ለግብርና ምርት ምቹና ለም ናት በምትባለው አገራችን የፍራፍሬዎች ዋጋ ጣሪያ የነካ ነው። በኢትዮጵያ መዲና አዲስ አበባ ዛሬ አንድ ኪሎ ብርቱካን 80 ብር፣ አንድ ኪሎ አፕል 130 ብር፣ አንድ ኪሎ ማንጎ ደግሞ 40 ብር ይሻጣል። ይህ የዋጋ ንረት የመጣው በኢትዮጵያ ፍራፍሬ የሚያበቅሉ ተስማሚ አካባቢዎች ሳይኖሩ ቀርተው ሳይሆን እኛ በፍራፍሬ ልማት ላይ አለመስራታችን ነው። የሚመረቱት ፍራፍሬዎችም በዓይነታቸው ውስንና በምርታቸውም በጣም ዝቅተኛ ስለሆኑ ነው። ለዚህ ነው በኢትዮጵያ የሚመረተው ፍራፍሬ የህዝቡን ፍጆታ መሸፈን አቅቶን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በማውጣት በተለይ ብርቱካንና አፕል ከውጭ እያስመጣን የምንገኘው።
ብዙ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በፍራፍሬና በሌሎች የደን ዛፎች አለመሸፈናቸው ዛሬ የአየር ንብረት ለውጥ የኢትዮጵያ ምርትና ምርታማነት ስጋት እየሆነ ከመጣ ውሎ አድሯል። ይህ ለሰዎች ልጆች ህልውና ፈተና እየሆነ ያለው ችግር ዛሬም ስጋቱና ተፅዕኖው እየበረታ መጥቷል። ዛሬ የበርሀማነት መስፋፋት፣ የወንዞችና የሀይቆች የውሀ መጠን መቀነስና መድረቅ፣ የሙቀት መጨመር፣ ሀይለኛ ጎርፍና የዝናብ እጥረት ዓለማችን እያስተናገደች ያለችው ተጨባጭ እውነታዎች ዳፋው ለኢትዮጵያ ተርፏል። ይህን ችግር ለመፍታትም ሀገራት የራሳቸውን ርምጃ በመውሰድ ላይ ይገኛሉ።
ዛሬ በአየር ለውጥ ምክንያት በሚፈጠር ድርቅ፣ ጎርፍ፣ የአየር ብክለት የሰዎች ህይወት ፈተና ላይ እየወደቀ ነው። በኢትዮጵያም በድርቅ ምክንያት አርሶ አደሩ የለፋበት ሰብል ምርት ይታፈስበታል ተብሎ ሲጠበቅ ከስሞ ይቀራል። በተለይ ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ለድርቅ የምትጋለጥ ሀገር ነች። ዝናብ ላይ ብቻ የተመሰረተ ግብርና ስትከተል የቆየች ሀገር ናት። ይህም ለድርቅ አደጋ ተጋላጭ ሲዳርጋት ቆይቷል። ይህን የድርቅ ተጋላጭነት መቀነስ በስፋት ዛፍ መትከል አማራጭ ሳይሆን ግዴታ ሆኗል። በአረጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የዕፅዋት ሽፋንን ማሳደግ አየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን አሉታዊ ተፅዕኖ ከመቋቋም ባሻገር የምናጣጥመው ፍሬም የምናገኝበት መሆን አለበት ። በተለይ ደግሞ የሚተከሉት ዛፎች ሲደክመን ማረፊያ፣ ስናያቸው ቀልብን የሚስቡ ብቻ ሳይሆን ሲርበን የምንበላው ውሃ ሲጠማን ጥማችንን የሚያስታግሱ ፍራፍሬዎችም መሆን አለባቸው። ይህ ማድረግ ሲቻል ነው አርሶ አደሩም የሚተክላቸውን የፍራፍሬ ችግኞች እንደ ልጁ ተንከባክቦ የሚያሳድጋቸው። የፍራፍሬ ልማቱ የሰብል ምርታማነትን ከማሳደግ በሻገር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ያግዛል፤ ለወጣቶች የስራ ዕድል ይፈጥራል፤ ድህነትን በእጅጉ ለመቀነስ ይረዳል። በጥቅሉ ኢትዮጵያን ወደተሻለ የዕድገት ምዕራፍ ለማሸጋገር ትልቅ ዕገዛ ያደርጋል።
ስለዚህ ኢትዮጵያ ፍራፍሬ ልማት ላይ ከፍተኛ ስራ መስራት የሚጠበቅባት ይሆናል። በተለይ በመጪዎቹ አምስት ዓመታት ፍራፍሬ ልማት ላይ ሰፊ የዘመቻ ስራ ያስፈልጋል። ዛሬ ብዙ የዓለም አገራት ባላቸው ውስን መሬት ፍራፍሬን በማልማት የህዝባቸውን ፍጆታ ከመሸፈን ባሻገር ለውጭ ገበያ በማቅረብ ኢኮኖሚያቸውን እየደገፉበት ነው። ለምሳሌ እሥራኤል ጃፋ የተባለውን ብርቱካን ለዓለም ገበያ በማቅረብ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የምታገኝ አገር ናት።
ኢትዮጵያም የግል ባለሀብቱንና አርሶ አደሩን በማሳተፍ ፍራፍሬ ልማት ላይ ትኩረት ብትሰጥ በአገራችን የሚታየውን የፍራፍሬ የተጋነነ ዋጋ ከማረጋጋት ባለፈ ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት እንችላለን። ፍሬፍሬ ሆነ ሌሎች አገር በቀል ችግኞችን መትከል የአየር ንብረት ለውጥ የሚያደርስውን ተፅዕኖ መቋቋም ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያስገኝልናል። ለዚህም ነው መንግስት የተራቆቱ አካባቢዎችን በዛፍ መሸፈን የህልውና ጉዳይ ነው የሚለው። በ2011 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ የመጀመሪያውን የአረጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ሲያስጀምሩ ችግኝ መትከልና ኢትዮጵያን አረንጓዴ ማልበስ ለኢትዮጵያዊያን ትልቅ ትርጉም እንዳለው ገልፀዋል።
በቅርቡም “ኢትዮጵያን እናልብሳት“ በሚል መሪ ቃል ለሶስተኛ ጊዜ የሚካሄደውን አገር አቀፍ የአረጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ይፋ አድርገዋል። በዚህ መርሃ ግብርም አገር በቀል የዛፍ ችግኞችን ከመትከል ባሻገር የፍራፍሬ ችግኞችም የሚተከሉ መሆኑን ተናግረዋል። በወቅቱም እንደተናገሩት “እኛ ኢትዮጵያውያን ከዛፍ ጋር ከፍተኛ ትስስር አለን ። ስናርስ ሞፈርና ቀንበር የምናዘጋጅበት፣ ስንታመም በብዙ የኢትዮጵያ ገጠሮች አምቡላንሳችን ከእንጨት የተሰራ ወሳንሳ ነው። ስንተኛ አልጋችን ነው፤ ለቤት መስሪያ ማገራችንና ምሰሷችን ነው፤ ስንቀመጥ በርጩማችን ነው፤ ስንደክምና ስናረጅ ምርኩዛችን ነው፤ ስንጓዝና ሲደክመን የምናርፍበት ማረፊያ ጥላችን ነው፤”
ስለዚህ በየዓመቱ በክረምት ወቅት በሚካሄደው በአረጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከዛፍ ችግኞች በተጨማሪ ፍራፍሬ ችግኞች ላይም ትኩረት ማድረግ አስፈላጊ ነው። በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች ሲርበን የምንበላቸው፣ ውሃ ሲጠማን ጥማችንን የምናስታግስባቸው ፍራፍሬዎች በየአንዳንዱ አርሶ አደርና የከተማ ነዋሪ ጓሮ ያስፈልጋሉ። ሙዝ፣ ማንጎ አቮካዶ፣ ፓፓያና አፕል ያሉ የፍራፍሬ ችግኞች በስፋት መትከልና ተከባብክቦ ማሳደግ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው። ለልጆቻችንና ለእኛም ጤንነት የምናስብ ከሆነ ዘላቂ የፍራፍሬ ልማት ማካሄድ ይኖርብናል። በተለይ በብዛት ፍራፍሬ የማይበቅልባቸው አካባቢዎች ከአካባቢው ስነ ምህዳር ተስማሚ የሆኑ ፍራፍሬዎችን በስፋት በማልማት የአርሶ አደሩንም ገቢ፣ የመንግስትንም የውጭ ምንዛሬ ወጪና የህብረተቡን የፍራፍሬ ፍጆታ ማሟላት ያስፈልጋል።
ይህ ኢትዮጵያን አረንጓዴ የማልበስ መርሃ ግብር ፍራፍሬ ችግኞችን በብዛት ከመትከል ባሻገር የደን ሽፋኑን ስለሚያሳድግ አገራችንን ሳቢና ለምለም ከማድረጉ በተጨማሪ የመሬት ለምነትንም ይጨምራል። በርሀማነትንም መከላከል ያስችላል። የውሀ ፍሰቱን ለመጨመርም ይረዳል። ዘላቂ የምርት እድገት እንዲኖር ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል። በዚህ ዘርፈ ብዙ ጥቅም የሚያስገኘው የአረጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ሁሉም ዜጋ መሳተፍ አለበት።
ይህ የአረጓዴ አሻራ የማስቀመጥ ውጤት የሙቀት መጨመር፣ ድርቅ፣ ከባድ ጎርፍ፣ የዝናብ መጠን መቀነስና የዝናብ ወቅት መዛባት የበርሀማነት መስፋፋትና ለግብርና ምርት መቀነስ ብሎም ፍሬ አልባነት ዘላቂ መድሃኒት ነው። አካባቢያችንም ለዓይንም ይማርካል፣ ውሃ የማይጠፋበት ስለሚሆን የትኛውንም ልማት ለማካሄድ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። በዚህም እናድጋለን፣ እንለወጣለን፤ ኢትዮጵያ ከለማችና ሀብታም ከሆነች ሁሉም በየቤቱ እንደየፍላጎቱ የሚበላውና የሚጠጣው ከተገኘ ፍቅር ይጨምራል። እርስ በርስ ያስተሳስረናል። ስለዚህ ሁሉም ዜጋ በአረጓዴ አሻራ መርሃ ግብሮች በመሳተፍ እንደ እሸት ቀጥፎ የሚባላቸውን ፍራፍሬዎችን መትከል ይኖርበታል።
መንግስትም ደን ክምችት አነስተኛ በሆኑባቸውና በተራቆቱ አካባቢዎች ኢትዮጵያን አረንጓዴ በማልበስ ይበልጥ ትኩረት አድርጎ ቢሰራ በአጭር ጊዜ ጥሩ ውጤት ማምጣት ይቻላል።
ጌትነት ምህረቴ
አዲስ ዘመን ግንቦት 5 ቀን 2013 ዓ.ም