ግንባታቸው ባልተጠናቀቀ ጅምር ህንፃ ውስጥ እንደ ባንክ ያሉ ትላልቅ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ሳይቀሩ በኪራይ መጠቀም በመለመዱ ህንፃውን የሚያስገነባው አካልም ህንፃውን ሰርቶ ከማጠናቀቅ ይልቅ ለኪራይ አገልግሎት በሚውለው ላይ ብቻ ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራ እስከሚመስል ድረስ በጅምር የቀሩ ህንጻዎች እየበዙ ይገኛሉ። እንዲህ ያለው ልማድ የሚገነቡ ህንፃዎች ከፍታ አይታወቅም የሚል ጥርጣሬ እያሳደረ እና ጥያቄም እያስነሳ ነው። አንዱ የደህንነት ጉዳይ ነው። ግንባታ እየተካሄደ ተገልጋይ ደግሞ በሥረኛው የአገልግሎት መስጫ ውስጥ ለመጠቀም ሲገባ ለጉዳት ቢዳረግስ፣ተጠያቂውስ ማነው? ህንፃው በጅምር ለረጅም ጊዜ መቆየቱ በወጭና በተለያዩ ነገሮች ሊያሳድር ስለሚችለው ተጽዕኖ፣ጅምር ህንፃ ለኪራይ አገልግሎት መዋሉ ገንቢው አካል ቀሪውን እንዳያጠናቅቅ አያዘናጋውም ወይ? የሚሉት ይጠቀሳሉ። ህጉስ ምን ይላል?
በኮንስትራክሽን ሥራዎች ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን የህንፃ ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ በረከት ተዘራ፤ ህጉን መሠረት አድርገው እንዳስረዱት፤ በ2001ዓ.ም እና 2003ዓ.ም በወጣው የህንፃ አዋጅ ላይ የህንፃ ግንባታው ሳይጠናቀቅ ወይንም ፈቃድ ሳያገኝ ለአገልግሎት ማዋል እንደማይቻል በግልጽ በመመሪያው ተቀምጧል። በ2010ዓ.ም ላይ የህንፃ ማሻሻያ መመሪያ ወጥቷል። በተለይም ጅምር ህንፃን መገልገል በሚለው የመመሪያው ክፍል በአንቀጽ 19.5 በህንፃ ሹም ደህንነቱ አስጊ አለመሆኑ ከተረጋገጠና በከፊል ለተጠናቀቀ ህንፃ የመጠቀሚያ ፈቃድ ሊሰጥ ይችላል የሚል ሰፍሯል። ፍቃዱ ሲሰጥ መሟላት ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎችም በአንቀጹ ላይ ሰፍረዋል። ከነዚህ መካከል አንዱ በህብረተሰብ እና እንደተሽከርካሪ ባሉ ቁሳቁሶች ላይ አደጋ አለማስከተሉን ማረጋገጥ፣የከተማ ገጽታ ግንባታ ላይ ሊኖረው ስለሚችለው ተፅዕኖ፣የህንፃ መዋቅራቸው መጠናቀቁን፣የፍሳሽ ማስወገጃዎችና የውሃ መስመሮቻቸው እንዲሁም የኤሌክትሪክ አገልግሎታቸው፣በትክክል መሰራታቸው፣የአደጋ ጊዜ መወጣጫዎች ስለመኖሩ፣አካል ጉዳተኞችንም ታሳቢ ያደረገና ሌሎች አስፈላጊ የተባሉ ዝርዝር ነገሮች ሳይሟሉ ለአገልግሎት መብቃት እንደሌለባቸው መመሪያው ይደነግጋል።
በመመሪያ ቢኖርም ተግባራዊነቱ ላይ ግን ክፍተት መኖሩን አቶ ሞገስም ይጠቅሳሉ። እርሳቸው እንዳሉት ለግንባታ የሚውሉ ግብአቶች መንገድ ዘግተው ለመተላለፍ አስቸጋሪ የሚሆንበት ሁኔታ በስፋት ይስተዋላል። እንዲህ ያሉ ክፍተቶችን ደግሞ ተከታትሎ እንዲስተካከል ማድረግ የህንፃ ሹም ኃላፊነት ነው። ‹‹ህጋዊ ያልሆነ ግን ህግ ሆኖ የሚታይበት ሁኔታ ነው የተፈጠረው። ለምን ሆነ ተብሎ ሲጠየቅ በተለያዩ ባንኮች የሚከራዩት ህንፃ ባንክ ለህንፃው ባለቤት ስላበደረው ወጭውን ለማካካስ እንዲረዳው ነው የሚል ነገር ይሰማል። ይሄ ደግሞ የግንባታ ዘርፉን ብቻ ሳይሆን የከተማን ገጽታን ያበላሻል›› ሲሉም አቶ በረከት አክለዋል።
በባለሥልጣኑ በኩል ክፍተቱን ታሳቢ ያደረገ ሥራ በመሥራትና በዘላቂነትም ስለተቀመጠው የመፍትሄ እርምጃ አቶ በረከት ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ ባለሥልጣኑ ከተቋቋመ አጭር ጊዜ ከመሆኑና በተለያዩ ምክንያቶች አዲስ አበባ ከተማ ላይ የመገልገያ ፈቃድን በተመለከተ ያከናወነው ሥራ የለም። የድሬዳዋ፣አዳማ፣አምቦ ከተሞችን ግን ለማየት ሞክሯል። ባለሥልጣኑ የተከተለው አቅጣጫ ከእርምጃ በፊት ማስተማር በሚለው ላይ ነው። ባለሥልጣኑ በተንቀሳቀሰባቸው አካባቢዎች ሁሉም የህንፃ ሹሞች እኩል የሆነ ግንዛቤ፣ወጥ የሆነ የህንፃ ግንባታ አመራርና አፈፃፀም አለመኖሩን ተገንዝቧል። ባለሥልጣኑ ቅኝት ባደረገባቸው አካባቢዎች ያለውን ክፍተት እንደ ግብአት ወስዷል። ክፍተቶችን ለይቶ ወጥ የሆነ አሰራር እንዲኖር ግንዛቤ የመፍጠሩ ስራ ቢቀድምና በሂደት ደግሞ እርምጃው ቢከተል ክፍተቱ እየቀነሰ ይሄዳል። ዘላቂ መፍተሄ የሚሆነው ግን ሁሉም ህጉን ተከትሎ እንዲሰራ ማድረግ፣ከህግ ውጭ የሆነውን ደግሞ ተጠያቂ ማደረግ ነው። ለቁጥጥር ሥራውም የሚያግዘው ህግ ሲተገበር ብቻ ነው።
በግንባታው ላይ የተሰማሩት የሚያነሷቸው የግብአት አቅርቦት እጥረትና የዋጋ መናር በአስፈፃሚው አካልም ምቹ ሁኔታ አለመፈጠርና ሌሎችም የሚያነሷቸው ቅሬታዎች እንዴት ይታያል ለሚለው ጥያቄም አቶ ሞገስ በሰጡት ምላሽ ፤በመንግሥትም ሆነ በግለሰቦች የግንባታ ፕሮጀክቶች መቼ ተጀምረው መቼ እንደሚጠናቀቁና ሊያጋጥማቸው ስለሚችለው ችግርም ቀድሞ በዕቅድ የመመራት ክፍተቶች አሉባቸው። ቀድሞ በዕቅድ ያልተካተተ ነገር ደግሞ ከባንክ ብድር፣ከአስፈጻሚው አካል ድጋፍ ለማግኘት እንቅፋት ይገጥማቸዋል። አንዳንዶች የግንባታ ቦታ በትክክል ሳይረከቡ ግንባታ ውስጥ የሚገቡበት ሁኔታ መኖሩን ከተሞክሮ ማየት ተችሏል። እንዲህ ያሉ አካሄዶች ደግሞ የሌላውን መብት የሚጋፉ ሆነው አላስፈላጊ ጭቅጭቆችን እያስነሱ ይገኛሉ። በመሆኑም ያዋጭነት ጥናት ሳይኖራቸው ወደ ግንባታ እንዳይገቡ የሚል አቅጣጫ ተቀምጧል። በግብአት በኩል የሚነሳው ጥያቄም ከውጭ ሀገር የሚገቡትን በሀገር ውስጥ የመተካት አማራጮችን መጠቀሙ የተሻለ ይሆናል።
በዘርፉ እየተነሱ ላሉት ክፍተቶች ተጠያቂ የሚሆኑት አካላት እነማናቸው ለሚለውም አቶ በረከት እንደገለጹት፤ አንዱ ኮንትራክተር (ተቋራጭ)፣አማካሪና ግንባታውን የሚያከናውነው ወይንም ባለቤት የየራሳቸውን ኃላፊነት ካለመወጣት የሚመጭ ችግር ክፍተት ሲሆን፣ለክፍተቱ መፈጠርም ሙስና፣ቅድመ ግንባታ ላይ አቅዶ አለመንቀሳቀስ ይጠቀሳል።
ህንፃዎች ሳይጠናቀቁ ለአገልግሎት መዋል የለባቸውም በሚለው የሚስማሙት የመስቀል አደባባይ ፕሮጀክት ዋና ዳሬክተር አማካሪ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ የአርክቴክቸር ህንፃ ግንባታና ከተማ ልማት ኢንስቲትዩት መምህር አርክቴክት ብሥራት ክፍሌ፤ሆኖም ግን የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ ማስገባት ይገባል ይላሉ። እንደርሳቸው ማብራሪያ ባደጉት ሀገራት የብድር ጥያቄ ሳይሆን የሚቀርበው ባንኮች ተበዳሪ እንዲኖር ነው የሚያበረታቱት። የሀገራቱ ባንኮች በተቃራኒው ተበዳሪ ጠፋ ነው የሚሉት። ብድርን ለማበረታታትም ሲሉ የወለድ መጠናቸው እጅግ አነስተኛ ነው። ወለድ የማይጠይቁም አሉ። ይህ የሚሆነው ገንዘቡ ወደግሉ ዘርፍ እንዲገባ ስለሚፈለግ ነው። በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ግን በግንባታው ዘርፍ የተሰማሩ ከባንክ ብድር ለማግኘት ይቸገራሉ። የብድር ወለዱም ከፍተኛ ነው። በዚህ ነባራዊ ሁኔታ ካየነው ግን ጅምር ህንፃዎች ለኪራይ አገልግሎት መዋላቸው አግባብ እንደሆነ ተደርጎ ይወሰዳል። ይሄ ሁኔታ ባለበት ህንፃዎች በተያዘላቸው ጊዜ መጠናቀቅ አለባቸው ብለን አስገዳጅ ነገር ከወሰድን ህንፃ ወደማይሰራበት ደረጃ እንዳይደርስ መፈተሽ ያስፈልጋል። ጅምር ህንፃዎች ለአደጋ አጋላጭ አለመሆናቸውና የሌሎችንም በማይጋፋ መልኩ በተቆጣጣሪው አካል አስፈላጊው ክትትልና ቁጥጥር ተደርጎባቸው ለአገልግሎት የሚውሉበት መንገድ ቢመቻች የተሻለ ይሆናል። ህጉም በተወሰነ ደረጃ ይደግፋል። ክፍተቱ ለመልካም ነገር የወጣ መመሪያ ግን መሸራረፉ ነው። ክፍተቱ እየበዛ ሲሄድ ደግሞ መመሪያው ልክ አይደለም ይባላል።
ለመልካም ነገር ተብለው የሚወጡ መመሪያዎች የጊዜ ገደብ ሊኖራቸው አይገባም ወይ? የህንፃውን ባለቤትስ አያዘናገውም? ለሚለው ጥያቄም አርክቴክት ብሥራት በምላሻቸው ገበያው (ማርኬት ኢኮኖሚው) ይወስነዋል። እያንዳንዱ ሰው ያለውን ሁኔታ በማየት ነው ውሳኔ ላይ የሚደርሰው። ገንቢው አላግባብ ይዞ ቢቀመጥ ገበያው ገፍቶ ወደርሱ በመሄድ እንዲሸጥ ስለሚገፋፋው ክፍተቱ የት ጋር እንደሆነ ይለያል። አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ለአብዛኛው የሚጠቅመውን አማራጭ ማየት ነው። አብዛኛው አልሚ አቅሙ በፈቀደ ፍጥነት ግንባታውን አጠናቅቆ ገቢ ማግኘት የሚፈልግ ይመስለኛል። አይዘናጋም ወይ የሚለውም በግላቸው ብዙ የሚያስኬድ አድርገው አይወስዱም። 10 ወለል ያለው ህንፃ አጠናቅቆ የሥረኛውን በማከራየቱ ቀሪዎቹን ቢያዘገያቸው ከእያንዳንዱ ክፍል ሊያገኘው የሚችለው ጥቅም እንደሚቀርበት የማይገነዘብ አልሚ ስለማይኖር መዘናጋት የሚለው ብዙ አያስኬድም። ይልቁንም ለመጠናቀቅ የደረሱ ግንባታዎችን የሚመለከተው አካል ድጋፍ በመስጠት እንዲጠናቀቁ ማድረጉ የተሻለ አማራጭ እንደሆነ ያምናሉ። በተለይም ባንኮች ትልቅ ሚና እንዳላቸው ይገልፃሉ። ድጋፉና ክትትሉ ከተጠናከረ እንደ ሥጋት የሚነሱት የከተማ ገጽታ ግንባታ ላይ ስለሚኖረው ተጽዕኖ፣የግንባታ መጓተቶች እንደሚቀየሩ ያምናሉ። ሌላው መፍትሄ ብለው የጠቆሙት ከአልሚው ጋር ስምምነት በማድረግ ከፊሉ የህንፃ ክፍል ለመኖሪያ አግልገሎት የሚውልበት መንገድ ቢመቻች ችግሩን በተወሰነ ደረጃም ያቃልላል።
ጅምር ህንፃዎች ለኪራይ አገልግሎት እንዲውል ይበረታታል የሚለውን ሀሳብ የሚጋሩ ከሆነ ያልተጠናቀቁ ሥራዎች በሚከናወኑበት ወቅት ተገልጋይ ላይ ለሚደርስ ጉዳት ማን ተጠያቂ ይሆናል? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም በሰጡት ምላሽ ለዚህ የማያሻማ የግንባታ ህግ ተቀምጧል። በግንባታ ሂደት ወቅት ለሚደርስ ማንኛውም ጉዳት ተቋራጩ ኃላፊነት ወስዶ ነው የሚሰራው። ተቋራጩ ኢንሹራንስ ስላለው ተጠያቂ ነው። ሆኖም ግን ተቋራጩ ሥራዬን እየሰራሁ ነው እያለ ባለቤት የተወሰነውን ክፍል ካከራየ ጥያቄ ያስነሳል። የሚለከተው አካል ሊያየው ይገባል። ‹‹በእኔ እምነት ለኪራይ የሚውሉ ጅምር ህንፃች ከባድ ሥራ ወይንም የመዋቅር ሥራ የሚቀራቸው መሆን የለባቸውም። አነስተኛ የማጠናቀቂያና የማሳመር ሥራዎች ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላሉ ተብለው የሚጠበቁ ባለመሆናቸው ለኪራይ አገልግሎት መዋላቸው ክፋት የለውም››ሲሉም ተናግረዋል።
በጅምር ህንፃዎች አደጋን ከመከላከል አንፃር ስላለው ጥንቃቄም አርክቴክት ለገሀር አካባቢ አብሲኒያ ባንክ የሚያስገነባውን ህንፃ ለአብነት አንስተዋል። ከሥር አገልግሎት እየሰጠ ከላይ ደግሞ ግንባታውን ያከናውናል። በእግረኛው ላይ አቧራ እንዳይበን፣ሲተላለፍም ጥበት እንዳይኖር፣እንቅፋትም እንዳይገጥመው የተደረገው ጥንቃቄ በአርአያነት ይጠቀሳል። ከላይ ከባድ ነገር እንኳን ቢወድቅ መሸከም የሚችል ነገር በመሰራቱ ስጋቱን ቀንሶታል። ቀላል በሆነ መከላከያ በመጠቀም ግንባታ ማካሄድ ጉዳቱ እንደሚያመዝን ገልጸዋል። በእርሳቸው እምነት መፍትሄ እያለው ግን ትኩረት አለመስጠት ነው።
የፋይናንስ ምንጭ መኖሩን ሳያረጋግጡና የአዋጭነት ጥናትም ሳያደርጉ እየሰራሁ እጨርሳለሁ በሚል እሳቤ ወደ ሥራው የመግባት ሁኔታ መኖሩን መታዘባቸውን የገለጹት ሌላው አስተያየት ሰጭ የከተማና የአርክቴክቸር ቅርስ ትምህርት ክፍል ኃላፊና መምህር ተባባሪ ፕሮፌሰር ፋሲል ጊዮርጊስ በኪራይ ገቢ ግንባታውን ለመጨረስ የሚደረግ እንቅስቃሴ በስፋት መኖሩን በመጠቆም፤ ትልቁ ችግርም ለግንባታ የሚውል ገንዘብ እጥረት እንደሆነ ያስረዳሉ። እርሳቸው እንዳሉት አንዳንዴ ደግሞ በቅድመ ግንባታ ወቅት የታቀደውና ከግንባታ በኋላ ሌላ ሀሳብ ይመጣና የዲዛይን ለውጥ ይመጣና ግንባታውን ወደ ማሻሻል ሥራ ይገባል። በነዚህና በተለያዩ ምክንያቶች በተለይ በግል አልሚዎች የሚከናወኑ የህንፃ ግንባታ ሥራዎች ሳይጠናቀቁ ለረጅም ጊዜ የሚቆዩባቸው አጋጣሚዎች ብዙ ናቸው። በሰው ላይ ጉዳት በማድረስም ይሁን ለህንፃው ደህንነት ሲባልና የደህንነት ሥጋትን ለመቀነስ ግንባታን በጊዜ ማጠናቀቅ ይመከራል። በአልሚው በኩል ከሚነሱት የፋይናንስ እጥረት በዋናነት የሚጠቀስ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የግብአት አቅርቦት በቂ አለመሆንና በዋጋም ከሚታሰበው በላይ መሆኑ በአልሚዎች በኩል ሲነሳ በተለያየ አጋጣሚ እንደሚሰሙ ተባባሪ ፕሮፌሰሩ ተናግረዋል። ክፍተቶችን ለይቶና የሚመለከታቸው አካላት ተቀራርበው ችግሩን ለመፍታት ጥረት ካላደረጉ ግንባታዎች ተቋርጠው ረጅም አመት ሲቀመጡ ህንፃው አርጅቶ ለተለያየ ጉዳት የሚጋለጥበት አጋጣሚ እንደሚፈጠርም አመልክተዋል። የከተሞች የህንፃ ግንባታ መሥፈርትና የአልሚዎች አቅም አለመጣጣምም የራሱ የሆነ ተግዳሮት እንዳለውም አመልክተዋል። ተደራራቢ የሆኑ ችግሮችን ፈትቶ ግንባታውን ማጠናቀቁ አማራጭ የሌለው መፍትሄ እንደሆነም መልዕክት አስተላልፈዋል።
መሬትን በፍትሐዊነት ለመጠቀምና የቦታ ጥበትን ለማቃለል፣ብሎም ከተሞች ውብና ምቹ እንዲሆኑ ግንባታዎች ወደላይ እንዲከናወኑ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ያስገድዳል። ይሁን እንጂ በሌላ በኩል ገጽታን የሚያበላሽና የኢኮኖሚ አቅምንም የሚፈትን ከጥቅሙ ጉዳቱ የሚያመዝን ሥራ ውስጥ መግባት ኪሳራው ከግለሰብ አልፎ ሀገርንም እየጎዳ መሆኑ በግልጽ የሚታይ እንደሆነ ነው ሀሳባቸውን ካካፈሉት ባለሙያዎች መረዳት የሚቻለው። አሁን አረፈደም እንደሚባለው የእርማቱ ሥራ ቢጠናከርና ህጋዊ አሰራር ቢበረታታ መልዕክታችን ነው።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሰኔ 1/2013