ምርጫ የብዙሃንን ተሳትፎ የሚፈልግ የፖለቲካ ሂደት ነው:: ጥቂቶች ሮጠው ጥቂቶች የሚያሸንፉበት የሩጫ ውድድር አይደለም:: ምርጫ የሀገርንና የህዝብን ህልውና የሚወስን ትልቅ የዴሞክራሲ መሳሪያ ነውና ከጅምሩ እስከ ፍጻሜው ድረስ ልዩ ጥንቃቄን ያሻል:: ከላይ ምርጫ በአንድ ቀን የድምጽ ቆጠራ ውጤት የሚገለጽ ቅጽበታዊ ትዕይንት ሳይሆን ከጅምሩ እስከ ፍጻሜው በበርካታ ቀናት ብሎም አመታትን የሚጠይቅ ልዩ ዝግጅት የሚፈልግ ክንውን ነው:: ይህ በአይነቱ ልዩ የሆነና በየአምስት አመቱ የሚመጣን ልዩ እንግዳ ለሀገርና ለወገን በሚጠቅም መልኩ ለማስተናገድ የምርጫው ዋነኛ ተዋናዮች የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ ይገባል:: በሌላ አነጋገር መራጮች፤ ተመራጮችና አስመራጮች አንድ ምርጫ ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የማይተካ ሚና እንዳላቸው ይታመናል::
መራጮች ከሚወዳደሩ ፓርቲዎች ውስጥ የተሻለ የሚሉትን ለስልጣን የሚያበቁ ወሳኝ ኃይሎች ናቸው:: እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት የትየለሌ ከሆኑት ፓርቲዎች ውስጥ ለሀገርና ለወገን የሚበጀውን መርጠው ለስልጣን የማብቃቱ ኃላፊነት የተጣለው በመራጮች ላይ ነው:: ስለዚህም መራጮች ከመመረጣቸው በፊት የሚመርጡት ፓርቲ ለሀገርና ለወገን ምን ያህል ይበጃል የሚለውን አበክረው ሊያስቡበት ይገባል:: ‹‹አስር ጊዜ አልመህ አንድ ጊዜ ቁረጥ›› እንደሚባለውም ካሉት ከ50 በላይ ፓርቲዎች ውስጥ ሀገሪቱን ካለችበት ቅርቃር የትኛው ሊያላቅቃት ይችላል፤ ድህነትና ኋላ ቀርነትን የትኛው የማስወገድ ብቃት አለው፤ ስራ አጥነትን ችግር ለማቃለል የትኛው ፓርቲ የተሻለ ፖሊሲና ስትራቴጂ ይዞ መጥቷል፤ ለሰላምና ጸጥታ ዘብ የቆመው ፓርቲ የትኛው ነው፤ የወጣቶችንና ሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተሻለ ፖሊሲ ይዞ የመጣው የትኛው ፓርቲ ነው የሚሉትን መስፈርቶች በመመዘን ለሀገርና ለወገን የሚጠቅም ፓርቲ ለመምረጥ ከወዲሁ መዘጋጀት አ ለባቸው::
በተለይም አሁን ኢትዮጵያ ያለችበት ሁኔታ ከውስጥም ከውጭም በርካታ ጠላቶች የተነሱባትና ሉዓላዊነቷን የሚፈታተኑ አካላትም ሀገሪቱን ለማዳከም ቀን ከሌት የሚሰሩበት ወቅት በመሆኑ ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅና ሀገሪቱም ወደ ዴሞክራሲ ሽግግር እንድታደርግ የመራጩ ሚና የማይተካ ነው:: ምርጫውን ሰበብ በማድረግም ሁከትና ብጥብጥ ለማንገስ ምክንያት የሚፈልጉ የፖለቲካ ፓርቲዎችንና ለውጭ ባዕዳን ተላላኪ የሆኑ ባንዳዎችን በመገሰጽና በማውገዝ የምርጫውን ሰላማዊነት መጠበቅ መራጩ ህዝብ ሊወጣው የሚገባው ኃላፊነት ነው::
በምርጫው ሂደት ውስጥ ዋነኛ ተዋናይ የሆኑት ተመራጮችም ከባድ ሀገራዊ ኃላፊነት አለባቸው:: እዚህ ጋር ተመራጮች ስንል የፖለቲካ ፓርቲዎችና ለምርጫቸው ያዘጋጇቸው ተመራጮቻቸው ማለታችን ነው:: የአገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሕዝብ ድምፅ ለመዳኘት ራሳቸውን ከወዲሁ ማዘጋጀት መጀመር ይጠበቅባቸዋል:: የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚዳኙት የሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤት እንደሆነ በሚታሰበው የሕዝብ ድምፅ ብቻ መሆኑ መታወቅ አለበት:: የፖለቲካ ፖርቲዎች ሐሳባቸውን ለሕዝብ ለመሸጥ ከመውጣታቸው በፊት፣ የቤት ሥራቸውን መጨረስ ይጠበቅባቸዋል:: ለሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉ የሚፈለገውን ዲሲፕሊን ያላሟላ የፖለቲካ ፓርቲ ለሕዝብ ብያኔ መቅረብ አይችልም:: የፖለቲካ ፓርቲዎችን የሚመሩ ሰዎች ከፍተኛ የሆነ ብቃት፣ ልምድና ሥነ ምግባር ያስፈልጋቸዋል:: ራሳቸውን ለሰላማዊና ለዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ጨዋታ ሕግ ማስገዛት የማይችሉና ግልጽና የተብራራ አጀንዳ የሌላቸው ፓርቲዎች፣ ሕዝብ ፊት በመውጣታቸው የሚያተርፉት ነገር እንደሌለ ሊረዱ ይገባል:: ሕዝብን በጉልበት፣ በማታለል፣ የማይጨበጥ ቃል በመግባት ወይም አገር በማተራመስ ሥልጣን መሻት እንደማያዋጣ መረዳት ይገባል:: የሐሳብ ልዕልና የሚኖረው በሀቅ፣ በአገርና በሕዝብ ተቆርቋሪነት በሚደረግ ፉክክር ብቻ ነው:: የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆነው ሕዝብ ፊት ለመቅረብ ይዘጋጁ:: ገዥው ፓርቲም ከመቼውም ጊዜ በተለየ የፖለቲካ ምኅዳሩን ያስፋ:: ለመጪው ምርጫ የሚደረገው ዝግጅት ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች በእኩልነት የሚያሳትፍ መሆን ይጠበቅበታል::
የፖለቲካ ፓርቲዎችና ተመራጮቻቸው በኢትዮጵያ አንድነትና በሕዝቡ አብሮነት ላይ የጋራ ራዕይ ሊኖራቸው የግድ ይላል:: በኢትዮጵያ ምድር ለምርጫ እየተወዳደሩ ኢትዮጵያ ሲባል የሚከፋቸውና የሕዝቡን አብሮነት መስማት የማይፈልጉ ወገኖች አሁንም አይጠፉምና ከወዲሁ አካሄዳቸውን ሊለዩ ይገባል:: እኔ ካላሸነፍኩ ሰላማዊ ስልጣን ሸግግር አይታሰብም ከሚል ግላዊ አስተሳሰብ በመላቀቅ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት እንዲያሸንፉ መታተር ከሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚጠበቅ ሀገራዊ ግዴታ ነው:: ከሥልጣን በላይ የአገር ጉዳይ ግድ የሚላቸው ፖለቲከኞች ለሰላማዊና ለዴሞክራሲያዊ ፉክክር ራሳቸውን ዝግጁ ያድርጉ:: ከግላዊና ከቡድናዊ ጥቅም በላይ የአገር ህልውና መቅደም አለበት::
ዴሞክራሲ ነጻ ገበያ ነው:: ሃሳብን ለመራጩ ሸጦ ስልጣን ለመያዝ የሚደረግ ፉክክር ነው:: በዚህ ሂደት ውስጥ ህዝብን የሚገዛ ሃሳብ ማመንጨት የማይችሉ እና የዕውቀት ድሃ የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ብዙውን ጊዜ ከነጻ ፉክክር ይልቅ የአሻጥርና ሴራ ፖለቲካን ምርጫቸው ሲያደርጉ ይታያሉ:: እነዚህ ለውይይትና ለድርድር ከመዘጋጀት ይልቅ፣ በረባ ባልረባው ጉዳይ መነታረክ የሚወዱ ዘመኑን የማይመጥኑ ፖለቲከኞች ናቸው:: ፀብ አጫሪነት፣ ጥላቻ፣ ቂም በቀልና ሴረኝነት ዋነኛ መገለጫዎቻቸው ናቸው:: በተለይም እነዚህ ሴረኞችና ጥላቻ ነዢዎች ቀንድ አብቅለው ሊዋጉ የሚመጡት በምርጫ ወቅት እንደሆነ ካለፉት አምስት ምርጫዎች የተረዳነው ሀቅ ነው:: ሆኖም የኢትዮጵያ ህዝብ ላለፉት አምስት ምርጫዎች ሲቀለድበት እንደኖረው ሁሉ ዛሬም በእነዚህ ሴረኛ ኃይሎች ዳግም እንዲቀልደበት አይፈልግም:: በስመ ምርጫ ጥላቻ የሚነዛበት፤ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት የሚዋረዱበት እና ጥቂቶች ሮጠው ጥቂቶች የሚያሸንፉበት ውድድር እንዲኖር የኢትዮጵያ ህዝብ አይፈቅድም::
ስለዚህም የፖለቲካ ፓርቲዎች ሀገርና ህዝብን በማስቀደም ፍትሃዊና ሰላማዊ ምርጫ ለማድረግ መዘጋጀት አለባቸው:: ምርጫም ሆነ የፖለቲካ ተሳትፎ የሚኖረው ሀገር ስትኖር ነውና ቅድሚያ ለህዝብና ለሀገር የሚለውን መርህ በማስቀደም ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሊተጉ ይገባል:: ተደጋግሞ ሲነገር እንደሚሰማውም በምርጫው ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት እንዲያሸንፉ ከወዲሁ የጋራ አቋም ሊይዙ ይገባል::
ባለፉት አመታት በሀገራችን የተካሄዱት አምስት ምርጫዎች ኢ-ዲሞክራሲያዊና ኢ-ፍትሃዊ ናቸው ብሎ ካስፈረጃቸው ጉዳዮች መካከል የአስመራጮች ገለልተኛ አለመሆን አንዱ ነው:: አስመራጮች ከየትውኛም የፖለቲካ ፓርቲ ወገንተኝነት በጻዳ መልኩ ሁሉንም ምርጫ ተዋናዮች የማገልገል ግዴታና ኃላፊነት አለባቸው:: አንዱን ጠቅሞ ሌላውን ከሚጎዳ ተግባር መራቅ ይጠበቅባቸዋል:: ሁልጊዜም ቢሆን አስመራጮች መቆም ያለባቸው ለእውነት፣ ለፍትሃዊነትና ለዴሞክራሲ መርሆች መሆን አለበት::
ስለሆነም መራጭ፣ ተመራጭና አስመራጭ ግዴታቸውን ከተወጡ ስድስተኛው ምርጫ እንደተባለው ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት የሚያሸንፉበት ነጻ፣ፍትሃዊና ዴሞክራሲ ምርጫ ይሆናል::
እስማኤል አረቦ
አዲስ ዘመን ሰኔ 3/2013