር 2 የስኳር ፋብሪካ እና ጣና በለስ ቁጥር ሶስት የስኳር ፋብሪካ ይሰኛሉ፡፡
የፋብሪካዎቹ ግንባታ አለመጠናቀቅ ህዝቡን ለምሬት መንግስትን ደግሞ ለከፍተኛ ኪሳራ የዳረገ ነው፡፡ የፋብሪካው ግንባታ ባለመጠናቀቁ በተደጋጋሚ ሸንኮራ አገዳ እንዲወገድ ተደርጓል፡፡ ይህም ለፋብሪካው ከቦታው በተነሱት አርሶ አደሮች ዘንድ ቁጭት ፈጥሮ ቆይቷል፡፡
በቦታው ከታቀዱ ሦስት ፋብሪካዎች መካከል ግንባታው ተጠናቆ ሰሞኑን ወደ ምርት የተሸጋገረው የጣና በለስ ቁጥር አንድ የስኳር ፋብሪካ ነው፡፡ ጣና በለስ ቁጥር አንድ የስኳር ፋብሪካ በ18 ወራት ለማጠናቀቅ ታቅዶ ነበር ወደ ስራ የተገባው፡፡ ሆኖም የፋብሪካው ግንባታ ከታቀደለት የመጠናቀቂያ ጊዜ ስምንት ዓመታት በላይ ፈጅቶ ነው የተጠናቀቀው፡፡
የስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አሥፈጻሚ አቶ ወዮ ሮባ እንደተናገሩት በሙከራ ምርት ላይ የሚገኘው እና ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በተገኙበት የተመረቀው የጣና በለስ ቁጥር አንድ የስኳር ፋብሪካ በቀን ስድስት ሺህ ቶን ሸንኮራ በመፍጨት ስድስት ሺህ ኩንታል ስኳር ማምረት ጀምሯል፡፡ ፋብሪካውን ወደ ሙሉ አቅም በማሳደግ ከሚቀጥለው ታህሳስ ጀምሮ በቀን 12 ሺህ ቶን ወይም 120 ሺህ ኩንታል አገዳ በመፍጨት በዓመት ከ2 እስከ 2 ነጥብ 6 ሚሊዬን ኩንታል ስኳር ማምረት ይቻላል፡፡
ከታቀደለት ጊዜ ስምንት ዓመታት የዘገየው ይህ ፋብሪካ በ2010 ዓ.ም የተደረገውን ለውጥ ተከትሎ መንግስት የዘገዩ ፕሮጀክቶችን ፈጥኖ ለማጠናቀቅ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ፕሮጀክቱን ከቀድሞ ኮንትራክተር ጋር የነበረውን ውል በማቋረጥ የተሻለ ስራ አፈጻፀም ላለው የውጭ ኮንትራክተር በመስጠት ወሳኝ ርምጃ በመውሰድ እንዲጠናቀቅ ተደርጓል። ይህም በለውጥ መንግስት የሪፎርም አቅጣጫ የተበላሹ ነገሮችን በማስተካከል የብልጽግና ጉዞ ማሳካት እንደሚቻል ያረጋገጠ ነው ብለዋል፡፡
በፊት ፕሮጀክቱን ይዞ ከነበረው ኮንትራክተር ውሉ ሲቋረጥ በገለልተኛ ወገን በተሰራ ግምገማ ለማረጋገጥ እንደተቻለው ፕሮጀክቱ 65 በመቶ ገደማ ላይ ይገኝ እንደነበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ አብራርተዋል። ፋብሪካውን ለማጠናቀቅ የተመደበው በጀት ግን ሙሉ በሙሉ በቀድሞ ኮንትራክተር ተወስዶ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ፕሮጀክቱን እንደ አዲስ ለማስጀመር የበጀት ምንጭ አልነበረም፡፡ ፕሮጀክቱ ተጠናቆ አገልግሎት እንዲሰጥ መንግስት ባሳየው ቁርጠኝነት ለአዲሱ የቻይና ኩባንያ 95 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር በሀገር ውስጥ ገንዘብ በማመቻቸት ፕሮጀክቱን ለማስጨረስ ተጨማሪ ወሳኝ ርምጃ መወሰዱን አውስተዋል፡፡
በተወሰደው ቁርጠኛ ርምጃ ኮሮና ያሳደረውን ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ዘርፈ ብዙ ጫናዎችን እና በፋብሪካው ይስተዋሉ የነበሩ ሌሎች ችግሮችን በመቅረፍ በአንድ ዓመት ከመንፈቅ ጊዜ ውስጥ አጠናቆ ወደ ምርት ማስገባት ተችሏል፡፡
ፋብሪካው በሙሉ አቅም ማምረት ሲጀምር በተረፈ ምርቱ 45 ሜጋ ኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጨትም ይቻላል፡፡ ከዚህ ውስጥ 20 ሜጋ ዋቱን ፋብሪካው ለራሱ የሚጠቀም ሲሆን፤ ቀሪውን 20 ሜጋ ዋት ወደ ብሄራዊ የኤሌክትሪክ ቋት የሚልክ ይሆናል፡፡
በአሁኑ ወቅት በፋብሪካው 20 ሺህ የሚሆኑ ዜጎች በቀጥታ፣ በተዘዋዋሪ፣ በቋሚ እና በጊዜያዊነት የስራ እድል ተጠቃሚ እየሆኑ ነው፡፡ ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምር የስራ እድል ተጠቃሚ የሚሆን ህዝብ ቁጥር በእጥፍ እንደሚያድግም አቶ ወዮ ጠቁመዋል፡፡
ለሸንኮራ ልማት ከሚያስፈልገው 20 ሺህ ሄክታር ማሳ ውስጥ 16 ሺህ ሄክታር ማሳ ላይ የመስኖ መሰረተ ልማት ግንባታ ተከናውኖ ውሃ ገብ ማድረግ የተቻለ ሲሆን፤ ከዚህም ውስጥ 13 ሺህ ሄክታር መሬት በሸንኮራ አገዳ ተሸፍኗል፡፡ የሰራተኞች መኖሪያን ጨምሮ ለፋብሪካው አስፈላጊ የሆኑ መንገዶች ግንባታም ተጠናቋል፡፡
በአጠቃላይ ለፋብሪካው ከ19 ነጥብ 9 ቢሊዬን ብር በላይ ወጪ መደረጉን የጠቆሙት አቶ ወዮ፤ ፋብሪካውን ወደ ሙሉ አቅም ለማሳደግ ተጨማሪ 1 ነጥብ 9 ቢሊዬን ብር እንደሚያስፈልግ ነው የተናገሩት፡፡
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ሰኔ 5/2013