የሚኒስትሮች ምክርቤት የ2014 በጀት አመት የፌዴራል መንግሥት ረቂቅ በጀት 561 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር እንዲሆን ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል:: ምክርቤቱ ባካሄደው 97ኛ መደበኛ ሥብሰባው ለበጀት ዝግጅቱ ታሳቢ የተደረጉ የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታዎች ተለዋዋጭነት እንደተጠበቀ ሆኖ አሁን ለሚታዩ የኢኮኖሚ ተግዳሮቶች መፍትሄ ለመስጠት እንዲሁም በ2013 በጀት ላይ ለውጦችን ማድረግ የሚያስገድድ ሆኖ በመገኘቱ የተጨማሪ በጀት ጥያቄና የወጪ አሸፋፈን ማስተካከያ ተግባራዊ እንዲሆን የውሳኔ ሀሳብ ቀርቧል::ምክርቤቱ እንዳብራራው ተጨማሪ በጀት ያስፈለገበት ከዋነኛ ምክንያቶች አንዱ በሰሜኑ የአትዮጵያ ክፍል ህግ ለማስከበር ከተወሰደው እርምጃ ጋር ተያይዞ የተከሰቱ ወጪዎች ሲሆን፣ሌላው በድርቅ ለተጎዱ፣ ለተፈናቀሉ እና ለተመላሾች ለእለት እርዳታ፣ የኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል፣ ለማዳበሪያ አቅርቦት ድጎማ፣ ለጎርፍ መከላከል፣ ለማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ለአቅም ግንባታ ፕሮጀክትና የመጠባባቂያ በጀቱ በማለቁ በቀጣይ ወራቶች ለሚያስፈልጉ የተለያዩ ወጪዎች የመጠባበቂያ በጀት መመደብ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ነው::
ተጨማሪ በጀቱም ታክስ ካልሆኑ ገቢዎች፣ ከሀገር ውስጥ ብድር እና ከልማት አጋሮች በተገኘ ብርድና እርዳታ የሚሸፈን ብር 26 ነጥብ4 ቢሊዮን ተደግፎ ቀርቧል:: ምክር ቤቱም በተጨማሪ በጀት አጀንዳ ላይ በጥልቀት ከተወያየ በኋላ በሙሉ ድምጽ በማጽደቅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል::ተጨማሪ በጀቱም ታክስ ካልሆኑ ገቢዎች፣ ከሀገር ውስጥ ብድር እና ከልማት አጋሮች በተገኘ ብድርና እርዳታ የሚሸፈን ብር 26 ነጥብ4 ቢሊዮን ተደግፎ ቀርቧል:: ምክር ቤቱም በተጨማሪ በጀት አጀንዳ ላይ በጥልቀት ከተወያየ በኋላ በሙሉ ድምጽ በማጽደቅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል::
ምክር ቤቱ በሁለተኛ ደረጃ የተወያየው በ2014 የፌዴራል መንግስት በጀት ላይ ሲሆን፣ባለፉት ዓመታት የተመዘገበው የኢኮኖሚ፣ማህበራዊ ልማትና እድገት የመንግስት ኢንቨስትመንት ያደረገው ከፍተኛ አስተዋጽኦ በግምባር ቀደምትነት የሚጠቀስ እንደሆነ ተመልክቷል:: በአጠቃላይ በኢኮኖሚው ላይ የማክሮ ፋይናንሻል፣ የመዋቅራዊ አደረጃጀትና ቁልፍ የዘርፍ ማሻሻያዎች ተግባራዊ በማድረግ፣በተጀመሩ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ለማጠናቀቅ ጥረት በማድረግ እንዲሁም በጥናት ላይ በመመስረት የመንግስት ልማት ድርጅቶችን በከፊልም ሆነ በሙሉ ወደ ግል በማዛወር ረገድ የተሳካ የማክሮ ኢኮኖሚ ማስተካከያዎችን ማድረግ ተችሏል ነው ያለው ምክር ቤቱ::
የ2014 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግስት በጀት ለመደበኛ ወጪዎች ብር 162 ቢሊየን፣ ለካፒታል ወጪዎች ብር 183 ነጥብ 5 ቢሊየን፣ ለክልሎች የሚሰጥ ድጋፍ 203 ነጥብ 95 ቢሊየን፣ ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ድጋፍ ብር 12 ቢሊየን በጠቅላላ ድምር ብር 561 ነጥብ 67 ቢሊዮን በጀት በረቂቅ አዋጅ ተደግፎ ቀርቧል:: የ2014 የፌደራል መንግስት በጀት ከ2013 በጀት ጋር ሲነጻጸር የ18 በመቶ ብልጫ ያለው ሲሆን፣የበጀት አመዳደቡም የኢትዮጵያን የብልጽግና አቅጣጫዎች መሰረት ያደረገ መሆኑን በጥልቀት በመገምገም ግብዓቶችን በማከል በሙሉ ድምጽ በማጽደቅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ምክር ቤቱ በሙሉ ድምጽ ማጽደቁን ከፋና ብሮድካስት የተገኘው መረጃ ያመለክታል::
ከባለፈው አመት ከፍ ያለ በጀት መመደቡና የፋይናንስ ምንጩ ላይ እንዲሁም አሁን ካለው የውጭ ምንዛሪ ጋር በተመጣጣኝነቱ ዙሪያ በሃሮማያ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ኃላፊና የምጣኔ ሀብት መምህር ፍሬዘር ጥላሁን በሰጡት ትንታኔ በጀት በተፈጥሮ ከቴክኖሎጂ መስፋፋት፣ከከተማ ዕድገትና ከሰዎች ፍላጎት መጨመር፣ከዋጋ ንረት ጋር በተያያዘ፣በአጠቃላይ ከሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ጋር በሚመጥን መልኩ የመንግሥት በጀት እያደገ መሄዱ ይጠበቃል:: ወደኋላ ያሉ ታሪኮችም የሚሳዩት ከመት አመት ጭማሪ መኖሩን ነው::በጀት ማለት የሀገሪቱን የጤና፣የትምህርት፣የመሠረተ ልማት፣ምግብ አቅረቦትና ሌሎችም አቅርቦቶች ያካተተ ማለት ሲሆን፣በበጀት አመቱ 561 ነጥብ 7ቢሊየን ብር ሲበጀት ይህን ያህል ብር የሚፈጅ ሥራ ይሰራል ማለት ነው::
መንግሥት በጀት የመጨመር አቅሙ ምን ያክል ነው የሚለው ነው መታየት ያለበት:: ይሄ ደግሞ በየአመቱ በሚያዙ ዕቅዶች ይወሰናል:: እንደሀገር በተለያየ ዘርፍ ስኬታማ ለመሆን የ10 አመት መሪ ዕቅድ ተነድፏል::ዕቅዱን ስኬታማ ለማድረግ ገንዘብ ወሳኝ በመሆኑ ለሥራው የሚበቃውን በጀት መበጀት ይጠበቅበታል:: በጀት ደግሞ በሁለት ይከፈላል::አንዱ የመንግሥት የወጭ በጀት ሲሆን፣ሌላው የገቢ በጀት ነው::ገቢ ማለት መንግሥት የሚሰበስበው የገንዘብ መጠን ነው::የመንግሥት የገቢ ምንጭ ደግሞ ከነጋዴው፣ከሰራተኛውና ከተለያየ ምንጭ የሚሰበስበው ግብር ነው::
ኢትዮጵያ ዝቅተኛ ግብር ሰብሳቢ ከሚባሉ ሀገራት መካከል እንደሆነች የጠቀሱት የምጣኔ ሀብት መምህሩ ፈሬዘር፤ያም ሆኖ ግን ከጥቂት አመታት ወዲህ እየተከናወነ ያለው የገቢ አሰባሰብ እየተሻሻለና ገቢውም እያደገ መምጣቱን አመልክተዋል::ከዚህ አንፃር መንግሥት ለቀጣይ አመት በጀቱን ከፍ አድርጎ ሲያቅድ ከግብር የሚሰበስበውን፣ከውጭና ከሀገር ውስጥ በብድርና ዕርዳታ የሚያገኘውን ታሳቢ እንደሚያደርግ ገልጸዋል:: እንደ መምህሩ ማብራሪያ እየተገባደደ ባለው በጀት አመት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውሶች በስፋት የተስተዋሉበትና ገቢ ያልተገኘበት::ትርፍ የሌላው ወጭ የነበረበት ጊዜ ነበር ለማለት ይቻላል::ከአምናው ከፍ ያለ በጀት የመመደቡ ሚስጥርም የዋጋ ንረቱ፣ የሚሰሩ ሥራዎች መብዛት ወይንም የዕቅድ መለጠጥ፣ በዚህ ላይ ደግሞ የብልጽግና ዘመን መሆኑ ሰፋ ያለ ሥራ ይጠበቃል::እነዚህ ሁታዎች ለበጀት እድገቱ አሳማኝ ሊሆኑ ይችላሉ::መጨነቅ የሚያስፈልገው የፋይናንስ ምንጩ ላይ ነው:: በዕርዳታ፣በብድር የሚገኝበት ዕድል አለ ወይ የሚለው ቀድሞ ታሳቢ ካልተደረገ ሊሰሩ የታቀዱት ሥራዎች ውጤታማነታቸው ሊያነጋግር ይችላል::
‹‹በጀት አጥፊም አልሚም ነው››ያሉት መምህሩ፤በጀት አለአግባብ ሲለቀቅ ኢኮኖሚው ላይ የዋጋ ንረት እንደሚያስከትልና ከፍተኛ ሆኖ ግን በአግባቡ ማስተዳደር ከተቻለ የዋጋ ንረት እንዲቀንስ እንደሚያደርግ አመልክተዋል::የዋጋ ግሽበትን ታሳቢ ተደርጎ የተበጀተ በጀት ውጤት ላይ ደካማ ከሆነ አፈጻጸሙ ሊፈተሽ እንደሚገባና ጥናትም እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል:: የተበጀተው በጀትና የውጭ ምንዛሪ ነባራዊ ሁኔታ የተጣጣመ እንዳልሆነ ለሚሰጠው አስተያየትም መምህሩ እንዳስረዱት እያሻቀበ ከመጣው የውጭ ምንዛሪ ጋር ያልተመጣጠነ መሆኑ ይጠበቃል:: የምስት መቶ ቢሊየን ብር የመግዛት አቅም ከባለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ የሆነ ልዩነት ላይኖረው ይችላል:: ወቅታዊ የመግዛት አቅም ነው መታየት ያለበት::
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሰኔ 4/2013