በኢትዮጵያውያን ዘንድ መከባበር የሥነ ምግባር መገለጫ ሳይሆን የባህል ነፀብራቅ ጭምር ነው። ይህ ጥብቅ መስተጋብር ለዘመናት የህዝቦች ማንነት አንዱ አካል ሆኖ የቆየ ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን አደጋ እየገጠመው፣ ጥብቅ መሰረቱ እየተሸረሸረ መምጣቱን በርካቶች ይናገራሉ። የዝግጅት ክፍላችንም በጉዳዩ ዙሪያ የስነልቦና ባለሙያ የሆኑትን ወይዘሪት ሀና ሁሴንን አነጋግሮ የሚከተለውን ይዘን ቀርበናል።
እኛ ኢትዮጵያውያን የእርስበርስ ክብርና መቻቻል ውበታችን ነው። በልዩነቶች ውስጥ አብሮነትን ገንብተናል። መከባበር የሀገራችን መገለጫና ሀብት ነው ማለት እንችላለን። የሀገራችን ምቹ የሆነ አየር ፀባይ እና ምድራዊ አቀማመጥ ለተለያዩ የባህልና ሃይማኖት መገኛ አድርጎናል። የኋላው ከሌለ የፊቱ አይኖርምና አባቶቻችንም ይህን አስጠብቀዋል፤ ሀገርና ድንበርንም ከጠላት ተከላክለዋል። በልዩነታችን ውስጥም ቢሆን ከጥንት ጀምሮ የምንጋራው ትልቅ እሴት መከባበር ነው።
መከባበር ለአንድ አካል ወይም ድርጊት የምንሰጠው ቦታ ወይም ግምት ሲሆን መከባበር ከሌሎች ሰዎች ጋራ ለመኖር ወሳኘነት አለው። በግል ህይወታችን እንዲሁም በህብረተሰብ ውስጥ ዘላቂ የሆነ ሰላም እንዲኖረን መከባበርን ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ ነው። በዕለት ተዕለት ኑሯችን ውስጥ መከባበር ራሱን በተለያዩ አጋጣሚዎች ይገልፃል። በቤተሰባዊ ግንኙነት፤ በባልና ሚሰት መካከል፤ በጎረቤት አና በጓደኞች፤ በህዝብ አገልግሎት መስጫዎች እና ሙያዊ ግንኙነቶች ወዘተ ውጤታማነት ላይ ያለው ተጽዕኖ ትልቅ ነው።
የህይወት መርህ የሚመሰረተው ራስን በማወቅ እንደመሆኑ መቻቻልም በህብረተስብ ውስጥ እርስ በርስ በመተዋወቅ ይጀምራል። የአንድ ህብረተሰብ መግባባት መጠንም ግለሰቡ ራሱን በሚገልፅበት መንገድና ባለው ተቀባይነትም ይወሰናል። መንገዳችን የተለያየ ቢሆንም የሌሎችን ማንነት እስካልጣሰ ድረስ መቻቻል አብሮነትን ይሸከማል። በልዩነት ውስጥ መከባበር ከመቻቻል ከፍ ያለ የአዕምሮ ብቃት ይጠይቃል። መከባበር መቻቻልን ሲያቅፈው የአንድ ማህበረሰብ ጤነኝነት ይረጋገጣል።
እሴቶቻችን እርስ በርስ ተደጋጋፊ በመሆናቸው የመከባበር አለመኖር አደገኛ ነው። የማህበረሰብ ህልውና በወግና ባህል ታጅቦ የሚዘረጋው በአመኔታ እና የፍትህ መዋቅሩ ጥንካሬ ላይ ነው ማለት እንችላለን። ሰው በሰውነቱ ብቻ የሚያገኘው ሰብአዊ መብቱ መከበር ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ግን በህበረተስቡ ዘንድ ሊወርድም ከፍ ብሎ ሊታይም ይችላል። ባለፉት ዘመናት የክበር መለኪያ ተደርገው የሚወስዱት የዘር ሐረግ፤ ስልጣን፤ ገንዘብ ሲያልፍም ጀብደኝነት እንደነበረ ሁሉ አሁንም በዚህ ዘመን የተለያዩ መለኪያዎች ይቀመጡለታል።
የመከባበር አለመኖርም ይህን የክብር ክፍፍል ወይንም የዋጋ ምዘና በእጅጉ ያዛባዋል። በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ ተቀባይነት የሚያገኙ ጉዳዮች በማህበረሰቡ ስነ ልቦናዊ ንቃት ይወሰናሉ። ለአንዱ ልክ የሆነው ለሌላው ልክ ሳይሆን ሲገኝ በንግግር ወደ አንድ ነጥብ መድረስ ሳይቻል ሲቀር “Let’s agree to disagree” (“ባለመስማማት መስማማት” እሚባለው) የሚል መሰረታዊ መቻቻል እንደ ብቸኛ አማራጭ ይወሰዳል። ከእንዲህ ዓይነት ስምምነት ለመራቅ ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል በሚባል ደረጃ ብዙ ፈታኝ ነገሮች ይገጥሙታል። አንዳንድ ጥቃቅን ግጭቶችም ከአፈና (Suppression) አምልጠው ትልቅ ጉዳት እንዲያደርሱም ያደርጋል።
ግጭቶች መመለስ የማይቻልበት ደረጃ ላይ ሳይደርሱ ለማብረድ ሃይልን ከመጠቀም በፊት ቀድመው መፍትሄ በመሆን ሀገራችንን ከከፋ ችግር ለማዳን የሃይማኖት መሪዎች፣ የሀገር ኩራት የሆኑ አርአያዎች፤ ብሎም በህብረተሰቡ ዘንድ በዕድሜ የተከበሩ ሽማግሌዎችና አዛውንት ከፍተኛ ድርሻ ነበራችው። ህዝቡም ቢሆን ከከበሩት አዋቂያን የሚሰጡ ተግሳፆችና ምክሮችን ቆም ብሎ ለመመርመር የሞራል ብቃትና ልህቀት የነበረው ቢሆንም በአሁኑ ሰዓት ግን እውነታው ከዚህ የራቀ ሆኗል።
መከባበርም ሆነ መቻቻል ሊያቆሙት የማይችል የሚመስል ተስፋ አስቆራጭ የማህበረሰባዊና ቤተሰባዊ ቀውስ ውስጥ ሳንወድቅ አልቀረንም። ተጠያቂ አካልም ሆነ ሂደት በዛም በዚም ብናሳድድ መከባበር ላለመኖሩ የሚጨበጥ አንድ ምክንያት መገኝቱ ያጠራጥራል።
ሰዎች በስልጣኔ ጫና አይቀሬነት የአኗኗራቸው መንገድ በተቀየረ ቁጥር ግላዊ የሆነ ባህርያቸውና የነፃነት ትርጓሚያቸው ከህብረተሰብ በአንድ አንድ ጉዳዮች በመቅደም በማይጠበቅ መልኩ በሌሎች መንገዶች ወደ ኋላ በማሽቆልቆል ከማህበረስቡ ይገነጠላሉ። መገንጠል ስንል ተገፍቶ ወይም በራስ አድራጊነት ሊሆን ይችላል። የቤት አሰራሮቻችን ብሎም አሰፋፈራችን የሚያሳየም ዘመን አመጣሸ ስልጣኔ ምን ያህል ከእሴቶቻችን እንዳዘናጉን ማየት ይቻላል።
ተግሳፆች እና የተቃውሞ ገለፃዎች በየግዜው ከተቁዋማት እና ተፅእኖ አድራጊዎች ቢሰጥም ውሃ ቢወቅጡት እንቦጭ እየሆነ እንዲያው ይታለፋል። ለምን? መጀመርያውንም በመሸፋፈን ላይ የተመሰረተ አድር ባይ መቻቻል ከመግባባት አያደርስም ብንል ማሳነስ እንጂ አይበዛም። መከባበር መተዋወቅን መቀበልን ይሻል። ከራስ ወዳደነትና በምክንያት ላይ ያልተመሰረት ንግግሮችን ወደ ኋላ በማለት በነፃ መድረክ በውይይት ሲደረጅ መከባበር ዘላቂነት ይኖረዋል። ተሰሚነት ያላቸው አካላት በአጉል ቦታ ሲገኙ የተከታዮቻቸውንም አቋም በማንገዳገድ ጉዳት ያደርሳሉ – አድርሰዋልም። ያልተጣሩ ዜናዎች እና ስም ማጥፋቶችም በሰፊው በተሰራጩበት በአሁኑ ጊዜ ታላላቆቻችንን ድምፅ ማሳጣት በጣም ቀላል ሆኗል። ለዚህ ተጠያቂ ማበጀት መቻሉንም እንጃ!
የግለሰቦች የህይወት መርህ በስነ ስርዓት አለመደራጀት ከራስ አልፎ ህብረተሰብ ላይ ያለው ተፅእኖ ይህ ነው የሚባል አይደለም። ሌሎችን ለማክበር ራስን ማወቅ፣ መረዳት እና ማክበር ግድ ይለዋል። ታላላቆቹን የሚያከብር ህዝብ ለራሱ የሚሰጠው ዋጋ በብር ኖቶቹ ሳይቀር ይገለጣል። የነገ ሰው ይበለንና ነገን ስላም እንዲሆን በፍቅር እና ሰብዓዊነት ላይ የተመሰረተ መደማመጥ፥ መቻቻል፤ ከፍ ሲልም መከባበር እንዲኖረን ሁላችንም ወደ ውስጣችን እንደምናይ ተሰፋ አደርጋለሁ።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ሰኔ 1/2013