ለሰው ልጅ መሰረታዊ ፍላጎት ከሆኑት ከምግብ፣ ከመጠጥ፣ ከልብስ በተጨማሪ ፈታኝ የሚሆነው የመኖሪያ ቤት ነው። መኖሪያ ቤት ለሰው ልጆች መሰረታዊ ከሚባሉት መካከል ዋነኛው በመሆኑ ነው ኢትዮጵያውያን ልዩ ትኩረትና ቅድሚያ የሚሰጡት። መኖሪያ ቤት ከክልል ከተሞች በበለጠ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ለሚኖር ነዋሪ ትልቅ ፈተና ሆኖ ቆይቷል። ታድያ ዓመት ከዓመት በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ የመጣውን የመኖሪያ ቤት ፍላጎትና መሻሻል ያልቻለውን አቅርቦት ለማጣጣም በአሁን ወቅት መንግስት የተለየዩ አማራጮችን አቅርቦ ወደ ሥራ ገብቷል።
መንግስት ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች ታሳቢ በማድረግ ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ገንብቶ ለማስተላለፍ ጥረት ሲያደርግ የነበር ቢሆንም ችግሩ ግን ሊቃለል አልቻለም። ለዚህም የሚገነቡት ቤቶች ከሚመጣው ፍላጎት ጋር ያልተጣጣሙ እና ቤቶቹም በአግባቡ ለተጠቃሚው ተደራሽ መሆን ያለመቻላቸው በምክንያትነት ይጠቀሳሉ። ታድያ እነዚህና መሰል ችግሮች የመኖሪያ ቤት በከተማው የቅሬታና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሆኖ ቆይቷል። ስለሆነም መንግስት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በአሁን ወቅት በከተማው የሚስተዋለውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ የተለያዩና አዳዲስ አማራጮችን በመጠቀም ወደ ሥራ ገብቷል።
የችግሩን ስፋትና ጥልቀት በሚገባ የተረዳው ከተማ አስተዳደር የዜጎች አንገብጋቢ ጥያቄ ለመመለስ አምስት አይነት የቤት ልማት አማራጮችን ተከትሎ ነው ወደ ትግበራ የገባው ። ከአምስቱ የቤት ልማት አማራጮች መካከል በትግበራ ላይ ያለው የ40/60 ፣ የ20/80 አና የ10/ 90 ፕሮግራም አንዱ ሲሆን፤ የማህበራት ቤቶች ፣ የመንግስት ኪራይ ቤቶች፣ መንግስትና የግል ባለሀብቱ በጋራ በመሆን የሚገነቡት እንዲሁም ፒፒፒ (public privet partnership) የተባሉ አማራጮች ናቸው።
ከእነዚህ አምስት የቤት ልማት አማራጮች በተጨማሪም ከተማ አስተዳደሩ በከተማዋ ያሉትን የቀበሌ ቤቶች በአግባቡ ለመጠቀም እያደረገ ያለው ጥረት ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም። እስካሁን ከነበረው ልምድ ታይቶ በማይታወቅ መንገድ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች በህገወጥ መንገድ ተይዘው የነበሩ የቀበሌ ቤቶችን በማስለቀቅ ለአቅመ ደካሞች፣ ለአካል ጉዳተኞች እና የመኖሪያ ቤት ተቸግረው ለረጅመ አመታት ሲነገላቱ ለነበሩ ዜጎች ተደራሽ በማድረግ ላይ ናቸው።
በአዲስ ከተማ፣ ቂርቆስ፤ ልደታና ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተሞች ከህገወጦች በመንጠቅ የተላለፈው በምሳሌነት የሚጠቀስ ነው ። በእያንዳንዱ ክፍለ ከተማ በህገወጥ መንገድ ተይዘው የነበሩ ከመቶ የሚበልጡ የቀበሌ ቤቶችን ከህገወጦች በማስለቀቅ ለችግረኞች ማስተላለፍ ችለዋል። ይህም ጥቂት የማይባሉ ዜጎችን እፎይ ያደረገ የከተማ አስተዳደሩንም ያስመሰገነ ተግባር ሆኖ አግኝተነዋል ። ከዚሁ ጎን ለጎንም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችሉ ሌሎች የቤት ልምት አማራጮችን እየተከተለ ይገኛል።
መንግስት በዋናነት እየሰራበትና በትግበራ ላይ ካለው የ40/60 እና የ20/80 ፕሮግራም በተጨማሪ፤ አቅምና ፍላጎት ያለቸውን ዜጎች በአንድ ላይ በማሰባሰብ በማህበራት መኖሪያ ቤት መገንባት እንዲችሉ ዕድሉን ያመቻቸና ምዝገባውን አጠናቅቆ ወደ ሥራ ለመግባት ጉዞ ጀምሯል። የመንግስት ኪራይ ቤቶችንም እንዲሁ ተግባራዊ በማድረግ ለዜጎች ተደራሽ ለማድረግ ዝግጅቱን አጠናቅቋል። የግል ባለሀብቱ የሚገነባው የሪልስቴት የጋራ መኖሪያ ቤቶችም እንዲሁ አቅሙ ለሚፈቅድ ግለሰብ የተመቻቸ አማራጭ ነው። ከእነዚህ ሁሉ አማራጮች በተጨማሪም አብዛኛውንና መካከለኛ እንዲሁም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች ተደራሽ ማድረግ ያስችላል የተባለው መንግስት እና የውጪ ባለሀብት በጋራ የሚያለሙት ትልቅ ግምት የተሰጠው የቤት ልማት አማራጭ ነው።
ይሄንን ተግባራዊ ለማድረግም የቅድመ ዝግጅት ስራዎች የከተማ አስተዳደሩ እያደረገ ይገኛል። ከዚህም ለአብነት የሚጠቀሰው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከአረብ ኢሚሬትስ ኩባንያ ጋር እንዲሁም ከደቡብ አፍሪካው ፕሮፐርቲ 2000 ኩባንያ ጋር ያደረጉት የጋራ ስምምነት ፈርማ ተጠቃሽ ነው። ይህ አምስተኛው የቤት ልማት አማራጭ በህዝቡ ውስጥ ትልቅ ተስፋ የሚሰጥ ስለመሆኑ ብዙዎች ያነሳሉ። ለዚህም ምክንያቱ የቤት ግንባታ በባህሪው ከፍተኛ ወጪን የሚጠይቅ በመሆኑ ኩባንያዎቹ የተሻለ የፋይናንስ አቅርቦት በማድረግ ግንባታውን በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ያጠናቅቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በፋይናንስ እጥረትም ይሁን በሌላ የግንባታ መጓተት ለቤት ልማት አንዱ እንቅፋት እንደሆነ ያነሱት ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፤ እነዚህ ሁለት የውጭ ኩባንያዎች ባስቀመጡት የጊዜ ገደብ ቤቶቹን ተገንብተው ለተጠቃሚዎች ተደራሽ ይሆናሉ። ኩባንያዎቹ የተሻለ ቴክኖሎጂ ተጠቅመው ባስቀመጡት የጊዜ ገደብ የሚገነቡት ቤቶችም መካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ዜጎች ተደራሽ እንደሚሆን ገልጸዋል።
ከተማ አስተዳደሩ ከአረብ ኢሚሬትስ ኩባንያ ጋር የፈጸመው ስምምነት 30 ሺ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት ሲሆን ይህም በከተማዋ ለሚገኙ ነዋሪዎች አንገብጋቢ ለሆነውን የመኖርያ ቤት ጥያቄ ምላሽ መስጠት ያስችላል። የውጭ ባለሀብቱ በመጀመሪያው ዙር ከሚገነባቸው 30 ሺ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በተጨማሪ በቀጣይ ተጨማሪ ቤቶችንም የሚገነባ ይሆናል። በቅርቡ በዘመናዊ መልክ ለሚጀመረው 30 ሺ የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ የሚውል 68 ነጥብ አራት ሄክታር በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ጎሮ ተብሎ በሚጠራው አካበቢ መሬት ዝግጁ መደረጉ ተገልጿል።
በተጨማሪም ከተማ አስተዳደሩ በቅርቡ 500 ሺ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት ከደቡብ አፍሪካው ፕሮፐርቲ 2000 ኩባንያ ጋር የጋራ ስምምነት መፈረሙ ይታወሳል። ይህም በከተማው የሚስተዋለውን የቤት እጥረት ለመፍታት ያለመ ፕሮግራም ሲሆን በቀጣይ አምስት ዙር ከአንድ ሚሊዮን በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት የሚሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ጠቅሰዋል። ከደቡብ አፍሪካው ፕሮፐርቲ 2000 ኩባንያ ጋር የተደረገው ስምምነትም የዚሁ እቅድ አካል ሲሆን ኩባንያው በመጀመሪያ ምእራፍ 100 ሺህ ቤቶችን የሚገነባ እንደሆነም ታውቋል።
ከተማ አስተዳደሩ ከውጭ ባለሀብቶች ጋር በጋራ በመስራት የሚገነባቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች በዝቅትኛ ወለድና በረጅም ጊዜ ክፍያ ለተጠቃሚዎች የሚቀርቡ ናቸው። በመሆኑም አብዛኛውን እንዲሁም ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች ተደራሽ በማድረግ በከተማዋ የሚስተዋለውን የመኖሪያ ቤት እጥረት ማቃለል የሚያስችል ይሆናል ተብሎ ይገመታል። ለቤቶቹ ግንባታ አራት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ዶላር በጀት መያዙም በስምምነቱ ወቅት ተገልጿል።
ከተማ አስተዳዳሩም ከመሬት አቅርቦት ጀምሮ የመሰረተ ልማት እና ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን በማቅረብ ለመኖሪያ ቤት ግንባታው ቅድሚያ በመስጠት በጋራ ለመስራት ያለውን ዝግጁነት ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በተለያየ ወቅት ሲናገሩ ተደምጠዋል። ከዚህም ባለፈ ቤቶቹ በተመጣጣኝ ዋጋ የሚቀርቡ በመሆናቸው በከተማዋ የሚስተዋለውን የመኖሪያ ቤት ችግር ትርጉም ባለው መልኩ መቅርፍ የሚያስችል እንደሆነ ይታመናል።
የፕሮፐርቲ 2000 ኩባንያ ሥራ አስኪያጅ ናፒ ኤዲ ሞዲሴ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ያለው ምቹ አስተዳደር ለስራ እንዲመጡ ያደረጋቸው መሆኑን ጠቅሰው፤ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚታየውን የመኖሪያ ቤት ችግር ከመቅረፍ ባለፈም ለበርካታ ወጣቶች የሥራ እድል መፍጠር የሚቻል መሆኑን እና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንደሚኖርም ነው የተናገሩት ። በቤቶቹ ግንባታ ወቅትም 90 በመቶ ያህሉ ሰራተኞች ኢትዮጵያውያን እንደሚሆኑና ከፍተኛ ቁጥር ላለው ወጣት የሥራ ዕድል ይፈጠራል ያሉት ሥራ አስኪያጁ፤ ቤቶቹ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተገንብተው የሚጠናቀቁና ለተጠቃሚዎች መተላለፍ እንዲችሉ ግንባታው በከፍተኛ ቁርጠኝነት የሚሰራ መሆኑ ተገልጿል።
የዜጎች አንገብጋቢ ጥያቄ የሆነው የመኖሪያ ቤት እጥረትን ለመቅረፍ የተደረገው ጥረት እንዳለ ሆኖ ከ650 ሺ በላይ የ20/80 እና 40/60 ተመዝጋቢዎች ገና ቤት በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ። ከዚህ በተጨማሪም በርካታ ቤት ፈላጊ ነዋሪዎች ቤት በመፈለግ ላይ እንዳሉ ይታወቃል። ታድያ ከተማ አስተዳደሩ ይህንን ችግር በመረዳት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በርካታ ስራዎች እንዲሁም የተለያዩ አማራጮችን ተግባራዊ በማድረግ በሚቀጥሉት አምስት አመታት ውስጥ ከአንድ ሚሊዮን ቤቶች በላይ ለመገንባት አቅዶ እየሰራ ይገኛል።
ለቤት ልማቱ ዋናው ችግር የፋይናንስ አቅርቦት እና የውጭ ምንዛሪ በመሆኑ ያነሱት ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፤ ይህንኑ ችግር ለመፍታትም የፋይናንስ እና የቴክኖሎጂ ብቃት ካላቸው ሶስት ዓለም አቀፍ አልሚዎች ጋር በጋራ እየሰሩ እንደሆነ ተናግረዋል። ከእነዚህ መካከልም በየተባበሩት የአረብ ኤሚሬትስ መንግስት ድጋፍ አማካኝነት ከዋዲ አልሲደር ካምፓኒ እንዲሁም ከደቡብ አፍሪካው ፕሮፐርቲ 2000 ኩባንያ ጋር የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለማስገንባት የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት ይጠቀሳል።
እንደሚታወቀው የመኖሪያ ቤት ዋና ችግር የአቅርቦት እና የፍላጎት አለመጣጣም ቢሆንም የተገነቡትን የጋራ መኖሪያ ቤቶችም በፍትሃዊነት ለተጠቃሚ ማድረስ ያልተቻለበት ሁኔታ አለ። ስለሆነም በቤት ልማት አስተዳደር ዙሪያ ያለውን ችግር በማጥናት ችግሩን ለይቶ የመፍታት ሥራ እየተሰራ ይገኛል። በመሆኑም ከተማ አስተዳደሩ በ2011 ዓ.ም እጣ ወጥቶባቸው ነገር ግን መተላለፍ ያልቻሉ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን የመሰረተ ልማት ችግር በመፍታት አብዛኞቹን ቤቶች ለባለ እድለኞች እያስተላለፈ ይገኛል።
በ1997 ዓ.ም ተመዝግበው በመጠባበቅ ላይ ያሉ የመኖሪያ ቤት ፈላጊ ዜጎች የመረጃ ማጥራት ስራዎችን እየተሰራ ሲሆን የመረጃ ማጥራት ሥራው እንደተጠናቀቀም ቤቶቹ ለተጠቃሚዎች የሚተላለፉ ይሆናል።
ሌሎች የመኖሪያ ቤት ፈላጊ ተጠባባቂዎችም እንዲሁ እጣ ያልወጣባቸውን ቤቶች እና በአሁን ወቅት በፍጥነት እየተገነቡ ያሉትን የጋራ መኖሪያ ቤቶች ጨምሮ ከስር ከስር ምላሽ የሚሰጥ ይሆናል። ይህም ትርጉም ባለው መንገድ በከተማዋ ያለውን የመኖሪያ ቤት እጥረት የሚያቃልልና ለዜጎች እፎይታን የሚሰጥ ይሆናል።
ፍሬህይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሰኔ 5/2013