የፖለቲካውን በትረ ሥልጣን ለመጨበጥ የሚደረገው የምረጡኝ ቅስቀሳ የሀገራችንን አየር አውዶታል። ገጠር ከተሞቻችንም በእጩዎቹ የቅስቀሳ ፖስተሮች ተጥለቅልቀው ፈክተዋል። ለፎቶግራፍ አንሺዎች፣ ለባነርና ለቲ-ሸርት አታሚዎች የገበያው አኬር የያዘላቸው ይመስላል። እንኳንም “የዲሞክራሲ ፈጣሪ የግሪክ አማልክት” እንጀራቸውን ከፈቱላቸው። “ሁሉ ድሃ ሁሉ አማራሪ” ቢሆን ፈጣሪም ሆነ መንግሥት ስለሚሰላቹ ለአንዳንዶች ይህን መሰሉ አጋጣሚ ሲሳካላቸው ልናመሰግን እንጂ ሊከፋን አይገባም። ለምንስ ብለን?
ጨዋታን ጨዋታ ስለሚያነሳው “ዕድሜ ለሰሞኑ የምርጫ ቅስቀሳ ይሁንና” ሀገሬ በዚህን ያህል ቁጥር ባለ ማስተርስ፣ ባለ ዶክትሬትና ፕሮፌሰሮች የበለጸገች መሆኗ የገባኝ የከበቡንን የምርጫ ባነሮችና ፖስተሮች ስመለከት ነው። ይህንኑ የእጩዎች “ፕሮፋይል” ብቻ እንደ መረጃ አቅርበን በዓለም ደረጃ ብንወዳደር ምናልባትም በተማሩ “የፖለቲካ እጩዎች” አቅራቢነት የአንደኛነትን ክብር ሳንጎናጸፍ የምንቀር አይመስለኝም። እንኳን የምርጫ ቅስቀሳን ከእኛ ሊማሩ ለሚፈልጉት ጀማሪ ሀገራት ቀርቶ “ከእኔ ወዲያ ምርጫ ለአሳር” ባዩዋን “የዓለም የዲሞክራሲ ጠበቃ” (የጠብ ዕቃ) መሆኑን ልብ ይሏል፤ ጉልበተኛ ሀገርም “በተማሩ የፖለቲካ ሥልጣን ተፎካካሪዎች” ብዛት ሳናስከነዳ የምንቀር አይመስለኝም።
የዓይን እማኝ ስለነበርኩበት የዳግማዊ ጆርጅ ቡሽና አልበርት አርኖልድ ጎር (አል ጎር) እ.ኤ.አ የ2000 ዓ.ም የምርጫ ውድድር ጠቀስ አድርጌ ልለፍ። የዘንድሮው የሀገሬ የምርጫ ውድድር ቢያንስ ቢያንስ የእጩዎች የትምህርት ደረጃ “ከነሙሉ ክብሩና ጥቅሙ” ከለበሱት ጥቁር ካባ ጋር አደባባይ ስለተሰጣ አሜሪካ ሆይ በምሁራን እጩዎች ቁጥር ኢትዮጵያ “አሥር እጥፍ!” እንዳስከነዳችሽ አሜን ብለሽ ተቀበይ ብለን ብንፎክር የሚታዘበን ይኖራል ብዬ አልጠረጥርም። ቢያንስ ቢያንስ እነርሱ ከማስተርስና ከዶክትሬት ይልቅ ቅድሚያ የሚሰጡት ለውጤት ስለሆነ “ብንፎክር” በጉራ ሂሳብ አይተመንብንም። ቢታዘቡንም ቀናተኞች አፍረው ጨዋዎቹ አብረውን የሚያጨበጭቡ ይመስለኛል።
የስልጡን ሀገራት የፖለቲካ ተወዳዳሪዎች በዋነኛነት የሚያተኩሩት ሊሰሯቸው ባሰቧቸውና መንግሥት አልሰራቸውም ብለው በሚያምኑት ጭብጦች ዙሪያ ሲሆን የእኛዎቹ ደግሞ በመወራረፍና በመናናቅ ብርቱዎች ስለሆኑ በዚህም መስፈርት ተስተካካይ አይኖረንም። ይበልጥ ማነጻጸሪያችንን እናጉላው ካልንም “በእጩዎች የፎቶግራፍ አነሳስ ቄንጥ” ስልጡን ተብዬዎች እንኳን ከእኛ ቢያንሱ እንጂ በፍጹም አይበልጡንም።
አራተኛ መከራከሪያ ካስፈለገም አብዛኞቹ የእኛ እጩ ተወዳዳሪዎች ከአሁን ቀደም የፖለቲካ ሠፈርተኞች ያለመሆን ብቻም ሳይሆን ስለ ፖለቲካ ለማውራትና ሲወራም ለመስማት ጥዩፍ መሆናቸው በራሱ ብዙ ነጥብ ያስጥልልናል። እነዚህ “ፖለቲካና ኮረንቲን” ባልዋለበት እያዋሉ ሲሸሹ የኖሩ “የድል አጥቢያ አርበኞች” በምን ተዓምር “መሪ የፖለቲካ ተዋናይ” ሊሆኑ እንደቻሉ ስናስብ ትዝብት ብቻም ሳይሆን መገረማችንም ዛሬም ድረስ ገንፍሎ አልወጣልንም።
“ይብላኝ ለኢትዮጵያ! ይብላኝልን ለወደፊታችን!” ብለን ብንቆዝምም አያስፈርድብንም። ስለምን? ቢሉ በአንድ ሌሊት ሃያና ሠላሳ ጊዜ በመኝታችን ላይ እንደምንገላበጠው ለካንስ በፖለቲካው ምህዳርም ለመገለባበጥ ቀላል ኖሯል ብለን ተደንቀናል። መደነቅ ብቻም ሳይሆን ሳቃችንን ተመልክተው ጥርሳቸው ውስጥ አንዳያስገቡን በመስጋት አፋችንን በማስክ እንደሸፈንን እየተንከተከትን ስቀናል። ብዕራችንና አፋችን አላርፍ ብሎ እንጂ “መገለባበጡ” መብታቸው እንደሆነ ጠፍቶንም አይደለም። ደግሞስ “ይቅናቸውም አይቅናቸው” በዚህም ሆነ በዚያ ተሹለክልከው “በግሪኳ የፖለቲካ አድባር ፈቃድ” በለስ የሚቀናቸው ከሆነ የሚመሩትና የሚያስመርሩት እኛኑ አይደል? “የሚያድግ ልጅ አይጥላህ” እንዲሉ “የሚያሸንፍ ፖለቲከኛ አይጥመድህ” ብለን ብሂል በመፍጠር ብንሰጋ ልክ እንደ እነርሱ ሁሉ እኛም መብታችን ነው።
በዚህ ሁሉ ትርምስምስ መካከል “ግርግር ለሌባ ይመቻል” እንዲሉ የእኛ የተራ ዜጎች “የዕለት ማዕድ” የሙት ኅሊናቸውን ቀብር ባስፈጸሙ ነጋዴዎችና ባለሃብቶች አደጋ ላይ መውደቁ እኛን ግፉዓን ዜጎችን በአያሌው አሳስቦናል። ምርጫ ይሉት አባዜ በመጣ ቁጥር የሚፈጠረው የገበያ እብደት ዜጎችን እስከ መቼ እያስለቀሰ እንደሚኖርም አልገባንም።
በምርጫ ክርክር ወቅት “ኢትዮጵያን እንደ አዳምና ሔዋኗ ገነት” እየሳሉ፤ ሥልጣን በያዙ ማግስት ደግሞ “ባለፀጋው ሰውና አልዓዛር” በቅዱስ መጽሐፍ (ሉቃስ 16፡19-31) ውስጥ እንዳስተዋወቁን ዓይነት ሲኦልን ተመስለው የሚያንገበግቡን “ፖለቲከኞች” ጉዳይ እነሆ ሸክም ሆኖብን በንዴት እየተንጨረጨርን ፀጉራችን እንዲመለጥ ወይንም ለነጭ ፀጉር እንድንበቃ ምክንያት ሆኖናል።
የዕለት ጉሮሯችንን የምንደፍንባቸውን መሠረታዊ ሸቀጦች በተመለከተም “የዋጋ ውድነት” የሚለው ገለጻ አይመጥነውም። ልብ በሉልኝ በአፍሪካ አህጉርና በዓለም ደረጃ በቀንድ ከብት ሀብቷ ምንትስኛ እያልን በምንመጻደቅባት ሀገር የአንድ ኪሎ የአኞ ሥጋ ዋጋ ከ800-1000 ብር ሲገባ “መንግሥታችንም” ሆነ “ተፎካካሪ” ተብዬ የሥልጣን ጥመኞች እነሆ እስከ ዛሬ ድረስ “ኬሬዳሽ” በማለት ሃሳባቸውን ሁሉ በምርጫው ላይ አተኩረው ሕዝቡን ረስተውታል። “ድሃ በህልሙ ጮማ ባይቆርጥ ኖሮ…” ብለውም የሚያፌዙብን ይመስላል። እኛስ ቢሆን መች ተረታንላቸው፤
“ከሰው ቤት እንጀራ አልጫ መረቁ.
የእናት እጅ ይሻላል ዘንጋዳ ደረቁ።”
እያልን በዘፈን ምርጫ መቆዘምን ተያይዘነዋል።
አንድ ኪሎ ሽሮ የወር ደመወዛችን ግማሽ ዋጋ ሲቆረጥለት፣ የጤፍ ዋጋ ሰማይ ሰማያት ነክቶ እንደ ሮኬት ሲተኮስ የንግድ ሥርዓቱን ከመቆጣጠር ይልቅ ወንበዴ ነጋዴዎቹ “ምስኪኑን ሕዝብ ጋጡ” ተብለው የተፈቀደላቸው እስኪመስል ድረስ ናላችን እየዞረ ነው። እንዳቅሚቲ ቤታችን ኩሽና ውስጥ ለገሸርናት ማብሰያ ምድጃ የሲሊንደር ጋዙ ዋጋ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ 120% ጨምሮ 2000 ብር ሲገባ ኡ!ኡ! ብለን ስንጮህ “ምን ነካችሁ” ብሎ ጆሮ የሰጠን ፖለቲከኛ አልገጠመንም። “በዶላር እጥረትና በዓለም ገበያ ዋጋ…” የሚለው “ፖለቲካዊ ምክንያት” ጋዝ ጋዝ እያለ እንደሚያጥወለውለን ለሚመለከተው ክፍል ማን በነገረው?
በቅርቡ “አሜሪካ ፊት ነሳችን” የሚለውን ዜና ያደመጡና ልጆቻቸው ዘንድ ከርመው የመጡ አንድ ዘመናይ እናት “ወዮልሽ ጤናዳምና በሶብላ፣ ጉድ ፈላብሽ ቆስጣ፣ ድንችና ካሮት፣ ዶላሩ ከዬት አባቱ መጥቶ ኢምፖርት ትደረጊያለሽ?” ብለው ቤተሰቦቻቸውን በሳቅ ሲያንፈራፍሩ አንዱ ታዳሚ ሆኜ አብሬያቸው እያረርኩ ስስቅ አምሽቻለሁ።
“ስንዴና ማሽላ አንድ ላይ ስንቆላ፣
እያረረ ሳቀ የባህር ማሽላ።”
የሚለው ጥንታዊ ቅኔ የሚሰራው ለወራሪው ኢጣሊያ ብቻ ሳይሆን እኛም ዐውዱን ብናሻሽልና ጥቂት ቃላት ብንለዋውጥ ዐውዳችንን በሚገባ ይወክልልናል። “ከውጭ የምናስገባው ስንዴ” የሚለው አሰልቺ ገለጻ ምክንያት የሆናቸው ሆድ አደር ይሉኝታ ቢስ ነጋዴዎችና ዳቦ ጋጋሪዎች በዋጋና በሚዛን ስርቆት እየደበደቡ “ሲያስለቅሱን” መንግሥት አላወቀም፣ አልሰማም ብንል ፌዝ ይሆናል።
ምስር፣ ዘይት፣ ሽንኩርት፣ አተር፣ ጤፍ፣ ቅቤ፣ ማር፣ ጎመን፣ ሰላጣ፣ ቡና፣ ስኳር ልጆቻችንን የሚመክትልን በቆሎ፣ የበሶ፣ የገንፎና የቅንጬ እህል ወዘተ. ስማቸው እንጂ ህልውናቸው ከገበያ ላይ ጠፍቶ እንደ ዳይኖሰር በሙዚዬም ብቻ ተደርድረው በቅርቡ እንደምናያቸው መተንበይ “ሃሰተኛ ነብይ” አያሰኝም። ምክንያቱም ገበያው አብዷል። ነጋዴው አብጧል። ቸርቻሪው ተናዳፊ ሆኗል። ተጠቃሚው ሕዝብ ነፍዟል። መንግሥት “ለሽ ብሎ ተኝቶ” እያንኮራፋ ይመስላል። ሕዝብ ይጮኻል መንግሥት “አትቀስቅሱኝ” ብሏል።
ሰሞኑን የምንሰማቸውና ሲመረቁ የምናስተውላቸው የልማት ፕሮጀክቶች አማላይም አስጎምጂም ናቸው። “ፕሮጀክቶችን ማስጀመር ብቻም ሳይሆን ማስመረቅንም” ዓላማ አድርገው “ሪቫን በመበጠስ” ፋታ ላጡት ሹሞቻችን ከወንበር ከፍ ብለንና ብዕራችንን አሹለን “አሹ!” ብለን ብንመርቃቸው አይበዛባቸውም። ከሁለት ሺህ ስልሳ በላይ መሠረተ ልማቶች በመመረቅ እንቅልፍ ላጡት “ብረቷ” የመዲናችን ከንቲባ አዴ አዳነች “ገለቶማ!” ብለን በግልም በማኅበርም ስንመርቃቸው ስለምንውል ዕድሜያቸው እንደሚለመልም አንጠራጠርም። ፈጣሪ የድሆችን እምባና ጩኸት እንደሚሰማ ያስተማሩን ወላጆቻችን ምሥጋና ይድረሳቸው። የምንመርቃቸው እንደሚባረኩ፣ የምንረግማቸውም እንደሚኮነኑ ማወቅ የሚገባቸው አለማወቃቸው ግን ያሳስበናል።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችንም ቢሆኑ እያስፈጸሟቸው ያሉትን ግዙፍ ፕሮጀክቶች ስናስተውል (ሰኔ 3 ቀን 2013 ዓ.ም በዋልታ የተላለፈው ዶኪዩመንተሪ ፊልም ዋቢ ይሆናል) “እንደ ቅዱስ ላሊባላ ሌሊት ሌሊት መላዕክቶች እያገዟቸው ይሆንን!?” ብለን እስከ መገረም ደርሰናል። የመደመር ፍልስፍናቸውና የብልፅግና ራእያቸው በምልዓት የተሳካ ዕለትማ እኛ ባለ ሀገሮቹ “አሹ ኢትዮጵያ!” ብለን ስንደነቅ ባዕዳን ባህር ማዶኞች ደግሞ `Amaizing! How on earth!” ብለው በሹክሹክታም ቢሆን ማድነቃቸው አይቀርም።
እንዲያም ቢሆን ግን “ሃብታም የዓመቱን፤ ድሃ የዕለቱን!” እንዲሉ የገበያው እብደትና የማዕዳችን ጦም ማደር ሕዝቡን እያማረረ ተስፋ ወደመቁረጥ እያቃረብን ስለሆነ ወደ ፈጣሪም ወደ መንግሥት ጆሮም እንዲደርስ “አቤት! አቤት! አቤት!” እያልን ባዶ መሶባችንን አደባባይ ላይ ዘርግተን እንማጠናልን። ሲብስብንም “እኔ የምሞተው ዛሬ ማታ፤ እህል የሚደርሰው በፍልሰታ!” እያልን በረጅሙ በተዘረጋው የመንግሥት ራእይ እንጠራጠራለን።
የየክልሉ ባለሥልጣናትም ሆኑ የታላቋ ከተማችን ክብርት ከንቲባ “ሪቫን ለመቁረጥ” በሚጣደፉባቸው ጎዳናዎች ግራና ቀኝ በሚገኙ የሕዝብ መገበያያ ስፍራዎች ቆም እያሉ የገበያውን እብደት ቢያዩልን አይመጥናቸውም ይሆን? ወይንስ የሥልጣን ፕሮቶኮላቸው ስለማይፈቅድ? መልስ ባይሰጡንም እንጠይቃለን። ባያነቡትም እንጽፋለን። ሌላው ቢቀር እንደምን መከራ ተሸክመን እንደኖርን ለልጆቻችን በጽሑፍ ማቆየቱ አንዱ የአደራ መወጫ ዘዴ ስለሆነ የውትወታ ጩኸታችንን አናቋርጥም። “ሳትታክቱ ጸልዩ!” ብሎ ቃል በተገባልን የወንጌል ትዕዛዝ ላይ ተስፋ በመጣልም ወደ ፀባኦት ከመቃተት አንቦዝንም።
አንድ ፌዘኛ የፌስ ቡክ ጦማሪ ሹማምንቶቻችን ቀን ከሌት እየተረባረቡበት ያለውን የፕሮጀክቶች የምረቃ ሥነ ሥርዓት በተመለከተ በስላቅ ያሽሟጠጠበትን ገለጻ ባልወደውም የፈጠራ አቅሙን ግን አድንቄለታለሁ። እንዲህ ነበር የጻፈው፤ “አዳዲስ የግንብ አጥሮችን እየገነባችሁ ያላችሁና መኖሪያ ቤቶቻችሁን ሰርታችሁ ያጠናቀቃችሁ ወገኖቼ ጠንቀቅ በሉ። የየከተሞቻችሁ ሹማምንቶች “የሕዝብ መገልገያ መርቀን ስራ አስጀመርን” ብለው ለሚዲያ አሳልፈው ይሰጧችኋል። ዳሩ እኛን ቅን አሳቢ ዜጎችን አይመለከትም እንጂ ምፀቱማ ግሩም ገላጭ ነው።
ለማንኛውም የሰሞኑን የ“ምረጡኝ ቅስቀሳ” ሳስብ “እጩዎቻችን” ምን ሲያልሙ ያድሩ ይሆን ብዬ መጠየቄ አልቀረም። እንደሚመስለኝ ህልም የቀን ሃሳብና ድርጊት ነፀብራቅና ውጤት ስለሆነ አንዳንድ ባለ አምፑል ምልክት ተፎካካሪዎች በህልማቸው የሚታያቸው አምፖላቸው “ቦግ ብሎ ሲበራ ወይም ድርግም ብሎ ሲጨልም” እየቃዡ የሚጨነቁ ይመስለኛል። አንዳንዶችም “ሚዛናቸው” ከፍና ዝቅ እያለ ሲዋዥቅ፣ ባለ ቡጢዎችም በተገዳዳሪዎች ሲዘረሩ ወይንም ሲዘርሩ፣ በጣት ምልክቶች ተምሳሌትነት የተወከሉትም እንዲሁ ሃሌ ሉያ እያሉ ሲዘምሩ አለያም ኤሎሄ እያሉ በመቃተት ሲወራጩ የሚያድሩ ይመስለኛል።
አይሆንላቸውም እንጂ ቢሆንላቸውማ የትኞቹም ፖለቲከኞቻችን “አዋይ የራቀው የዕለት እንጀራ ማዕዳችን ባዶነት በሌሊት ህልም ተገልጦላቸው ገበታችን በምግብ ሲትረፈረፍ፣ የብሔርና የጎጥ ፍልሚያው ተወግዶ ሕዝቡ በሰላም ተዘልሎ ሲቀመጥ ቢታያቸው፣ ሀገራቸው ከፍ ብላ በዓለም ፊት ስትሞሸር በህልማቸው ቢበራላቸው፣ ከሽልብታቸው ሲነቁም ወደ ፈጥነው ወደ ተግባር ቢጣደፉ በምን ዕድል እያልን እንመኛለን። ፈጣሪም ይህንን መሰሉን ህልምና ራእይ እንዲሰጣቸው እየጸለይን የሰኔ 14ትን ተስፈኛ ቀን በጉጉት እየጠበቅን አዋዋላችን እንዲሰምር እንናፍቃለን። ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ግንቦት 5 ቀን 2013 ዓ.ም