ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ብዙ ሂደቶችን አልፎ ሰኔ 14 ድምጽ የሚወሰንበት ቀን እንዲሆነ ቀን ተቆርጧል። በዚህ ሂደት ውስጥ የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎና ተመራጭነት ምን ይመስላል፤ የተገቡ ህጋዊ መስመሮችስ በምን መልኩ እየተጓዙ ነው። እንዲሁም ወቅታዊ ሁኔታው በአካል ጉዳተኞች መነጽር ምን ይመስላል? የሚሉና መሰል ጥያቄዎችን በማንሳት ከኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌደሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይነህ ጉጆ ጋር ቆይታ አድርገናል። መልካም ንባብ እንዲሆን በመመኘት ታነቡት ዘንድ ጋበዝን።
አዲስ ዘመን፡- የአካል ጉዳተኞችን መብት ከማስጠበቅ አንጻር የሌሎች አገራት ተሞክሮ ምን ይመስላል፤ ከዚህ አንጻር በአገር ውስጥ ያለው እንዴት ይገለጻል?
አቶ አባይነህ፡- በአለም አቀፍ ደረጃ አሁን ብዙ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ቢኖር የአካል ጉዳተኞች ነገር ነው። በዚህም በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ የአካል ጉዳተኞች መካተታቸውን ለማረጋገጥ ሰፊ ሥራዎች እየተከናወኑ ናቸው። ሩቅ ሳንሄድ በቅርባችን ያሉ አገራትን በልማትና መሰል ነገሮች እንዲሳተፉ ማድረግ ያለባቸውን ያህል እየተጓዙ ነው። በስፖርቱ አለም ጭምር ራሱን እያገዘ እንዲኖር አስችለዋል። ብናነሳ ፓርላማ ውስጥ ጭምር በቋሚነት ካላቸው የፓርላማ ወንበር ውስጥ ዘጠኙ የአካል ጉዳተኞች ነው። ማንኛውም ፓርቲ ቢያሸንፍ ከአካል ጉዳተኛ ማህበራት ውስጥ አንድ መስማት የተሳነው፣ አንድ አይነስውር፣ አንድ አካል ጉዳት ያጋጠመው፣ አንድ ከአዕምሮ እድገት ውስንነት እየተባለ ይገባል። ይህ ደግሞ የአካል ጉዳት በሁሉም ሰው እንዲቀመጥ ያደርጋል። በህግ ብቻ ሳይሆን በተግባርም ለመተርጎም ያግዛል። ፖሊሲና ህግ ሲወጣም የእነርሱ ጉዳይ እንዲካተት ያደርጋል።
የእኛ አገር ነባራዊ ሁኔታ ግን ከዚህ በብዙ መንገድ የራቀ ነው። ምክንያቱም ከትምህርት ብንነሳ 92 በመቶ የአካል ጉዳተኛ ከትምህርት ውጪ እንደሆነ ትምህርት ሚኒስቴር ሲገልጽ ነበር። ይህ ግን ትክክል አይደለም። ዜጋዬን በትምህርት ተደራሽ አድርጌያለሁና አካል ጉዳተኞች አልተማሩም ይጣረሳሉ። እንደዜጋ እንዳልታዩም አመላካች ነው። ተጠያቂነትም ያመጣል። ይህንን ሲናገርም ከእነሀፍረቱ ሊደበቅ ይገባዋል እንጂ አስተማርኩ ማለት አልነበረበትም። ግን ማንም ምላሽ የሚሰጥ ስላልሆነ አልተደረገም።
ምርጫ ቦርድም አሁን ካርድ ያወጡና በተመራጭነት የቀረቡ ምን ያህል ናቸው የሚለውን ለመመለስ ያልፈለገው የአካልጉዳተኞች በአጠቃላይ ምን ያህል ናቸው የሚለው መረጃ ስለሌለው ነው። ስለዚህም የአካልጉዳተኞች ጉዳይ በአገር ደረጃ ብዙ ሥራ የሚጠይቅና ዳዴ እያለ ያለ ነው።
በቅርቡ የአለም የምግብ ድርጅት ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው ኢትዮጵያ አምስት ነጥብ አንድ በመቶ አካል ጉዳተኞችን ወደ ሥራ ባለማስገባቷ ከዓመታዊ እድገቷ ትቀንሳለች ይላል። ነገር ግን መንግስት እያወቀ አልሄደበትም። በሌላ በኩል ሲታይ ደግሞ ከኢትዮጵያ አልፈው አለም መለወጥና መምራት የቻሉ አካልጉዳተኞች መኖራቸው አገር ምን ያህል እንዳጣቻቸው የሚያሳይ ነው። ለዚህም በአብነት የሚነሱት እስካሁን ዜግነቱን ሳይቀይር በአሜሪካ መስማት የተሳናቸው ማህበር ፕሬዚዳንት የሆነው አንዱ ነው። በተመሳሳይ የአፍሪካ አካል ጉዳተኞች ፎረም ፌደሬሽን ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ሲመራ የነበረውም ኢትዮጵያዊ አካል ጉዳተኛ ነው።
የፊላንድ ዊልቸር ተጠቃሚ ማህበር ፕሬዚዳንትም ኢትዮጵያዊ ነው። ሆኖም እዚህ ያሉትን ማንም አንስቷቸው እንዲህ እንዲሆኑ እያደረጋቸው አይደለም። ከዚያ ይልቅ ዛሬም ድረስ ልፋታቸው አይታይም። ቴክኖሎጂው በረቀቀበት ጊዜ አካል ጉዳተኞች በአገራችን ትልልቅ ተብለው በሚጠሩ ዩኒቨርሲቲዎች ጭምር የተመቻቸ ቦታ ሳያገኙ ሰው እያነበበላቸው አሁንም የሚፈተኑ ናቸው። መንግስት የሴቶች ተሳትፎን በሚኒስትር ደረጃ 50 በመቶ አድርሻለሁ ሲል የአካልጉዳተኞችን አንድ በመቶ እንኳን አላካተተም። አሁን ከለውጡ በኋላ መሻሻሎች ይታያሉ። ለዚህም ማሳያው በስርዓተ ትምህርት ውስጥ ተካቶ የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ እንዲታይ መደረጉ አንዱ ነው። ይሁንና ችግሩ የተጠራቀመ ስለሆነ መፍታት አልተቻለምም። ስለዚህም በአገር ደረጃ ብዙ መስራትን ይጠይቃል። መንግስትም ቢሆን ትኩረቱን ማስፋት አለበት።
ለ20 ሚሊዬን አካል ጉዳተኛ በሚመጥን መልኩ ሥራዎች ሊከወኑ ይገባል። ለአብነት በአዲስ አበባ ብቻ ቢታይ የቤት ጉዳይ ሲነሳ አካልጉዳተኛውን ያገናዘበ አይደለም። ለአካል ጉዳት አልባውም ጉዳተኛውም እኩል ክፍያ ይጠየቃል። አጠናቅ ሲባልም በእኩል መንገድ ነው።
እንደውም የሚገጣጠመው ሳይቀር ቤቱ ውስጥ ተወርውሮለት ግባ ይባላል። ይህ ደግሞ ከትኩረት ማነስ የመነጨ ድርጊት ነው። እናም የተጀመረውን እንዳይቆም መንግስት ሲደጉም አካልጉዳተኛው እንደፈለገው ከሚንቀሳቀሰው እኩል ሊሆን አይችልምና ድጎማው እርሱንም ታሳቢ ያደረገ መሆን አለበት። አካል ጉዳተኛውን ያገናዘበ ኮንዶሚንየም እየተሰራ ስላልሆነ ይህም መታሰብ ይኖርበታል። የትራንስፖርት ጉዳይም ቢሆን እንዲሁ መመርመር ያለበት ነው። የባቡሩ ብቻ ቢታይ ሊፍት የተገጠመለት ቢሆንም አንዱም አይሰራም። እናም የህዝብ ገንዘብ የፈሰሰበት ንብረት አገልግሎቱን ካልሰጠ ጠቀሜታው ምንም ነው። ስለዚህም መታየት አለበት።
አዲስ ዘመን፡- አገራችን ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ካልሆኑ አገራት ተርታ ትሰለፋለች ይባላል። ይህንን ከመለወጥ አኳያ ፌደሬሽኑ ምን ሰርቷል?
አቶ አባይነህ፡- እንደ ፌደሬሽን ብዙ ተግባራትን ከውነናል። መርሀችን ‹‹ያለኛ ስለኛ ምንም ነውና አሳትፉን›› የሚል ስለሆነ ካሳተፉን የማናኖረው አሻራ የለም። በዚህም አዲሱ የሲቪል ማህበረሰብ አዋጅ መሻሻል ላይ አሻራችንን አኑረናል። ለተግባራዊነቱም ለመስራት የቦርድ አባል ሆኖ እንዲቀጥል ሁለት አባሎችን አስገብተናል። ከዚህ ጋር በተያያዘ የምርጫ ህጉ ላይም ብርቱ ተሳትፎ አድርገን የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ በደንብ የሚታይበትን ሁኔታ አመቻችተናል። አፈጻጸሙ ጥያቄ ውስጥ ቢገባም። አካልጉዳተኞችን በመራጭና በተመራጭነት ወደ ፊት ለማምጣት የተያዘ ነገር እንዳለ ለማየት ተችሏልም። ለአካል ጉዳተኞች ምቹ አከባቢ ከመፍጠር አንጻር ምን አይነት ህጋዊ መሰረት ተቀመጠ የሚለውንም አይተናል። ለአብነት ኮሮጆ የሚቀመጥበት ቦታ ምን መምሰል አለበት፣ አይነስውራን ራሳቸው የመረጡትና ባመኑት ፓርቲ ላይ ብቻ ምልክት እንዲደረግላቸው ምን ምቹ ነገር አለ፤ ስልጣኑ ተሰጥቷቸዋል ወይ የሚለውንም ለማረጋገጥ ተሰርቷል።
ሌላው እንደፌደሬሽን በአገር ውስጥ ያሉ ህጎችን ነቅሶ አውጥቶ ለመንግስት መስጠት ነው። መሻሻል ያለባቸው ላይ እንዲሻሻሉና የሌሉ ህጎች እንዲወጡም ግፊት እያደረገ ይገኛል። የአካል ጉዳተኞች ህግም እንዲወጣ መንግስትን በማሳመን ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሰራ ነው። የረቂቅ ሥራውም ተጠናቋል። የፍትሀብሔር ህጉ ይሻሻላል ብሎ በአለም አቀፍ ቀርቦ ምስጋና ቢያገኝም እስከዛሬ ለውጥ አላሳየም። በዚህም እውር፣ ዲዳ፣ ደንቆሮ፣ ሽባ ምናምን የሚሉ ክብረነክ ቃላት ሳይቀሩ እንዳሉ ናቸው። ማንም ይህንን ቢልም ተጠያቂ አይሆንም። ስለዚህም እንደ ፌደሬሽን ይህ እንዳይሆን ብዙ ትግል እያደረግን ነው።
ከመረጃ ጋር ተያይዞም እንዲሁ ለአይነስውራንና መስማት ለተሳናቸው ምን ምቹ ሁኔታ እንዳለ ያየንበት ሁኔታ አለ። በአዋጅ አዋጁ ለአይነስውራን በብሬል ታትሞ እንዲሰጣቸው ከማድረግ አኳያ የሚያስገድድ ህግ አለ ወይ፤ ተካቷል ወይ የሚለውን የተሰራ ሥራም አለ። በተመሳሳይ መስማት ለተሳናቸውም በምልክት ቋንቋ መረጃዎች እንዲደርሷቸው ምን ያህል ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል የሚለውንም በማዕቀፍ ደረጃ ለማየት ተሞክሯል። ከዚያ ባሻገር አካል ጉዳተኞች በጉዳታቸው ምክንያት እንዳይገለሉ ምን የተለየ እድል በህግ ደረጃ ተሰጥቷቸዋል።
የስልጠና ጣቢያዎችና አቀባበሎች ምን መምሰል አለባቸው የሚለውም ታይቷል። አካል ጉዳተኞች ፖለቲካ ፓርቲን ወክለው የመምጣት እሳቤን እንዲያራምዱ ምን ነጻነት አላቸው፤ ፓርቲዎችስ የአካል ጉዳተኞችን አቅም አምነው ለማሳተፍ ዝግጁ ናቸው ወይ የሚለውም በህግ ማዕቀፉ ዘርዘር ተደርጎ እንዲታይና እንዲቀመጥ አድርገናል። ያው አፈጻጸሙ ጥያቄ ውስጥ ቢገባም። እናም እንደ አጠቃላይ በፌደሬሽን ደረጃ በሦስት ጉዳዮች ላይ ከምርጫው ጋር በተያያዘ እየሰራን እንገኛለን።
የመጀመሪያው አጠቃላይ የምርጫ ሂደቱን መታዘብ ነው። ይህንንም በድጋፍ ሳይሆን እንደማንኛውም ማህበር ፈቃድ ተሰጥቶን ነው እያደረግነው የምንገኘው። ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ 241 የአካል ጉዳተኞችን በታዛቢነት በማሰልጠን ፈቃዱ ተሰጥቷቸው ባጅ ጭምር ተሰርቶ ተሰጥቷቸዋል። ይሁን እንጂ ሙሉዎቹ ወደ ሥራ እንዲሰማሩ አልሆነም። በደቡብ፣ በሲዳማ፣ በአማራና ኦሮምያ እንዲሁም አዲስ አበባ ብቻም ነው ታዛቢዎችን ማሰማራት የቻልነው። ለዚህ ደግሞ ያለን አቅም ውስንነት በዋናነት ይጠቀሳል። ስለሆነም ከእነዚህ ውስጥ 120 የሚሆኑት ናቸው የተሰማሩት። ይህ የሚያሳየው ደግሞ አካል ጉዳተኞች በገንዘብ ምክንያት የመታዘብ መብታቸው ታቅቧል ማለት ነው።
ሁለተኛው እየሰራን የምንገኘው ተግባር የመራጮች ትምህርት ሲሆን፤ በእነዚህ በተመረጡ ቦታዎች ላይ ብቻ ይከናወናል። ለዚህ ደግሞ ካርድ የወሰዱ አካል ጉዳተኞችን በማህበራችን አማካኝነት አባሎችን ብቻ ለማወቅ ተችሏል። ምክንያቱም አባል ለመሆን ክፍያና ፈቃደኝነትን ይጠይቃል። ይህንን አምኖ የሚመጣው ውስን ነው። በዚህም በሙሉ የአካል ጉዳተኞችን በእነዚህ ቦታዎችም ለማስተማር አዳግቷል። እንደውም አስተማርን ለማለት ያህል እንጂ በአማካኝ በአንድ ክልል ከ50 የበለጡ ሰዎች ለማስተማር አይገኙም። ስለሆነም 20 ሚሊዬን የሚሆን አካል ጉዳተኛ እያለ በዚህ ደረጃ ማስተማሩ ካለማስተማር ተለይቶ የሚታይ አይደለም።
በተቋሙ ከ40 ያላነሱ ሰዎች የአሰልጣኞች ስልጠና ወስደዋል። በዚህም ከ540 እስከ 600 የሚደርሱ አካል ጉዳተኞች እስካሁን መሰልጠንም ችለዋል። ሆኖም በህጉ እኛ የመጠየቅ እንጂ ሌላ ተሳትፎ የማድረግ ግዴታ አልተጣለብንም። መንግስትን ለምን አላደረግክልንም ብሎ መጠየቅ ብቻ ነው ስራችን። ነገር ግን እንደ አገር ሲመጣ ተጠይቆም ምላሽ በማይኖርበት ሁኔታ ዳር ብንቀመጥ ተሰሚነታችን ያከትምለታልና ይህንን ማድረጉን ትተን መሳተፉና መግፋቱ እንደሚበጀን አውቀን እየሰራን ነው።
አዲስ ዘመን ፡- በስድስተኛው አገርአቀፍ ምርጫ በምርጫ የመሳተፍና ታዛቢነት ዙሪያ እንደ ማህበር ያለው እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?
አቶ አባይነህ፡- ብሔራዊ ምርጫው ሰኔ 14 ቀን ተቆርጦለታል። በዚህም ፌደሬሽኑ ከመዋቅር ስንነሳ በአገር አቀፍ ያሉ ሁሉም ብሔራዊና ክልላዊ የአካል ጉዳተኛ ማህበራትን ባቀፈ መልኩ ለሁሉም አካል ጉዳተኞች ድምጽ በመሆን እያገለገለ ያለ ተቋም ነው። ከዚህ አንጻርም ከጫፍ እስከጫፍ ያሉ ወደ 20 ሚሊዬን በላይ የሚገመቱ የአካል ጉዳተኞች ድምጽ ይመለከተናል ብለን እየሰራንም እንገኛለን። ከዚህ በመነሳትም ብሔራዊ ምርጫውን ስንመለከት ገና ከመነሻው በአዲሱ በለውጥ ዘመን መንግስት ትኩረት አድርጎ በአዲስ መልክ ምርጫ ቦርድን ሲያቋቁም የማቋቋሚያ አዋጁ ጭምር የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ፌደሬሽን በነቂስ በመሳተፍ የነቃ ተሳትፎ አድርጓል።
በተሳትፏችን የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ በአዋጁ እንዲካተት የተደረገበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ይህ ደግሞ እስከዛሬ ካለው የምርጫ ሂደት በአንጻራዊነት የተሻለና ያካተትነው ብለን እንወስዳለን። አካታችነት አለ ሲባልም በዋናነት የምርጫው ተደራሽነት ለአካል ጉዳተኞች ምን ይመስላል የሚለው ይታያል። በዚህም ተደራሽነትን በሦስት መልኩ ከፍሎ ማየት ይቻላል። የመጀመሪያው መረጃ ሲሆን፤ ምርጫውን በተመለከተ ለአካል ጉዳተኞች በአግባቡ ደርሷል ወይ የሚለው ይታያል። ሁለተኛው አካል ጉዳተኞች በመራጭነት ፣ በተመራጭነትና በታዛቢነት እንዲሳተፉ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ፤ ተካተዋል ወይ የሚለው ነው። በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ መሰረተ ልማቱ ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ነወይ የሚለው ይነሳል። ጣቢያው ድረስ በመሄድ መምረጥ ይችላሉ ወይ የሚለውም ይታያል። ይህ ዘርዘር ተደርጎ ሲነሳ በወረቀት ደረጃ መኖሩ ታይቷል። አፈጻጸሙ ግን በጣም ብዙ ችግሮች ያሉበት ሆኖ አግኝተነዋል።
አዲስ ዘመን፡- እንደተባለው በህግ ማዕቀፍም ሆነ በአዋጅ እንዲሁም በመመሪያ ደረጃ ብዙ ስለአካል ጉዳተኞች ይባላል፤ ይቀመጣልም። ከዚህ አንጻር ተግባራዊነቱን እስካሁን ባለው የምርጫ ሂደት እንዴት አያችሁት?
አቶ አባይነህ፡- እስካሁን የተነሳው ከህግ ማዕቀፍ አንጻር ምን ተሰራ የሚለው ሲሆን፤ ለአካል ጉዳተኞች ተሳትፎ ከአንድ እስከ አምስት ከነበሩት ምቹ ሁኔታ ፈጥሮ የስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ጥሩ እድል የሰጠ ነው ሊባል ይችላል። ምክንያቱም የስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ማካሄድ እንችላለን የተባለበት ህግ ላይ ቅርጽ የያዘ ህግ እንዲኖረን አድርጓል። በዚህም ህጉን ተከትለን በምንሄድበት ጊዜ አሁን ወደ መጨረሻው ምዕራፍ የተሸጋገረው ምርጫ ባሳለፈው ሂደት ውስጥ ስጋቶችን አሳድሮብናል። ከስጋቶቹም በአንደኝነት ደረጃ የሚጠቀሰው ህጉ መሬት ላይ ወርዶ እየተሰራበት አለመሆኑ ነው። የወረቀት ህግ ብቻ ነው እንድንል ያስቻሉን ብዙ ችግሮች ተፈጥረዋል።
በዋናነነት የሚነሳው የአካባቢ ተደራሽነት ሲሆን፤ አካል ጉዳተኞች ዋጋ እንዲከፍሉ እየተደረገም ነው። የምርጫ ካርድ በሚወሰድበት ጊዜ ፌደሬሽኑ በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ምርጫ ካርድ አካል ጉዳተኞች መውሰድ እንዲችሉ ሲያስተምር ነበር። ነገር ግን ሲሄዱ የተለያዩ ችግሮች ያጋጥማቸዋል። ካርድ ሳይወስዱ የተመለሱ ጭምርም አሉ። የአንዱን ጉዳት ሲሰማ ሌላው ተስፋ ቆርጦም ቀርቷል። እነዚህ ወገኖች ደግሞ ካርዱ አልፏቸዋል። በዚህም በነቂስ ወጥተው ምርጫ ካርድ ወስደዋል የሚል እምነት የለንም።
ምርጫ ቦርድ በራሱ ከህግ ውጪ አካሄዶችን እየተከተለ ይገኛል። ለዚህም ማሳያዎች አሉን። ለአብነት መረጃ ስንጠይቅ ምላሽ መስጠት አይፈልግም። እናም ስንት አካል ጉዳተኞች የምርጫ ካርድ ወሰዱ፣ ስንቶቹ በፓርቲዎች ውስጥ ገብተው በአገር ደረጃ ተመራጮች ናቸው የሚለውን አናውቅም። ይህንን መረጃ የሚሰጠው መንግስት ብቻ ነው። መንግስት ደግሞ ምርጫ ቦርድን ወክሎ እየሰራ ይገኛል። ስለሆነም ይህንን ባላገኙበት ሁኔታ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮላቸው የመመረጥና የመምረጥ መብታቸውን እየተጠቀሙ ነው ለማለት አልቻልንም።
በሌላ በኩል አካል ጉዳተኞች በመራጭነት፣ በተመራጭነት በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ ምን አይነት ችግሮች አጋጥሟቸዋል የሚለውን በህግ ደረጃ እንዲያይ ተቀምጧል። እስካሁን በዚህ ዙሪያ እንደ መንግስት ሪፖርት የቀረበ ነገር እንዳለም ጠይቀናል። ምላሹ ግን አሁንም የለም። ስለዚህም ይህን እያየው ነው ለማለት ያስቸግረናል። ምርጫ ቦርድ በመንግስት በጀትና ከለጋሽ አካላት በሚያገኘው ገንዘብ የሚንቀሳቀስም ነው። ነገር ግን ግልጽ ባልሆነ መንገድ እስከዛሬ ድረስ ከፌደሬሽኑ ጀምሮ የፋይናንስ ድጋፍ ብንጠይቅም ምንም ምላሽ አልሰጠም።
የአለምአቀፍ የአካል ጉዳተኞች መብት ጥበቃ ኮንቬንሽን በግልጽ እንዳስቀመጠው መንግስት የአካልጉዳተኞች ተልዕኳቸውን ሊያሳኩ በሚንቀሳቀሱበት ወቅት በተለይም ማህበራት ቴክኒካልና ፋይናንሽያል ድጋፍ ማድረግ አለበት ይላል። ሆኖም መርሁ ተጥሶ ምንም አይነት ድጋፍ እየተደረገልን አይደለም። በራሳችንና በአጋዥ አካላት እገዛ ነው ያለነው። እንደ ፌደሬሽን ለመታዘብ ፈቃድ ወስደን እየተንቀሳቀስን እንገኛለን። አካል ጉዳተኞችን መልምለንና አሰልጥነን በታዛቢነት አሰማርተናል።
አዲስ ዘመን፡- በክልል፣ በዞንና በወረዳ እንዲሁም በፓርቲ ደረጃ ያለውስ ተሳትፎ እንዴት ይገለጻል?
አቶ አባይነህ፡- በቁጥር ደረጃ ምርጫ ቦርድ ካልገለጸና ካልነገረን በስተቀር የሚታወቅ ነገር የለም። ለዚህ ደግሞ ምርጫ ቦርድን ጠይቀን ያገኘነው የለም። ያለመረጃም ነው ስልጠናዎች እየተሰጡ የሚገኙት። በማህበራችን በኩል ይህንን ያህል አካል ጉዳተኞች ተመራጭ ናቸው፤ ይህንን ያህሉ ደግሞ ካርድ አውጥተዋል ብንል መረጃውን ያዛባዋል። ምክንያቱም የአካል ጉዳት ያለባቸው ሁሉ የማህበሩ አባል አይደሉም። እናም ሙሉ መረጃ ለመግለጽ ያዳግታል። ሲቀጥል ምርጫ አባልና አባል ላልሆኑት ብቻ የሚሰጥ ነጻነት ስላልሆነ ለሁሉም መስራትን ይጠይቃል። ለዚህ ደግሞ ምቹ ሁኔታዎች ያስፈልጋሉ። ይህ ነገር ባለመመቻቸቱም ብዙ የታጣ ነገር እንዳለ ይሰማኛል።
አስፈጻሚው ቁርጠኛ መሆን ካልቻለ መመሪያ ብቻ ዋጋ የለውም። በነቂስ ወጥተን የተሳተፍንበት የህግ ማዕቀፍ አካል ጉዳተኞችን በሚመለከት ብዙ ነገሮችን ያስገድዳልም ያዛልም። ሆኖም አስፈጻሚው አካል ከፓርቲዎች ጋር ቁርኝት ፈጥሮ ያሳተፉትን አካልጉዳተኛ አቅርቡ ቢል በአንድ ቀን የሚያደርገው ነበር። ነገር ግን ቁርጠኝነቱ የላላ በመሆኑ አልተገበረውም።
በሌላ በኩል ምርጫ ቦርድ በአካል ጉዳተኞች የመረጃ ተደራሽነት ላይ መስራት ቢኖርበትም ወጥተው እንዲመርጡና ቅስቀሳ እንዲያደርጉ ያበረታታበት ሁኔታ የለም። ለአብነትም መስማት የተሳናቸውና አይነስውራንን ብናነሳ ብዙ እክሎች ገጥሟቸዋል። ከእነዚህ መካከልም መስማት የተሳናቸው ምልክት ቋንቋን በመጠቀም መልዕክቶችን ማስተላለፍ ባለመቻሉ የምርጫ ካርድ ማውጫ ጊዜ መራዘሙንም ሆነ ምርጫው መራዘሙን አላወቁም ነበር። የእያንዳንዱን ፓርቲ ማኒፌስቶም ቢሆን በደንብ የሚረዱበት ሁኔታ ስላልተፈጠረ ማንን መምረጥ እንዳለባቸው ግራ ተጋብተዋል። በተመሳሳይ አይነስውራንም ብሬን ይዘጋጃል ቢባልም ተግባራዊነቱ ግን የለም በሚባል ደረጃ ላይ በመሆኑ የዚህ ተጠቂ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- ብዙ ፓርቲዎች ሴቶችን እንጂ አካል ጉዳተኞችን አግኝተው ማሳተፍ እንዳልቻሉ ያነሳሉ። ችግሩ የማን ነው ይላሉ?
አቶ አባይነህ፡- የእንትናና የእንትና ማለቱን ብንተወው እንኳን ትኩረት አለመስጠት ዋነኛ ምንጩ እንደሆነ አምናለሁ። ምክንያቱም በህግ ደረጃና በውይይቶች ላይ ተሳታፊ ተደርገን ብዙ ነገሮች መፍትሄ እንደሚያገኙ ተስፋ ተሰጥቶናል። ሆኖም ወደ ተግባሩ ሲገባ የተለየ ቅርጽ ይዟል። ለምሳሌ ፓርቲዎች አጣን ካሉ የእነርሱ ትኩረት አለመስጠት ያመጣው እንደሆነ አምናለሁ። ምክንያቱም አካል ጉዳተኛው ያለው ከእነርሱ ደጅ መሆኑ ግልጽ ነው። አምኖ ማሳተፍና ስልጣን መስጠቱን ካልፈሩ በስተቀር አጣን የሚለው አያስኬዳቸውም። ሰፈሩ ላይ ያለን አካል ጉዳተኛ ትቶ ለማሳተፍ አጣሁ ቢልም ያስቃል።
ገዢው ፓርቲ ከ2ሺህ በላይ እጩዎችን አስመዝግቧል፤ ስንት የአካል ጉዳተኞችን እንዳሳተፈ ግን አልገለጸም። ይህ ቢሆን ኖሮ ምርጫ ቦርድ ባይሰጥም በተሳተፉት ፓርቲዎች ብዛት እጩዎችን ማወቅ ይቻል ነበር። ማኒፌስቶ ሲተዋወቅም ቢሆን የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎ አይጠየቅም፤ አይጠራምም። ይህ ሲሆን እያየ ደግሞ ምርጫ ቦርድ ዝም ነው ያለው። ስለዚህም በምርጫ ትግበራው የአካል ጉዳተኞች ትኩረት ማነስ በስፋት የሚታይበትና ጥያቄዎች መልስ የማያገኙበት ሆኗል።
እንደ አገር መታየት ያለበት 20 ሚሊዬን ህዝብ ከቤተሰቡ ጋር ቢቀናጅ ከአገራችን ትልቅ የሚባለውን ክልል ይሸፍናል። አንድ ሦስተኛውን የሚይዝም ነው። ይህንን ያህል ህዝብ ወደጎን ትቶ ዲሞክራሲያዊና ፍትሀዊ ምርጫ እናካሂዳለን ማለት አይቻልም። ስለሆነም ምርጫ ቦርድ ፍትሀዊነቱን ለአካልጉዳተኞች ጭምር ማሳየት አለበት። ለምሳሌ ምርጫውን የማስፈጸሚያ ማንዋል ሲጸድቅ ለአካል ጉዳተኞች ማበረታቻ የተባለው ብዙ ነገር ነው። ነገር ግን ይህንን ተከታትሎ ሲያስፈጽመው አይታይም።
ራሱም እየፈጸመው ነው ለማለት ይቸግራል። ለዚህም ማሳያው ለአካል ጉዳተኛውና ላልተጎዳው ቅስቀሳ ሲያደርግ ያለው ማበረታቻ በምንም መልኩ እኩል አይሆንም። በዚህም ይህንን ታሳቢ ተደርጎ በማዕቀፍ ደረጃ ተቀምጧል። 25 በመቶ ለአካል ጉዳተኞች ጭማሪ ይሰጣል ይላል። ተፈጻሚነት ግን ሲኖረው አይታይም። በተመሳሳይ በፓርቲም ሁኔታ ይህ ህግ አለ። ግን የመፈጸም ሁኔታው እንብዛም ነው። ስለዚህም የአካል ጉዳተኞች የምርጫ ተሳትፎ እንዳይረጋገጥ ህጉን የማስፈጸም የምርጫ ቦርድ አቅም ላይ ውስንነቶች እንዳሉ እናያለን።
አሁንም ምርጫ ቦርድ ራሱን ማየትና የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ጉዳዬ ነው ማለት ይጠበቅበታል። ፓርቲዎችም እንዲሁ። ጥሪ አድርገንም እንኳን ከጥቂቶች ውጪ የሚታደም የለም። ጥሩንም፣ ኑልንም ሁለቱም ችግር ያለበት ነበር። የፓርቲዎች ማኒፌስቶ በብሬል እንዲቀርብልን ስንጠይቅ አንድ ፓርቲ ብቻ በሁለት ገጽ የስብሰባ ማንዋል ይዞልን መጥቷል። ስለዚህም አሳውቁን እንቢ፤ እንመካከር አንችልም የሆነ ጉዳይ ሆኗል። ስለዚህም ህግ ላይ የተቀመጠ ስለሆነ ፓርቲዎችም ሆኑ ምርጫ ቦርድ ሀላፊነታቸውን ይወጡልን ማለት እወዳለሁ።
አዲስ ዘመን፡- የአካል ጉዳተኞች የምርጫ ተሳታፊነት ሲታይ የዘንድሮ ምርጫ ምን ምቹ ሁኔታ አለው? ተግዳሮቱስ?
አቶ አባይነህ፡– ተስፋው ቅድም እንደተባለው እስከ አምስት ከነበሩት ምርጫዎች በህግ ላይ ያሳተፈ መሆኑ ነው። ተካታችነትን በአንድ ጉዳይ አሳይቷል። ወደፊትም ጭምር ለመጠየቅ የሚቻልበትን እድል ሰጥቷል። ሆኖም አፈጻጸሙ ተስፋችንን እያጨለመው ነው። በዚህም አካል ጉዳተኞች በዘንድሮው ምርጫ ሙሉ ለሙሉ ይካተታሉ የሚል እምነት የለንም። የአካል ጉዳተኛ ማህበራት ሲነሱ አንድ ነገር ጠንቅቆ ማወቅ ያስፈልጋል። ይህም በአካል ጉዳተኞች ዙሪያ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ በህግ የተደነገገው ለመንግስት ብቻ ነው። የፌደሬሽኑ ሚና ጠያቂነት ብቻ ነው።
የአለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ኮንቬንሽንን አገራችን ከዛሬ 11 ዓመት በፊት ፈርማ ወደ ተግባሩ ገብታለች። በፈረመችው ኮንቬንሽን በግልጽ እንደተቀመጠው ማንኛውንም መንግስት ያልፈጸመውን ጉዳይ መጠየቅና ሁኔታው የማይፈታ ከሆነ ለአለምአቀፉ ማህበረሰብ ማሳወቅ ነው ስልጣኑ። ይሁን እንጂ እኛ ከዚህ አልፈናል። ምክንያቱም ገና እያደገች ያለችውንና ተስፋ የምንጥልባትን አገር በአለምአቀፉ ማህበረሰብ ማስቀለም አይገባንም ብለን እናምናለን። ነገር ግን አንዱን ብቻ ከምርጫ ጋር አያይዘን ብናነሳ ችግር እንዳለ መጥቀስ ይቻላል። ይህም አገራት የአካል ጉዳተኞችን የፖለቲካ ተሳትፎ ማረጋገጥ አለባቸው ይላል። ሆኖም ከህግ ውጪ ተግባሩ እየታየ አይደለም። እነ ኬኒያን እንኳን ብናነሳ ከእኛ በኋላ ተነስተው አፈጻጸማቸው ልቋል። ስለዚህም መፈረም፣ ህግ ማውጣት ሳይሆን በተግባር ማሳየት ላይ ነው የአገሪቱ ችግርና ይህንን ማየት ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ አኳያ የቀጣዩንም የምርጫ ጉዞ መታደግ ትንሽም ያተርፋልና ምን መደረግ አለበት ይላሉ?
አቶ አባይነህ፡- እንደእኔ እምነት ብዙው አልፏል። ብዙ አካልጉዳተኞችን ያሳተፈ ነገርም የለም። ሆኖም ጨለማ ከሚሆን ያረፈዱባቸው ጉዳዮች ላይ መስራት ይገባል። ከእነዚህ መካከል የምርጫ ቦታ ምቹነት አንዱ ሲሆን፤ አካል ጉዳተኞች ኮሮጆው ድረስ እስኪሄዱ ያሉ ቦታዎች መስተካከል አለባቸው። ምርጫ ቦርድም ለአካል ጉዳተኞች የተሰጡ መብቶችን ማክበርም ሆነ ማስከበር አለበት። ለምሳሌ ባጅ አድርጎ የሚንቀሳቀሰውን ታዛቢ ማን ነው የፈቀደልህ የሚልና የሚያባርር አካል ብዙ ነው። ስለሆነም ይህንን ሀይ ማለት ይጠበቅበታል። ቦታውንም አመቺ የማድረግ ሀላፊነት አለበትና ይህንን ያድርግ።
ሚዲያውም ቢሆን የአካል ጉዳተኞች የምርጫ ጉዳይ ላይ ሲዘግብ አልነበረም። ችግሮቻቸውንም አላሳየም። ምክንያቱም ችግሮቹ ቀደም ብለው ታውቀው ቢሆን ኖሮ መፍትሄ ይበጅላቸዋል። ነገር ግን አልታዩም ሳይታዩም አክትመዋል። እናም አሁን በጣም ጥቂት አካል ጉዳተኞች ካርድ ወስደዋልና እነርሱም በቤታቸው እንዳያስቀምጡትና አሻራቸውን እንዳያሳርፉ እንዳናደርጋቸው እንስራ። በችግር ውስጥ ሆኖ የመጣው ድምጻቸው እንዳይታፈን መንግስት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሲቪል ማህበራት፤ ህዝብና ሚዲያው ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።
መላውን ህብረተሰብ ቀስቅሶ አካል ጉዳተኞች በምርጫው ድምጻቸውን እንዲሰጡ ማድረግና ምቹ ሁኔታ
መፍጠር እንዲችልም መረባረብ ያስፈልጋል። በተለይም የመረጃ ክፍተቶች ላይ የስራ ጫና ባይበዛብን እንላለን። ምክንያቱም አዳዲስ መረጃዎችን ለመስማት የተሳናቸው ለማድረስ ዳግም ጫና እየተፈጠረብን ይገኛል። ይህንን ማድረግ ላይ ደግሞ መንግስት መስራት መቻል አለበት። እንደውም ምርጫው ላይ የሚኖሩ ለውጦች ባይፈጠሩ ደስታችን ነው።
አዲስ ዘመን፡- ወቅታዊ ሁኔታዎችና የአካል ጉዳተኝነትን ከኮሮና አንጻር እንዴት ያነሱታል ? ያለውስ እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?
አቶ አባይነህ፡– ኮሮና ከአካል ጉዳተኝነት አንጻር ሲታይ በተጋላጭነት ብቻ በብዙ መንገድ ከአካል ጉዳት አልባው ይለያል። ከፍ ያለ እንደሆነም ታምኖበት ብዙ ነገሮች ቅድሚያ ሲሰጡ ቆይተዋል። ይሁን እንጂ አሁን ከመጣው ክትባት አኳያ ሲታይ እጅግ የሚያሳዝንና እንደመንግስት የሚያሸማቅቅ ድርጊት በአካል ጉዳተኞች ላይ እየሆነ ይገኛል። ይህም ተጋላጭነታቸው ቢታመንበትም ቅድሚያ ክትባት እንዲያገኙ ግን ምንም አይነት ምቹ ሁኔታ አልተፈጠረላቸውም።
ጤና ሚኒስቴር በቅርቡ ያወጣው ማንዋልም በጣም አሳፋሪ ነው። ምክንያቱም ተጋላጭ ናቸው ብሎ ሲሰራ ቆይቶ እስከ አምስት ከዘረዘራቸው ውስጥ አላካተተም። በዚህም አካል ጉዳተኞች በየትኛውም ቦታ ቢሄዱ ተጋላጭ ናችሁ ብሎ የሚያስተናግዳቸው እንዳይፈጠር አድርጓል። ኑሯቸውንም ያከበደው ከቀደመው ይልቅ ይህ እድል አለመሰጠቱ ነው። አሁንም ቢሆን ይህ እድል መመቻቸት ይገባዋል በማለት ጥያቄ እያቀረብን እንገኛለን። መፍትሄው መቼ እንደሚመጣ ባይታወቅም።
ሌላው ከኮሮና ጋር በተያያዘ አካልጉዳተኛው ላይ እየተከሰተ ያለው ከኢኮኖሚ ጋር የተያያዘው ጉዳይ ሲሆን፤ አካል ጉዳተኛው በአብዛኛው በሚባል ደረጃ ከዝቅተኛው ማህበረሰብ ውስጥ የተወለደና እየኖረ ያለ ነው። አሁን ደግሞ የኑሮ ውድነቱ ከአቅም በላይ ሆኗል። እናም የሚፈልገውን ለመከወን በሚንቀሳቀስበት ሁኔታ ላይ በኮሮና የመያዙ ምጣኔም ሆነ ሌሎች ችግሮቹን የመቋቋም ደረጃው እየከፋበት ይገኛል። በተለይም በልመና ላይ የሚገኘው አካል ጉዳተኛ ለዚህ ነገር ተጋላጭነቱ እጅግ የከበደ ሆኖበታል። ምክንያቱም የሚያገኘው ገንዘብ በልቶ ለማደርም ያስቸግራል። ለዚህ ደግሞ የሚሰጠው አካል መቀነሱና የገንዘቡ የመግዛት አቅም ከፍ ማለት ሁኔታውን አባብሶታል።
አዲስ ዘመን፡- በየቦታው ያለው ግጭት በተለይ ለአካል ጉዳተኞች ፈታኝነቱ የበዛ እንደሆነ ይታሰባል። እርስዎ በዚህ ዙሪያ ምን ይላሉ?
አቶ አባይነህ፡- ግጭት በባህሪው በሁሉም ዘንድ የሚወገዝ ነው። በተለይ ደግሞ አካልጉዳተኞች ግጭቱን በሁለት መንገድ ከሌላው በተለየ መልኩ አጥብቀው ያወግዙታል። የመጀመሪያው የሞት የበኩር ልጅ የሚሆኑት እነርሱ ናቸው። ምክንያቱም ሮጠው ማምለጥ የሚችሉ አይደሉም። ሁለተኛው ደግሞ ግጭት በራሱ አዳዲስ አካልጉዳተኛን የሚፈጥር ፋብሪካም በመሆኑ ብዙ ነገሮችን ያከብዳል። በዚህም እንደ አካል ጉዳተኛ የድል ሁሉ ጫፍ በጠረጴዛ ዙሪያ መሸነፍ ነው ብለን እናምናለን። ይህንንም ማድረግ እንደሚያስፈልግ እንመክራለን።
በአገራችን ያለው ግጭት በዋናነት ትኩረቱ ብሔር ሲሆን፤ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ሀይማኖትን ሽፋን ሲያደርግ ይታያል። ከዛሬ 27 ዓመት በፊት የተቀበረና ህጻናቱን ያሳደገ ነው። እድገቱ ጎልምሶ ፍሬውን ሲያሳይ የሚከሰትም ነው። እኛ የአካል ጉዳተኞች በግጭቶች ተለይተን ልንመታ የምንችልበት ሁኔታ ብዙም አይደለም። ምክንያቱም ብሔርም ሀይማኖትም ቢኖረን የሚያስተሳስረን ጉዳይ አካል ጉዳተኝነት ብቻ ነው። ለእኛ ለአካል ጉዳተኞች ትልቁ ብሔራችንም ሆነ ሀይማኖታችን የአካል ጉዳተኝነታችን ነው። ስለሆነም እኛን የሚጎዳን በችግሩ ውስጥ ያለው መሯሯጥና አለማምለጥ መቻል እንጂ እነዚህ አይሆኑም።
ፍላጎታችንም ቢሆን አንድ ነገር ላይ የሚያርፍ ነው። ይህም ለሰላም ዘብ መቆም ሲሆን፤ እስካሁንም የዚህችን አገር ሰላም በማረጋገጥ አኳያ ትልቁን ሚና ሲጫወት የቆየው የአካል ጉዳተኛው ነው። ከዚህም በኋላ ቢሆን ብሔርን ፣ ሀይማኖትን ሽፋን አድርገው የሚሰሩትን በመቃወምና ለሰላም መስራታችንን በማስፋት ህልውናው አድርጎ ይንቀሳቀሳል።
አዲስ ዘመን፡- አካል ጉዳተኞች በአገሪቱ ጉዳይ ላይ ምን ያህል አሻራቸውን እያሳረፉ ነው ብለው ያስባሉ?
አቶ አባይነህ፡- የአገር ጉዳይ የሁሉም ነው። ስለዚህም አካልጉዳተኞች በሁሉም መስክ የራሳቸውን አሻራ ለማሳረፍ የሚጥሩ ናቸው። ከእነዚህም ውስጥ በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ ህዳሴው የእኔ ነው በማለት ከቦንድ ግዢ እስከ ስጦታ ድረስ የደረሱ መዋጮዎችን ላለፉት ሰባት ዓመታት ሲያደርግ መቆየቱ አንዱ ነው። በተመሳሳይ ከእዚሁ ሳንወጣ በቅርቡ ከሚታየው ሁኔታ አንጻር ማለትም ከአባይ ፖለቲካ ጋር የሚመጡ ከባድ ጫናዎችን ለመመከትና ሁኔታውን ለማስረዳት እንደ ፌደሬሽን ብዙ ተግባራት ተከውነዋል። እኛ ድሃዎች መጠቀም እንዳለብን ለአለሙ ማህበረሰብ እያስረዳንም ነው። ለአብነትም ከጎረቤት አገራት የአካል ጉዳተኞች ማህበራት ጋር በተጠናከረ ሁኔታ መስራት መጀመራችን በዋናነት ይጠቀሳል። እንደውም በቅርቡ ከግብጽ የአካል ጉዳተኞች ማህበራት ጋር 13 ልኡካንን ይዞ በመሄድ ጥልቅ ውይይት አድርገን በአራት ከተሞች ለአምስት ቀናት ዞረን ማስተማርም ችለናል። የአካል ጉዳተኛ ማህበረሰቡንም ለማስረዳት የሞከርንበት ሁኔታም ነበር።
በአሜሪካ የቪዛ ማዕቀብ ዙሪያ መንግስት እንደ መንግስት መቀበል አለበት ያለውን ነገርም እንደ አካል ጉዳተኛ ማህበራት ፌደሬሽን ጉዳዩ በቀላል የሚታይ ስላልሆነና ኢትዮጵያ ከሦስት ሺህ ዓመት በላይ ሉዓላዊነቷን የጠበቀች አገር ማንም ሊያስገድዳት እንደማይችል ደብዳቤ ጽፈን በግልጽ ቋንቋ ሀሳባችንን በአለምአቀፉ የአካል ጉዳተኞች ማህበር በኩል መልዕክታችን እንዲደርስ አድርገናል። ይህ ደግሞ ቆም ብለው እንዲያስቡበት ያደርጋል የሚል እምነትም አለን። ከዚህ ባሻገርም መንግስት የአረንጓዴ አሻራ ሲልም አንዱም ቦታ ላይ ሳንቀር እየተሳተፍን እንገኛለን። ወደፊትም ከነበረው በላይ እንሳተፋለን። አገር ስትለማ እኛም አብረን እናድጋለንና።
አዲስ ዘመን፡- አገራችን ላይ እየተደረገ ያለው የውጪ ጫና በተለይም የአሜሪካን ማዕቀብ እርስዎ እንዴት ተመለከቱት? እንዴትስ መፈታት መቻል አለበት ብለው ያስባሉ?
አቶ አባይነህ፡- ማዕቀቡ በእኛ መነጸር የተሳሳተና ተገቢነት የሌለው ነው። ስህተት ውስጥ የከተታቸው የቀደመ አሰራርና የመንግስት እንቅስቃሴ ግንዛቤውን አዛብቶበታል የሚል ይሰማኛል። የችኮላ ውሳኔም የወሰነ እንደሆነ ግልጽ ነው። በፍጹም ከሦስት ሺኅ ዓመት በላይ ሉአላዊነቷን ጠብቃ የኖረችን አገር ይህ ተግባራቸው የሚገባት አይደለም። ተግባራቸው ከነበረ ታሪክ አንጻርም አይገናኝም። ተራ የነበረ ጥቅም ሊያልፍ ይችላል። ነገር ግን እንደመንግስት ምን አልባትም እነርሱ ያቀረቡትን አማራጭ በመንግስት ደረጃ አልያም በግል ዶክተር አብይ አልተቀበለም ብለው አስበው ይሆናል ይህንን ሀሳባቸውን የገለጹት። ስህተቱም ከዚህ የሚመነጭ ነው። ኢትዮጵያዊ ይቀበላል ወይ የሚለውን አላዩም። በመብቱ ሲመጣበት አሻፈረኝ እንደሚል አልተረዱም። ማንነቱን፣ ታሪኩን አሳልፎ ለሌላ አገር የሚሸጥ ዜጋ እንዳልሆነም አልተገነዘቡም። ሉአላዊነቱን አሳልፎ የሚሰጥ ኢትዮጵያዊ የለምን በደንብ አልመረመሩትም።
110 ሚሊዬን ህዝብ ኢኮኖሚው ንሮ ምሳውን በልቶ ራቱን ሳይደግም እንደውም አንድ ጊዜ ብቻ ተመግቦ መኖር የቻለው ሉአላዊነቱን ላለማስነካት ነው። አሁንም ከመቀነቱ አውጥቶ ለህዳሴ ግድቡ የሚለግሰውም ነገ አልፎልኝ እኖራለው እንጂ እገዛለሁ ብሎ ስለማያስብ ነው። ስለዚህም ይህንን አይቶ የሉአላዊነት ጉዳይ የዚህ ህዝብ አቋም ነው ብሎ አለመውሰድ እንዲሁም የግለሰቦች አቋም ነው ብለው ማመናቸው ነው እንዲሳሳቱና የማይገባ ውሳኔ ላይ እንዲደርሱ ያደረጋቸው። ስለሆነም አልረፈደባቸውምና ቆም ብለው ማስተዋል ይገባቸዋል።
ድርጊታቸው መሰረት የለሽና እዚህ የሚያደርስ ነገር የሌለው ነው። ስለዚህም እኛ የምንፈልገው የአሜሪካ መንግስት ለምን እንደማንፈልገው ሊያናግረን ይገባል። መነሻና መድረሻውንም ሊያይ ይገባል። በጭፍን ዳቦ ካልበላህ ትሞታለህ ቢባል እኔ ላንተ ከማጨብጨብ ይልቅ ዳቦ ሳልበላ አገሬ ሳትደፈር ብሞት ይሻለኛል የሚል ዜጋ መኖሩንም ማሰብ አለበት። በመጸሐፍ ቅዱስ ‹‹ ባያድነንም እንኳን አንሰግድም›› እንዳሉት አይነቶች ያሉባት አገር በመሆኗ ይህንን ግንዛቤ ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል። ስለዚህም በመስጠት ብቻ ሉአላዊት አገርን ሊገዛን የሚችል ሀይል እንዳላቸው ማመን የለባቸውም።
ኢትዮጵያን በጉልበት፣ በአዲስ ቴክኖሎጂና በጠመንጃ እንዲሁም በተራ ድጎማ ማስፈራራት ማንም ሊገዛት አይችልም። ኢትዮጵያ እጅ የምትሰጠው በጋራ መብላትና መስራት እንዲሁም መነጋገር ላይ ብቻ ነው። በፍቅር ትረታለች። እውነትንና ፍቅርን ብቻ ይዛ የምትጓዝም አገር ነች። ስለዚህም በውሸት በሌላ የፈለገ ማዕቀብ ቢጣል አትሸነፍም። ነገሩ ከዚህም ሊብስ እንደሚችል ይታመናል። ሆኖም ማንም ኢትዮጵያ በአገሩ ሉአላዊነት አይደራደርም። ይህ አቋም ደግሞ የብልጽግናና የዶክተር አብይ አቋም ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያዊ መሆኑን አሜሪካውያን ሊያውቁት ይገባል። ምንአልባት ብልጽግናን የሚደግፉ አይደግፉትም የሚቃወሙ ይደግፉታል ብለው ከሆነ አሁን አሜሪካ ችግር ውስጥ ትገባለች። ጥንቃቄ ሊወሰድበት የሚገባውም የኢትዮጵያውያንና የፓርቲን አቋም መለየቱ ላይ ነው።
የኢትዮጵያዊያን አቋም አሜሪካውያን ወንድሞቻችን ናቸው። በሚሊዬን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የሚያለሟት አገር ነችም የሚል ነው። በግብራቸውም አገራቸውን እያሳደጉላቸው እንደሆነ ማሰብ ያስፈልጋቸዋልም ነው። የረጅም ጊዜ ግንኙነታችን እንዳይሻክር ሀሳባቸውን ማየትም ያስፈልጋቸዋል ነው። የፖርቲ ለፓርቲ መሻከር በጊዜ ሂደት አመራሩ ሲቀየር ይፈታል። የህዝብ ለህዝብ መሻከር ግን በቀላሉ የሚፈታ አይሆንምና የአሜሪካ መንግስት ጥንቃቄ ማድረግ አለበት። የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብም ቢሆን በዚህ ድርጊት መደናገጥ የለበትም። ምክንያቱም ይህ ሀሳብና ተግባር ለመላው ዜጋ ግልጽ ነው። ጫናው አትለሙምን የያዘና ህዳሴ ግድባችንን የሚመለከትም ነው።
አባይን የመጠቀም መብት አለን። ስንጠቀምም ማንንም አንጎዳም። ይልቁንም በራሳችን ሰርተን ሌሎችን እንጥቀም ነው ያልነው። የመንግስት አቋምም ቢሆን ይህ ነውና መደናገጥ የለበትም። ነገር ግን መንግስትም ሆነ ህዝቡ ጥንቃቄ ሊወስድባቸው የሚገቡ ነገሮች አሉ። ከእነዚህ መካከልም በዋናነት የምንናገራቸው ነገሮችን መጠንቀቅ አንዱ ነው። ተገቢ ያልሆኑ ባነሮችንም ይዞ መውጣት ለበለጠ ችግር ያጋልጣልና ነገሩ የመንግስትና የህዝብ አቋም ባይሆንም ግለሰቦች በሚያደርጉት የራሳቸው አጀንዳ ማስፈጸም እንዳንታለል ረገብ ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል። እኛን የሚገልጸን ኢትዮጵያዊነት ያለው ቀለም እንጂ ጥላቻ አይደለምና እርሱ ላይ ሁሉ ነገር በአግባቡ መሆን አለበት። የምናስተላልፋቸው ሀሳቦችና መልዕክቶች በግልጽ ቋንቋ ሉዓላዊት አገር ነን የሚል ብቻ ቢሆን መልካም ነው።
ክብራችሁን እንጠብቃለን፤ ክብራችሁን ጠብቁ። ተከባብሮ መኖር ብቻ ነው የሚያስተሳስረን የሚል መሆን አለበት። አሜሪካ እኛን በምንም መልኩ አልዘለፈችም። መብቷን ተጠቅማ ነው አላደርግም የሚል ማዕቀብ የጣለችው። ስለዚህም ነገሩ እኛን የሚጎዳ መስሎ ስለታየን ነገሩን በበሰለ መንገድ ማስረዳት እንጂ መዝለፍ አያስፈልግም። የኢትዮጵያዊነት ወኔና እልህን ቆም በማድረግ ጥበባዊነታችንን በመጠቀም በፍቅር ለማሸነፍ መታተር ያስፈልገናልም። ከአሜሪካዊያን ጋር በሰላም መኖር እንደ ደሃ አገር በጣም ትልቅ ጥቅም አለው። በቀላሉ የአካል ጉዳተኞችን ብቻ ብንወስድ ክራንች ጭምር የሚመጣውና የሚለገሰው ከዚያ ነው። በቅርቡ ኢትዮ ቴሌኮም ሳይቀር አሳልፈን የሰጠነው በአሜሪካ ለሚሰራ ድርጅት ነው። በጂኦ ፖለቲክስም ቢሆን ኢትዮጵያ አፍሪካ ቀንድ ላይ ያለች በመሆኗ ተጠቃሚዋ አሜሪካ መሆኗን ከግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋታል። ስለዚህም ተደጋግፈን እንሰራለን የምንል ነንና ይህንን ትስስር ነው ማጥበቅ ያለብን። ይህ ሲሆን ደግሞ ሉአላዊነታችንን በማስጠበቅ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻ የሚያስተላልፉት መልዕክት ካልዎት?
አቶ አባይነህ፡- አሁን ያለው ለውጥ መሬት ረግጦ የታሰበው ነገር እንዲፈጸምና ተስፋችን እንዲለመልም ሁሉም የድርሻውን ይወጣ። ወደ ፊታችን ያለው ምርጫውም ቢሆን ሰላማዊ፣ ፍትሀዊ፣ ዲሞክራሲያዊ እንዲሆንም መንግስት፣ ሲቪል ማህበረሰቡ፣ ሚዲያውና መላው የህብረተሰብ ክፍል ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል የሚል ነው። የሚፈጠሩ ማንኛውም ግጭቶችን እንድናቆምም አካል ጉዳተኛና ቤተሰቦቹ ይማጸናሉ። ምክንያቱም ግጭት ሲፈጠር ሦስት ነገሮችን በዋናነት ያጠፋል። የመጀመሪያው አካል ጉዳተኞችን ይገላል። ሁለተኛው የአገርን ኢኮኖሚ ማድቀቅ ብቻ ሳይሆን ያልተረጋጋ ኢኮኖሚን ይፈጥራል። ሦስተኛው በህዝቦች መካከል መቃቃርን ያመጣል። ስለሆነም ለዚህ ሁሉም ማህበረሰብ በኢትዮጵያዊነት ስሜት መረባረብ አለበት።
በማሸነፍና መሸነፍ ማመንና ዘመኑን የዋጀ ሥራ መተግበርም ይኖርብናል። ስልጣንን አሳልፎ በመስጠት የሚመጣውን ጥቅም ማየትም አስፈላጊ ነው። ትናንት አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝና ዶክተር አብይ አህመድ ሲቀባበሉ የነበረው ሰላም ምን ያህል እንደነበረ ብዙዎቻችን አይተናል። ስለሆነም አሁንም ከውጪ ጫናው ጋር እየታገልን የአገራችንን ነባራዊ ሁኔታ በማስተካከል ፤ ከኮሮና ራሳችንን በመጠበቅ ተስፋ የምናደርጋትን አገር እንገንባ ማለት እፈልጋለሁ።
አዲስ ዘመን፡– ስለሰጡን ማብራሪያ እናመሰግናለን።
አቶ አባይነህ፡– እኔም አመሰግናለሁ።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ግንቦት 30/2013