‹‹ኢትዮጵያውያንን ከሀገራቸው ታስወጣቸው ይሆን እንጂ ሀገራቸውን ከልባቸው ማስወጣት አትችልም›› የሚለው አባባል እውነት እንደሆነ እየተመለከትን ነው:: ኢትዮጵያ የተጋረጠባትን ችግር በመጋፈጥ ለሀገራቸው አለኝታ የሆኑት በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዛሬ በየትኛውም አለም ድምጻቸው የሚሰማ የወገን መከታ መሆን ችለዋል::
በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከሶስት ሚሊየን እንደሚዘል መረጃዎች ያሳያሉ::ይህ የህብረተሰብ ክፍል የተሻለ ኑሮ ፍለጋ፣በፖለቲካ ተጽእኖ፣ለትምህርት ወዘተ ሀገሩን ለቆ የወጣና ኑሮውንም በአውሮፓና አሜሪካ የመሰረተ ነው::
የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበረሰብ እስካሁን በነበረው ሁኔታ በሀገር ውስጥ ዴሞክራሲ እንዲሰፍንና ልማት እንዲረጋገጥ ድምጹን ሲያሰማ ቆይቷል:: በተለይም የኢህአዴግ መንግስት የሚፈጽማቸውን የመብት ጥሰቶችንና አፈናዎችን በመቃወም የነበረው መንግስት በህዝብ አመጽ እንዲገረሰስ የበኩሉን ሚና ተጫውቷል::
በዶክተር አብይ የሚመራው የለውጥ መንግስት ስልጣኑን ከያዘ በኋላ ዲያስፖራው ቀደም ሲል ከሚታወቅበት መንግስት የመቃወምና የመተቸት አካሄድ ተላቆ በተለያዩ ልማቶች ላይ አሻራውን ወደ ማሳረፍ ተሸጋግሯል::ለህዳሴ ግድብ፣ ለገበታ ለሀገር፣ ለመከላከያ ሰራዊት ድጋፍና በየጊዜው ለሚደርሱ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ያለውን ገንዘብ በማዋጣትና በሀሳብና በዕውቀት በመደገፍ ሀገራዊ ግዴታውን በመወጣት ላይ ይገኛል::
በተለይም በትግራይ ክልል የተካሄደውን ህግ የማስከበር ዘመቻ በመደገፍ ያሳየው ሀገራዊ ተቆርቋሪነትና አለሁ ባይነት በእጅጉ የሚያስመሰግነው ነው:: የህውሓት አሸባሪ ቡድን እራሱ ቆስቁሶ በጋየበት የሕግ የበላይነትና የህልውና ዘመቻ ህዳር 19 ቀን 2013 ዓ.ም በአንጸባራቂ ድል ቢጠናቀቅም በውጭ ሀገራት የሚገኙ የቡድኑ ርዝራዦች የከፈቱት ሀሰተኛ የሚዲያና የኮሚኒኬሽን ዘመቻ ግን መጠነ ሰፊ ነው:: በዚህ የሀሰት ፕሮፖጋንዳም ኢትዮጵያ በውጭው ዓለም ስሟ እንዲጎድፍና ኢትዮጵያውያንም አንገታቸውን እንዲደፉ እስከዛሬም ያላበራ ውርጅብኝ እየደረሰባቸው ይገኛል:: ከዛም አልፎ ኢትዮጵያ ያልተረጋጋችና ለመፍረስ የቀረበች ሀገር እንደሆነች አድርጎ በመሳል የውጭ ኃይል እንዲገባ ግፊትም በማድረግ ላይ ይገኛሉ::
በተለይም ለዘመናት የጥቅም ቁርኝት ከነበራቸው የምዕራባውያን ኃይሎችና ሚዲያዎቻቸው ጋር በማበር ሀገሪቱ እንድትዳከምና ብሎም እንድትፈርስ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም:: በኢትዮጵያ ላይ የሚያሴሩ ባንዳዎችና ባዳዎች አንድ ላይ በመሆን ሀገሪቱ ከጀመረችው የለውጥ መንገድ ለማሰናከል ወጥመዳቸውን ዘርግተው በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ:: አሸባሪው ህወሓት ጦርነቱን እንደቀሰቀሰ እየታወቀ በነበረው የጥቅም ግንኙነት ብቻ አሜሪካና ምዕራባውያን በኢትዮጵያውያን ላይ ፈርደዋል፤ ማዕቀብ በሚል ሰበብም በኢትዮጵያውያን አመራሮች ላይ ወደ አሜሪካ የመግባት ዕገዳ ጥለዋል:: በሉዓላዊነቱ የማይደራደረው የኢትዮጵያ ህዝብ የኢትዮጵያን ውድቀት ለሚሹ ኃይሎች ባለመንበርከክ እና እንደአባቶቹ የሀገሪቱን ሉዐዓላዊነት ባለማስደፈር ታሪክ ለመስራት ተዘጋጅቷል::
የአሸባሪው ህወሓት ርዝራዦች የሚያደርጉት ሀገር የማጠልሸትና ሉዓላዊነትን ለባዕዳን ኃይሎች አሳልፎ የመስጠት ክህደት ያሳመማቸው በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ቀፎው እንደተነካበት ንብ ከዳር እስከዳር መንቀሳቀስ ጀምረዋል::በዋሽንግተን፣በጣሊያን፣ በካናዳ ኦታዋ፣ ሞንትሪያል፣ በቶሮንቶ፣ በክችነር፣ በሎንዶን ኦንታሪዮ፣ በኤድመንተን፣ በሊትብሪጅ እና በካልጋሪ ከተሞች ሰፊ የታቃውሞ ሰልፎችን በማድረግ ለሀገራቸው ያላቸውን ቀናኢነት አሳይተዋል::በተለይም ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ መንግስት የወሰደውን የህግ ማስከበር እርምጃ የሉዓላዊነት ጉዳይ መሆኑ እየታወቀ የአሸባሪው ቡድን ደጋፊዎችና የእነሱ ጥቅም ተጋሪዎች ባናፈሱት ፕሮፓጋንዳ አንዳንድ አለምአቀፍ ተቋማት እና መንግስታት እውነታውን ባላገናዘበ መልኩ እየወሰዱት ያለውን ጣልቃ ገብነት እንደሚቃወሙ ባካሄዱት ሰልፍ ገልጸዋል::
ድርጊቱ ተጎጂውን በዳይ አድርጎ የሚፈርጅ አቋም በመያዝ በሃገር ላይ የተለያዩ ጫናዎችን ለማሳረፍ የከፈቱትን ያልተገባና ከእውነት ያፈነገጠ ጫና እንደሚቃወሙም ሰልፈኞች የገለጹ ሲሆን ኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ የሚገቡ ተቋማትና አገራት ድርጊታቸውን እንደሚቃወሙና አሸባሪው ቡድን በንጹሃን ላይ ያደረሰውን ጭፍጨፋ እንደሚያወግዙም ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ አስረድተዋል:: በሂደቱም የኢትዮጵያ መንግስት ወንጀለኞችን ለህግ ለማቅረብ ለወሰደው እርምጃ ያላቸውን ድጋፍም ገልፀዋል::
በተለያዩ የዓለም ክፍል የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የተለያዩ መፈክሮችን በማሰማት ምእራባውያንና አሜሪካ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ከመግባትና የማይገባ ጫና ከመፍጠር እንዲቆጠቡ አሳስበዋል::እነዚህ የኢትዮጵያ ድንቅ ልጆች በተለይ አሜሪካ የጣለችው የባለስልጣናት ዝውውር ገደብ እውነታ ላይ ያልተመሰረተና የአሜሪካና ኢትጵያን የቆየ ግንኙነት ያላገናዘበ መሆኑን በመግለጽ ተቃውሟቸውን እያሰሙ ይገኛሉ:: ለሚኖሩበት ግዛት አስተዳዳሪዎችም እውነታውን በማስረዳት አሜሪካ የወሰደቸችው አቋም የተሳሳተ መሆኑን በማስረዳት የበኩላቸውን የዜግነትግዴታቸውን በመወጣት ላይ ይገኛሉ::
ከዚሁ ጎን ለጎንም ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ቦንድ በመግዛት በልማቱም የማይናቅ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ይገኛሉ::በተለይም ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል የህግ ማስከበር ዘመቻ ውስጥ ከገባችበት ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ለታላቁ የህዳሴ ግድብ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ቀጥሏል:: በካናዳ የተቋቋመው የጥምረት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በአንድ ቀን 142 ሺህ 900 የካናዳ ዶላር አሰባስበዋል:: በዘንድሮው አመት ብቻ በካናዳ የተለያዩ ግዛቶች ውስጥ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውየያን ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በስጦታ ብቻ ከ300 ሺህ የካናዳ ዶላር በላይ ተሰብስቧል።
በአጠቃላይ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን ከሀሰተኛ ፐሮፖጋንዳ ለመታደግ እያደረጉት ያለው ጥረት የሚበረታታና በሰው ሀገር ከኑሮ ጋር ግብግብ እየገጠሙም ቢሆን ለሀገራቸው ቅድሚያ እንደሚሰጡ ያሳየ አኩሪ ገድል ነው::ያለምንም የብሄርና የሃይማኖት ልዩነትም በተለያዩ የዓለም ሀገራት ያደረጉት ሉዓላዊነት የመታደግ ተግባርም በታሪክ የሚመዘገብ አኩሪ ተግባር ነው:: ከዚሁ ጎን ለጎንም ለህዳሴው ግድብ እያደረጉት ያለው ድጋፍ በብልጽግና ጎዳና ላይ ለምትገኘው ኢትዮጵያ ትልቅ ስንቅ መሆን ችሏል::
በመሆኑም በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከውስጥና ከውጭ ኃይላት ጋር በቅንጅት እየሰሩ ያሉትን የህወሓት ቡድን ርዝራዦችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድና የተረጋጋች፣ የበለጸገችና የታፈረች ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ ለማስረከብ በዲያስፖራ አባላት የተጀመረው ሀገርን የመታደግ ዘመቻ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት እንላለን::
እስማኤል አረቦ
አዲስ ዘመን ሰኔ 2/2013